
ርእሳችን አዲስ አይደለም፤ ሀገር ያወቀው፣ ፀሀይ የሞቀው ነው። ይሁን እንጂ፣ በርእሱ የታቀፉት ቃላት እያንዳንዳቸው ተራ ቃል ሳይሆኑ ጽንሰ-ሃሳብ (ኮንሴፕት) ናቸው። “ሰው”፣ “ቤት”፣ “እንጀራ”… የሚሉትን ወስደን እንያቸው ብንል አይደለም የጋዜጣ ገጽ መሬትና ሰማዩ እንኳን እሚበቃን አይመስልም። አባባሉን ላቀበሉን አያት ቅድመ-አያቶቻችን (ከዘፈኑ በፊት እነሱ ናቸውና ያሉት) ምስጋና አቅርበን ወደ ተነሳንበት እንሂድ።
በማንኛውም መለኪያም ሆነ መስፈርት ቢታይ፣ ቢመዘን፣ ቢለካ፣ ቢሰፈር … የሰው ያው የሰው እንጂ የራስ ሊሆን አይችልም። ከጊዜ ርዝመትና አብዝቶ መለመድ/መልመድ የተነሳ የራስ ሊመስል ይችል ይሆናል እንጂ በምንም መንገድ የሰው ሀብትም ሆነ ርስትና ጉልት የራስ ሊሆን አይችልም፤ ሆኖም አያውቅም። በጉልበት እንኳን እናድርገው ቢባል ከሥነልቦና እርካታ ጀምሮ ምንም አይነት ሠብዓዊ ስሜት የለውም፤ ጊዜውን ጠብቆም ሂያጅ ነው።
“የሰው ቤት እንጀራ …” እንዳልነው ሁሉ ከሱ የማይተናነሰው “የሰው ወርቅ አያደምቅ” እሚል ሥነቃላዊ ሀብትም አለንና እሱንም ከርእሳችን ጋር በተለዋዋጭነት እየተጠቀሙ ነገሩን መብላት እንኳን ቢቀር ማብላላት ያስፈልጋልና መቸም ቢሆን መቸም የሰው ወርቅ ሊያደምቅ አይችልም፤ አድምቆም አያውቅም። ምናልባት የሰው (የተውሶም ይሁን የኪራይ) ወርቅ አንድ ሊያደርግ የሚችለው ተግባር ቢኖር ማዘናጋትና የራሳችን ወርቅ እንዳይኖረን ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ እዚህ እንደምናወራው ቀላል ሳይሆን እጅግ ከባድና ከባርነት ያልተናነሰ አገዛዝ ነው።
በየትኛውም መንገድ ቢታይ የሰው ወርቅም ሆነ የዘንጋዳ እንጀራና መረቁ በማንኛውም ጤነኛ ሰው ለጤነኛ ሰው የሚመከር አይደለም። የሰው ልጅ ለሰው ሁሉ የሚመክረው የተሻለውን ነውና ምክሩ ልክ እንደ መጽሐፉ “ጥረህ ግረህ በላብህ ብላ” ከሚለው ማእቀፍ የሚወጣ አይሆንም።
ማንም ሊገምተው እንደሚችለው ማንኛውም ጤናማ ሰው ለጤናማ ሰው ሊሰጥ የሚችለው ምክር “ጥረህ ተጣጥረህ የራስህ ይኑርህ” ነው፤ ባጭሩ መግለፅ ከተፈለገም “ራስህን ቻል” ከመሆን አያልፍም። ራስህን ቻል…
ራስን አለመቻል ጣጣው ብዙ ሲሆን የሚጀምረውም ከውስጥ፣ ከሥነልቦና ነው። ራሱን ያልቻለ ሰው (ሀገርም ይሁን ሌላ) አንገተ ሰባራ ነው፤ “ቢጭኑት አህያ ቢለጉሙት ፈረስ” ከሚለው ዜማ ብዙም የራቀ አይደለም፤ ምን ጊዜም “ሲጠሩት አቤት” እንጂ ሌላ አያውቅም፤ ቢያውቅም እውቀቱን የመጠቀም መብት የለውም፤ የረጂነትና ተረጂነት አገዛዝ ያንን አይፈቅድምና ያለው መብት “አቤት” ብሎ “ወዴት?” ማለት ብቻ ነው። ባይሆን ኖሮ አሁን እየሆነ ያለው (የተረጂዎች ስጋትና ፍርሃት) ሁሉ ባልሆነ ነበር።
“ተረጂነት”ም እንበለው “ረጂነት”፤ “ርዳታ”ም እንበለው “ልገሳ”፤ ወይም ሌላ የፈለግነውን የዳቦም ሆነ የክርስትና ስም ብናወጣለት ዞሮ ዞሮ ያገኘነው ነገር ከሰውና የሰው የሆነ ሀብትና ንብረት ነው። “የሰው ወርቅ አያደምቅ” እንደተባለው አያደምቅም፤ “ከሰው ቤት እንጀራ…” እንደተባለው እንጀራው የሰው ነውና ቢበሉት አያጠግብም። ወይም፣ ሰውነት አይሆንም። ቢሆን ኖሮ ዘላለም አለማቸውን ሲረዱ የኖሩ ሁሉ ዛሬ “ጉዴ ነው” እያሉ ባላዜሙ ነበር። እነዛም “ቆይ እሰራላችኋለሁ” እያሉ ባልፎከሩም ነበር።
ብዙ ጊዜ፣ በንግግር ደረጃ ብቻ ሆነ እንጂ፣ “ተረጂነት ክብርን እና ሉዓላዊነትን ዝቅ እሚያደርግ ነው”፤ “ተረጂነት ሰው አዋራጅ ነው”፤ “ተረጂነት ኢትዮጵያን የማይመጥን ክብረ-ነክ ተግባር ነው”፤ “ተረጅነት ተመፅዋችነት ነው፤ ተመፅዋችነት ደግሞ የበታችነት ነው”፤ የበታችነት በበኩሉ ዝቅተኝነት ነው።
በመሆኑም ተረጂነት ከማንነት፣ ከሀገር (ኢትዮጵያዊነት)፣ ሉዓላዊነት… ጋር ቢያያዝ የሚገርም አይሆንም። የሚገርመው በሚነገረው ልክ ሆኖ አለመገኘት ነው። ተረጂነትን እንደ አማራጭ መንገድና አዋጭ ቢዝነስ አድርጎ በማየት ሙጭጭ ማለትና እዛው የተረጂነት ስልቻ ውስጥ መቅረቱ ነው ዘላለማዊ ግርምትን የሚፈጥረው። ባይሆን ኖሮ ጅብ በጮኸ ቁጥር መበርገጉ ባልመጣ ነበር።
እንደምናውቀው ተረጅነት የሀገር በቀል እውቀት ውጤት አይደለም። ተረጂነት መጤ ነው፤ ተረጂነት ጠባቂነት ነው፤ ተረጂነት በሰው ገንዘብ አይንን ቁልጭ ቁልጭ ማድረግ ነው፤ ተረጂነት መገዛት ብቻ ሳይሆን ለዘመናዊ ቅኝ ተገዥነት እጅ መስጠት ነው። ተረጂነት ያለ መሥራትና ስንፍና ውጤት ነው።
“ኢትዮጵያን አይመጥንም” ሲባልም ሁሉ በጇ፤ ሁሉ በደጇ ሆኖ እየለ እንዴት … ማለት ነውና ኀዘኑ መሪር ነው። በተለይ ረጂው አካል ድንገት ነሽጦት ብድግ ብሎ “ከዛሬ ጀምሮ አቁሜያለሁ” ያለ ለታ ኀዘኑ ከመሪርነትም አልፎ ቅስም ሰባሪ ይሆናል።
በፌስቡክ ገፁ አማካኝነት ሳይታክት ስለ ሀገሩ የሚፅፈው ጌታቸው ወልዩ ከዚሁ ከረጂ/ተረጂነት ትርክት ጋር በተያያዘ አንድ ያሰፈረው ቁም ነገር ያለ ሲሆን፣ እሱም፡-
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተሸነፈችው ጀርመን፤ ኑሯዋ ተናግቶ፤ ችግሯ በዝቶ ሳለ፤ ምዕራብና ምሥራቅ ተብላ ለሁለት ተከፍላ የርዳታና ድረሱልኝ ጥያቄም ስታቀርብ፤ ከ1928 እስከ 1933 ዓመተ- ምህረት (እ.ኤ.አ ከ1936-1941) ድረስ በፋሺስት ጣልያን ወረራ ተፈጽሞባት ጠላቶቿን አሳፍራ፣ ከንቱ የወራሪነት ቅስማቸውን ሰባብራ፣ እጅግ መራር የሽንፈት ጽዋ ግታና አንድነቷን አሳይታ፣ ሉዓላዊነቷን አስከብራና ስሟን በደማቅ ወርቅ ቀለም አሰማምራ የጻፈችው ምሥራቅ አፍሪካዊቷ የጀግኖች ሀገር- ኢትዮጵያ ሁለት መቶ ሺህ ዶላር የሚገመት ቡና እና በርካታ ጣቃ ብርድ-ልብስ ስጦታ የላከችላት መሆኑን የምታውቁ ስንቶቻችሁ ናችሁ? የሚ ለው ነው።
የጌታቸውን ጥያቄ በጥያቄነቱ አልፈነው፣ ቁም ነገሩን ስንመረምረው ተረጂነት ብርቅ አለመሆኑን፤ መርዳትም ሆነ መረዳት ያለና የነበረ እንደሆነ፤ በችግር ጊዜ መደራረስ ሰዋዊ (ሀገራዊ) ባህርይ ሆኖ እናገኘዋለን። ጌች ባይነግረንም፣ የተረጂነት ችግሩ እዛው ተረጂነትን ለምዶና ተላምዶ፤ (ዛሬ የአውሮፓን ኢኮኖሚ እንደ እምትመራው ጀርመን ከተረጂነት ውልቅ ብሎ በመውጣት ረጂ መሆን ተስኖ) ከተረጅነት ጋር በፍቅር ወድቆ፣ ተረጂነትን እንደ ፍም እሳት እየሞቁ ለእንቅልፍ በመመቻቸት ተደላድለው ሲተኙና ተመፅዋችነት ደዌ ሆኖ ሲገኝ ነው።
ረጂነት ከሚበላና እሚጠጣውም አልፎ የፖለቲካ ተረጂነትና ጥገኝነት ድረስ ከዘለቀ ደግሞ ጥገኝነቱ ጫማ ስር እስከ መነጠፍ ድረስ ያወርዳልና ፖለቲካውም ፖለቲካ አይሆን፤ ፖለቲከኛውም ፖለቲከኛ አይደለምና “ፍረስ” የተባለለ እለት መፍረሱ፤ “ግደል” የተባለ ለታ መግደሉ የግድ ይሆናል ማለት ነው።
እናጠቃልለው፣ በላይኛው – በተድበሰበሰ ሃሳብ ለማለት የተፈለገው ተረጂነት ምን ጊዜም ጥገኝነት መሆኑን፤ ጥገኝነት ለተመፅዋችነት እንደሚያጋልጥ፣ ከተረጂነት ይልቅ ብቸኛውና አዋጪው መንገድ መሥራት ብቻ መሆኑን (በቁጭትም ሊሆን ይችላል) ማሳየት ነው። ለጋሽ ሀገራት ራሳቸውን ሲያማቸው ተለጋሽ (ተረጂ) ሀገራት ሆዳቸውን የሚቆርጣቸው ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን ይሄው የረጂ-ተረጂነት (የበላይና የበታች) ግንኙነት ነው። ስለዚህ:-
ከሰው ቤት እንጀራ አልጫ መረቁ፣
የእናት ቤት ይሻላል ዘንጋዳ ደረቁ።
የተባለውን ጠበቅ በማድረግ ወደ ሥራ ማተኮር፤ ተረጂ መንግሥታት (ሀገራት) “ከተረጂነት አስተሳሰብ መላቀቅ እና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ” እሚሉትን ወደ ተግባር መቀየር፤ ልክ እንደ ጀርመን ዳግም ላለመረዳት እራስን መቻል እንጂ፤ ገና ለገና “አቁሜያለሁ” ስለተባለ መበርገግ ፋይዳ የለውም።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 3 ቀን 2017 ዓ.ም