
ሰሞኑን ከተካሄደው 38ኛው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ቀደም ብሎ 46ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ መካሄዱ የሚታወስ ነው። በዚሁ የሥራ አስፈጻሚዎች ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣለች። ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ መመረጧም በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም እድገት ዙሪያ ላበረከተችው አስተዋጽኦ የተሰጠ ዕውቅና መሆኑን ብዙዎች የሚስማሙበት እውነታ ነው።
የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚጀመረው እኤአ በ1953 በኮሪያ ነው። ሁለቱ ኮሪያ የገቡበትን ግጭት ለማርገብ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የቀረበላትን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ተቀብላ በውጤታማነት ካጠናቀቀች ወዲህ ስሟ በጉልህ ሲነሳ ቆይቷል። ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ኃይል ጋር በመሆኑ በኮሪያ ጦርነት ድልን ተቀዳጅታለች።
በዚህ ጦርነት ላይ የኢትዮጵያን ጀግንነት ዓለምን ያስደመመ ነበር። አንድም ወታደር ሳይማረክ ግዳጇን በሙሉ በጀግንነት አጠናቃ ተመልሳለች። ይህ ጦርነትም ኢትዮጵያውያን የጀግኖች ሀገር መሆኗን ዓለም እንዲያውቀው ከማድረጉም ባሻገር በመበታተን አደጋ ውስጥ የነበረችውን ሳውዝ ኮሪያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል እና ዛሬ ለደረሰችበትም የእድገት ደረጃ እንድትበቃ የኢትዮጵያ ሚና ወደር አልነበረውም።
በመቀጠልም በኮንጎ የሰላም ማስከበር ዘመቻ ኢትዮጵያ አምስት የሚደርሱ ኢሊኮፍተሮቿን እና የአየር ኃይሏን ጭምር በማንቀሳቀስ ውጤታማ ሰላም የማስከበር ተግባር አከናውና ተመልሳለች። እ.ኤ.አ ከ1960-64 የተካሄደው የኮንጎ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ሀገሪቱን ከእርስ በእርስ ጦርነት የታደገ እና ኮንጎ እንደ ሀገር እንድትቀጥል መሠረት የጣለ ነው። በዚህ የሰላም ማስከበር ሂደት ውስጥ ጠቅል ብርጌድ የሚል ስያሜ የተሰጠው የኢትዮጵያ የሠራዊት ክፍል ታሪክ ጽፎ ተመልሷል። ይህ ሚና ዓለም ሁልጊዜም የሚያስታውሰው ነው።
እ.ኤ.አ በ1993 በሩዋዳ መንግሥት እና በተቃዋሚ ኃይሉ መካከል በተነሳ ግጭት በርካታ ቀውስ ተፈጠረ። ንጹሃን ተገደሉ፤ የተረፉትም ተሰደዱ።
የተባበሩት መንግሥታትም ሁኔታውን ለማብረድ የሰላም አስከባሪ ኃይል በሩዋንዳ አሰማራ። ሆኖም የተሰማራው የሰላም አስከባሪ ኃይል በአግባቡ የሰለጠነ ባለመሆኑ በሁለቱ ኃይላት መካከል የተነሳውን ግጭት ማስቆም አልቻለም። ጭራሹንም የዘር ጭፍጨፋ ሲካሄድ ማስቆም ተሳነው፤ አልፎ ተርፎም የራሱን ሠራዊት ከእልቂት ማዳን አልቻለም።
ስለዚህም የጸጥታው ምክር ቤት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመገንዘብ ሁልጊዜም በጀግንነቱ የሚታወቀውን እና በሰላም ማስከበር ተግባሩ አንቱታን ያተረፈውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በሰላም አስከባሪነት እንዲሠማራ ውሳኔ አሳለፈ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትም የተሰጠውን ተልዕኮ አንግቦ በሩዋንዳ አደገኛ በሚባሉ ገጠራማ አካባቢዎችና መንደሮች ውስጥ ተሰማራ። በስምሪቱም በርካታ ነፍሶችን ከሞት አዳነ፤ ሴቶችና ሕፃናት ላይ ይደርስ የነበረውን ዕልቂት ታደገ። ለብዙዎችም ተስፋ ሆኖ ተገኘ። ዛሬ የአፍሪካ ኮከብ የሆነችው ሩዋንዳ ለበርካታ ዓመታት ጨለማ ጊዜያትን አሳልፋለች። በዓለም ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ የተካሄደባት ሩዋንዳ ከህመሟ እንድታገግም እና በሂደትም የተረጋጋች ሀገር እንድትሆን ኢትዮጵያ ትልቅ ሥራ ሠርታለች።
የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከምሥራቅ አፍሪካም ባሻገር ለምዕራቡም የአህጉሪቱ አካባቢዎች የተረፈ ነው። ተልዕኮ ከታደጋቸው ሀገራት መካከልም አንዷ ላይቤሪያ ስትሆን በወቅቱ ፕሬዚዳንት ሆነው የቆዩት ቻርለስ ቴለር ሥልጣን መልቀቅን ተከትሎ እ.ኤ.አ ከ1999 እስከ 2003 ድረስ ላይቤሪያ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገባች። በዚህ የእርስ በእርስ ጦርነት ብዙዎች ሕይወታቸው ተቀጠፈ፤ ሴቶች ተደፈሩ፤ በርካቶች አካባቢያቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዱ። በአጠቃላይ ላይቤሪያ የምድር ሲኦል ሆነች። በዚህ ወቅት እንደተለመደው የጸጥታው ምክር ቤት የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል በላይቤሪያ እንዲሰማራ ወሰነ። ለአፍሪካ ወንድሞቹ ምቹ የሆነው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሞትን ሳይፈራ አደገኛ በሚባሉ ቀጣናዎች ጭምር በሀገሪቱ ግዛት ተሰማራ። ከሞት ጋር ግብ ግብ ገጥሞም ላይቤሪያን ከእልቂት መታደግ እንደቻለ የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ።
የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት ከተሰማራ በኋላ በላይቤሪያ አንጻራዊ ሰላም ወረደ። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ወደ ቀያቸው ተመለሱ። ላይቤሪያ በሂደት የተረጋጋች ሀገር መሆን ቻለች። ባለፉት 15 ዓመታትም ሶስት ሰላማዊ ምርጫዎች ተካሂደው ሀገሪቱ ዴሞክራሲ ሽግግር ማድረግ ችላለች። ዛሬ ላይቤሪያ ኮሽታ የማይሰማባት ሀገር ለመሆን በቅታለች።
ኢትዮጵያ ከእነዚህ ሀገራት በተጨማሪ፤ በሱዳን፤ በሱማሊያ፤ በሩዋንዳ እና ቡርንዲ እንዲሁም በደቡብ ሱዳን የሰላም ማስከበር ዐሻራዋን አኑራለች። የተባበሩት መንግሥታት ከተቋቋመ ወዲህ በዓለም ላይ 46 የሚጠጉ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ተካሂደዋል። ከእነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ በ12ቱ በመሳተፍ በዓለም ላይ በሁለተኝነት እንዲሁም በአፍሪካ ቀዳሚውን ሥፍራ በመያዝ ዕውቅናን አግኝታለች።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላምና ደኅንነት ተቋም ዳይሬክተር የነበሩት የአሁኑ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)፤ እ.አ.አ. በ2018 ‹‹Africa in the Global Security Governance: A Critical Analysis of Ethiopia’s Role in the UN Peacekeeping Operations›› በሚል ርእስ ባስነበቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው፤ ‹‹… የተባበሩት መንግሥታት እ.አ.አ ከ1948 እስከ 2013 በዓለም ዙሪያ 67 የሰላም ማስከበር ዘመቻዎችን ማካሄዱን በመጥቀስ፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በዚህ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እ.አ.አ ከ1950ዎቹ እስከ 2017 በ12ቱ ተልዕኮዎች ውስጥ መሳተፏንና በአጠቃላይም እ.አ.አ. እስከ 2017 ድረስ 90 ሺህ የሚሆኑ የኢትዮጵያ ወታደሮችም በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ዘመቻ በመሳተፍ አኩሪ የጀግንነት ገድል መፈጸሟን ጠቅሰዋል።
የታሪክ መዛግብት እንደሚጠቁሙት፤ ኢትዮጵያ በዓለማችን ሰላም እንዲሰፍን ከተባለ ቃል-ኪዳን ሀገሮች ማኅበር /League of Nations/ እስከ ተባበሩት መንግሥታት /United Nations/ መቋቋም ድረስ ብቸኛ አፍሪካዊትና የጥቁር ሕዝቦች ተወካይ በመሆን ደማቅ የሆነ ዐሻራዋን አኑራለች። የአፍሪካ ሕዝቦች ሰላም፣ አንድነትና ወንድማማችነት እንዲሰፍን- የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን /Organization of African Union፣/ የአሁኑን የአፍሪካ ኅብረትን /African Union/ በማቋቋም ግንባር ቀደሙንና ትልቁን ሚና የተጫወተች ባለ ታላቅ ታሪክ ሀገር ናት።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሰሜን አሜሪካ እስከ ካረቢያና ጃማይካ፣ ከኮሪያ ልሣነ ምድር እስከ መካከለኛው ምሥራቅ፣ በአፍሪካ በኮንጎ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በኮትዲቯር፣ በብሩንዲ፣ በሩዋንዳና በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን በሰላም አስከባሪነት ጀግና ልጆቿን በመላክ ለአፍሪካና ለዓለም ሀገራት ሁሉ ትልቅ ባለውለታ ናት።
ከዚህ የታሪክ እውነታ ጋር ተያይዞም የተባበሩት መንግሥታት እ.ኤ.አ. በ2020 ባወጣው መረጃ መሠረትም፤ የአፍሪካ መዲና፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ- በአፍሪካና በመላው ዓለም ባደረገችውና አሁንም እያደረገችው ባለው ‘የሰላም አስከባሪነት’ የጎላ ተሣትፎዋ ምክንያት በአፍሪካ ‘የአንደኝነትን’፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ‘በሁለተኛነት’ ደረጃ አስቀምጧታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋዊ ድህረ ገጽ ላይ ሰፍሮ እንደሚታየው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት በመሰማራት ያደረገችውን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ እውቅና ሰጥቶት እናገኛለን። የተባበሩት መንግሥታት በሰጠው ዕውቅና ኢትዮጵያ የሕይወት መስዋዕትነትን ጭምር በመክፈል በተለያዩ ሀገራት ውጤታማ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርታ ውጤት አስመዝግባለች። ሰላም የሰፈነባት ዓለም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በማገዝ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
የምሥራቅ አፍሪካ በዓለም ላይ ያልተረጋጋ ከሚባሉትና ለሽብርተኞች መፈልፈያነት ምቹ ሥፍራዎች ናቸው ተብለው ከሚታወቁት አካባቢዎች አንዱ ነው። ኢትዮጵያ የምትገኝበት አካባቢያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ለሽብርተኝነት ተጋላጭ ቢያደርጋትም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ሽብርተኞችን እያሳፈሩ ሲመልሱ ቆይተዋል። በዚህ አኩሪ ተግባራቸውም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ከበሬታን አጎናጽፏቸዋል።
ኢትዮጵያ ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎንም ሽብርተኝነትን በመከላከል አኩሪ ታሪክ አላት። በሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የአልሻባብ ኃይል ለማስወገድ ሠራዊቷን ከሁሉ ቀድማ ያሰማራችው ኢትዮጵያም ነች። ሠራዊቱም በሀገሪቱ ከገባ ጀምሮ አልሻባብ እየተዳከመ በመምጣቱ ሕዝቡ ብሎም በቀጣናው አንጻራዊ ሰላም እንዲሰፍን አስችሏል። በዚህ አኩሪ ተግባሯም ኢትዮጵያ የቡድኑ ቀዳሚ ኢላማዎች ከሆኑት ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም፣ እስካሁን ድረስ ከሙከራ የዘለለ ይህ ነው የሚባል ጥቃትን ለመፈጸም አልቻለም።
ስለዚህም የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሕይወቱን ገብሮ በርካታ ሀገራት ሀገር ሆነው እንዲቀጥሉ እና የተሻለ ኢኮኖሚ እና የዲሞክራሲ ባሕል እንዲገነቡ የማይተካ ሚና ተጫውቷል። ኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ባይኖር ኖር በርካታ ሀገራት እንደ ሀገር የመቀጠል እድላቸው የመነመነ ይሆን ነበር።
ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ሩዋንዳ እና ላይቤሪያን የመሳሰሉ ሀገራት ዛሬ በተሻለ የሰላም ሁኔታ ውስጥ ከመገኘታቸውም በላይ በኢኮኖሚ ረገድም ከፍተኛ መሻሻል ያሳዩ ሀገራት ለመሆን በቅተዋል። ዘግናኝ የዕልቂት ታሪካቸው ተዘግቶ ዛሬ የሰላም ተምሳሌት እስከ መባል ደርሰዋል።
ለሰባ ሁለት ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ብዙዎችን ከጥፋት የታደገ እና ሰላም የሰፈነባትን ዓለም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ ያገዘ አኩሪ ተግባር ነው። የአፍሪካ ኅብረት የሰጠውም ዕውቅና በተገቢው ወቅት የተሰጠ ከመሆኑም በሻገር ላለፉት ለሰባ ሁለት ዓመታትም የኢትዮጵያ የሰላም ተልዕኮ አጋር ሆኖ የቆየው የተባበሩት መንግሥታትም ተመሳሳይ ዕውቅናዎችን መስጠቱ የሚታወስ ነው።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም