በራስ ወርቅ መድመቅ

በዘመናችን ፋሽን የአብዛኛው ሰው የእለት ከእለት የኑሮው አንድ አካል መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል። ምን ልብላ? ምን ልጠጣ? ከማለት ባልተናነሰ መልኩ ምን ለብሼ? በምን ላጊጥ? የሚለው ጉዳይ በተለይም በከተሜው ሕዝብ ዘንድ ጎልቶ እየታየ መጥቷል። መቼም ሁሉም ሰው ማለት ይቻላል ቆንጆ ሆኖ በሌሎች ዘንድ መታየትን አይጠላም፣ አይጠላም ብቻ ሳይሆን ይወዳል። ይህን መውደዱም ተፈጥሯዊ ነው ተብሎ ይታመናል። በአንዳንዶች ዘንድ ግን በፋሽን ተውቦ፣ አምሮና አጊጦ መታየትን ከመውደድም ያለፈ እንደ ግዴታ የሚታይበት አጋጣሚ ትንሽ አይደለም። “ፏ! ፈሽ! ብለን ካልቀረብን ውሏችን ውሎ መልካችንም መልክ አይመስለንም” የሚሉ የፋሽን ተከታዮች ቁጥር ቀላል አይደለም።

ታዲያ በፋሽን አምሮና ተውቦ የመታየት ጉዳይ ሲነሳ ፋሽን መከተል የራሱ አሉታዊና አዎንታዊ ተፅእኖ አለውና ስንቶቻችን በፋሽን ለመዋብ የምንጨነቀውን ያህል የምንከተለው ፋሽን ከባሕልና ማህበረሰባችን አኳያ ተጨንቀን እንዋባለን? ስንቶቻችንስ የሀገራችንን ወግና ባሕል፣ ሥርዓትና ልማድ በጠበቀ መልኩ ፋሽንን እንከተላለን? የሚለው ጉዳይ ብዙ ጊዜ አነጋጋሪ ነው።

አንዳንዴ ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍራችን አለባበሳችን ሌሎች ላይ አይተን ከወደድነው አሊያም ከምናደንቀው ሰው በመኮረጅ ሊሆን ይችላል። ከዚያም የወጭ ወራጁ ዓይን እኛ ላይ መሆኑን ስናይ ‘አቤት ምን ያህል ቆንጆ ሆኜ ብታያቸውና ብማርካቸው ነው እንደዚህ የሚያፈጡብኝ..’ እያልን በልባችን ስንብሰለሰል፤ የተገላቢጦሽ “አዬ ይሄማ ከአማኑኤል ያመለጠ እብድ መሆን አለበት… ደግሞ ብላ ብላ ላባዋ የረገፈ ዶሮ መስላ መጣች…” የሚል ይገጥመናል።

አለባበሳችንን ተመልክቶ ሰው “ከዓይን ያውጣሽ፣ ከዓይን ያውጣህ” ይለኛል ብለን ስንጠብቅም ‘ዓይንህ ይውጣ’ ሊመጣብንም ይችላልና ነገሩ ‘ያሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ’ እንዳይሆንብን የምንከተላቸው የፋሽን ከማኅበረሰባችን ሞራልና ስብዕና ጋር የሚሄድ መሆኑን ቀደም ብለን ማሰብ እንደሚገባ ይታመናል።

ፋሽን የዘመናዊነትና የሥልጣኔ ምልክት ነው። ፋሽንን መከተልም ክፋት የለውም። መጥፎነቱ ግን በማይጠቅሙን መጤ ፋሽኖች ተከትበን የምንኖርበትን ማኅበረሰብ ሥርዓት መጠበቅ ካልቻልን ነው። ያኔ የራሱ የሆነ ትልቅ አደጋ አለው። ‘ሲያዩት ያላማረ ሲበሉት ያቅራል’ የሚለው ማኅበረሰባችን ቀድሞ ስብዕናችንን የሚለካው በሚያየው ገጽታ ስለሆነ በውስጣችን ያለውን ጥሩ ነገር ለማሳየት ብንጥር እንኳን አይሆንልንም።

በዘመናችን ወቅቱ የዋጃቸውን ፋሽኖች ከባሕልና ወጋችን አኳያ መከተል ከባድ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የሀገራችን ቱባ ባሕሎች ከማንም በላይ ለፋሽን ምቹ ናቸው። ትልቁ ፈተና የሚገጥመን ማኅበረሰባችን ፋሽን የማይወድ ስለሆነ አይደለም። ፈተናው ያለንን አውደ ብዙ ባሕል ተጠቅመን ከዘመኑ ጋር የሚጣጣም የራሳችን የሆኑ ፋሽኖችን መፍጠር ሲያዳግተን ነው።

በምዕራባውያን የባሕል ወረራ ተፅእኖ ውስጥ ወድቀን ከባሕልና አይነኬ እሴቶቻችን የሚፃረሩ ፋሽኖችን እንከተል ካልን ከሰፊው ማኅበረሰባችን ጋር እንደሚያጋጨን ሳይታለም የተፈታ ነው። የጥንቱ ባሕልና ወግ እንደወረደ ሙጭጭ ብለን ስንቀር ደግሞ ከዘመኑ ጋር እንጋጫለን፤ ስለዚህ ቁልፉ የሚገኘው ባሕልን ከዘመኑ ጋር የማጣጣም ፈጠራ ላይ ነው። የፋሽን ወረራ የባሕል ወረራን የሚያስከትል፣ ጋሻና ጦር ይዘን የማንመክተው እረቂቅ ነገር በመሆኑ በትኩረት ማጤኑ የሁልጊዜም የፋሽን ተከታዮች የቤት ሥራ ነው።

ኢትዮጵያ በፋሽን ረገድ የታደለች ሀገር ናት። ከራያ እስከ ቆቦ፣ ከሶማሌ እስከ ባሌ፣ ከሽሬ እስከ አደሬ፣ ከጎጃም እስከ የም፣ ከጎንደር እስከ አፋር፣ ከጉራጌ እስከ ሀረርጌ ኧረ! ስንቱ ተነስቶ ያልቃል። እኚህን ሁሉ ቱባ ባሕሎች ይዘን የሌላውን ከቋመጥን ሀገራዊ ኩራታችን ብቻ ሳይሆን ጥልቁ ማንነታችንም በማይረባ ቅራቅንቦ ይሸፈናል። ዋናው ቁም ነገር ቬሎን ትተን በሀበሻ ቀሚስ እንሞሸር አይደለም፤ ቬሎ ብለን ለሰርግ ጊዜ የምናጌጥበትን ልብስ እንደ ወረደ ከሌላው ዓለም አምጥተን ከምናጌጥ ከሀገራችን ከቱባ ባሕሎች ጋር አስተሳስረን እኛን በሚገልጽ መልኩ አሰናድተን ልንደምቅበት አንችልም ወይ? ነው።

በርግጥ እንደ ምሳሌ ባነሳነው የሰርግ ቬሎ ሙሽሮች በሰርጋቸው ወቅት ማጌጡን በተወሰነ ደረጃ እያስቀሩ መጥተዋል። በከተሞችና ፋሽን ተከታዮች ነን በሚሉ ሰዎች ሳይቀር ከዘመናዊው ቬሎ ይልቅ ሰርጎች በሀገር ባሕል ልብሶች እየደመቁ መጥተዋል። በዚህ ረገድ ሰፊ ለውጥ እስካሁን ማየት ባይቻልም ጅምሩ አበረታችና ሊያድግ የሚችል ነው።

ይህን ጅምር ለማሳደግና የሚታይ ለውጥ ለማምጣት በሀገራችን እውቅ የፋሽን ዲዛይነሮች የተጀመሩ አበረታች የፈጠራ ሥራዎች አሁን አሁን ብቅ እያሉ ቢገኙም የራሳችንን ቱባ ፋሽን በመከተል ሀገራችንን ለዓለም ማሳየቱ የእያንዳንዳችን ድርሻ ነው። ቁጥር ስፍር ከሌላቸው ባሕሎች እየተቀዱ በዘመናዊ መልኩ እየተፈሸኑ ለገበያ የሚቀርቡ አልባሳቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰፊ ተቀባይነት ማግኘት እንደቻሉ ይታወቃል።

ለዚህም የሀገራችን ዲዛይነሮች የፈጠራ ጥበብ ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል። በቂ ነው ማለት ግን አይቻልም። ዲዛይነሮች ተጨንቀውና ተጠበው ባሕልን ከዘመናዊ ፋሽን ጋር ሲያስተሳስሩ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን የማግኘት ችግር እንደሌለ መመስከር የሚያስችሉ ማስረጃዎች ብዙ ናቸው። ይህም ዲዛይነሮች የባሕል ወረራን የመመከት ትልቅ ጉልበት እንዳላቸው ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ በሰርግም ይሁን በሌሎች ኩነቶች የሚዘወተሩ ፋሽኖችን ከባሕልና ወግ ጋር አስተሳስራ ለመጠቀም ያላት እምቅ ሀብት ገና አልተነካም። ዲዛይነሮች በዚህ ረገድ የባሕር ውሃ በጭልፋ ተቀድቶ እንደማያልቀው ሁሉ እያንዳንዱን ባሕል እየፈተሹ በማውጣት በጥበብ እጃቸው ዳብሰውና ዘመኑን ዋጅተው እንዲወጡ ተኝተው ማደር የለባቸውም። ይህንንም የባሕል፣ ወግና የሞራል ግዴታቸው አድርገው ሊሠሩበት ይገባል።

በሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You