
በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ ስማቸው በጉልህ ከሚጠቀሱ ተጫዋቾች አንዷ ነች። ሉሲዎቹን ባገለገለችባቸው ሁለት አስርት ዓመታት የብሔራዊ ቡድኑ አምበል ከመሆን ጀምሮ ያልሰጠችው የለም። በርካታ የእግር ኳስ ክብሮችንም ከብሔራዊ ቡድን እስከ ክለብ በማሳካት ተጠቃሽ ነች።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ውድድርን 2004 ዓ.ም ላይ ማካሄድ ሲጀምር አምስት ክለቦች በተሳተፉበት የውድድር ዓመት አስራ አንድ ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ኮከብ ግብ አስቆጣሪና የውድድሩም ኮከብ ተጫዋች ነበረች።
አንቱታን ያተረፈችው ኮከብ ብርቱካን ገብረክርስቶስ፣ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ ታሪክ የራሷን አሻራ በማሳረፍ ባለፉት በርካታ ዓመታት ለተፈጠሩ ሴት ከዋክብት ተጫዋቾች በስነምግባሯ ጭምር አርዓያ ሆና ትነሳለች። ብርቱካን ዛሬም እግር ኳስን እርግፍ አድርጋ አላቆመችም፣ በክለብ ደረጃ መጫወቷን ቀጥላለች። ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀ የብሄራዊ ቡድን ግልጋሎቷን ግን “እዚህ ጋር ጨርሻለሁ” በማለት ሰሞኑን ከዚህ በኋላ በሉሲዎቹ ስብስብ ውስጥ እንደማትታይ ይፋ አድርጋለች። ሶከር ኢትዮጵያም በክብር እንደምትሸኝ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ የፌዴሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን ያገኘውን ሃሳብ አስነብቧል።
“ብርቱካን እጅግ ድንቅ ተጫዋች ለብዙዎች ሴት ተጫዋቾች ተምሳሌት የሆነች ጠንካራ ሴት ናት። ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎላት እንኳን አክብራ ነው መጥታ ለፌዴሬሽኑ ያሳወቀችው፣ ይህ ያላትን መልካም ስብዕና ያሳያል። ስለዚህ ይሄን ያህል ዓመት አቋሟ ሳይዋዥቅ ረጅም ዓመት መቆየት መቻል ለሙያ መታመንን ያሳያል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ከዩጋንዳ አቻው ጋር በሚኖረው ጨዋታ ብርቱካንን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በክብር ይሸኛታል” በማለት አቶ ባህሩ ስለ አንጋፋዋ ኮከብ ሽኝት የታሰበውን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልጸዋል።
ከኤግልስ እስከ አዲስ ኮከብ ፣ ከደደቢት እስከ ዳሸን ቢራ፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስከ ብሔራዊ ቡድን ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በእግር ኳሱ ድንቅ ብቃት እያሳየች የቀጠለችው አንጋፋዋ ተጫዋች ብርቱካን፤ በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ በጉልህ ስማቸው ከሚጠቀሱ ስመ ጥር ተጫዋቾች አንዷ ስለመሆኗ ብዙዎች ይስማማሉ።
ከስምንት ዓመት በፊት በብሄራዊ ቡድን ፍልሚያ ለሉሲዎቹ ተሰልፋ በሴካፋ ውድድር ላይ ኮከብ ተጫዋች ሆናለች። በክለብ ደረጃ በሊግ ክብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ከደደቢት ጋር ዋንጫ ማንሳት ችላለች። በከፍተኛ ዲቪዚዮን ውድድር ላይም የተከታታይ ኮከብነት ሽልማቶችን ጠራርጋ ወስዳለች። ደደቢት በነበረችበት ጊዜም ክለቡ ለሌሎች አርአያ እና ተምሳሌት በመሆን ልዩ ተሸላሚ ነበረች።
አስደናቂዋ የ36 ዓመት የአማካኝ ስፍራ ተጫዋች ከሜዳ ላይ ድንቅ ብቃቷ ባሻገር ግሩም ባህሪዋ በብዙዎች ይወደሳል። የቀድሞ ክለቧን ደደቢትን ስትቀላቀል የተከፈላት ሰላሳ ሺህ ብር በወቅቱ ትልቅና የመጀመሪያዋ ሴት ኢትዮጵያዊት ተጫዋች አሰኝቷት እንደነበርም ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ቆይታዋ ስኬታማ ጊዜን ያሳለፈችው ብርቱካን ከብሔራዊ ቡድኑ ማግለሏን አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ፣ ለሀገሯ ባበረከተችው አስተዋጽኦ እና በቡድኑ በነበራት ቆይታ እጅግ ደስተኛ መሆኗን በመግለፅ ለወጣት ተጫዋቾች ዕድል ለመስጠት እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሷን ተናግራለች።
ውሳኔዋን ተከትሎም በብሔራዊ ቡድን ቆይታዋ ላሰለጠኗት አሰልጣኞች ፣ አብረዋት ለተጫወቱ ተጫዋቾች እና በእግር ኳስ ሕይወቷ አስተዋጽኦ ላደረጉት በሙሉ እንዲሁም ከጎኗ ላልተለዩ ደጋፊዎች ያላትን ላቅ ያለ አክብሮት “ለወጣት ተጫዋቾች ዕድል ለመስጠት ይህንን ወስኛለሁ። በብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ ላሰለጠኑኝ አሰልጣኞች አብረውኝ ለተጫወቱ ተጫዋቾች እና በእግር ኳስ ሕይወቴ አስተዋጽኦ ላደረጉት በሙሉ ላቅ ያለ አክብሮት አለኝ።” በማለት ገልፃለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም