
ዜና ሀተታ
ሰላሟና ፀጥታዋ የተጠበቀ፣ በምጣኔ ሀብት ያደገችና ማኅበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ውህደት ያላት አፍሪካን እውን የማድረግ ኃላፊነትን ከቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተረከበው የአፍሪካ ኅብረት ኃላፊነት ነው::
ኅብረቱ ይህን ዓላማ እንዲያሳካ ተቋማዊ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተወስኖ ሥራ ከተጀመረ ዘጠኝ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ተቋማዊ ማሻሻያው የአፍሪካ ኅብረት ለሚገጥሙት ፈተናዎች አስተማማኝ መፍትሔ በመስጠት ኅብረቱ ለ‹‹አጀንዳ 2063›› ስኬት የመሪነት ሚና እንዲኖረው ያስችለዋል ተብሎ ታምኖበታል::
ተቋማዊ የማሻሻያ አጀንዳው ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በሂደቱ ውስጥ ስኬት የተገኘባቸው ተግባራት መኖራቸው ባይካድም፣ ከአህጉሪቱ እምቅ አቅም፣ ከኅብረቱ ትልቅ ርዕይ እና ከአፍሪካውያን ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር የማሻሻያ ትግበራው በሚጠበቀው ልክ እየተጓዘ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ተገልጿል::
አፍሪካ በሰውና በተፈጥሮ ሀብት የታደለች አህጉር የመሆኗ፣ የአፍሪካ ኅብረት ትልልቅ ኃላፊነቶችንና ዓላማዎችን የመያዙ እንዲሁም በርካታና አሳሳቢ የሆኑ ዘርፈ ብዙ ችግሮች በአፍሪካውያን ላይ የመጋረጣቸው እውነታዎች የኅብረቱን ተቋማዊ የማሻሻያ አጀንዳ እጅግ አስፈላጊ እና በፍጥነት ሊጠናቀቅ የሚገባ ያደርጉታል:: ተቋማዊ የማሻሻያ አጀንዳው እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ መከናወን እንዳለበት አፍሪካውያን መሪዎችና ምሁራን ይገልጻሉ::
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በቅርቡ በናይሮቢ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት፣ ኅብረቱ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ውስብስብ ችግሮች ውጤታማ ምላሽ የሚሰጥ ጠንካራ፣ የተዋሃደና ስኬታማ ተቋም ሊሆን ይገባል:: ለዚህ ደግሞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ፖለቲካዊ ቁርጠኛነት የሚታይበት ተቋማዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል::
አዲሱ የዓለም ጂኦፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ከባቢ የኅብረቱን ተቋማዊ ማሻሻያ እጅግ አስፈላጊ እንደሚያደርገው ጠቁመው፤ ‹‹የአፍሪካ ኅብረት ራሱን ችሎ የሚቆመው 75 በመቶ በጀቱንና 25 በመቶ የሰላም ማስከበር ድጋፍ ተልዕኮዎችን ለማሟላት ያስቀመጥናቸውን ግቦች ማሳካት ስንችል ብቻ ነው:: ማሻሻያውን የኅብረቱ የህልውና ዋስትና ጉዳይ አድርገን መመልከት አለብን›› ብለዋል::
ተቋማዊ ማሻሻያውን በስኬት በመፈፀም የኅብረቱን አቅምና ዓላማ ሙሉ በሙሉ እውን ለማድረግ፤ አካታችነትን ማረጋገጥ፣ የፋይናንስ ሉዓላዊነትን ማስከበር፣ የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳዎችን ማስቀደምና ማደራጀት፣ ጠንካራ የምክክር ባሕልን ማዳበር እና በዓለም አቀፍ መድረኮች የኅብረቱን አጀንዳዎች ጥንካሬና ተሰሚነት ማሳደግ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንደሆኑ አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የኅብረቱን የአሠራር ዘዴዎች ማሻሻል የሥራ ቅልጥፍናን በማረጋገጥ ለተቋማዊ ማሻሻያው ስኬታማነት ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አመልክተዋል::
እንደ ፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ፣ የአካታችነት መርህ የኅብረቱ አባል ሀገራትና ባለድርሻ አካላት አበርክቶዎች በማሻሻያው ሂደት ውስጥ ተገቢውን ቦታ እንዲያገኙ ያስችላል:: ለኅብረቱ በራስ አቅም አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ መፈለግ ወሳኝ ተግባር ነው:: ለዚህም አህጉራዊ የግል ዘርፍ ኢንቨስትመንትን ማበረታታትን እንደ አንድ አማራጭ መጠቀም ይቻላል::
በአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ ሂደት ውስጥ በተሠሩ ሥራዎች አንዳንድ ውጤቶች ተገኝተዋል:: ለዚህም የኅብረቱን ቁልፍ ተቋማት የማደራጀት ተግባራት ተጠቃሽ ናቸው:: በዚህ ረገድ ፕሬዚዳንት ታዬ ‹‹ስብስባዎቻችንን አስተካክለናል፤ ኮሚሽኖችን ሪፎርም አድርገናል፤ ቁልፍ የኅብረቱን ተቋማት አሠራራቸውን ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አሻሽለናል›› በማለት ለጥረቶቹ እውቅና መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል::
የአፍሪካ ኅብረት የሚመራቸውን የሰላም ማስፈን ተልዕኮዎች ለማስፈፀም የሚውሉ ዘላቂ የገንዘብ ምንጮችን ለማግኘት የተጀመሩ ጥረቶችን አድንቀው፤ የኅብረቱን የሰላም ማስፈን ተልዕኮዎች የሚያስተባብር ጠንካራ መዋቅራዊ አደረጃጀት እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል:: ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ተቋማዊ ማሻሻያ አጀንዳ ስኬታማ ትግበራ ቁርጠኛ እንደሆነችም ፕሬዚዳንት ታዬ ተናግረዋል::
በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ የብሉ ኢኮኖሚ እና የዘላቂ አካባቢ ልማት ኮሚሽነር ጆሴፋ ሊዮን ኮሬያ ሳኮ በበኩላቸው እንደሚገልጹት፤ ኅብረቱ ከለጋሾች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ጥገኛ መሆኑ ትልቅ ፈተና ሆኖበታል:: ምንም እንኳን መጠነኛ እድገት ቢያሳይም አባል ሀገራት ለኅብረቱ እቅድ ማስፈጸሚያዎች የሚያበረክቱት የገንዘብ ድጋፍ አሁንም እጅግ አነስተኛ እንደሆነና በርካታ አባል ሀገራት ለዓመታዊ መዋጮ ክፍያ ውዝፍ እዳ እንዳለባቸው ይገልጻሉ:: 75 በመቶ የሚሆነው የገንዘብ ድጋፍ የሚገኘው ከውጭ አጋሮች በተለይም ከአውሮፓ ኅብረት እና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው። የአፍሪካ ኅብረትን ፋይናንስ ለማድረግ ቀደም ሲል የተወሰኑትን ውሳኔዎች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ይናገራሉ::
‹‹ኅብረቱ አብዛኛውን ገቢ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ኅብረት በርዳታ የሚያገኝ መሆኑ በራሱ አንዱ ተግዳሮት ነው›› የሚሉት የፐብሊክ ፖሊሲ ባለሙያው ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር)፤ እስካሁን አጥጋቢ ውጤት ባይገኝባቸውም አፍሪካን ለማቀናጀት የጀመራቸውን በተለይም አህጉሪቷን በንግድ የማስተሳሰር ሙከራዎችን የበለጠ በማጠናከር ጠንካራ አፍሪካዊ ተቋም መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ::
ኅብረቱ እነዚህን ችግሮች መፍታት ሲችልም ጠንካራ፣ ተሰሚነት ያላት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነባች አፍሪካን እውን ለማድረግ መንገዱ የተቃናና ግቦቹ የሰመሩ ይሆንለታል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም