አማራጭ መፍትሄ- የድጋፍ መቋረጡ የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ

ዶናልድ ትራምፕ 47ኛ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ሆነው በቅርቡ በዓለ ሲመታቸውን ፈፅመዋል። “ቅድሚያ አሜሪካ” በሚል መርሃቸው የሚታወቁት ዶናልድ ትራምፕ ፣ከበዓለ ሲመታቸው በኋላ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት እንድትወጣ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ በዩ ኤ ስ ኤይድ በኩል ለታዳጊ ሀገራት የምታደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ለጊዜው እንዲታገድ ቀጭን ትእዛዝ ሰጥተዋል።

በዓለም ጤና ድርጅት በኩል አሜሪካ በተለይም ለታዳጊ ሀገራት የምታደርገው ድጋፍ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚወስድ ይነገራል። የአሜሪካ ከዚህ ግዙፍ ድርጅት መውጣት ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጤናው ዘርፍ ለታዳጊ ሀገራት የምታደርገው ድጋፍ በእጅጉ እንደሚቀንስ አጠያያቂ አይደለም። በተለይ ወትሮም ቢሆን በአሜሪካ ድጋፍ ላይ የተንጠለጠለው ኢትዮጵያን ጨምሮ ገና በእድገት ሀሁ ላይ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ጤና ዘርፍ ከዚህ የአሜሪካ ትእዛዝ በኋላ ትልቅ ውጣ ውረድ እንደሚገጥመው ይጠበቃል።

ኢትዮጵያም ብትሆን ከዚህ የዶናልድ ትራምፕ ከዓለም ጤና ድርጅት የመውጣት ውሳኔ ተፅእኖ ማምለጥ አትችልም። ከዚህ በፊት አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅት አባል በመሆኗ አብዛኛው የጤና ድጋፍ በቀጥታ ለታዳጊ ሀገራት ይውል ነበር። ይህም አሜሪካ በዓለም ጤና ድርጅት በኩል በተለይ ለታዳጊ ሀገራት የምታደርገው ሁሉን አቀፍ የጤና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማል።

አሜሪካ ከዓለም የጤና ድርጅት እንደምትወጣ ካሳወቀች በኋላ የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም በድርጅታቸው የሠራተኛ ቅጥር እንዲቆም ማድረጋቸውንና 8 ሺህ የሚደርሱ የድርጅቱ ሠራተኞችም አላስፈላጊ የሚባሉ ጉዞዎችን እንዳያደርጉ ማገዳቸው ተነግሯል። የዓለም ጤና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባላት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ላይ ዶክተር ቴዎድሮስ ከድርጅቱ ጋር ውል ከፈጸሙ ኮንትራክተሮች ጋር የዋጋ ድርድርም ይካሄዳል ማለታቸውም ተሰምቷል። በዚህ ድርድርም ከድርጅቱ ኮንትራት ከወሰዱት በኩል የተሻለ የክፍያ ቅነሳ ይገኛል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

አሜሪካ እስከዛሬ ከድርጅቱ በጀት አንድ አምስተኛውን ትሸፍን እንደነበረና ከድርጅቱ ስትወጣም ይህን ገገንዘብ ማን ሊሸፍን እንደሚችልም ግልጽ እንዳልሆነ እየተነገረ ነው። በትራምፕ እቅድ መሠረት ሀገራቸው ከጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ጥር 22 ቀን 2026 ዓ.ም አንስቶ ከዓለም የጤና ድርጅት አባልነት እንደምትወጣ ተነግሯል። በጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር 2025 አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት በጀት 18 በመቶውን እንደሸፈነችም መረጃዎች ያመለክታሉ።

የድርጅቱ አሃዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ደግሞ ዋሽንግተን እ.ኤ.አ በ2024 ዓ.ም ለኤች አይ ቪ እና ሄፐታይትስ መርሃ ግብር ከሚያስፈልገው በጀት 75 በመቶውን፤ ለቲቢ 61 በመቶ በድሃ ሀገራት የጤና ሥርዓቶችን ለማጠናከር ከሚያስፈልገው በጀት ደግሞ 29 በመቶውን ስትሰጥ እንደቆች ይነገራል። አሁን ዋነኛው ጥያቄ ‹‹አሜሪካን ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ስትወጣ የሚፈጠረውን ጉድለት የሚሸፍን ገንዘብ ከየት ይመጣል?›› የሚለው ሆኗል።

በሌላ በኩል የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (USAID) ዋና ቢሮ ሠራተኞች በቤታቸው እንዲቆዩ ትእዛዝ መተላለፉን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በቅርቡ ዘግበዋል። ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት አጀንሲን እየመሩ የሚገኙት “ፅንፈኛ የዘራፊዎች ቡድን ናቸው፤ ለዚያም ነው ለማባረር ውሳኔ የምናሳልፈው” ማለታቸውን ተከትሎ ሠራተኞቹ ወደ ቢሯቸው እንዳይመጡ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸውም ተነግሯል።

በፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር የመንግሥት ተቋማትን ሪፎርም ለማድረግ ሥልጣን የተሰጣቸው ቱጃሩ ኤለን መስክ ከውሳኔው በስተጀርባ ቁልፍ ሚና እንዳላቸውም እየተገለፀ ይገኛል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የዩ ኤስ ኤይድ ዋና ዓላማ “ለሌሎች ሀገራት ርዳታ መስጠት ሳይሆን የአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም ለማሳካት አጋዥ ሚና መጫወት ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

ድርጅቱ ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት እና ብሄራዊ ጥቅም መሳካት የሀገሪቱ አንድ በመቶ በጀትን ተጠቅሞ እየሠራቸው የሚገኙ ሥራዎች በትራምፕ አስተዳደር ተቀባይነት እንደሌላቸውም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል። አሁን ድርጅቱን እየመራ ያለው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዩ ኤስ አይ ዲን በፌዴራል ተቋማትንና በቢሮዎች ላይ ለውጥ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ኮንግረስንና ሌሎች ሕጋዊ አካላትን በማማከር እንደሚወስን አስታውቋል።

አሜሪካ በዓለም ጤና ድርጅት በኩል በተለይ ለአፍሪካ ሀገራት ለበሽታ መከላከል ሥራዎች ዳጎስ ያለ ገንዘብ በርዳታ ታፈሳለች። የተለያዩ ክትባቶችን፣ የህክምና መሣሪያዎችንና ሌሎች ለጤናው ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ ሙያዊ ድጋፎችን በማድረግ ረገድም ሚናዋ የጎላ ነው። አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ታዲያ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነቷ የምትወጣ መሆኑ እርግጥ ከሆነ በዚህ የአሜሪካ ድጋፍ ላይ ተንጠልጥለው የቆዩ ሀገራት ሌላ አማራጭ መንገድ መፈለግ እንዳለባቸው ይታመናል።

ኢትዮጵያም የዚሁ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትእዛዝ ተፅእኖ ተጋላጭ ናትና ከዚህ ውሳኔ ተፅእኖ ለመላቀቅ የራሷን መፍትሔ መፈለግ ይጠበቅባታል። በርግጥ አሜሪካ ለጤናው ዘርፍ ከምታደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍ በቀላሉ መላቀቅ እንደማይቻል ይታወቃል። ነገር ግን ለዚህ ውሳኔ የአጭርና የረጅም ጊዜ መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል።

የአጭር ጊዜ መፍትሄ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ውሳኔው እንዲዘገይ ከአሜሪካ ጋር በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ጥረት ማድረግ ነው። ለዚህ ምሳሌ ተደርጎ የሚወሰደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ባሳለፉት ውሳኔ ምክንያት በጎረቤት ሀገራቱ ካናዳና ሜክሲኮ ላይ የጣሉት ተጨማሪ የ25 በመቶ የንግድ ታሪፍ በሀገራቱ መካከል በተደረገ ድርድር ለ30 ቀናት እንዲራዘም መደረጉ ነው። ኢትዮጵያ ይህንን ስልት ብትጠቀም የአጭር ጊዜ መፍትሄ መሆን ይችላል።

ከአማራጮች ውስጥ አንዱ የአጋር ሀገራትን ወዳጅነት ማጠናከር ይገኝበታል። እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ከቻይና፣ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ እና ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት አላት። ከሀገራቱ ጋር በድጋፍ፣ በትብብርና በልዩ ልዩ መስኮች ላይም ትሠራለች። ይህንን አጋርነት በጤናው ዘርፍ ላይ በማድረግ ሀገራቱ የኢትዮጵያን እቅዶች እና ፕሮጀክቶች እንዲደግፉ በዲፕሎማሲ ጥረት ማግባባት ያስፈልጋል።

ሌላው የጤናው ዘርፍ አጋር ሊሆን የሚችለው አውሮፓ ህብረት ነው። ህብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች እንደሚሠራ ይታወቃል። በመሆኑም ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ለመሙላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን ጨምሮ የአጋርነት ስምምነቶችን ማድረግ ያስፈልጋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ለምሳሌ UNAIDS, WHO) ጋር በጤናው ዘርፍ ስምምነቶችን ማድረግ ያስፈልጋል።

ሌላው ዘላቂ የሆነው መፍትሄ የመንግሥት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት፣ የአካባቢ ማህበረሰብ ተሳትፎ፣ የሲቪክ ማህበራትን ማጎልበትና ማደራጀት ነው። የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ድጋፍ እንደሚያሻው የሚያስገነዝቡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት መሳብ ተጨማሪ መፍትሄ ነው። ይህንን ማድረግ መቻል አጋር አካላት ትኩረት እንዲሰጡና ክፍተቱን ለመሙላት እንዲሠሩ ገፊ ምክንያት ይሆናል።

በመጨረሻም ለአጭር ጊዜ መንግሥት ከአጋር አካላት ለጤናው ዘርፍ ቀጥተኛ ድጋፍ ማግኘት ቁልፍ ቢሆንም በረጅም ጊዜ እቅድ ግን ይህንን ማስቀረት ይኖርበታል። መንግሥት የራሱን የልማት ሞዴል በመገንባት በውጪ ርዳታ ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነስ ቀዳሚው ሥራ ሊሆን ይገባል።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You