
የዓለም የሥራ ድርጅት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2015 ጀምሮ ይፋ ማድረግ በጀመረውና በመስከረም ወር በወጣው የ2024 የዓለም የማኅበራዊ ጥበቃ ሪፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓለም ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የማኅበራዊ ጥበቃ ሽፋን ማግኘት መቻሉን አመላክቷል። ነገር ግን ሦስት ነጥብ ስምንት ቢሊየን ሰዎች አሁንም ከሕይወት ተግዳሮቶች እና ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖዎች እንዳልተጠበቁ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ 10 ሚሊየን ገደማ ሰዎች የማኅበራዊ ጥበቃ ሽፋን እንደሚያገኙ ጥናቶች ያሳያሉ። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ እየተተገበረ የሚገኘውን የ5ኛው ምዕራፍ የልማታዊ ሴፍቲኔት አፈፃፀም ለመገምገም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በኅዳር ወር አጋማሽ በተካሄደ መድረክ መንግሥት ትርጉም ባለው ዘላቂ የማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል እና ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል። በዚህም ባለፉት ዓመታት የዜጎች ሕይወት ላይ ለውጥ ያመጡ ውጤታማ ሥራዎች መመዝገባቸው ተወስቷል። በቀጣይም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ድህነት ቅነሳ ላይ የሚሠራው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተጠቁሟል።
የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው በ2017 በጀት ዓመት ከዓለም ባንክ የልማት ፖሊሲ ትግበራ ጋር በተያያዘ 45 ቢሊየን ብር ለገጠር ሴፍቲኔት ፕሮግራም ጥቅም ላይ ውሏል። በዚህም 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎችን በገጠር እና በከተማ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ሕዳር 19 ቀን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካጸደቀው 500 ቢሊየን ብር ገደማ ተጨማሪ በጀትም አብዛኛው ለሴፍቲኔት ፕሮግራም የሚውል መሆኑ ተነግሯል።
የኢፌዴሪ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በ2007 ዓ.ም. የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ መውጣቱን ተከትሎ ስትራቴጂ ወጥቶለት ፕሮግራሞቹ በትክክለኛ መንገድ እንዲሄዱ የማድረግ ሥራዎች ተሰርተው፤ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያ የምትተገብረው የሴፍቲኔት ፕሮግራም ሰዎች የገንዘብና የምግብ ርዳታ የሚያገኙበት ብቻ ሳይሆን ሰርተው መለወጥ የሚችሉበት ፕሮግራም መሆን አለበት ተብሎ ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ተብሏል የሚሉት ሚኒስትሯ፤ ሰዎች ባገኙት ትንሽ ድጋፍ የራሳቸውን ሥራ ሰርተው ለዘለቄታው ከተረጂነት ወጥተው ሕይወታቸውን መቀየር እንዲችሉ ታስቦ ምርታማ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተቀርጿል ነው የሚሉት።
ፕሮግራሙ ሲጀምር በገጠር ያሉ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመደገፍ እንደነበር ጠቁመው፤ በገጠሩ ላይ የተመዘገበውን ውጤት በማየት ከግብርና ሚኒስቴር እና ከከተማ ልማት ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የከተማ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተጀምሯል። ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ከመርዳት አኳያ በጎዳና ላይ የሚገኙ ዜጎችን አንስቶ መደበኛ ሕይወት ውስጥ እንዲቀላቀሉ በማድረግ ረገድ የጀመርነው ሥራ እንደ አፍሪካም ሆነ እንደ ዓለም ባንክ አዲስ ተሞክሮ ነው። በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ሴቶች፣ ሕጻናት፣ አረጋውያን እና በተለያዩ ሱሶች ተጠምደው ወደ ጎዳና የሚወጡ ወጣቶች አሉ። እነዚህ ወደ ማገገሚያ ማዕከላት እንዲገቡ በማድረግ የምንሠራው ሥራ ነው። በ11 ከተሞች ተጀምሮ አሁን ወደ 88 የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም እንዲስፋፋ ተደርጓል ብለዋል።
ከልመና ወጥተን ራሳችን በራሳችን መረዳዳት አለብን ብለን የማኅበረሰብ ጥምረት አደረጃጀትን ከቀበሌ ጀምሮ በመፍጠራችን ማኅበረሰቡ እያዋጣ ሰዎች ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት ከዛው ማኅበረሰቡ ውስጥ እያሉ እንዲታገዙ በማድረግ ከምንጩ የማድረቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ይህ ሥራችንም በሌሎች ሀገራት እንደ ትልቅ ተሞክሮ የተወሰደ ነው ሲሉም ያክላሉ።
የማኅበራዊ ጥበቃዎች ሲባል የሚነሳው አንዱ ነገር የመብት ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ኤርጎጌ (ዶ/ር)፤ እንደሚታወቀው በአንድ አካባቢ ላይ ግጭት ሲኖር ብዙ ነገሮችን ያመሰቃቅላል። በዚህ ምክንያት ወደ ኋላ የሚቀሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ። በተለይም ደግሞ ጥቃት የሚደርስባቸው ሕጻናትና ሴቶች መጠቀም እንዲችሉ ከዓለም ባንክ ጋር ፕሮግራም ቀርጸን እየሠራን ነው። ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎችም እንደዚሁ ፕሮግራሙን ተግባራዊ እያደረግን ነው። ብዙ ሀብት ፈሰስ በማድረግ የአንድ መስኮት አገልግሎት እየሰጠን ነው። መጠለያዎችንም በማቋቋም ተጎጂዎች እንዲጠለሉ በማድረግ የስነልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ እያደረግን ነው። ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉም ባዶ እጃቸውን መሄድ የለባቸውም በሚል የክህሎት ስልጠና እየሰጠን የፈረሰባቸውን እና ያጡትን መተዳደሪያቸውን እንደገና ማቋቋም እንዲችሉ እንደግፍ በሚል በተለይም ለሴቶች ትኩረት በመስጠት እየሠራንባቸው ያሉ በጣም ሰፊ ፕሮግራሞች አሉ ብለዋል።
አያይዘውም በሁሉም ፕሮግራሞች የሚረዱ ወገኖች እየተጠቀሙ ያሉት ወገኖች በትክክል የሚገባቸው ናቸው ወይስ አይደሉም የሚለውን ለመለየት የዲጂታል ሥርዓትን ማጠናከር ተገቢ ሥራ ነው። የማሕበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ከፋይዳ መታወቂያ ጋር እንዲያያዝ በማድረግ ተደራራቢ ተጠቃሚዎችን ከፕሮግራሙ ለማውጣት እንዲሁም በፕሮግራሙ መታቀፍ እያለባቸው ወደ ኋላ የሚቀሩ ዜጎች እንዳይኖሩ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከሕግ አኳያ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ በቅርቡ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ማሻሻያዎች እንዲደረጉባቸው እየተንቀሳቀስን ነው የሚሉት ሚኒስትሯ፤ ቅጣቶች አስተማሪ መሆን እንዲችሉ የማድረግ እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። በተለይም የሕጻናት ጥቃት ቁጥሩ እየጨመረ ስለሆነ ዲጂታል ሥርዓት ዘርግተናል። ከቀበሌ ጀምሮ አንድ ሕጻን ጥቃት ሲደርስበት ወዴት እንደሄደ እና ምን አይነት እልባት እንደተሰጠው የሚያሳይ የልጆች ጉዳዮች የሚከታተል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሥርዓት ዘርግተናል። ሶሻል ወርከሮች በታብሌት ይመዘገባሉ። ያን ሂደት ከማዕከል ሆኖ በመከታተል እያንዳንዱ ጉዳይ መፍትሄ እንዲያገኝ ማድረግ የሚያስችል አቅም ፈጥረናል ነው ያሉት።
መልሰው ደጀኔ (ዶ/ር) “Policy Coherence and Social Protection in Ethiopia: Ensuring No One Is Left Behind” በሚል ርዕስ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ 2019 ባካሄዱት ጥናት የኢትዮጵያ መንግሥት አጠቃላይ የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲን በመቅረጽ ማኅበራዊ ጥበቃን ለማሻሻል ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱን ገልጸዋል።
ተመራማሪው የኢትዮጵያ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም በአፍሪካ ሁለተኛው ትልቁ የማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ የተጀመረው አሁን ሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ጠረጴዛ ላይ በነበረበት ወቅት ነው። መንግሥት እርዳታ ላይ ብቻ ያተኮረ ማኅበራዊ ጥበቃ ጠባቂነት እንዲመጣ ያደርጋል የሚል ስጋት ስለገባው ከርዳታ ወጥተን ልማታዊ እናድርገው የሚል ውሳኔ ላይ በመድረሱ የተገባበት አካሄድ ነው ይላሉ።
ከአምስት ዓመታት በፊት እኔ ባጠናሁት ጥናት በልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉ ሰዎች ቀጥተኛ ድጋፍ ከሚያገኙት አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ አጥቢ እናቶች እና ነብሰ ጡሮች ውጭ ያሉት በዕለታዊ ሥራ ተሰማርተው ሠርተው ነው የሚከፈላቸው። ሰዎቹ በቀን 39 ብር አካባቢ እየተከፈላቸው በሳምንት አራት ቀን ነበር የሚሰሩት። በወቅቱ በአካባቢው የቀን ሥራ የሚሠራ አንድ ሰው በቀን የሚከፈለው 60 ብር ነበር። መንግሥት በሴፍቲኔት ፕሮግራም የታቀፉት ዜጎች 60 ብር የሚከፈላቸው ከሆነ ሥራ የመሥራት ፍላጎት አይኖራቸውም በሚል የ21 ብር ልዩነት እንዲኖረው አድርጓል በማለት መንግሥት የሴፍቲኔት ፕሮግራሙን ሲተገብር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረጉን ያስረዳሉ።
ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሙ ሥራ ፈጥሮ ሰዎችን በማቋቋም ዘለቄታ ያለው ከአጭር ጊዜ ድጋፍ አስተሳሰብ የወጣ በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥትን እና እንደ ዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ዩኤስ ኤይድ ያሉ ታላላቅ የልማት አጋሮችን በአንድነት ያጣመረ ስኬታማ መሆኑን የፖሊሲ ተመራማሪው ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማገገሚያ ማዕከላት እንዲገቡ በማድረግ ወደ መደበኛ ሕይወት በመመለስ በሠራው ሥራ ሚኒስትሯ ኒውዮርክ ድረስ ተጠርተው እውቅና ተሰጥቷቸዋል የሚሉት ተመራማሪው፤ መንግሥት በዚህ ረገድ ትልቅ ሥራ ነው የሠራው። በቀጣይ ተመልሰው እንዳይወጡ እንዲሁም ሌሎችም ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ሥር ነቀል የሆነ ሥራ መሥራት አለበት ሲሉ ያሳስባሉ።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ልማታዊ ሴፍቲኔት የኢትዮጵያ ተሞክሮ ነው። ሌሎች አገራት ላይ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ተብሎ ነው የሚተገበረው። ይህን ተሞክሯችን ሞዴል ሆኖ ለሌሎች ሀገራት ማካፈል መቻላችን እንደ ኢትዮጵያ ከሌሎች የምንማረው ነገር እንዲሁም ለሌሎችም የምንሰጠው ነገር መኖሩን ያረጋገጠ ነው። ኢትዮጵያ በማኅበራዊ ጥበቃ ፕሮግራሞች ያላት ተሞክሮ እንደ ጥሩ ትምህርት ተወስዶ ለሌላ ሀገር ማካፈላችን፣ ሀገራችን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የምትሆን ሀገር መሆኗን ያሳያል ነው የሚሉት፡፡
በገጠርም በከተማም በተገበርናቸው የሴፍቲኔት ፕሮግራሞች ውጤቶች ተመዝግበዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ አሁን አጥብቀን እየሠራን ያለነው ሥራ ሰዎች በሴፍቲኔት ፕሮግራሙ በቋሚነት ታቅፈው ተቀምጠው የሚኖሩበት እንዳያደርጉት የራሳቸውን ሥራ እየሰሩ መለወጥ የሚችሉበትን ሥርዓት ነው እንደ መንግሥት እየዘረጋን ያለነው። ልማታዊ የሴፍቲኔት ፕሮግራማችንም በገጠርም በከተማም ውጤታማነቱ ስለታየ ዓለም ባንክም ከእኛ ጋር ቀጥሎ በገጠር አራተኛው በከተማ ደግሞ ሦስተኛው ምዕራፍ ፕሮግራም በመተግበር ላይ የሚገኘው ብለዋል።
ትልቁ ነገር ግን ሕዝባችን ከተረጂነት እና ከልመና ወጥቶ በራሱ አቅም ሰርቶ ከችግር የሚወጣበትን እና መደበኛ ሕይወት የሚኖርበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው መሥራት ያለብን ብለን እንደ መንግሥት የጀመርነው ሥራ አለ። የምግብ ዋስትና ማረጋገጥን በስንዴ እንደጀመርን ሁሉ በሌማት ትሩፋትም እውን ለማድረግ እንዲሁም የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞችን በማስፋት ማኅበረሰቡ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሥራዎች እየሠራን እንቀጥላለን ሲሉም አክለዋል፡፡
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ የካቲት 4 ቀን 2017 ዓ.ም