
አዲስ አበባ ፦ የአፍሪካ ኅብረት ለአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ እንዲፈታ ግፊት እያደረገ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላምና ደኅንነት ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶዬ ገለጹ። በአፍሪካ ሀገራት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ከፕሪቶሪያው ስምምነት ትምህርት ሊወሰድበት እንደሚገባ አመለከቱ።
አምባሳደር ባንኮሌ በአሕጉሪቱ ስላለው የሰላም፣ ደኅንነትና የዴሞክራሲ ስርፀት ለመገናኛ ብዙኃን ትናንት በሰጡት መግለጫ፤ በመላው አሕጉሪቱ ከሰላምና ደኅንነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አመልክተዋል። የአፍሪካን ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሔ ለመፍታት ኅብረቱ ግፊት እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል ።
በኮንጎ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን፣ ሳሕል፣ ሊቢያ፣ ሞዛምቢክ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ጠቁመው፤
በኮንጎ ሪፐብሊክና በሱዳን ከሚስተዋለው ግጭት ጋር ተያይዞ በኅብረት የሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት ውይይቶች መደረጋቸውን አመልክተዋል። በኮንጎ ሪፐብሊክ ባለው ግጭት እየተሳተፉ ያሉ አካላት ችግራቸውን በውይይት እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረቡንም አስታውቀዋል።
በሱዳን ከዓመታት በፊት ኢ-ሕገመንግሥታዊ በሆነ መልኩ የመንግሥት ለውጥ በመደረጉ ከአፍሪካ ኅብረት አባልነት መታገዷን አስታውሰው፤ በግጭቱ ተዋናዮች መካከል ፖለቲካዊ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በግጭቱ የንፁሓን ግድያ፣ የፆታዊ ጥቃትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተስተዋለ ነው ያሉት አምባሳደር ባንኮሌ፤ ለችግሩ ከውይይት በዘለለ ምንም ዓይነት ወታደራዊ መፍትሔ ሊኖር እንደማይችል አስገንዝበዋል።
ኅብረቱ በሞዛምቢክና በሊቢያ እየተስተዋለ ያለውን ግጭት በመፍታት ሁሉን አቀፍ ሰላም ለማምጣት በቅርበት እየሠራ እንደሆነም አመልክተው ፤ ኅብረቱ በመላው አፍሪካ የሚስተዋሉ ግጭቶች ሁሉን አካታች ምክክሮች ተደርገው መፍትሔ እንዲያገኙ ፍላጎት እንዳለው፤ ለዚህም ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትና የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት በሶማሊያ ያለውን ግጭት ለማብረድ ሚናቸውን እየተጫወቱ ነው። ከኅብረቱ የሰላም ፈንድ 10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ተደርጓልም ብለዋል፡፡
አፍሪካዊ ችግሮችን ለመፍታት በሕወሓትና በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት መካከል የተደረገው የፕሪቶሪያው ስምምነት ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል ።
ባለፈው ዓመት በጋና፣ ቦትስዋና፣ ሴኔጋልና ሞሪሽየስ ምርጫ በማካሄድ ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር የተደረገባቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል ።
ኅብረቱ በአሕጉሪቱ ሰላም ለማምጣት ለሚያደርገው ጥረት ስኬት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም