የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት

የየካቲት ወር ለጥቁር አፍሪካውያን (በተለይም ለኢትዮጵያ) የድል ወር ነው ማለት ይቻላል:: በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በየካቲት ወር በርካታ ዓለም አቀፍም ሆነ የሀገር ውስጥ ፖለቲካዊ ሆነቶች ተከናውነዋል:: እንደየቀናቸው ወደፊት የምናየው ሆኖ ለዛሬው በጥር ወር መጨረሻ እና በየካቲት ወር መጀመሪያ የተከናወኑትን እናስታውሳለን:: ከእነዚህም አንዱ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምሥረታ ነው:: በሌላ በኩል በዚሁ ሳምንት የኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት አመሠራረት ታሪክም አለ:: ሁለቱን ዘርዘር አድርገን ከማየታችን በፊት ሌሎች የዚህ ሳምንት ታሪካዊ ክስተቶችን እናስታውስ::

ከ175 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 27 ቀን 1842 ዓ.ም የወሎ፣ የጎጃምና የትግራይ ንጉሥ የነበሩት ስመ ጥሩ የዓድዋ ጀግና ንጉሥ ሚካኤል አሊ ተወለዱ:: ንጉሥ ሚካኤል ብዙ ክዋኔዎች በሚደረጉበት እና ወሎ ደሴ ከተማ በሚገኘው አይጠየፍ አዳራሽ ይታወሳሉ::

ከ112 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 27 ቀን 1905 ዓ.ም አሜሪካዊቷ የመብት ተሟጋች ሮዛ ሉዚ ማካውሌ ፓርክስ (ሮዛ ፓርክስ) ተወለዱ:: ሮዛ ፓርክስ የአሜሪካ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ‹‹የመጀመሪያዋ ሴት የሲቪል መብት ተሟጋች›› ሲል የጀግና የክብር ዕውቅና ሰጥቷታል:: ሮዛ ፓርክስ ዓለም አቀፍ የመብት አቀንቃኝ በመሆን ብዙዎችን አነቃቅታለች::

ከ60 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 27 ቀን 1957 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ ግንባታው ተጠናቆ ተመረቀ::

ከ80 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 29 ቀን 1937 ዓ.ም ዝነኛው ጃማይካዊ የሬጌ ሙዚቃ አቀንቃኝ፣ ሮበት ኔስታ ማርሌይ (ቦብ ማርሌይ (Bob) ተወለደ:: ቦብ ማርሌይ ጥቅምት 24 ቀን 1973 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ተጠምቆ፣ ‹‹ብርሃነ ሥላሴ›› የሚል የክርስትና ስም ተሰጥቶታል:: ቦብ ማርሌይን ያጠመቁት ሊቀ ጳጳስ በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትን ይመሩና ያስተዳድሩ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ይስሃቅ ነበሩ:: ቦብ ማርሌይ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አድናቂዎች ያሉት ሲሆን፤ የእርሱ ምስል ያለበትን ቲሸርት ለብሰው የሚታዩም ብዙ ናቸው::

ከ45 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት በዛሬዋ ቀን የካቲት 2 ቀን 1972 ዓ.ም ‹‹አልወለድም›› የሚለውን ዝነኛ መጽሐፍ ጨምሮ በርካታ ተውኔቶችን፣ ድራማዎችን፣ ግጥሞችንና ሌሎች የጽሑፍ ሥራዎችን ያዘጋጀው ደራሲ አቤ ጎበኛ ሞተ:: አቤ ከአማርኛ በተጨማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋም ተነባቢ መጻሕፍትን መጻፍ የቻለ ታላቅ ደራሲ ነበር::

ከ170 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት የካቲት 3 ቀን 1847 ዓ.ም ደጃዝማች ካሣ ኃይሉ፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከመንገሳቸው በፊት የመጨረሻውን የዘመነ መሳፍንት ጦርነት፣ የሰሜንና የትግራይ ገዢ ከነበሩት ከደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም (የዳግማዊ ቴዎድሮስ ባለቤት የእቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ አባት) ጋር አደረጉ::

ከጦርነቱ 2 ቀናት በኋላ፣ የካቲት 5 ቀን 1847 ዓ.ም፣ ‹‹የኮሶ ሻጭ ልጅ›› ተብለው የተናቁት፣ ‹‹… ደግሞ ለቆለኛ አንድ ወርች ስጋ ምን አነሰው?›› ተብለው በአማቶቻቸው የተቀለደባቸው … ካሣ ኃይሉ፣ ደጃዝማች ውቤ ኃይለማርያም ሊነግሱባት አስጊጠው ባሰሯት ድርሳነ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በጳጳሱ በአቡነ ሰላማ እጅ ተቀብተው፣ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሰ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኑ::

አሁን ወደ አፍሪካ የኢኮኖሚክ ኮሚሽን አመሰራረት እንሂድ::

ከ64 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 29 ቀን 1953 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (United Nations Economic Commission for Africa) ሕንፃ ተመረቀ:: በምርቃት ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ለዕይታ የበቃውና ባማረ መልኩ ምርቃቱን ለማብሰር የተቀረጸው የንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መልዕክት ‹‹ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ሕዝብ የወደፊት እድገት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ አስበው የመሠረቱትን ይህን ህንጻ ጥር 29 ቀን 1953 ዓ.ም የአፍሪካ አዳራሽ ብለው ሰየሙት›› ይላል::

በርካታ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁነቶች የሚከወኑበት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (በእንግሊዘኛ ምሕጻረ ቃል ኢ.ሲ.ኤ የሚባለው) ሕንፃ የተመረቀው ጥር 29 ነው ቢባልም በአንዳንድ መረጃዎች ግን ጥር 30 ቀን ነው ይባላል:: አብዛኞቹ ሰነዶች የሚያሳዩት በዚህ ሳምንት መሆኑን እንጂ ቀኑ በትክክል ጥር 29 ወይም 30 መሆኑን ግን የሚያረጋግጥ ነገር አላገኘንም:: የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የትውስታ ዘገባዎቻቸውን የሠሩት በዚህ ሳምንት ቢሆንም ትክክለኛ ቀኑን የገለጹ ግን አላገኘንም:: ለማንኛውም በዚህ ሳምንት በጥር ወር መጨረሻ ነውና ወደ ታሪኩ::

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከአራት ዓመታት በፊት ‹‹የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ ታሪክ›› በሚል በሠራው ፕሮግራም፤ ሕንጻው የተሠራው ለአፍሪካዊ ጉዳዮች ነው::

ይህ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በ1950 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ተፈረመበት:: በመሐል አዲስ አበባ ካዛንቺስ የሚገኘው ይህ ሕንጻ በስድስት ሚሊዮን ብር ወጪ ተገነባ::

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት የሚገኝበት ሕንጻ 55 ሺህ ካሬ ቦታ ላይ ያረፈ ነው:: የተሠራውም የአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ሊመከርበት ታስቦ ነው:: በዚህም መሠረት የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ሦስተኛውን ጠቅላላ ስብሰባ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተናገደ በዚሁ አዳራሽ ሆነ::

ቤተ መጻሕፍት እና ሌሎች ሰፋፊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ያሉት ይህ ግዙፍ ሕንጻ፤ የአርክቴክት ባለሙያውም ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ ኢንጂነር ጌታቸው ማህተመሥላሴ ይባላሉ::

የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የወንበሮች አቀማመጥ፣ የሊቀመንበር 8፣ የአማካሪዎች 36፣ ለተመልካች 48፣ ለአስተርጓሚ 8 ለጋዜጠኞች 225፣ ለልዩ እንግዳ 37 ወንበሮች ነበሩ::

ይህ አዳራሽ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከተመሰረተበት ጊዜ ድረስ 70 ሺህ የውጭ እና 30 ሺህ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እንደጎበኙትም ይነገርለታል:: በመግቢያው ላይ በሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የተሳሉ ሥዕሎች ይገኛሉ:: ይዞታቸውም በቅኝ ግዛት ሥር የወደቀችውን አፍሪካን ማሳየት ነበር::

ይህ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት 60ኛ ዓመቱ ተከብሯል:: ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝግጅቱ ላይ እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አፍሪካን በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በሰላም ጉዳዮች ውጤታማ ትብብር እንዲኖራቸው አግዟል::

ከዓለም አቀፋዊ ተቋማት ጋር በማስተዋወቅ ረገድ ነጻ የንግድ ቀጣና ምስረታ ሂደትና አፍሪካውያን የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙ በማነሳሳት ተቋሙ የተጣለበትን ኃላፊነት እንደተወጣም ገልጸዋል::

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ቬራ ሶንግዌ ፤ ኮሚሽኑ ባለፉት 60 ዓመታት ለአፍሪካ አንድነትና ዕድገት ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለው ነበር::

በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በአፍሪካ ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን በላይ ዜጎች ያሉ ሲሆን፤ ኢኮኖሚያቸው ሁለት ነጥብ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር የደረሰ በመሆኑ ያለውን ሀብት በቅንጅትና በትብብር ሥራ ላይ ማዋል እንዳለባቸው አሳስበው ነበር::

ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ይባላል፤ ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥትም ይባላል:: ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ያለው ደርግ ነው:: ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት የተባለው ደግሞ በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ነው:: ምሥረታውም የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን 25ኛ ዓመት የንግሥና በዓል አስመልክቶ ስለነበር ነው ኢዮቤልዩ (25ኛ ዓመት) የተባለው:: ይህ ቤተ መንግሥት በአሁኑ አስተዳደራዊ ሥርዓት የፕሬዚዳንት መኖሪያ የሆነው ፍልውሃ አጠገብ ያለው ቤተ መንግሥት ማለት ነው::

ይህ ቤተ መንግሥት ከ69 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ጥር 30 ቀን 1948 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት መስጠት እንደጀመረ ይነገርለታል::

የኢዮቤልዩ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከአጼ ኃይለሥላሴ ጀምሮ የነበሩ ንጉሣዊ አልባሳትን፣ ከልዩ ልዩ ሀገራት የተበረከቱ ስጦታዎችን፣ የዱር እንስሳት ማቆያ፣ ቤተ መጻሕፍትን እንዲሁም የትም የማይገኙ ታሪካዊ ቁሳቁሶችን የያዘ ሲሆን፤ ለሙዝየምነት የሚያበቃ በቂ ክምችት እንደያዘም ይነገርለታል::

ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ፤ የቀድሞውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ለቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) በስጦታ ከማስረከባቸው በፊት 25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓለ ሲመታቸውን ሲያከብሩ ያሠሩት ይህ ቤተ መንግሥት ዘመን ተሻጋሪ ውብ የኪነ ሕንጻ (አርክቴክቸር) ጥበብ የተንፀባረቀበት ነው::

ቤተ መንግሥቱ በሀገር በቀል ዛፎችና አንበሳን ጨምሮ በተለያዩ የዱር እንስሳት የተሞላና የተዋበ ነው:: የቤተ መንግሥቱ ውስጣዊ ክፍልም እንዲሁ በተለያዩ ውብና ውድ ዕቃዎችና ጌጣጌጦች የተዋበ መሆኑ ይታወቃል::

ይህ ቤተ መንግሥት ባለፉት ስድስት አሥርት ዓመታት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ዶክተር ሙላቱ ተሾመ፣ ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ አሁን ደግሞ አቶ ታዬ አፅቀ ሥላሴ ለሥራና ለመኖሪያ ተስተናግደውበታል::

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አራት ኪሎ ታላቁ ቤተ መንግሥት ውስጥ በተሠራላቸው ቤት መኖራቸው አይዘነጋም:: ለአንዳንድ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር ብዙም አልተገለገሉበትም:: ንጉሡ በብርጋዴር ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ከተመራው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥትን ለቀው ከ1954 ዓ.ም ጀምሮ ለ13 ዓመታት እስከ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ድረስ በዚህ ቤተ መንግሥት ውስጥ ኖረዋል:: በኋላም ወታደራዊው መንግሥት ንጉሡን ከሥልጣን አስወርዶ ይህንን ቤተ መንግሥት ተረክቧል:: መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በኮሎኔል መንግሥቱ የሚመራው ደርግ ይህንን ቤተ መንግሥት ኦፊሴላዊ ዝግጅቶችን ለማካሄድና እንግዶችን ለመቀበል ተጠቅሞበታል::

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You