ሃማስ በተሰጠው ቀነ-ገደብ ታጋቾችን እንዲለቅ እስራኤል አስጠነቀቀች

ሃማስ ያገተብኝን ሰዎች እስከ መጪው ቅዳሜ የማይለቅ ከሆነ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ለመሻር እገደዳለሁ ስትል እስራኤል አስጠነቀቀች።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ ባስተላለፉት መልእክት፤ ሃማስ እስከ መጪው የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም እኩለ ቀን ድረስ ያገታቸውን ሰዎች የማይለቅቅ ከሆነ እስራኤል ስምምነቱን ሰርዛ ወደ ጦርነት ትገባለች ብለዋል።

ሃማስ በበኩሉ ለተኩስ አቁም ስምምነቱ ተግባራዊነት ይሁንታ ማሳየቱን አስታውቆ ፤ እስራኤል ወደጋዛ የሚገባ ሠብዓዊ ርዳታ ማገድን ጨምሮ ወሳኝ የሚባሉ ቁልፍ ስምምነቶችን ጥሳለች ሲል ኮንኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ኔታንያሁ የሃማስን ወቀሳ አስተባብለው፤ የእስራኤል ታጋቾች የሚለቀቁበት ጊዜ መራዘሙን ተከትሎ ጋዛ እና አካባቢው ጦራቸው እንዲዘምት ማዘዛቸውን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት በመጪው ቅዳሜ ሶስት ታጋቾች ይለቀቃሉ የተባለ ቢሆንም እስራኤል እየጠበቀችው ያለው በሃማስ ቁጥጥር ስር ያሉ ሰባ ስድስት የሚደርሱ ታጋቾችን እንደሆነ በእስራኤል የሚገኙ ከፍተኛ ሚኒስትር ተናግረዋል። ሃማስ ሶስት ሳምንታት የሚፈጀውን የመጀመሪያ ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት በማወሳሰብ እና በማዘግየት ለዚህም ተጠያቂዋ እስራኤል ናት የሚል ምላሽ መስጠቱ ተአማኒነት የሌለው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሃማስ በቁጥጥሩ ሥር የሚገኙትን የሶስቱን ታጋቾች መልቀቂያ ጊዜ ለማዘግየት መወሰኑን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል የገባችውን የተኩስ አቁም ስምምነት ሙሉ በሙሉ መሰረዝ አለባት ሲሉ ተደምጠዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሃማስ ሥር ያሉ ሁሉም ታጋቾች እስከ መጪው የካቲት ስምንት ድረስ ካልተለቀቁ ጦርነቱ እንዲቀጥል መመሪያ አስቀምጠዋል፡፡

በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰፍኖ የነበረው አንጻራዊ ሰላም ለዳግም ጦርነት አቧራውን እያነሳ እንደሆነ ከሁለቱም ወገን የሚሰሙት ድምጾች እያመላከቱ ይገኛሉ። አራት ሰዓታትን የፈጀውን የእስራኤልን የጸጥታ ካቢኔ ስብሰባ ተከትሎ የአሜሪካው አቻቸው ያስተላለፉትን መልዕክት እንደሚደግፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት አረጋግጠዋል፡፡

አክለውም ሃማስ የተኩስ አቁም ስምምነቱን በመጣስ እና ታጋቾችን ላለመልቀቅ የያዘውን ጠብ አጫሪ አቋም ተከትሎ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በጋዛ ሰርጥ ውስጥ እና በአካባቢው እንዲሰማራ በትናንትናው እለት ትዕዛዝ ሰጥቻለው ሲሉ ተደምጠዋል። ይህ ርምጃ በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በአጭር ጊዜም ይጠናቀቃል ብለዋል። ዜጎቻቸው እስካልተለቀቁ ድረስ ጦርነት ለመጀመር ያላቸውን ቁርጠኝነት በገለጹበት ወቅት ፤ ካቢኔያቸው በውሳኔያቸው ይሁንታን እንዳሳየ አያይዘው ገልጸዋል።

እስከ ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ታጋቾችን እንዲለቅ ቀነ ገደብ የተቀመጠለት ሃማስ ያን ማድረግ ከቻለ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ይቀጥላል፤ ያን ማድረግ ካልቻለ ግን የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተሽሮ ቡድኑ እስኪረታ ድረስ ጠንካራ ውጊያ ለማድረግ እንደተዘጋጁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

እስካሁን ድረስ ሃማስ አስራ ስድስት የሚሆኑ ታጋቾችን ሲለቅ እስራኤል በበኩሏ በእስር ላይ የነበሩ አምስት መቶ ስልሳ ስድስት ፍልስጤማውያንን ለሃማስ አስረክባለች። ለሶስት ሳምንታት በሚቆየው የመጀመሪያ ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት በሃማስ በኩል ሰላሳ ሶስት እስራኤላውያን ታጋቾች ይለቀቃሉ ተብሎ ስምምነት እንደተደረገና በእስራኤል በኩልም፤ አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ የፍልስጤም ታሳሪዎች ይለቀቃሉ ተብሎ እንደነበር ይታወቃል።

ባለፉት የጦርነት ወቅቶች እስራኤል በጋዛ ላይ በወሰደችው ጥቃት ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የጋዛ ህንጻ እንደወደመ፣ የብዙዎችን ሕይወት እንደተቀጠፈ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በጋዛ የሚገኝ ጤና ሚኒስቴር መግለጹን የዘገበው ቢቢሲ ነው፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You