ኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች ነው

-የስደተኞች ቁጥር ቢጨምርም ዓለም አቀፉ ድጋፍ ቀንሷል

አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ ከጎረቤት እና ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እንደምታስተናግድ የኢፌዴሪ የስደትና ተመላሾች አገልግሎት ገለጸ። የስደተኞች ቁጥር ሲጨምር በተቃራኒው የዓለም አቀፉ ድጋፍ እየቀነሰ መሆኑን ጠቁሟል።

የኢፌዴሪ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ስለሺ ደምሰው በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችንና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ተቀብላ ታስተናግዳለች። ይህ ቁጥር ከአንዳንድ ሀገራት የሕዝብ ቁጥርም በላይ ነው። ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች በዋናነት ከአፍሪካ ቀንድ እና ከምሥራቅ አፍሪካ አካባቢ የሚመጡ ቢበዙም፤ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከምዕራብ አፍሪካ እና ከሌሎች የዓለም ሀገራትም የመጡ አሉ ብለዋል።

እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፤ ከጎረቤት ሀገራት የሚመጡ ስደተኞች የሚበዙ ሲሆን በአጎራባች ሀገራቱ መግቢያ በኩል በተዘጋጀላቸው የስደተኛ መጠለያ ውስጥ ይኖራሉ።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎትም በየአካባቢዎቹ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንዳሉት አመልክተው፤ ከሶማሊያ የሚመጡ ሶማሌ ክልል ውስጥ፣ ከደቡብ ሱዳን የሚመጡ በጋምቤላ ክልል፤ ከሱዳን የሚመጡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልሎች ፤ በተዘጋጁ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ይስተናገዳሉ።

የኤርትራ ስደተኞች እንዲሁ በአዋሳኝ ክልሎች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ እንደሚስተናገዱ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪው ተናግረዋል።

‹‹በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት ለስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች ማዕከላት ተቋቁመዋል›› ያሉት አቶ ስለሺ፤ ሥራዎች የሚሠሩት ከአጋር አካላት ጋር እንደሆነ ተናግረዋል።

በዋናነት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጄንሲ እና ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ከሚሠሩ አጋር አካላት ጋር ይሠራል። የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በዋናነት የመምራትና እንቅስቃሴዎችን የማስተባበር ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ  በኢትዮጵያ ባለው የስደተኛ ቁጥር ልክ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ አይደለም። በዚህም ምክንያት ሥራው ከባድ ነው። እንደ መንግሥት ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኛ እና ጥገኝነት ጠያቂን ሰላሙን አስጠብቆ፣ መሬትን ሰጥቶ፣ ያሉ ሀብቶችን እንዲጠቀሙ ፈቅዶ ሥራውን ማስኬድ ትልቅ ቆራጥነትና ቅልጥፍና የሚጠይቅ ነው።

አሁን ላይ ባለው ዓለም አቀፍ አዝማሚያ ግን ድጋፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሆኑን ጠቁመው፤ የገቡትን ቃል እየፈጸሙ አይደለም። በተቃራኒው ርዳታ የሚፈልገው የስደተኛው ቁጥር ደግሞ እየጨመረ ነው። የሚጠበቅባቸው አካላት ተገቢውን ኃላፊነት ስላልተወጡ ለስደተኞች የሚሰጠው አገልግሎት ከደረጃ በታች ይሆናል ማለት ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስደተኞችን እያስተናገደ መሆኑን ተናግረዋል።

ስደተኞችን ርዳታ መስጠት ብቻ ሳይሆን ወደ ልማት ማስገባትም ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ስለሺ፤ ወደ ልማት ሲገቡ የሚያስተናግዳቸውን ማህበረሰብም ይጠቅማሉ፤ ለራሳቸው ለስደተኞችም እውቀትና ክህሎት እንድኖራቸው ያደርጋል። ይህን ለማድረግ ግን በመንግሥት ብቻ የሚቻል ስለማይሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ እንዲሳተፉበትም ጥሪ አቅርበዋል።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You