መገናኛ ብዙኃን ለከተማዋ ቱሪዝም ትውውቅ

መንግሥት ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱን የቱሪዝም መስህቦች በሚገባ በመገንዘብ፣ ቱሪዝሙ ለምጣኔ ሀብት ያለውን ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት ይህ ሀብት ለሀገር ምጣኔ ሀብት እንዲውል ማድረግ የሚያስችሉ የቱሪስት መዳረሻ ልማት ሥራዎች ማከናወኑን ትከትሎ ተጨባጭ ለውጦች ተመዝግበዋል::

የቱሪስት መዳረሻ ልማት ከተከናወነባቸው መካከል አዲስ አበባ ትጠቀሳለች:: በከተማዋ የፌዴራል መንግሥቱም ከተማ አስተዳደሩም ዘርፉን ለማልማት በወሰዱት ተነሳሽነት በርካታ የቱሪስት መዳረሻ ልማቶች ተካሂደዋል::

ለእዚህም በርካታ መስህቦችን በአንድ ስፍራ እንዲያካትት ተደርጎ የታደሰው የቀድሞው የዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት የአሁኑ አንድነት ፓርክ፣ በሰፊ ስፍራ ላይ የተገነባው የወዳጅነት ፓርክ ፣ ለጎብኚዎች መዳረሻ እንዲሆን ተደርጎ የተገነባው የአዲስ አበባ ሳምባ በመባል የሚታወቀው የእንጦጦ አረንጓዴ ፓርክ በአብነት ሊጠቀሱ ይችላሉ::

በርካታ አገልግሎቶችን እንዲሰጥ ተደርጎ የታደሰው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዥዎችን አሳፍረው የመለሱበትን የዓድዋ ድል የሚዘክረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም፣ ከተማዋንም ሀገሪቱንም የስብሰባ ማእክል እንደሚያደርጋት የሚጠበቀው በሲኤምሲ አካባቢ እየተገነባ የሚገኘው የአፍሪካ ኮኔክሽን ማእክልና የመሳሰሉት ሌሎች ከተማዋን በቱሪስቶች ተመራጭ የሚያደርጓት ናቸው::

በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች እየተካሄደ ያለው የኮርደር ልማት በከተማዋ በትራንስፖርት መሠረተ ልማት ላይ ይታይ የነበረውን መሠረታዊ ችግር የሚፈታ መሆኑ፣ ከተማዋን ለመኖሪያም ለጎብኚም፣ ለሥራም ምቹ እያደረገ ያለበት ሁኔታም የከተማዋን አልፎም የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ የመዳረሻ ልማት ወደ ላቀ ከፍታ አድርሰውታል::

ከተማዋ በእዚህ ሁሉ የቱሪዝም ሀብት ምን ያህል ተጠቃሚ መሆን ጀምራለች? ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆንስ በማስተዋወቅና በመሸጥ በኩል ምን ያህል እየሠራች ነው? ተብሎ ሲጠየቅ መልሱ ልማቱን የሚመጥን የማስተዋወቅና መስህቦችን የመሸጥ ሥራ አልተከናወነም የሚል ነው:: ይህንንም የከተማዋ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮም በይፋ አስታውቋል::

ቢሮው ሰሞኑን በቱሪዝምና ኪነጥበብ ሥራዎች አዘጋገብ እና ፕሮግራም አዘገጃጀት ዙሪያ ለጋዜጠኞችና ከፍተኛ ኤዲተሮች በጊዮን ሆቴል በሰጠው ስልጠና ላይ በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማትና በመሳሰሉት የታየውን ግዙፍ ለውጥ በሚመጥን መልኩ መስህቦችን በማስተዋወቅና በመሸጥ በኩል በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አስገንዝቧል::

ለእዚህም የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪስት መስህቦችንና መዳረሻዎችን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ በሚያከናውናቸው ተግባሮች ሁሉ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቋል::

በዚህ ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ በርካታ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተሳተፉበት ስልጠና ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሁንዴ ከበደ ከለውጡ ወዲህ በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ መዳረሻዎችን በማልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ ይህን ወቅትም የበርካታ ዓመታት የዘርፉ ጥያቄዎች የተመለሱበት፤ በቱሪዝም ዘርፉ ትላልቅ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ሲሉ ገልጸውታል::

እሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቱ ለ60 እና 70 ዓመታት በመንግሥታዊ የቱሪዝም መዋቅር በኩል ስትሠራ ቆይታለች፤ ነገር ግን ዘርፉ በሚፈልገውና በሚመጥነው ደረጃ የቱሪዝም እንቅስቃሴ አልተደረገበትም:: አሁን ግን ዘርፉ በፖሊሲ ማሕቀፍ ጭምር ተደግፏል፤ በፖሊሲ ደረጃ መታቀፍ ብቻም ሳይሆን በተጨባጭም ዘርፉ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ያስቻሉ ትላልቅ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ግንባታዎች ተካሂደዋል:: እነዚህ ሁሉ የዘርፉ ትልቅ ለውጥ ናቸው::

ወደ ሥራ የገቡትና እየገቡ ያሉት አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እድሳት የተደረገላቸው መስህቦችም እንዲሁ ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል::

በዚህ ሁሉ ልክ ያሉትን የቱሪስት መዳረሻዎች በማስተዋወቅና በመሸጥ በኩል እየተሠራ አይደለም ሲሉ ያስገነዘቡት ምክትል የቢሮ ኃላፊው፤ ይህ ዘርፉን የማስተዋወቅና የመሸጥ ሥራ በመንግሥት ብቻ ሊከናወን እንደማይችል ተናግረዋል:: የግል ዘርፉ፣ ከምንም በላይ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን እዚህ ላይ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል::

እሳቸው እንዳሉት፤ አዲስ አበባ በሁሉም ነገር፣ በተለይ በቱሪዝም መዳረሻዎች ታድላለች:: የሀገሪቱ የቱሪዝም ጉዳይ ሲነሳ አዲስ አበባ ሳትጠቀስ አትታለፍም፤ ትላልቅ እድሎች አሉባት፤ ለቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉባት ከተማም ናት:: በመዳረሻም በመስህብም ከተመለከተን ታድላለች:: በሰው ሠራሽ በባህላዊ እጅግ የታደለች ናት::

ቀጣዩን ዘመን ስናስብም በጣም በርካታ እድሎች ይኖሯታል፤ እነዚህን ሁሉ እድሎች በተገቢው መንገድ ለመጠቀም የቱሪዝም ዘርፉን የኢኮኖሚው ምሰሶ ለማድረግ በተያዘው አቅጣጫ ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት ከ12 እስከ 18 ሚሊዮን መንገደኞችን እንደሚያጓጉዝ መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ ጥቂቱን መድረስ ቢቻል በከተማዋ ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ላይ እምርታዊ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም አመላክተዋል::

ይህን ሁሉ ስኬታማ ተግባር የሚመጥን የማስተዋወቅና የመሸጥ ሥራ መሠራት ይኖርበታል ሲሉ አስገንዝበው፣ ለእዚህም የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ ነው:: የቱሪዝም ሀብቶቹን እንዴት ማስተዋወቅና መሸጥ አለብን በሚለው ላይ ከሚዲያ አካላት ጋር እየተነጋገርን መሥራት ይኖርብናል፤ ስልጠናው ለእዚህ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉም ገልጸዋል::

ከኪነጥበብ አንጻርም እንዲሁ በከተማዋ በዘርፉ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አመልክተው፤ በእዚህ ላይም እንዴት መሥራት አለብን በሚለው ላይ እየተነጋገርን መሥራት ይኖርብናል ብለዋል::

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከሚዲያ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ዝግጁ ሆኖ ይህን መድረክ አዘጋጇቷል ሲሉ ጠቅሰው፤ በቀጣይም አብረን ለመሥራት ቁርጠኛ ነን ብለዋል::

በስልጠናው የምታገኙትን እውቀት፣ ልምዳችሁን ተጠቅማችሁ በግል እንቅስቃሴያችሁም የከተማዋን የቱሪዝምና የኪነጥበብ እንቅስቃሴ በማስተዋወቅ አግዙን ሲሉም ጠይቀዋል::

ስልጠናውን የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዲኖ (ዶ/ር) የቱሪዝም ሀብቶች እንዲጎበኙ ለማድረግ ከፍተኛ የሆነ የማስተዋወቅ ሥራ እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል::

ሊገበኙ የሚችሉ ብለን ላልይበላ፣ ኦሞ ሸለቆ፣ ጣና ሀይቅ፣ አክሱም፣ ሰሜን ተራራዎች፣ ወዘተ. እያልን ሃያ ሰላሳ መስህቦችን መዘርዘር እንችላለን ያሉት አብዱላዚዝ(ዶ/ር) በዘርፉ ተጠቃሚ የሚያደርገው የእነዚህ መስህቦች መኖር ብቻውን እንዳልሆነም አስገንዝበዋል:: መስህቦቹ ምን ያህል ታውቀዋል? በሀገር ውስጥም ይሁን በዓለም አቀፍ ሚዲያ ምን ያህል ተሄዶባቸዋል? ሲሉ ይጠይቃሉ:: ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰዎች የመጎብኘት፣ የማየት ልምድስ ምን ያህል ነው ሲሉ ጠይቀው፣ ኢትዮጵያን እየጎበኘ ያለው የውጭ ዜጋ እንጂ ኢትዮጵያዊው እንዳልሆነ ተናግረዋል::

በዚህ ላይ ለውጥ ለማምጣት አንዱ መንገድ ሚዲያው ላይ ከፍተኛ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት መሆኑን አመልክተው፣ ይህ ብቻውን ግን በቂ አለመሆኑን ተናግረዋል:: በጋዜጠኛው ላይ የባህሪና የልምድ ለውጥ እንዲመጣ ጭምር መሥራት ያስፈልጋል ሲሉም አስገንዝበዋል::

ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ማድረግ የሚያስችል ሥራ መሠራት ይኖርበታል ያሉት አብዱልአዚዝ፣ ሚዲያው በማስተዋወቅና በግንዛቤ ማስጨበጥ ላይ የባህሪ ለውጥ ማምጣት እንዳለበት አስታውቀዋል::

የቱሪዝም ጋዜጠኛው የቱሪዝሙን ጉዳዮች በተለያየ አንግል እያወጣ ማሳየት እንደሚኖርበት፣ ይህንንም ተከታታይነት ባለው መልኩ መሠራት ይጠበቅበታል ብለዋል::

በቱሪዝም ጋዜጠኝነት በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ክህሎት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል:: ለአብነትም የውጭ ቱሪስቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ ጠቅሰው፤ ለእዚም የውጭ ቋንቋ ማወቅ እንደሚያስፈልግ፤ በሌሎች የጋዜጠኝነት ሥራዎች ላይ የሚያስፈልጉ እንደ ሚዛናዊነት፣ ተአማኒት፣ ወዘተ ያሉትን የሙያ ሥነምግባሮች በሚገባ ተላብሶ መገኘትን ዘርፉም እንደሚፈልግ አመልክተዋል::

በመድረኩ የተገኘውና በከተማዋ የቱሪዝም ማስተዋወቅ ላይ ያነጋገርነው የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኛው ዘሪሁን ግርማ፤ ከአስር ዓመት በላይ በቱሪዝም ጋዜጠኝነት ላይ ሠርቷል፤ ውብ ሀገር የሚል የቴሌቪዥን ፕሮግራም ያዘጋጃል፤ በዘርፉም ያማክራል:: የኢትዮጵያ የባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች የሚዲያፎረም ፕሬዚዳንትም ነው::

አዲስ አበባ ከተማ ያላትን የቱሪዝም እምቅ ሀብት መለየት /ስፔሻላይዝ ማድረግ/ እንደሚገባ ይመክራል:: የትኛው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ከተማዋ ብትሠራ አዋጭ ይሆናል? የሚለውን ብንመለከት ገና ብዙ ያልተነካ ነገር እንዳለ እናያለን ይላል::

ቱሪዝም እንደ ሀገር ትልቅ የልማት ዘርፍ መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህን ዘርፍ እናሳድግ ከተባለ፣ ትልቁ ሥራ መሠራት አለበት ከተባለ ትልቁ ሥራ መሠራት የሚገባው ሚዲያ ላይ ነው ሲል ያስገንዝባል:: የሚዲያ ተቋማት በዚህ ውስጥ ትልቁን ሚና መውሰድ አለባቸው ይላል::

ተቋማቱ በየተቋማቸው የባህልና ቱሪዝም ጉዳይ ጥሩ አድርገው ሊሠሩ ይችላሉ፤ እንደ ተቋም ጥሩ ሥራ ሲሠሩ እንደ ሀገርም አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ የሚላቸውን ጋዜጠኞች መርጠው ማሰልጠን ይኖርባቸዋል::

እሱ እንዳለው፤ ስልጠና በሌለው መልኩ የሚሠራ የቱሪዝም ጋዜጠኝነት ብዙ ጊዜ ውጤታማ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም እንደ ሰው ጋዜጠኝነትን ሊማር ይችላል፤ ከዚህ በኋላ ደግሞ ቱሪዝም ራሱን የቻለ ባህሪ አለው፤ ይህን ለመዘገብ ደግሞ ጋዜጠኛው ተጨማሪ ነገር ያስፈልገዋል::

‹‹አብዛኞቹ ጋዜጠኞች አዲስ አበባን የሚዘግቡበትን መንገድ ከተመለከትን ተመሳሳይ ነው፤ ከተማዋ እያደገች ነው፣ የሆነ ነገር እየተሠራ ነው የሚል ዘገባ ይዘው ሲወጡ ነው የሚታዩት›› ሲልም ይገልጻል::

በመሠረቱ ከተማዋ ያላትን ሀብት መሰረት ያደረገ ሥራ መሠራት እንዳለበት አስታውቆ፣ በከተማዋ ግዙፍ የኮንቬንሽን ማእከል እየተገነባ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን የሚዘግብ ጋዜጠኛ በስብሰባ ቱሪዝም/ማይስ ቱሪዝም/ ላይ እውቀቱ ያለውን ባለሙያ ይዞ መቅረብ እንደሚኖርበትም አስገንዝቧል::

እሱ እንዳለው፤ ጋዜጠኛው ስለእያንዳንዱ ዘርፍ ማወቅ አለበት፤ ያመጣው ሰው ብቻ እንዲያወራ እድል መስጠት የለበትም፤ የጋዜጠኛው አተያይ መሠረታዊ መሆኑ መታወቅ አለበት:: ጋዘጤኛውን ከዚህ አኳያ ስንመለከት መሠረታዊ ክፍተት ይታበታል፤ በዚህ ላይ ተቋማቱ ስልጠና መስጠት አለባቸው ሲል አስገንዝቧል::

የትምህርት ተቋማትም እንዲሁ መሥራት እንዳለባቸው አመልክቷል:: በጆርናሊዝም ትምህርት ውስጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቱሪዝም ላይም ቢሠራ ብዙ ባለሙያዎችን ማፍራት ይቻላል ሲል ጠቁሟል::

‹‹እኔ ራሴን ያበቃሁት ተምሬ፣ ዓለም ላይ ያለውን ተሞክሮ አይቼ ነው፤ በራሴ ላይ ሠርቼ ነው›› ያለው ጋዜጠኛ ዘሪሁን፡ ይሄ ደግሞ በጣም ብዙ ጉዳት እንዳለው፣ ብዙ አቅም እንደሚጨርስም አስታውቋል:: መንግሥት እና ሌሎች አካላት የሚዲያ ሰዎችን በማብቃት በኩል የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ ለሀገር በጣም እንደሚጠቅሙም አመልክቷል::

ጋዜጠኛ ዘሪሁን እንዳስታወቀው፣ ከተማ አስተዳደሩ ጥሩ ሥራ ጀምሯል፤ ሚዲያን መሠረት ያደረጉ ሥራዎች መጀመሩ ጥሩ ነው፤ ሥራው ሊበረታታም ይገባል:: ቢሮው የከተማዋን ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም የሚመራ እንደመሆኑ በከተማዋ የሚከናወኑ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝምን የተመለከተ ሥራዎችን በመምራት በኩል ብዙ ይጠበቅበታል:: ለእዚህ ሚዲያ አጋዥ እንደሚሆነው ጠቅሶ፤ ለሚዲያው ባለሙያዎች ይህን አይነት ስልጠና መሰጠቱ ጥሩ ነው ሲል ተናግሯል::

ከተማዋ በጣም እየተስፈነጠረች፣ ከባለሙያውም በላይ እየሄደች ናት ሲሉም ጠቅሶ፤ ባለሙያው የሚሠራውን ከስር ከስር እያየ የጎደሉትን እንደሚጠቁም፣ መልካም ሥራዎች እንዲሰፉ እንደሚያመላክት ተናግሯል:: ያንን ሁሉ ማድረግ እንዲቻል ባለሙያውን ማብቃት ላይ መሥራት ያስፈልጋል ብሏል::

እንደ እሱ ማብራሪያ፤ ከተማዋ ከአፍሪካ ከተሞች በብዙ መልኩ ልዩነቷ እየሰፋ ነው:: ብዙ ሀብቶችን በውስጧ እየያዘች ትገኛለች፤ ስማርት ከተማ እየሆነች ናት፤ በስማርት ከተማ ውስጥ ታሪክ፣ ባህል አለ:: የተለያዩ የመዝናናት እና የመሳሰሉት የቱሪዝም አይነቶች አሉ::

ትላልቅ አዳራሾች እየተገነቡ ናቸው፤ ስብስባዎች ይካሄዳሉ፤ ጉዞዎች ሊደረጉ፣ ትላልቅ ኢግዚቢሽኖች ሊደረጉ ይችላሉ፤ ጋዜጠኛው ይህን ሁሉ በሚገባ እያየ መሥራት እንዲችል አቅሙን መገንባት አለበት፤ ለእዚህም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት፣ ትራቭል እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል::

የከተማዋን መስህቦች፣ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ፣ ሀብቶችን ለሚዲያ ባለሙያዎች ማስጎብኘት ያስፈልጋል:: በዚህ በኩል ቢሮው የጀመረው ጥሩ ነው፤ ይህን ጥረት የሚዲያው ዘርፍ አካላት ከሌሎች የተሻለ አቅም አላቸውና ማገዝ አለባቸው ሲልም አስገንዝቧል::

የማስተዋወቁ ሥራም ከተለመደው መንገድ መውጣት እንዳለበት ጠቁሟል፤ ቱሪዝም አሁን ሳይንስ ሆኗል፤ የበለጠ ሥራ መሠራት ይኖርበታል፤ ገጽታ መገንባት የሚባለው እንዳለ ሆኖ ቢዘነስ ነው ሲሉ አስታውቀዋል:: የማስተዋወቅ ሥራን እንደ ጋዜጠኛ ስትሠራ አተያይህ የተለየ መሆን አለበት ብሏል::

ኃይሉ ሣህለድንገል

አዲስ ዘመን  የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You