የምግብ ሉዓላዊነትና የአፍሪካውያን ቁርጠኝነት የላቀ ሚና

የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲናዋ አዲስ አበባ ከሰሞኑ ካስተናገደቻቸው ጉባዔዎች መካከል በመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አዘጋጅነት የተካሄደው ጉባዔ ይጠቀሳል። ይህ ‘የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባዔ 2025’ በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደ ጉባዔ በዓይነቱ ልዩና የመጀመሪያው መሆኑም ተነግሮለታል። በጉባዔው ላይ የአፍሪካ ሀገራት የቀድሞ መሪዎች፤ በዓለምአቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የዘርፉ ምሁራን፣ ተመራማሪዎችና የመንግሥታት ተወካዮች ተሳትፈዋል።

ጉባዔው የአየር ንብረት ተለዋዋጭነትን በመቋቋም የተሻለ የኑሮ ዘይቤ እና የመስኖ ልማትን ለማጎልበትና ዓለምአቀፋዊ ልምድና ተሞክሮዎችን ለመቀመር ብሎም ጠንካራ የመስኖ ሥርዓቶችን መተግበር ላይ ማዕከል ያደረገ ነው። ለሁለት ቀናት በተካሄደው በዚሁ የውይይት መድረክ የሀገራት የመስኖ ልማት እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀቀም ተሞክሮዎችን የሚያሳዩ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን፣ በተለይም የአፍሪካ ሀገራት ሰፊ የውሃ ሀብታቸውን ጥቅም ላይ በማዋል ዜጎቻቸውን ከተረጂነት ማላቀቅና የአሕጉሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት ማስከበር በሚችሉባቸው አንኳር ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተደርጓል።

በሌላ በኩል የጉባዔው በኢትዮጵያ መዘጋጀት ሀገሪቱ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረገጋጥ የምታደርገውን ሰፊ ርብርብ በማገዝ ረገድም የጎላ ሚና እንዳለው ተጠቁሟል።

ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት መፍጠር ለአንድ ሀገር ልዕልና ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ጉባዔው የኢትዮጵያን የወደፊት የምግብ ሉዓላዊነት በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬን በመፍጠርና የዘርፉን መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋልም ተብሏል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የመስኖ አውታሮችን ለማስፋፋት በመንግሥት ከፍተኛ ጥረት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው። ይሁንና ዘርፉ ከሚጠይቀው የፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ዕውቀት አንፃር ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በዚህ አይነት ዓለምአቀፋዊ ጉባዔዎች አማካኝነት ፋይናንስ አቅራቢዎችን ለማስተባበር፣ የመንግሥት እና የግሉን ዘርፍ ጥምረት በማጎልበት የማህበረሰቡን፣ የሴቶች እና ወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማስፋፋት ትልቅ ድርሻ እንዳለውም በመድረኩ ተመላክቷል።

እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊነትና ጫና በዘላቂነት በመቅረፍ የውሃ ሀብትን በአግባቡ ለማስተዳደር፣ የመስኖ ልማትን ለማስፋፋትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በመንግሥት በኩል ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው። ከእነዚህ ጥረቶች አንዱ የሆነው ግብርናው ከዝናብ ጥገኛነት እንዲላቀቅ ማድረግ ሲሆን፣ ለዚህም የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት ተልዕኮ ወስዶ እየሠራ ይገኛል።

ጉባዔው ከዓለምአቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎች ለመማር እና እነዚህን ልምዶች ለመቅሰም እና ተግባራዊ ለማድረግ እድል የሚፈጥርና የመስኖ ልማት ዘርፍን በእጅጉ የሚያጎለብት እንደሚሆንም ታምኖበታል። ዓለም አቀፋዊ ትብብር የሚፈጠርበት ሲሆን፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ባለድርሻ አካላት ዕውቀትና ግንዛቤ የሚያሳድጉበትና የሚወያዩበት መድረክ ነው።

ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የመስኖ ስልቶችን፣ ውሃ ቆጣቢ ቴክኖሎጂዎችን የሚተዋወቁበት፣ ተለዋዋጭ የሆነውን የአየር ንብረት ለመቋቋም የሚሠሩ ሥራዎችን ለሌሎች ልምድ የምታካፍልበት ሁነት ሆኖ አልፏል። በተጨማሪም ሀገሪቱ አዳዲስ የፋይናንስ አማራጮችን የምታይበት፣ ትኩረት የተነፈጉ የማህበረሰብ ክፍሎችን በንቃት የሚሳተፉበትና በመስኖ ልማት ተጠቃሚ የሚሆንበት ዕድል የሚፈጠርበት እንደሆነም ተመላክቷል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በመድረኩ ላይ እንደተናገሩት፤ አሕጉሪቱ ያላትን እምቅ የመስኖ አቅም በመጠቀም የግብርናውን ዘርፍ ሽግግር ለማሳለጥ ሁሉም ሀገራት ተቀናጅተው መሥራትና የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆን ይገባቸዋል።

አፍሪካ ሰፊና ለዓለም የሚበቃ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ብትሆንም በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተለይም በግብርናው ምርትና ምርታማነት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እየደረሰባት ይገኛል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በዋናነትም ዜጎቿ ተፅዕኖውን መቋቋም ተስኗቸው ለከፋ ችግር የሚጋለጡበት ሁኔታ እየሰፋ መጥቷል ብለዋል። ይህንን ችግር በዘላቂነት ለማስቀረት፤ ምርታማነትን ለማጎልበትና የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ የሀገራቱ መንግሥታት በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ በተለይም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ( ዶ/ር) ቁርጠኛ መሪነት እየተገበረቻቸው ያሉት የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የስንዴ መስኖ ልማትና የሌማት ቱሩፋት መርሃግብሮች የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ስርነቀል በሆነ መልኩ ለማሳደግ እያስቻሉ መሆናቸውን ፕሬዚዳንት ታዬ ይናገራሉ።

‹‹መንግሥት ቆራጥ አመራር በመስጠትና ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሥራ በመሥራቱ ኢትዮጵያ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ውጤት እያመጣች ትገኛለች›› ሲሉ ገልጸው፣ በተለይም የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን ተፅዕኖ ከመከላከል፤ የደን ሽፋኗን ከማሳደግ ባለፈ የሚሊየኖችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም ከፍተኛ አቅም እየሆነ መምጣቱን ያብራራሉ።

በሌላ በኩል የስንዴ መስኖ ልማት መርሃግብርን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መተግበር በመጀመሯ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከስንዴ አስመጪነት ወደ ራስን ችሎ አምራችነት መብቃት መሸጋገሯን ተናግረዋል። ‹‹ይህ ስኬት አፍሪካም ያላትን እምቅ አቅም በመጠቀም የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ እንደምትችል ትልቅ ማሳያ ነው›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ውጤቱ የተገኘው የተጠና እና በቴክሎጂ በተደገፈ የመስኖ ልማት ፣ በሜካናይዜሽንና በተሻሻለ የግብርና አመራረት ሥርዓት በመዘርጋቱ እንደሆነም ያስገነዝባሉ።

በተመሳሳይ ሀገሪቱ እየተገበረች ያለችው የሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር የዜጎቿን የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ፍትሃዊ የምግብ ተደራሽነት እንዲኖር፣ የአርሶአደሩን የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግና ሰፊ የሥራ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህ ስኬት ሊመጣ የቻለው ሀገሪቱ ለመስኖ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠትና በጀት መድባ በመሥራቷ ነው›› ብለዋል። የመስኖ ልማት በሀገሪቱ በከፍተኛ መጠን እያደገ ከምማጣቱ ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም በአርብቶ አደርነት በሚታወቁ የሀገሪቱ አካባቢዎች በቴክሎጂ በዘመኑ የመስኖ ልማት ሥራዎችን በስፋት ማካሄድ በመቻሉ የአርብቶ አደሩን አቅምና ምርታማነት ለማጎልበት መቻሉንም ጠቅሰዋል። ምርታማነት በማደጉም ለኢንዱስትሪው ሰፊ ግብዓት ለማቅረብና የሥራ እድል ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ያስረዳሉ።

በመሆኑም ይህንን የኢትዮጵያ ምርጥ ተሞክሮ መላው አፍሪካ ተግባራዊ በማድረግ የሕዝቦችን የምግብ ዋስትና ተደራሽነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ‹‹በዋናነትም የግብርናውን ምርታማነት ዘላቂ ለማድረግ የመስኖ ልማት ኢንቨስትመንትን ማስፋፋትና መዋለንዋይ ማፍስስ ይገባል›› ብለዋል።

የመስኖ መሠረተ ልማትን ለማሳደግ የአጋር አካላትና የግሉ ዘርፍ ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበው፣ ለዚህም በሀገራቱ መካከል ምርጥ ተሞክሮ መለወጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ። ይህም የመሪዎችን ቁርጠኝነት ፣ ጠንካራ ትብብር የሚሻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ ዶ/ር በበኩላቸው፤ ‹‹የአየር ንብረት ለውጥ ከሩቅ ሆነን የምንጠብቀው ስጋት ሳይሆን አሁን ላይ የተጋፈጥነው ችግር ነው›› ሲሉ አስገንዝበዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖውን መቋቋም የሚችል የግብርና ሥርዓትን ለመፍጠር ሁሉም ሀገራት ተቀናጅተው ሊሠሩ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ በመላው አፍሪካ የዝናብ እጥረት፣ የተራዘመ ድርቅ፣ ከፍተኛ አደጋ የሚፈጥር ጎርፍ በየጊዜው እያደገና እየተለመደ የመጣ ጉዳይ ነው፤ በዚህም ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ጥያቄ ውስጥ የገባበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

ይሁንና ሀገራቱ የግብርና ፖሊሲዎቻቸውን የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም በሚያስችል መልክ ከቃኙና ያለውን እምቅ የመስኖ አቅም ጥቅም ላይ ለማዋል በቁርጠኝነት ከሠሩ የዜጎቻቸውን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ብሎም ኢኮኖሚውን ቀጣይነት እውን ለማድረግ የሚያስችል ሰፊ እድል እንዳለም ሚኒስትሩ ያመለክታሉ፡፡

በዚህ ረገድ እንደ ሞሮኮ ፣ ህንድ፣ እስራኤል አውስትራሊያ ያሉ ሀገራት የመስኖ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና ከፍተኛ ፋይናንስ በመመደብ በዓለም ላይ ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ ካሳደጉ ሀገራት መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥትም ለመስኖ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ እምርታ ማስመዝገብ ችሏል›› ብለዋል።

የአፍሪካ ሀገራት በመስኖ ልማት ያላቸውን ተሞክሮ፣ ፈጠራ የታከለባቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች፣ ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ በዘርፉ በቂ ፋይናንስ በመመደብ የአሕጉሪቱን ግብርና ሽግግር እውን ማድረግ እንደሚገባቸው ይጠቁማሉ። በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ የመስኖ ልማትን ለማዘመን ፋይናንስ የዘርፉ ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንን ችግር ለመፍታት የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነም ይገልፃሉ።

በአፍሪካ ህብረት የግብርና ፣ ገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ የአካባቢ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፍ ሳኮ እንደተናገሩት፤ በአፍሪካ እየጨመረ የመጣውን ሕዝብ ለመመገብ የመስኖ ልማትን ማዘመንና ማስፋፋት ይገባል። ለዚህም በዋናነት የአፍሪካ ሀገራት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርና ለመገንባት እና ከተረጂነት የተላቀቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ድርቅን ጨምሮ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መቋቋም የሚችል የግብርና ሥርዓት ለመዘርጋት የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር አለባቸው።

ድርቅን ጨምሮ የተፈጥሮ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን መቋቋም የሚችል የግብርና አሠራር ለመተግበር የተጀመሩ ሥራዎች መስፋት እንዳለባቸው ኮሚሽነሯ አስገንዝበዋል፤ አፍሪካ ለእርሻ ሥራ ሊውል የሚችል ሰፊ መሬት፣ ጥቅም ላይ የሚውሉ በርካታ የውሃ አማራጮች ባለቤት መሆኗን ጠቅሰው፣ ሁለቱን ሀብቶች በማጣመር ልማቷን ማፋጠን ከሁሉም ሀገራት እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። ዓለም የሠለጠነባቸውን የመሰኖ ቴክሎጂዎች በመጠቀም የመስኖ መሠረተ ልማቶችን ማስፋፋት ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከሚሽነሯ እንዳብራሩት፤ እ.ኤ.አ የአሕጉሪቱ ሕዝብ ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል፤ በመሆኑም ይህንን የሕዝብ ቁጥር በአግባቡ ሊመግብ የሚችል በቂ ምርት ለማግኘት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይገባል። በዚህ ረገድ ኮሚሽኑ የተለያዩ የስትራቴጂ እና የድርጊት መርሃ ግብሮችን ቀርፆ እየተገበረ ይገኛል። በአፍሪካ ከርዳታ ጥገኝነት የወጣ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሁሉም ሀገራት በትብብር መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በጉባዔው በተካሄደው የፓናል ውይይት የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፤ ኢትዮጵያም በፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አስፋ ዶ/ር በኩል በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ምርታማነት ረገድ እያከናወነቻቸው ባለቻቸው የልማት ሥራዎች ዙሪያ ለታሳፊዎቹ ማብራሪያ ሰጥታለች። ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር ዘላቂ ልማት ለማምጣት አቅዳ በተገበረቻቸው የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የሌማት ቱሩፋትና የስንዴ ልማት ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ መቻሏን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ እስከ አሁን 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የሀገሪቱን የደን ሽፋን ስድስት በመቶ ማሳደግ ችላለች። የሚተከሉት ችግኞች ለምግብና ሥርዓተ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ ወሳኝ ሚና ያላቸው እንደ አቮካዶ ያሉ ፍራፍሬዎች በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው ዘርፈ ብዙ እየሆነ መጥቷል። ከዚህም ባሻገር ሀገሪቱ በስንዴ ራሷን በመቻል ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርትን በመቀነስ እና ሀገራዊ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።

በሌላ በኩል የሌማት ቱሩፋት መርሃግብር ኢትዮጵያ የምግብ አቅርቦትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ እያደረገላት መሆኑን ሚኒስትሯ አመልክተው፤ ከዚህም የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ ሊወስዱ እንደሚገባ አስታውቀዋል። ‹‹ንቅናቄዎቹ ለአፍሪካ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ምርጥ ተሞክሮ ናቸው›› በማለት ጠቅሰውም፤ ሀገሪቱ በዘርፉ የምታከናውናቸው ሥራዎች ለአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ወሳኝ ሚና ያላቸው መሆናቸውንና ይህንንም አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

ጉባዔው የአፍሪካ ሀገራት የመስኖ ልማት ሂደት ምን እንደሚመስል፤ በተለይም የቴክሎጂ አጠቃቀማቸው፤ የመሠረተ ልማት ዝርጋታና እነዚህን መሠረተ ልማቶች በመዘርጋት ረገድ ያለባቸው የፋይናንስ እጥረት ጉዳይ ተነስቶ በስፋት ውይይት ተደርጎባቸዋል። የአሕጉሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ በማሳደግ የመስኖ መሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት አቅምን ማጎልበት ይገባል ሲሉም ተወያዮቹ አፅዕኖት ሰጥተው መክረውበታል።

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You