«ፓርኮችን ለኢንቨስትመንት የመስጠቱ አሠራር ሊታረም ይገባል» – አቶ ኩመራ ዋቅጅራ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ረጅም ታሪክ ያለው መሆኑ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅትም እንደነ ጨበራ ጩርጩራ፣ አልጣሽ፣ ገራሌ፣ ግቤ ሸለቆን ጨምሮ በተለያየ ምድብ ውስጥ 87 በላይ የሚሆኑ የጥበቃ ቦታዎች ይገኛሉ። ምድቦቹ ተግባራቸውና ተልዕኮአቸው ተመጋጋቢነት ያለው ቢሆንም የየራሳቸው ባህሪያት፣ ዓላማ፣ ተግባር ያላቸው ናቸው።

እነዚህ ምድቦችም ፓርክ፣ መጠለያ፣ ጥብቅ ክልል፣ የአደን ቀበሌ እንዲሁም በሕጋዊነት ማኅበረሰብ ከልሎ የሚጠቀምባቸው በሚል ይገለፃሉ። በውስጣቸውም እንስሳትን ብቻ ሳይሆን ሰፊ የሆነ ደን፣ የትላልቅ ወንዞችና ጅረቶች መፍለቂያ፣ እንደ ራስ ዳሽን፣ ቱሉ ዲምቱ ያሉ ተራራዎች፣ ዋሻዎች፣ በአጠቃላይ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብቶች የሚገኝባቸው ናቸው።

ይህ እምቅ የተፈጥሮ ሀብት መገኛ የጥበቃ ቦታ የኢትዮጵያን ወደ 10 ነጥብ 6 በመቶ (10.6%) የቆዳ ሽፋን ይዞ ይገኛል። አብዛኞቹ ጥብቅ ቦታዎች በክልሎች ስር የሚተዳደሩ ቢሆንም የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በመከታተልና እንዲጠበቁ የማድረግ ኃላፊነቱን ተጥሎበታል።

ከምድር በላይ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች በአንድ ላይ ይዞ የሚገኘው ይህ ጥብቅ ቦታ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ስላለው አበርክቶ እና እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ለንባብ አቅርበናል።

አዲስ ዘመን፡ፓርኮች ለሀገር ኢኮኖሚ ያላቸው አበርክቶ እንዴት ይገለጻል?

አቶ ኩመራ፡ሀብቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት። አንዱ ኢኮኖሚ ማመንጨት ነው። ዘርፉ በገንዘብ የማይታመን ጉልህ ድርሻ ያበረክታል። በሥርዓተ ምህዳር በኩል ያለውን መመልከት ይቻላል። ለአብነትም ጥብቅ ቦታዎች የትላልቅ ወንዞችና ሀይቆች ጅረት መፍለቂያ ናቸው። ለአብነትም ከ40 በላይ ጅረቶችና ወንዞች ከባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ብቻ የሚነሱ ናቸው።

የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛን በመጠበቅ ረገድም ድርሻው ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ያላቸው ፋይዳ በገንዘብ ምን ያህል ያወጣሉ ተብሎ ሲገመት ከፍተኛ ነው። በፌዴራል መንግሥት ሥር የሚተዳደሩት ብቻ በሥርዓተ ምህዳር ያላቸው አበርክቶ ወደ ገንዘብ ቢቀየር ምን ያህል ይሆናል? ወይንም ይገመታል? በሚል ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለመፈተሽ ተሞክሯል። ግመታው የቆየ ቢሆንም በወቅቱ ወደ 90 ቢሊዮን ብር በላይ አካባቢ ነው የተገመተው። መረጃው እንደገና መከለስ ይኖርበታል። ባለሥልጣኑም በእቅዱ አካቷል።

በቀጥታ ያላቸውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ስንመለከት ደግሞ የመጀመሪያ ድርሻው ከቱሪዝም ጋር ይያያዛል። ዘርፉ ኢኮኖሚን የሚያመነጨው አንዱ በቱሪዝም አማካኝነት ነው። ሌላው በሕጋዊ የዱር እንስሳትን አርብቶ በመሸጥ ነው። ለምሳሌ የአዞ፣ የሰጎንና የጥርኝ እርባታዎችን መጥቀስ ይቻላል።

በሀገራችንም በተወሰነ ደረጃ እየተሞከረ ነው። ሌላው የኢኮኖሚ ማግኛ ምንጭ ስፖርታዊ አደን ነው። በሕግ የተፈቀዱና ቁጥራቸው ያልተመናመነና ዝርያቸው ለመጥፋት ሥጋት ያልተጋለጡ ያረጁ ወንዶች ተመርጠው በሕጋዊ መንገድ ተሸጠው ለአደን ይውላሉ። የአካባቢው መልከዓ ምድር ለፊልም ቀረፃም ውሎ ገቢ የሚያስገኝበትም ሁኔታ አለ። በዚህ ረገድ ዶክመንተሪ የሚሠሩ፣ እና በእንስሳት፤አእዋፋት እና ሌሎች ዝርያዎችን ላይ ምርምር የሚያደርጉ የውጭ ተመራማሪዎችም የገቢ ምንጮች ናቸው።

እንዲህ ካሉ ገቢ ማስገኛዎች ምን ያህል ገንዘብ መሰብሰብ አለበት ተብሎ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶች ይነደፋሉ። ሆኖም ግን አፍ ሞልቶ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ይሄን ያህል አስተዋጽኦ አበርክቷል ለማለት ብዙ ጥረትና ሥራ ይጠይቃል። ግን ደግሞ በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ያስገኛል። ዘርፉ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ አንዴ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በሀገር ውስጥ የተፈጠረው አለመረጋጋትና ጦርነት ምክንያቶች ተዳክሞ በመቆየቱ ገና በማገገም ሂደት ላይ ነው ያለው።

ይህም ሆኖ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 160 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ነው የታቀደው። የስድስት ወር አፈፃፀም የሚገኝበት ደረጃ ተገምግሞ አልተጠናቀቀም። ሆኖም ግን ቢያንስ ከ30 እስከ 40 በመቶ አፈፃፀም እንደሚኖር ይገመታል። እዚህ ላይ ግንዛቤ መያዝ ያለበት ዓመቱን ሙሉ ሥራ የለም። እንደሚታወቀው የቱሪስት እንቅስቃሴው ወቅታዊ ነው። አብዛኛው ገቢ የሚገኘው ከስፖርታዊ አደን ነው። ስለዚህም በያዝናቸው ወራት ሰፊ የቱሪስት ፍሰት ሰለሚኖር ገቢያችንም በዚያው መጠን እንደሚያድግ እናምናለን።

ከገቢ አንፃር ደፍሮ ለመናገር የማያስችለው እንደ ሀገር ካለን ሀብት እና ጎረቤት ሀገሮች ከዘርፉ ከሚያገኙት ገቢ አንፃር በንጽጽር ሲታይ ነው። ጎረቤት ሀገሮች ከዘርፉ በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ነው የሚያገኙት። የዱር እንስሳት ቱሪዝም የብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች የጀርባ አጥንት ነው። ደብል ዲጂፒ አስተዋጽኦ ያላቸው ናቸው። በዚህ ረገድ ምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካን፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያን መጥቀስ ይቻላል።

የዚህ ዘርፍ ዋና ማነቆ ብለን የምናነሳው አንዱ የትኩረት ማነስ ነው። እስከዛሬ ድረስ በነበረው ዘርፉ የኢኮኖሚ ፋይዳ አለው ብሎ እምነት ተጥሎበት ድጋፍ አልተደረገለትም ይሄም በግንዛቤ፣ እውቀትና አመለካከት ማነስ ሊገለጽ ይችላል። ለዚህ አንዱ ማሳያ አሁን ላይ ፓርኮችና በጥብቅ ቦታዎች እየደረሰ ያለው የደን ጭፍጨፋ፣ ለእርሻ ተግባር እና ለመኖሪያነት መዋል በዚህም የእንስሳት መሰደድና አለፍ ሲልም በእንስሳት ላይ የሚደርሰው ጉዳት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።

ከታች ከትምህርት ቤት ጀምሮ ትውልድ ላይ ትልቅ ሥራ መሠራት ይኖርበታል። እውቀት ሲዳብር፣ ግንዛቤ ይፈጠራል፤ አመለካከትም ይቀየራል። ይህ ሲሆን ደግሞ ሀብቱ ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና ጥቅሙ ይታወቃል። ሁሉም ሀብቱን እንደራሱ አድርጎ ይጠብቀዋል ማለት ነው።

ሌላው ዘርፉ ተደራሽ እንዲሆን የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንት ላይ የሚስተዋለው የትኩረት ማነስ ነው። ይህም በቂ ሀብት መድቦ በተሻለ አደረጃጀት ካለመንቀሳቀስ ጋር የሚያያዝ ነው።

ሆኖም ዘርፉ በተለያየ ጫና እና ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሀብት ወይንም ገቢ እያስገኘ ነው። በሙሉ አቅም ቢሠራ ግን ዘርፉ ከሌሎች የኢኮኖሚ ምንጮች ባልተናነሰ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት የቱሪስት መዳረሻዎች ልማት በስፋት እየተካሄደ መሆኑ በዘርፉ ላይ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ነገሮችም መጥተዋል። ይህ ዘርፍ አንዱ የኢኮኖሚ ዘርፍ ሆኖ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ አስተዋጽኦው ከፍ እንዲል በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ነው።

አዲስ ዘመን፡የዘርፉን ማነቆዎች መፍታት ድርሻ ያላቸው አካላት እንዳሉ ቢታወቅም ባለሥልጣኑ የሚጠበቅበትን ድርሻ እንዴት እየተወጣ ነው?

አቶ ኩመራ፡– ትልቁ ነገር የችግሮቹን መንስኤዎች በጥልቅ ጥናት መረዳትና ችግሮችንም መነሻ አድርጎ የመፍትሔ ስልቶችን ማስቀመጥ ነው። በዚህ ረገድ በአመለካከት ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም እንቅስቃሴዎች ተጠናክረዋል። ትምህርት ቤቶች እና ልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት በማድረግም ችግሮችን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው።

ለፖሊሲ አውጭውም የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት ምክክሮችና ውይይቶች ይካሄዳሉ። ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም በእስካሁኑ እንቅስቃሴ ተቆርቋሪዎች፣ ደጋፊዎችና ተባባሪዎችን ማፍራት ተችሏል። በሕግ አካላት በኩልም ጥሩ በሚባል ደረጃ ድጋፍ እየተገኘ ነው። በመንግሥት በኩልም ሀብት ከመመደብ ጀምሮ እየተወሰዱ ያሉ የተለያዩ በጎ የሆኑ ርምጃዎች ተስፋ ሰጪዎች ናቸው።

በተጨማሪም የባለሥልጣኑን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ለመገንባትም ሥራዎች እየተሠሩ ነው። በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት፣ አሠራሮችን በመዘርጋት፣ ውጤታማ አደረጃጀቶችን እንዲፈጠር በማድረግ፣ የውጭ ተሞክሮዎችን በመቀመር፣ ውስጣዊ አቅምን በመገንባት ችግሮቹን ለመቅረፍ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

ከዚህ አንፃርም ተመራማሪዎች እንዲበዙ፣ የሥራ ግንኙነት፣ ትስስርና ቅብብሎሽ እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ በስፋት እየተሠራ ነው። ባለሙያዎች በሀገር ውስጥም በውጭ ሀገርም ሥልጠናዎች እንዲያገኙ እየተደረገ ነው። በዚህም በርካታ ለውጦች መጥተዋል።

ባለሥልጣኑ እስካሁን ባከናወናቸው ተግባ ራትም ከተባባሪ ተቋማት ጋር በመሆን ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎችና ወንጀል ፈፃሚዎችን ኬላና ኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ይዞ ለሕግ በማቅረብ ሰፊ ሥራ ሠርቷል። ሕገ ወጥነትን ለመከላከል የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችንና አነፍናፊ ውሾች በመጠቀም ረገድም ጥሩ ተሞክሮዎች እየታዩ ነው።

አዲስ ዘመን፡ፖሊሲዎችን መከለስ በተመለከተ አንስተዋልና ቢያብራሩልን?

አቶ ኩመራ፡በሥራ ላይ ያለው እና በ1997 ዓ.ም የወጣው የዱር እንስሳት ልማት ጥበቃ አጠቃቀም ፖሊሲ ረጅም ጊዜው ያስቆጠረ በመሆኑ መከለስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። የተከለሰው ፖሊሲ የዱር ሕይወት የሚል ነው። እንደ ሀገርም፣ አህጉርም፣ ዓለም አቀፍም ወቅቱን የሚዋጁ ነገሮችን ያካተተ ነው። የተከለሰው ፖሊሲ ከያዛቸው ሰፊ ነገሮች አንዱ የማህበረሰብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት፣ ቁጥራቸው እየተመናመኑ የመጡ ብርቅዬ የዱር እንስሳቶች ጥበቃ ላይ መሠራት ስላለበት ሥራ፣ ዓለምን እያሰጋ ስለመጣው የአየር ንብረት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ የሕግ ማስከበር ሥራን መሥራት ስለሚቻልበትና አቅም መፍጠር፣ ሀብት አጠቃቀም የሚሉ ጉዳዮች ናቸው። የተከለሰው ፖሊሲ የተዘጋጀውም በውስጥ አቅም ነው። በቅርቡም ለመንግሥት ይቀርባል።

አዲስ ዘመን፡ፓርኮችን ለመኖሪያ ነትና ለእርሻ ሥራ መጠቀም አሁንም ተግዳሮት ሆኖ የቀጠለ እንደሆነ ይታወቃል። ይህን ለመከላከል ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች በተለያየ ጊዜ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደነበርም ይታወሳል። ጥረቱ ከምን ደረሰ? ለምንስ ውጤት አላስገኘም?

አቶ ኩመራ፡ባለሥልጣኑ በሀገር ውስጥ ካሉትና ከዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ጋር ያለው ትብብርና ድጋፍም ጠንካራ ነው። መንግሥት ለዘርፉ ከሚመድበው ሀብት በተጨማሪ ያለው ክፍተት እየተሞላ ያለው ከአጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር በሚከናወነው ሥራ ነው። የሚያደርጉት እገዛ ከፍተኛ ነው። እነዚህ አጋር አካላት ወደ 60 በመቶ የሚሆነውን ሀብት ይሸፍናሉ። ሕግ የማስከበር፣ የአቅም ግንባታ፣ የምርምር ሥራውም በአጋር አካላት ነው የሚከናወነው።

ከአጋር አካላት ጋር ሰፊ ሥራ እየተሠራ ነው። ሰሜን ፓርክ፣ ባሌ፣ ነጭ ሳር፣ ማጎ፣ ኦሞ ባብሌ፣ ቃፍታ፣ ይጠቀሳሉ። ሀብት በመመደብና ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ በቅርቡ ጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ ላይም በተመሳሳይ ትልቅ ሀብት በመመደብና ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚከናወነው ሥራ ፓርኩ ትልቅ የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆን የሚያስችል ነው።

አዲስ ዘመን፡ከሌሎች በተለየ በማጎና ኦሞ ናሽናል ፓርኮች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ እንደሆነ ይነሳል። በዚህ ላይ ምን ይላሉ? አያይዘውም በባሌ መጠለያ ለኢንቨስትመንት ውሏል ስለተባለውም ይግለጹልን?

አቶ ኩመራ፡የችግሮቹ መነሻ ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት አለመስጠት ነው። የዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና ለሥነ ምህዳር መጠበቅ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ግንዛቤው ቢኖር ኖሮ ችግሮቹ ባልተፈጠሩ ነበር። ለዚህም ነው ግንዛቤ የመፍጠሩ ነገር አስፈላጊ የሚሆነው።

የጥበቃ ቦታዎችን ለኢንቨስትመንት የመስጠቱ ነገር ባብሌ ላይ ብቻ አይደለም። ኦሞ ላይም በሌሎችም በተመሳሳይ ይስተዋላል። ባለሥልጣኑ በሚችለው ሁሉ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የሚያስከትለውን ችግር በማሳየትና የመፍትሔ ሃሳብም በማቅረብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በውይይትና በንግግር ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው። ደን መንጥሮና እንስሳትንም ከውስጡ አስወጥቶ ለኢንቨስትመንት ማዋል ተገቢ እንዳልሆነ በማሳመን ብዙዎችን ለማስተካከልና ለመታደግ ተችሏል። በዚህ መንገድ ባብሌ ላይ ታስቦ የነበረው ኢንቨስትመንት ቀርቷል።

በሌሎችም ቢሆን የጋራ አረዳድ በመያዝ የማስቆሙ ተግባር ይቀጥላል የሚል እምነት ነው ያለው። ይሄን ውጤት ማምጣት የተቻለውም ግንዛቤ በመፍጠር ሥራ ነው። ለዚህም ነው ግንዛቤ መፍጠሩ ላይ ሰፊ ሥራ መሥራት የሚያስፈልገው። በማጎና ኦሞ ላይ በጉዳት ደረጃ የሚገለጸው አካባቢው ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ነው። የአካባቢው ማህበረሰብ መሣሪያዎችን የመጠቀም ልማድ አለው። አደንም የተለመደ ነው። በዚህ መካከል ሕግ ለማስከበር በሚደረግ ጥረት ጉዳቶች ያጋጥማሉ። ችግሩን ለመፍታት በአካባቢው ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሚመለከታቸው ጋር ሁሉ በምክክርና ውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው።

አዲስ ዘመን፡ዝርያቸው እየተመ ናመነ የመጣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት አደጋ ላይ መሆናቸውም ተደጋግሞ ይነሳል። አሳሳቢነቱ እንዴት ይገለጻል? መፍትሄውስ ምንድነው?

አቶ ኩመራ፡– የብርቅዬ ዱር እንስሳት ቁጥር እየተመናመነ መምጣት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ያለው። ዋልያን መጥቀስ ይቻላል። የዋልያ ቁጥር መጀመሪያም አነስተኛ ነው። በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በአነስተኛ ቦታ ነው የሚገኘው። ከዚያ ውጭ ሥርጭት የለውም። አንድ አደጋ ቢያጋጥም በቀላሉ የሚጎዳና የሚጠፋ ነው። ቁጥር አንድ የሚያሳስብ ነው። ቀይ ቀበሮም በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚያሳስበው። ቀይ ቀበሮ ወደ ሰባት አካባቢዎች ሥርጭት አለው ሆኖም ግን ቁጥሩ ከ400 በታች ነው።

ብርቅዬ ያልሆኑም ቁጥራቸው ተመናምኖ በአሳሳቢነት ደረጃ ላይ ያሉ አሉ። ዝሆን አንዱ ነው። ብዙ ምግብና ውሃ ስለሚፈልግ በየቀኑ ረጅም ርቀት ተንቀሳቅሶ ነው መኖር የሚችለው። በመሆኑም ሰፊ ቦታ ይፈልጋል። የዱር እንስሳት መኖሪያዎች በሕገ ወጥ ሰፋሪዎች መያዙ፣ ለእርሻና ኢንቨስትመንት መዋሉ ለእንስሳት ህልውና ሥጋት ነው የሚሆነው። ወደ ጠረፍ ጠጋ ብለው ያሉት ወደ ጎረቤት ሀገር ሊሻገሩ ይችላሉ። የዱር እንስሳቱ መኖሪያ መረበሽና ሥነ ምህዳሩ መዛባት ምክንያት ረጅም እንቅስቃሴ ማድረግን የተላመዱ እንስሳት እየተጎዱ ነው። ለአንበሳ፣ አቦሸማኔም እንዲሁ ሥጋት እየሆነ ነው።

አዲስ ዘመን፡ግጭት እና ጦርነት በጥብቅ ሀብቶቹ ላይ የሚያሳዳሩት ተጽእኖ እንዴት ይገለፃል?

አቶ ኩመራ፡– ፓርኮች፣ ጥብቅ ቦታዎች ተፈጥሮ የሚጠበቅባቸው አካባቢዎች ናቸው። የሰው ጣልቃ ገብነት የሌለበት፣ በተፈጥሮ በራሱ መስተጋብር ከእንስሳቱ ጋር ተሳስሮ የሚኖርበት ነው። የሰው ልጅም የሥነ ምህዳር አገልግሎት የሚያገኘው ከነዚሁ አካባቢዎች ነው። ሆኖም የፀጥታ ችግር ሲያጋጥም መሸሺያና መደበቂያ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይፈጠራል። ይሄ ደግሞ የተፈጥሮ ሚዛኑን ያዛባዋል። ለምሳሌ ቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክን መውሰድ ይቻላል።

ከ2013 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ጊዜያቶች ፓርኩ በሙሉ አቅም እየሠራ አይደለም። እንደ ዝሆን ያሉት በፓርኩ ውስጥ የሚገኙት እንስሳት ወደ ጎረቤት ሀገር ተሻግረው ይሂዱ፣ ይኑሩ ርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ምክንያቱም በነበረው አለመረጋጋትና ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ፓርኩ ውስጥ ገብቶ ስለነበር እንስሳቱም ሆኑ ፓርኩ በምን ይዞታ ላይ እንዳሉ ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል። የነበረው አለመረጋጋት አጭር ጊዜ ቢሆንም ሰሜን ተራሮች ፓርክ ላይም በተመሳሳይ ጉዳት ደርሷል።

የሰላም አለመኖር ለዱር እንስሳት ከፍተኛ ጉዳት እንደሆነ የጎረቤት ሀገራትን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ከዚህ ቀደም ዩጋንዳ ውስጥ በነበረው የርስበርስ ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የዱር እንስሳት አልቀዋል። ሩዋንዳም በተመሳሳይ በነበረው የእርስበርስ ጦርነት የዱር እንስሳት ተጎድተዋል። የሰላም እጦት ለዱር እንስሳት ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው።

ሆኖም ሰላም ባለባቸው አካባቢዎች ፓርኮች ለመስህብነት እየዋሉ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ፓርኮች እየተነቃቁ ነው። በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍሎች ጥሩ የቱሪስት ፍሰት አለ። ብሔራዊ ነጭ ሳር ፓርክ፣ ባሌ አካባቢም ጥሩ ነው። ቀደም ባሉት ጊዜያቶች በከፍተኛ ሁኔታ የቱሪስት መዳረሻ የነበረው ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪስት ፍሰቱ ቀንሶ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ መሻሻል እያሳየ ነው። የበለጠ በመሥራት ይህን ጥሩ ጅማሮ ማስቀጠል ይጠበቃል።

አዲስ ዘመን፡የዱር እንስሳት በሚኖሩበት ፓርክ ውስጥ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ አለ?

አቶ ኩመራ፡– የዱር እንስሳት ሕክምና ክፍል ተዋቅሯል። ይህ ክፍል በስፋት እየሠራ ያለው መከላከል ላይ ነው። በፓርኮች አካባቢ ያለውን የበሽታ ዓይነት መለየትና ለእርሱ መፍትሔ መስጠት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው። ከቤት እንስሳት ወደ ዱር እንስሳት የሚተላለፉ በሽታዎችን ለመከላከል የቤት እንስሳት እንዲከተቡ ይደረጋል። በሕክምና ደረጃ በተወሰነ ደረጃ ቀይ ቀበሮ ላይ ሙከራ ተደርጓል። ቁጥራቸው ብዙ ስላልሆነ የአፍ ክትባት ይሰጣል። በዚህ መልኩ ከሚደረገው ጥረት ውጭ በእንስሳቱ ተፈጥሮ መኖሪያ ውስጥ ሕክምና ለመስጠት ያስቸግራል።

አዲስ ዘመን፡ይሄን ግዙፍ የሀገር ሀብት ተንከባክቦና ጠብቆ ለሀገራዊ ምጣኔ ሀብት ለማዋል ከማን ምን ይጠበቃል?

አቶ ኩመራ፡ፓርኮች ውድ ሀብቶቻችን መሆናቸውን ሁሉም ሰው ሊገነዘበው ይገባል። ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምንጭ ከሆኑት ቡና፣ ወርቅና ሌሎችም ባልተናነሰ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ፋይዳ ያለው ነው። ለአብነት ቅርብ ያሉትን ጎረቤት ሀገሮች ከዘርፉ እያገኙ ያሉትን ጥቅሞች ማንሳት ይቻላል። ከዘርፉ በቢሊዮን ብር እያገኙበት፣ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎቻቸው የሥራ እድል እየፈጠሩበት፣ የሀገራቸውንም ገጽታ እየቀየሩና እውቅናም እያገኙበት ነው። ስለዚህ እኛ ይሄንን ለምን ማድረግ አቃተን ብለን መቆጨትና መፀፀት ካልሆነ በስተቀር ሊባል የሚችል ነገር የለም። መሆን ያለበት ከፀፀት ወጥቶ ዘርፉ የሚያድግበትን ሥራ መሥራት ነው።

አሁን ላይ ዘርፉ የኢኮኖሚ ፋይዳ እንዳለው ግንዛቤ ተይዞ እየተከናወነ ያሉት ተግባራት የሚያበረታቱ ናቸው። አዋሽ ብሔራዊ ፓርክ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን መንግሥት ትልቅ ሥራ እየሠራ ነው። የተሻለ ጥበቃ እንዲኖረው አካባቢውን በኤሌክትሪክ ሽቦ በመከለል ጭምር ነው እየተሠራ ያለው። ባሌ ላይም ተመራጭና ተወዳዳሪ የሆነ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን አስፈላጊውን ነገር የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው። ጨበራ ጩርጩራንም በተመሳሳይ ማንሳት ይቻላል። ሥራዎች ከተጠናከሩና የተሻለ ግንዛቤ ከተፈጠረ ሀብቱን ከአደጋ መጠበቅና ተጠቃሚ መሆን እንዲሁም ለትውልድ በቅርስነት ማስተላለፍ ይቻላል።

አዲስ ዘመን፡ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እናመሰግናለን።

አቶ ኩመራ፡እኔም አመሰግናለሁ።

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You