
ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ፡- ሕዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የረመዳን ወርን እርስ በእርስ በመረዳዳትና መልካም ተግባራትን በመፈጸም ማሳለፍ እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ አሳሰቡ።
በአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት የተዘጋጀው የረመዳን ወር አቀባበል የዑለማዎች፣ የኢማሞች እና የዱአቶች ሁለተኛ መደበኛ ኮንፈረንስ ትናንት ተካሂዷል።
ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ወርን በመረዳዳትና መልካም ተግባራትን በመፈጸም ማሳለፍ እንዳለበትም አሳስበዋል።
መስጊዶችን ስትመሩ ኢትዮጵያ እንደምትመሩ ማሰብ አለባችሁ ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የምታስተላልፉት መልእክትም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚደርስ ነው ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ የእምነቱ መሪዎችም ሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ ለሀገር ሰላምና አንድነት በመቆም የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት አመላክተዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ለችግር የተጋለጡ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ ጾምን ስንጾም እነዚህን ወገኖች ማስታወስና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው መቆማችንን ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ በበኩላቸው፤ ኡለማዎች በመጪው የረመዳን የፆም ወር ለሙስሊሙ ማህበረሰብ እውቀትን የሚያካፍሉበት መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።
ታላቁን የረመዳን ወርን ስንቀበል የእስልምና ሃይማኖት አስተምህሮዎችን የምንተገብርበት መሆን ይኖርበታል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ለተቸገሩ ወገኖችና ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራትን ጨምሮ መልካም ተግባራትን እንዲከናወን ማህበረሰቡን ማስተማር ይገባል። በተለያየ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ማቋቋም፣ አቅመ ደካሞችንና እና አረጋውያንን መደገፍ እንደሚያስፈልግም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የሀገር አንድነትና ሰላም ከማስጠበቅ አኳያ የኡለማዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አንፃር ሁላችንም ኃላፊነት በመውሰድ በመላው ሀገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሠራውን ሥራ መደገፍ ይገባናል ብለዋል።
በኮንፈረንሱ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እና የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤት ሰብሳቢ ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ፣ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ኤባ፣ ኢማሞች፣ ኡለማዎችና ዱአቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም