የደማቋ ሀገር የማይደበዝዝ ዐሻራ

ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ሥልጣኔ ያላት ሀገር ናት። ከሦስት ሺህ ዓመት በላይ ታሪክ ያላት የሚለው ሀረግ ከሜዳ የመጣ አይደለም። የጥንቱ ድንበራችን እስከ ደቡብ ግብጽ ድረስ ይደርስ እንደነበር በታሪክ ድርሳናት ተጠቅሷል። ይህ የጥንቷ ኢትዮጵያ ገናናነት በዘመናዊ ታሪኳም አልደበዘዘም። በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት በባርነት ውስጥ ለሚኖሩ ሚሊዮኖች ፋና ወጊ ሆናለች። የአፍሪካ ሀገራትን ከቅኝ ገዢዎች ጉያ ፈልቅቃ ለማውጣት በሊግ ኦፍ ኔሽን ውስጥ ብቻዋን ጮሃለች። በሀገራቱ መካከል የነበረውን ልዩነት በማጥበብ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ እውን እንዲሆን ትልቅ ሚና ተጫውታለች። ለመሆኑ ኢትዮጵያ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት እውን እንዲሆን ያደረገችው አስተዋጽኦ ምን መልክ አለው ? በቀጣይስ ታሪካዊ ሚናዋን ለማስቀጥል ምን ማድረግ ይኖርባታል ?

የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ኢትዮጵያ ታሪኳንና ቅርሷን ጠብቃ ከቅኝ ገዢዎች ነፃ ሆና የቆየች በተምሳሌትነት የምትጠቀስ ሀገር ናት። የዓድዋ ድል ትልቁ ታሪካችን ነው። ዓድዋ በአፍሪካ ምድር፣ በአሜሪካ እና በተቀረው ዓለም ያሉ ጥቁሮች በሙሉ የሚኮሩበት ነው። የጥቁሮችን መብት ለማስከበር ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል። ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1945 ሳንፍራንሲስኮ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት በኋላም በ1963 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት ዐሻራዋን ማስቀመጧም ደማቅ ታሪካዊ ሁነቶች ናቸው ይላሉ።

አፍሪካውያን በቅኝ ገዢዎች ተወርረው የነበረበትን ጊዜ ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ብዙ የውጭ ጸሐፍቶች የጻፉት ምስክርነት መኖሩን የሚጠቁሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ በተለይ ኢራቃዊው ኡምታ ዘላሪፍ የተባለው ደራሲ በአንድ መጽሐፉ መግቢያ ላይ ለስምንት ዓመታት በአፍሪካ ተዘዋውሮ መሥራቱን ጠቅሶ፣ አፍሪካውያን በቀያቸው በሀገራቸው ለፈረንጆች አገልጋይ ሆነው ሳገኛቸው በኢትዮጵያ ግን ነጭ ለኢትዮጵያውያን አገልጋይ ሆኖ ሲሠራ ተመልክቻለሁ ብሎ መጻፉን ይጠቅሳሉ።

ኢትዮጵያ አፍሪካውያን ለቅኝ ግዛት በተጋለጡበት ዘመን ነፃነታቸውን እንዲያገኙ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውስጥ የተጫወተችውን ትልቅ ሚና ሲያወሱም፤ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሀገራትን ዜጎች በምድሯ በማሰልጠን ወደ ሀገራቸው ሄደው ሀገራቸውን ነፃ ለመውጣት የሚደረገውን ትግል እንዲደግፉ ረድታለች። ለዚህ አስተዋጽኦ ኔልሴን ማንዴላ በታሪክ ተጠቃሽ ምስክር ነው። ብቸኛዋ አፍሪካዊት ሀገር በሆነችበት በሊግ ኦፍ ኔሽን ውስጥም ሀገራቱ ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ ድምጽ ሆናቸዋለች ይላሉ።

አፍሪካውያን ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ የኢትዮጵያን ውለታ አልረሱም። ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የባንዲራቸውን ቀለማት ሲመርጡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ላይ የሚገኙትን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማትን በመምረጥ ለሀገራችን ትልቅ ቦታ ሰጥተዋታል፤ ይሄ ትልቅ ክብሯ ነው ሲሉም ያክላሉ።

የአፍሪካ ኅብረትን ከኢትዮጵያ አንስቶ ወደ ኬንያ ለመውሰድ በግብጽና ሊቢያ የተደረጉ ብዙ ሙከራዎች የከሸፉትም የኢትዮጵያን ውለታ ጠንቅቀው በሚያውቁት የመላው አፍሪካ ሀገራት እምቢተኝነት መሆኑንም ያወሳሉ። አፍሪካውያን ለኢትዮጵያ ባላቸው ክብርና ፍቅር ምክንያት ጥያቄው በተነሳበት በእያንዳንዱ መድረክ ትልቅ ድል ተጎናጽፈናል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በሥልጣኔም በትምህርትም በእውቀትም ከሌሎቹ አፍሪካውያን የበለጠች ስለሆነች የእርሷን መሪነት እየተቀበሉ የሕብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ እንዲጸና አድርገዋል ነው የሚሉት።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲጠናከር ጉልህ ሚና ተጫውታለች። የአፍሪካ ኅብረት እውን በሆነበት ሂደት እና ከዚያ በኋላም የቀደመ ሚናዋን የሚመጥን ተሳትፎ በማድረግ ቀጥላለች የሚሉት የታሪክ ምሁሩ፤ አሁን 38ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባን በማስተናገድ ላይ የምትገኘው አዲስ አበባ የዓለም ሁለተኛዋ ኮንፍረንስ መድረክ ሆናለች። ቀደም ሲል ከኒውዮርክ እና ጄኒቫ በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃ ላይ ነበር የምትገኘው አሁን ግን ጄኒቫንም አሸንፋ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ይሄ እድገት ከሜዳ የመጣ አይደለም። አጀንዳ በመከታተል፣ በመቅረጽም ሆነ በመዘጋጀት የአፍሪካ ኅብረትን በመያዝ ውጤት እያመጣች መሆኑን የሚያሳይ ነው ባይ ናቸው።

አሁን እየተካሄደ ያለውን ስብሰባ እንኳን ከዓለም ዙሪያ የመጡ አንድ ሺህ ያህል ሚዲያዎች ሽፋን እየሰጡት እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ይህ ሁሉ ሚዲያ ወደ ሀገራችን መምጣቱ አንድ ትልቅ ዕድል ነው። ይህ ትኩረት እንዲሁ የተገኘ አይደለም። በኛ በኩል ዝግጅት አድርገን የኢትዮጵያን ማንነትና ክብር የምናሳውቅበት ትልቅ መድረክ መሆን አለበት ሲሉ ያሳስባሉ።

አዲስ አበባን ውብ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት መቀመጫነቷ የሚመጥን መሠረተ ልማትና ንጹህ አረንጓዴ አካባቢ እንዲኖራት የማድረግ ሥራ በመሆኑ ልማቱ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተው፤ ምክንያቱም መወዳደርና የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ማስተናገድ የምንችለው ውበታችን እና ሥልጣኔያችንን የሚያንጸባርቁ የመንገድም ሆነ የህንጻ ግንባታዎች ማካሄድ ስንችል ነው። ነባር አካባቢዎች በመፍረሳቸው ከኖሩበት አካባቢ በሚነሱት ነዋሪዎች ላይ ችግር ይፈጥራል። ነገር ግን ውጤቱን በማሰብ የመልሶ ማልማት ሥራውን በጸጋ መቀበል አለብን። ዋናው ነገር ሰዎች እንዳያኮርፉ ጥንቃቄ ይሻል። አስፈላጊው ካሳ እየተከፈላቸው የሚቋቋሙበትን እና የሚደራጁበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል።

አያይዘውም፤ እኔ በብዛት ወደ ውጭ ሀገር እጓዛለሁ። ከአንድና ከሁለት ወር በኋላ ተመልሼ ስመጣ ብዙ ለውጥ አያለሁ። ይህ በፈጣን ደረጃ እየተከናወነ ያለ ለውጥ መኖሩን ያሳያል። እየታየ ያለው ለውጥ የሚያስመሰግን እና የሚያኮራ ነው። ነገ ልጆቻችን አንዲት የበለጸገችና ያማረች ሀገር ይረከባሉ። በቅንነት ተቀብለን ይሄን ጊዜ ጎንበስ ብለን ማሳለፍ ይጠበቅብናል ሲሉ ይመክራሉ።

“እኛ የሚሠራ መሪ ነው የምንፈልገው። ዝም ብሎ አራት ኪሎ ተቀምጦ እንግዳ ተቀብሎ በመጋበዝ የሚያስተናግድ አይደለም። ለአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች ሀገር ዜጎች እንደመሆናችን ሰርቶ ውጤት ያለው ነገር ለትውልድ የሚያስረክብ ሥርዓት እንፈልጋለን” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ሥርዓት ሁልጊዜም ቋሚ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን የተረከብነውን ሀገር ልማት፣ ዕድገትና ክብር እንዴት ባለ መንገድ ይዘን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ አለብን የሚለው ሊያሳስበን ይገባል። እኛ ትልቁ ድክመታችን ይሄ ነው ባይ ናቸው።

በኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሠሩት አምባሳደር ተፈራ ሻውል በበኩላቸው፤ በዘመናት የመጡ የኢትዮጵያ መሪዎች ሁሉ ስለ አፍሪካ የሚያቀነቅኑት ሃሳብም ሆነ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ወሰን የለሽ እና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ጉልህ ዐሻራ ያኖረች ሀገር መሆኗን ሲያመለክቱ፤ ሀገራችን በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ላይቤሪያ፣ ሩዋንዳ እና ሶማሊያ ሰላም አስከባሪ በመላክ የሚስተካከላት የለም። ኮንጎ ነፃ ከወጣች በኋላ የነበረውን ችግር ለማረጋጋት ኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበራት። በኮንጎ የተሰማራውን ሰላም አስከባሪ ኃይል ይመሩ የነበሩት የጦር አዛዥ ጄኔራል ከበደ ገብሬ ነበሩ። የኮሪያ ታሪካችን እንደተጠበቀ ሆኖ አፍሪካን በተመለከተ ከኮንጎ በመጀመር በረዋንዳ፣ ላይቤሪያ፣ ብሩንዲ፣ ዳርፉል ሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን አብዬ እና ሶማሊያ የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርቶ የተባበሩት መንግሥታትን እና የአፍሪካ ኅብረትን ጥረት ደግፏል አሁንም እየደገፈ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል በጣም ያከብራል። ምክንያቱም ከጥንት ጀምሮ መስዋዕትነት ከፍሎ ለዓለም የጋራ ሰላም መስዋዕትነት ስለከፈለ ነው ብለዋል።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአባል ሀገራቱ ቀጣናዎች የሰላም መጠባበቂያ ኃይል እንዲቋቋም አድርጓል። በምሥራቅ አፍሪካ በተቋቋመው የቀጣናው ተጠባባቂ ኃይል ውስጥ እኔም ተሳትፌያለሁ። ወታደራዊ ክንፉ አዲስ አበባ እንዲሁም ማስተባበሪያ ቢሮው ደግሞ ናይሮቢ ሆኖ አሁንም ድረስ ያለ ኃይል ነው። ለዚህም ቀጣናዊ ኃይል መቋቋም ኢትዮጵያ የበኩሏን ድርሻ ተወጥታለች ሲሉም አክለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ሀገራት ነፃ እንዲወጡ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ጥሩ ታሪክ ያለው ድርጅት መሆኑን አንስተው፤ እንደ አውሮፓ ኅብረት የተጠናከረ ድርጅት እንዲሆን አፍሪካውያን ራሳቸውን በራሳቸው ካልረዱ ማንም አይረዳቸውም። አንዳንድ ሀገራት የሚያደርጉት ርዳታም የፖለቲካ ፍላጎታቸውን ለማስፈጸም የሚጠቀሙበት ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሚል አቋም በማራመድ ትታወቃለች። ይህ መርህ ለሁሉም ዓይነት የአፍሪካ ችግሮች የሚሠራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ሆነ ለአፍሪካ ኅብረት መመስረት ያደረገችውን አስተዋጽኦ እየተረከች ብቻ መኖር የለባትም የሚሉት አምባሳደር ተፈራ በቀጣይም የአፍሪካ ቀዳሚ ችግሮችን ለመፍታት በቀዳሚነት የመሪነት ሚና መጫወት እንዳለባት ይገልጻሉ።

ዋና ዋና ናቸው የሚሏቸውን የኅብረቱን ችግሮች በጠቆሙበት የንግግራቸው ክፍልም መወሰደ አለባቸው ብለው የሚያምኑባቸውን ቀጣይ ርምጃዎች በጠቆሙበት የንግግራቸው ክፍል፤ የአፍሪካ ሀገራት ቢሰባሰቡም ለድርጅቱ ሥራ ማስኪያጃ የሚያስፈልገውን በጀት በማዋጣት ረገድ ጥቂት ሀገሮች ናቸው ወቅቱን ጠብቀው የሚከፍሉት። የተቀሩት ይጓተታሉ። ይሄ ትልቅ ተግዳሮት ነው። መሐመድ ጋዳፊ በሕይወት በነበሩ ጊዜ የአንዳንድ ሀገራትን መዋጮ ይሸፍኑ ነበር። ይሄ ክፍተት መሞላት አለበት። ሌላው የዴሞክራሲ እና የሕግ የበላይነት ነገር ነው። እያንዳንዱ የአፍሪካ መሪ የሕግ የበላይነት እና ዴሞክራሲ በሕሊናው እንዲሰርጽ ካላደረገ አህጉሩ ከችግር ሊወጣ አይችልም። በሌሎች ርዳታ ላይ ተንጠልጥሎ ሳይሆን ሕዝብን በማስተባበር በራስ አቅም ደህነትን ማሸነፍ ይገባናል።

አንድ ኅብረት ሲቋቋም ጥንካሬው የሚወሰነው በአባላቱ ጥንካሬና ቆራጥነት ነው። እያንዳንዱ የሀገር መሪ የግል ጥቅሙን እስካስቀደመ ድረስ እንቅፋት ይኖራል። በኢስያ እና ላቲን አሜሪካም ተመሳሳይ ድርጅቶች አሉ። የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት አንድ ዓይነት ገንዘብ ይጠቀማሉ። ዜጎቻቸው እንደልባቸው ከአንዱ ሀገር ወደሌላው ይጓዛሉ። አፍሪካውያን እዚህ ደረጃ ለመድረስ ራሳችንን ታግለን ማሸነፍ አለብን። ያለበለዚያ ለሚቀጥለው ትውልድ የምናወርሰው ዕዳ ከፍተኛ ነው የሚሆነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳሉት ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመሸጋገር ትልቅ ጥረት መደረግ አለበት ብለዋል።

“አፍሪካውያን ብዙ ፈተናዎች አሉብን። የውስጥ ኅብረት የሌላቸው የአፍሪካ ሀገራትና መንግሥታት በውጪው ዓለም ከአውሮፓ፣ ከኢስያ፣ ከቻይና፣ ከአሜሪካ እና ከሌሎችም ጋር የሚያደርጉት ትብብር መስመር ሊይዝ አይችልም” የሚሉት አምባሳደሩ የራሳቸውን ችግር ማሸነፍ መቻል አለባቸው በማለት ያሳስባሉ።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ውክልና ማግኘት አለባት። ምክንያቱም በምክር ቤቱ የትኛውም ውሳኔ የሚተላለፈው ቻይናን ጨምሮ በአምስቱ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አሸናፊ ሀገራት ነው። አፍሪካን የመሰለ ትልቅ አህጉር በተባበሩት መንግሥታት ምክር ቤት እስካሁን አለመወከሉ ትክክል ባለመሆኑ መሻሻል ያለበት ጉዳይ ነው። ይሄ የጥቂት ሀገራት ስብስብ የሆነ ቡድን ብቻ ወሳኝ ሆኖ መቀጠል የለበትም። በዚህ የቤት ሥራ ዙሪያ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና መጫወት ይኖርባታል ነው የሚሉት።

እኛ ኢትዮጵያን መቻቻልን፣ መነጋገርን፣ መወያየትን እና መመካከርን በማስቀደም ኃይልን ከመፈለግ ይልቅ ፖለቲካዊ መፍትሔ በመፈለግ ለተቀረው አፍሪካ ምሳሌ መሆን ይጠበቅብናል ያሉት አምባሳደር ተፈራ፤ አፍሪካ እኛን ነው የሚመለከተው፤ እኛ ገደል ከገባን አፍሪካም ገደል ይገባል። ያለብን ኃላፊነት ተገንዝበን በልኩ እንቀሳቀስ የሚል ጥሪ በማቅረብ አስተያየታቸውን ቋጭተዋል።

ተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You