
‹‹እርሱ ባህልን አዋቂ ሳይሆን እራሱ ባህል ነው!›› ይሉታል የሙያ ባልደረቦቹ። በባህል ተሸምኖ በባህል የተሠራ የጥበብ ማድመቂያ ፈርጥ ነው። በተግባር የሚኖረውን ባህል ነው የሚመነዝረው:: በአቦሰጠኝ ሳይሆን ከታሪክ አጣቅሶ፤ በጥበብ ከሽኖ ለሌሎች ያስተላልፋል። ‹‹ለባህሉ ልቡ ስስ ነው›› ይሉታል፤ ተቆርቋሪነቱ ከብዙዎች ጋር እንዳጋጨው በቅርበት የተመለከቱ። ‹‹ያመነበትና መንፈሱ የነገረውን እንጂ ለገንዘብ ብሎ አይሠራም›› በማለት በልበ ሙሉነት ይመሰክሩለታል።
በእርሱ ዘንድ የሚባክን ጊዜ የለም፤ መንፈሱንና ስጋውን አስማምቶ አረፍ ካለ አንድ ጥበብ ይወልዳል። ቁጭ ብሎ ሲነሳ ከባህሉ ጋር ተጨዋውቶ አዲስ ነገር ቀምሮ ነው:: ፈጽሞ የጥበብ ምንጭ ደርቆበት አያውቅም፤ ዝናና ስም አያጓጓውም፤ ጥበብና ባህልን ለተጠሙ ከማይነጥፈው ምንጩ ጨልፎ ለመስጠት አይሰስትም::
በጥበብና በባህል ከሚቀልዱ ጋር ወዳጅነትም ኅብረትም የለውም። ካለመክሊታቸው በሙያው ውስጥ ያሉትን ይሞግታል:: “አለመቻል ሐጢያት አይደለምና በምትችለው መክሊትህ ተሰማራ” ወይም “ተሰማሪ” ብሎ እቅጩንም ይናገራል::
መክሊታቸውን አውቀው ለሚመጡት ግን በፍቅር ተንከባክቦ ከጥበብ ጋር አፈራርሞ ያጋባቸዋል:: ለደከመበት የሚጠይቀው ፍቅርና አክብሮታቸውን ብቻ ነው። ካላቸው በሚገባው ልክ ባይሆንም በጥቂቱ ይከፍሉታል:: ከሌላቸውም በብላሽ ይሰራላቸዋል:: እርሱ ሳይታወቅ ያሳውቃቸዋልና እምነት ያላቸው ከስኬት በኋላ መጥተው ይጎበኙታል፤ በዛው የሚጠፉትም ብዙዎች ናቸው:: ይህ ሰው የዛሬ“የህይወት ገፅታ” እንግዳ፤ ያልተዘመረለት የጥበብ ሰውና አንጋፋው የሙዚቃ ግጥም ደራሲና ተዋናይ ተስፋብርሃን ገ/ጻዲቅ (ኢንጅነር ባንጃው) ነው::
ትውልድና እድገት
የቀድሞው ወሎ ክፍለሀገር ወረኢሉ አውራጃ ጃማ ጎዶ የምትባል ትንሽ ቀበሌ ናት ያፈራችው:: በትውልድ መንደሩ ጥበብና ፍቅር ከባህልና ውበት ጋር ሸምነው አሳድገውታል::ከሙስሊሙና ክርስቲያን ቤተሰቦቹ የእምነት እኩልነትን፣ፈጣሪን መፍራትን፣በጎ ማድረግና ያለውን ማካፈልን ተምሯል:: የእረኝነት ዘመኑን ያሳለፈው ከሚጠብቃቸው ከብቶችና በግና ፍየሎች ድምፅ እኩል የአባቱ የአቶ ገብረጻዲቅ አኮርዲዮንን እንደሚንፎለፎለው ዥርት እየሰማ ነው::
ባለ አኮርዲዮኑ አባቱ ከሀገር ሀገር እየዞሩ ስለሚጫወቱ በልጅነቱ ከወሎ ከላላ እስከ ሸዋ መንዝ፣ ከመንዝ እስከ አጋሮ፤ ከአጋሮ እስከ አዲስ አበባ አብሯቸው እየተዘዋወረ ነው::እናቱን በልጅነቱ በሞት በመነጠቁ ክፉ በሚባሉ እንጀራ እናቶች ተሰቃይቷል:: ይሁን እንጂ መልካም ወገኖችም አላጣም፤ የእናቱ እናት አያቱ እንዲሁም ወደትወና ጥበብ የመሩትን አጎቱን ዛሬም ድረስ አይዘነጋም::
ከአባቱ አኮርዲዮን ዘወር ሲል ደግሞ የአጎቱ ሁሴን ሀሰኔ ቤት የማይመታ ግጥምና በሚያምር ዜማ የሚታጀበው ጨዋታ ይቀበለዋል:: አጎቱ ሁሴን ጨዋታ አዋቂ ነበርና ሁሉንም ነገር በዜማ እየከሸነ በትወና አያዋዛ ነበር የሚያቀርበው:: ታዳጊው ተስፋብርሃን ለእርሱ ተብሎ ባይወራም ለኔ ብሎ ነበር የአጎቱን ጨዋታ የሚሰማው:: አጎቱ ሁሴን የአሁኑ የደምብ አምስቱን ‹‹ኢንጅነር ባንጃውን›› ነው የሚያስታውስበት::የወሎውን ቱባ ባህል አጣጥሞ ሳይጨርስ የሸዋው የመንዜዎች ባህል ተቀብሎ አሳድጎታል:: ሁለቱ ባህሎች እኩል አንፀውታል እንጂ አላምታቱትም::
ተስፋብርሃን በአካባቢው ባሉ የቀለም ትምህርት ቤቶች ትምህርቱ እየተከታተለ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተምሯል:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመማር ወደ ወራኢሉ ከተማ አቅንቶ የነበረ ቢሆንም ነገሮች መልካም አልሆኑለትም::ያለው አማራጭ ሀገር ጥሎ መጥፋት ነበርና በዝናዋ ብቻ ወደሚያውቃት ደሴ ከተማ አቅንቷል:: ሶስት ቀናት ተዘዋውሮ ሲያያት ራሱን በራሱ ለማስተዳደርና ለማስተማር እንደማይችል በመረዳቱ ብዙ ጊዜ ሳያባክን አባቱ ጋር ወደ መንዝ ተመለሰ::
ጥበብ ናፋቂው መርማሪ ፖሊስ
መንዝ እንደደረሰ ያልጠበቀው አጋጣሚ ነበር የተቀበለው:: የኢትዮጵያ የፖሊስ ሠራዊት የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ ነበርና ሳያቅማማ ተመዘገበ። ፖሊስ እንዲሆን ያልፈቀዱት ዘመዶቹ ወደ ማሰልጠኛ በመሄጃው ቀን ቤት ዘግተው አስቀሩት:: ልቡ አንድ ጊዜ ሸፍቷልና በራሱ ትራንስፖርት ለገዳዲ ወደሚገኘው ፖሊስ ማሰልጠኛ በመሄድ ስልጠናውን ተከታተለ:: በኋላም አዲስ አበባ በሚገኘው ምድር ባቡር ጥበቃ ክፍል ተመደበ:: ለጥቂት ዓመታት በፖሊስነት ካገለገለ በኋላ ነገሮችን ፊት ለፊት በመናገሩና ለአለቆቹ ማጎብደድን ባለመልመዱ በግዳጅ ወደ አስመራ ፖሊስ ሠራዊት ክፍል ተዘዋወረ::
ወጣቱ ፖሊስ ተስፋብርሃን ቅር እያለውም ቢሆን አስመራን ከተመባት። በዝናዋ የሚያውቃት ከተማ ግን አልጨከነችበትም በፍቅር እጇን ዘርግታ ተቀበለችው:: ጥቂት እንደቆየ ወደ ሌላ ወረዳ ሲመደብ በአዲስ አበባው የፖሊስነት ቆይታው የነበረውን የኪነጥበብ ተሳትፎ የሚያውቁ አዛዥ ወደ ሙዚቃ ክፍል ቢመደብ የተሻለ ሊሠራ እንደሚችል በመጠቆማቸው አስመራ የሚገኘው የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃ ክፍልን ተቀላቀለ።በዚያው የሙዚቃን ሀ ሁ የሚማርበትን እድል አገኘ::
ግርምትን የሚጭረው ደግሞ የሙዚቃን ሀ ሁ ያስቆጥሩት በጥበብ አንጀታቸው በረሰረሰ፣ በበቁና በነቁት እነይስሃቅ ባንጃው እጅ መሆኑ ነው:: ሳክስፎንን ሜጀር አድርጎ መሠረታዊ የሚባለውን የሙዚቃ እውቀት ገበየ:: ጎን ለጎንም ያቋረጠውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በማታ አጠናቀቀ:: በአስመራ ዩኒቨርሲቲም ትምህርት ጀምሮ እንደነበር ይናገራል::
በአስመራ ሰማይ ስር
ዘመኑ 1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነው፤በአስመራ ፖሊስ ውስጥ በተቋቋመው ባንድ አባል ሆነ፤ ይህ ባንድ እንደማርች ባንድ ትላልቅ በዓላትን ለማድመቅና ለማጀብ የሚያገለግል በመሆኑ የሳክስፎን መሳሪያን እንዲጫወት ተመደበ:: መሠረታዊ የሙዚቃን ትምህርት በሚገባ ቢያጠናቅቅም ነፍሱ ከሳክስፎኑ ጋር ልትላመድ አልቻለችምና አጫጭር ድራማዎችን እየጻፈ ለሠራዊቱ ጭውውቶችን ማቅረብን ተያያዘው።
እነ ድምጻዊ ስዩም ጥላሁን፣ አክሊሉ ስዩም፣ጋሻው አዳል፣ ወይንሽት ጥሩነህ /በስልክ አነጋግረኝ በቀጭኑ ሽቦ/ እና ከሌሎች በወቅቱ ተደማጭ የሆኑ ድምጻውያን ጋር በመገናኘቱ የሙዚቃ ጥበብ በር እንደምትከፍትለት መተንበይ ባይከብድም እርሱ ግን ወደ ድራማው ነበር ያደላው::
ተስፋብርሃን አስመራ ከተማን የሚያስታውሰው ከኤፍሬም ታምሩ ሙዚቃ እኩል ነው። ጥሎበት ዛሬም ድረስ የኤፍሬምን ሙዚቃዎች ሲሰማ ነፍሱ ትደሰታለች፤ አብዝቶ ያደንቀዋል::ሙዚቃዎቹን ሲሰማ ግጥሞቹን እየጻፈ አብሮ እያዜመ በመሆኑ የግጥሙን ደራሲ ይልማ ገ/አብን ያሰኛኜት ብቃት ጭምር ያደንቅ ነበር::
ነፍሱ ለሙዚቃ ግጥም እንደተሰጠች ባያውቅላትም እርሱ ግን በሙዚቃ ግጥሞች እንዲሳብ ይልማ ገ/አብን ምክንያት ያደርጋል።የግጥሞቹን ቀለማት፣ ምጣኔና ምቱን ያስተምረው ነበር:: የተማረውን በተግባር ይሞክር ዘንድ አንድ ደብተር በመግዛት በውስጡ የታመቁትን ቃላት እያሽሞነሞነ በብዕሩ ጠብታ በስንኝ እየደረደረ ያሰፍራቸው ነበር::
ከእለታት በአንዱ ቀን የሙዚቃ ቀማሪው ይስሀቅ ባንጃው ከድምጻዊ ስዩም ጥላሁን ጋር ሙዚቃ ሊሠሩ ግጥም በመፈለግ ላይ ነበሩ::ይህን የሰማው ተስፋብርሃን እንደቀልድ ግጥሞች የደረደረበትን ደብተሩን ይዞላቸው ቀረበ:: በሙዚቃ ገጣሚነቱ የማያውቁትን ተስፋብርሃንን አልናቁትምና ሙሉ ደብተሩን ተቀብለው ሲመርጡ አስሩ ግጥሞቹ ይሁንታን አገኙና ዜማ ተሠራላቸው:: የተስፋብርሃን ግጥሞች በዜማ ሲከሸኑ እኔነኝ ያሉ ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ግጥም ሆኑና በፖሊስ ባንዱ ታጅበው ድምጻዊው ስዩም ጥላሁን ተወዳጅ ካሴት አድርጎ ሰደራቸው::
ለምሳሌ “አንች ወረተኛ ወረት የለመድሽው፣ ሲያምንሽ እየከዳሽ ልቤን አደማሽው” የሚለው ይገኝበታል።
የተስፋብርሃን የበኩር ሥራ የሆነው የስዩም ጥላሁን ካሴት ከአስመራ አልፎ በመላው ኢትዮጵያ እንደ ጣፋጭ ከረሜላ ተቸበቸበ::የሙዚቃ አፍቃሪያን ሁሉ ስዩም ስዩም ሲሉ ገጣሚው ተስፋብርሃንም ስሙ ባይጠራም ቆጥሮት የማያውቀውን 700 ብር ተከፈለውና የሚሆነውን አሳጣው:: ያኔ የገዛውን ሱፍ ዛሬም ድረስ ያስታውሰዋል። በአሥመራ ጎዳና ላይ በኩራት ደረቱን ነፈቶ ተዝናንቶበታል። ከጓደኞቹ ጋር ተገባብዞበታል:: የመንፈቅ ደመወዙን በአንድ ጊዜ ማግኘቱ ብቻ አልነበርም ያስፈነደቀው:: ከልቡ እንደሚያደንቀው ይልማ ገ/አብ ገጣሚ የሚለውን ማእረግ ማግኘቱና የሙዚቃ ግጥም መደርደር እንደሚችል በሚያደንቀው ይስሃቅ ስለተመሰከረለት ጭምር ነበር::
በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ በይፋ ወደ ሙዚቃው ዓለም ተቀላቀለ:: በኤፍሬም ታምሩ ሙዚቃዎች እየተመሰጠ፤ በእነ ይሳቅ ባንጃው የዜማ ቅመራ እየተደነቀ ወደ ጥበብ ቤት ተቀላቀለ:: ለግል ስሜቱ የጻፋቸው የዘፈን ግጥሞች እንዲህ ዘመን ተሻጋሪ ሆነው ዛሬ ላይ ይደርሳሉ ብሎ አላሰበም፤ በውስጡ እየተመላለሱ ሲያስቸገሩት ነው በዜማ ተዋዝተው በሙዚቃ እንዲወለዱ ለድምጻዊ ስዩም ጥላሁን የሰጠው::
የካሴቱ ሙሉ ግጥም የእርሱ ሲሆን ዜማው ደግሞ የአንጋፋው ዜማ ደራሲ ይስሀቅ ባንጃው ነበርና እንደተመኘለት ለድምጻዊው “አንች ወረተኛ” ይበልጥ ጣፈጠችለትና መጠሪያው እስክትመስል ድረስ ዘመናትን እያሸጋገረች እስከ ጉልምስና ዘመኑ አደረሰችው::
የያኔው ወጣት ፖሊስ ተስፋብርሃን በበኩር ሥራው እውቅናን ማግኘቱ አላኩራራውም፤ይልቁንስ የወቅቱ የአስመራ ሁኔታ ስላላስደሰተውና ከሙዚቃው ይልቅ ነፍሱ አብዝታ ወደ መረጠችው ትወና ያደላ ስለነበር ወደ አዲስ አበባ በ1983 ዓ.ም ዝውውር ጠየቀ።ተሳካለትና ወደ ምሥራቅ ሸዋ ፖሊስ ተመደበ፤በዝውውሩ ቢደሰትም በፀአዳዋ አስመራ ደምቃ ያገኛትን እጮኛውን ጥሎ መሄድ ከብዶት እንደነበር ያስታውሳል:: ይሁን እንጂ እጮኛውንና የሙያ አጋሩን ተወዛዋዧን መስከረም ታደሰን ለአስመራ አምኖ ከመስጠት ውጪ አማራጭ አልነበረውም፤ እንደማይከዳዱ ቃሉን ሰጥቷት ተሰናበታት::
ተስፋብርሃን ልቡን አስመራ ላይ አስቀምጦ ሞጆ ላይ ወንጀል መርማሪ ሆኖ መሥራት ጀመረ:: ሞጆ ከተማ ላይ በወንጀል ምርመራው የተዋጣለት ቢሆንም የነፍሱ ጥሪ የሆነውን ጥበብ ትቶ በመርማሪነት ለመቀጠል አልፈለገም::
አስመራ ላይ በአደራ አስቀምጦት የመጣው ልቡ ብቻውን ይሆን ዘንድ አልተፈረደበትምና በ1983 ግንቦት ወር ላይ የደርግ መንግሥት ሲፈርስ አደራውን ተቀብላ መስከረም ታደሰ ፍቅሩንና ቃሉን ጠብቃ በከፍተኛ ችግር ወደ አዲስ አበባ ገባች:: ብዙም ሳትቆይ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ተመደበች:: ሞጆ ላይ የነበረውን ብቸኝነቱን ተጋራችው:: ውጭ ሀገር ድረስ እየሄደች በመሥራት የተሻለ ገቢ ስለምታገኝ በኢኮኖሚ ጭምር ከመደገፍ አልቦዘነችም::
ዓመታት ተቆጠሩ በ“አንች ወረተኛ” ሙዚቃ ዝነኛ የነበረው ፖሊሱ ተስፋብርሃን ከሙዚቃ ርቆ ወንጀል ምርመራው ላይ ማተኮሩን ብዙዎች አልወደዱለትም:: ከነፍሱ ጥሪ ጋር የተራራቀው ሃምሳ አለቃ ተስፋብርሃን የወንጀል ምርመራ ሥራው በወቅቱ የነበረው ፖለቲካ ስላከበደበት ድንገት ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ መጣ::
የባከኑ ዓመታት – ስደት
መርማሪው ተስፋብርሃን በአንድ ጊዜ ከሃምሳ አለቃ ፖሊስነት ወደ ሥራ አጥነት ተቀየረ፤ ወትሮም የማታወላዳው የፖሊስ ደመወዝ ጥሪት ለመቋጠር አትሆንምና አዲስ አበባ ላይ አስቸጋሪ የሚባል ሕይወት ነበር የጠበቀው::
በአዲስ አበባ ቴአትር ቤቶች እየዞረ ከሚወደው ትወና ጋር እንዲያገናኙት ብዙ ደጅ ጠና። ጥበብ የጠራችውን ቤተ ጥበበኞቹ ባለመጥራታቸው ብዙም አልተገረመም:: ያለው አማራጭ ጥበብን ፍለጋ ከራሱ ጋር መምከር ነበርና አውጥቶ አውርዶ አንድ ክፉ ሃሳብ ብልጭ አለለት:: ሀገር ጥሎ መሰደድ፤ ከሁለት ወዳጆቹ ጋር በመሆን በሚያውቃት አስመራ ምጽዋ አድርጎ የመን ከዚያም ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት በመቀሌ አድርጎ የስደት ጉዞውን ጀመረ:: ጉዞው እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር ያስታውሳል።
በህይወት ዘመኑ ካሳለፋቸው አስቸጋሪ ጊዜያት ቀዳሚው ሆኖ ማለፉን ሲገልፅ “ስደት አይኑ ይጥፋ” ያሰኘዋል:: የሳዑዲ አረቢያ ጉዞ እጅግ አስቸጋሪና ህይወቱን ሊያሳጣው የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ያሳለፈበት ነበር:: “ከምጽዋ የመን ለመግባት የከፈልነው መስዋእትነት በቃላት የሚገለጽ አይደለም:: አይኔ እያየ ሰዎች ቀይ ባሕር ሲበላቸው ምንም ማድረግ አለመቻሌ ያሳዝነኛል፤ ሞትን የሚያስመኘውን ጉዞ በፈጣሪ ቸርነት አልፌ ጂዛን የሚባል የሳዑዲ ግዛት ደረስኩ። ከገባን በኋላም ቢሆን ከውሃ ጥም በተዓምር ነበር የተረፍነው፤ ምን ፍለጋ እንደሄድኩ እንኳን ግራ እስኪገባኝ ድረስ ነው የተሰቃየሁት:: በዛ ሁኔታ መኖር እንደማይቻል ሲገባኝ ጊዜ ሳላባክን በወራት ውስጥ ነው ሀገሬ ማሪኝ ብዬ የተመልስኩት” በማለት ያስታውሰዋል::
ስደተኛውን ሸገርና ፍቅረኛው መስከረም በጉጉት ይጠብቁት ነበርና አላሳፈሩትም እጃቸውን ዘርግተው ተቀበሉት:: ህይወት እንደ አዲስ ቀጠለ፤ በድጋሚ ከጥበብ ጋር የሚያገናኘውን መንገድ ማፈላልግ ጀመረ:: እንደ ከዚህ ቀደሙ ጥበብን በየቴአትር ቤቶቹ አልነበረም የፈለጋት::ይልቁንም በወቅቱ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጎጆ መውጫ የሚባል ድራማ ተላልፎ አድናቆትን አትርፎ ነበርና እነዛን ተዋንያን አፈላልጎ አገኛቸው::
ብዙም ሳይቆዩ የጎጆ መውጫ ደራሲና ተዋናዩን በምናቡ ከበደ እና መኮንን ተፈሪ ጋር ሆነው ቡድን አቋቋሙ:: ፈተና፣ ፍቅርተ እና ሌሎች አጫጭር ጭውውቶችን ለኢቲቪ እየሠሩ ወደ ትወናው ዓለም ነፍሱን መለሳት:: አንድ የሙሉ ጊዜ ቴአትር ሠርተው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ በማሳየት የተሻለ ገቢ አገኙ::
ዳግም ወደ ሙዚቃ
ተስፋብርሃን በትወናው ውስጥ ሆኖም ቀልቡ ከሙዚቃ ጋር አልተራራቁምና ወደ ሙዚቃው ዓለም ለመግባት ፍለጋውን አላቆመም ነበር:: አስመራ እያለ የሚያውቀው ድምጻዊ ሙሀመድ አወል ሳልህ ከአስመራ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከተሰደደበት አዲስ አበባ እንደ መጣ ሲሰማ በሚሠራበት ምሽት ቤት አፈላልጎ አገኘው:: አብረው ለመሥራት ተስማምተው ተስፋብርሃን የባንዱ መሪ በመሆን ሥራውን አሳለጠው:: በዚህ መሃል ለድምጻዊ መሐመድ አወል የሚስማሙ 10 ግጥሞችን ይዘው ወደ አቀናባሪው ሙሉጌታ አባተ ሄዱ:: ሙሉጌታ አባተ ያኔ ከሮሃ ባንድ መፍረስ በኋላ የመጣ ጎበዝ አቀናባሪ ነበር:: በተለይም ባህል ዘመናዊ የሚባለውን የሙዚቃ ስልት እያቀናበረ ለሀገራችን ሙዚቃ የማይዘናጋ አስተዋጽኦ ያበረከተ ነበር::
ተስፋብርሃን የሙዚቃ ሕይወቱ ብዙ ወዳጆችን እንዳፈራለት ይናገራል:: የሙሉጌታ አባተን ያህል ለነፍሱ የቀረበ የሙያ አጋር እንዳልነበረው ያስታውሳል:: ከአቀናባሪው ሙሉጌታ አባተ ጋር የነበራቸው ከ7 ዓመት ያላነስ ጊዜ በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የገዘፈውን አበርክቶ ያደረጉበት ጊዜ እንደነበርም ይናገራል። ሙዚቃን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያሳደጉበት የምናኔ ዘመናቸውም እንደነበርም ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል::
ተስፋብርሃንና የሙሉጌታ ቁርኝት የትወና ፍለጋውን አስትቶ ሙሉ በሙሉ ሙዚቃው ላይ እንዲያተኩር አድርጎታል:: እየተመካከሩ ስለሚሠሩ እጅግ በርካታ የሚባሉ ድምጻውያንን አፍርተዋል። የሙዚቃ አድማጩን የሙዚቃ ጥም ያረኩበት ጊዜም ሆነላቸው::
“በወቅቱ ሮሃ ባንድ የፈረሰበት ጊዜ ስለነበር ሙዚቃ መሥራት ታግዶ ነበር:: ይህ ጊዜ ለሙሉጌታ አባተ መልካም አጋጣሚን ፈጠረለት:: በሙዚቃ ይበልጥ እንዲመራመር እድል ሰጠው፤ ከዘመናዊ የሙዚቃ ምቶች ውስጥ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎችን በማስገባት እንደ ጎንደርኛ፣ ጎጃምኛ፣ የወሎና ሌሎችንም የሙዚቃ ስልቶችን በአንድ ኪቦርድ መፍጠር የተቻለበት ጊዜ ሆነ::“ያኔ አብረን አንድ ስቱዲዮ ነበር እየተመካከርን የምንሠራው እሱ ዜማውን ይፈጥራል፤ እኔ ግጥሙን እሠራልሁ፤ሙዚቃን እናሳብዳታለን” በማለት ነው ያን ወርቃማ ጊዜ የሚያስታውሰው::
“የማስተር ሳውንድ ሙዚቃ ቤት ባለቤት ወይዘሮ ፅጌ በላቸው ካሴት እንድንሠራላት ሃሳቡን አመነጨች። በወቅቱ የማናለቦሽ ዲቦ ‘አሳበለው’ በሚለው ዘፈኗ ነበር የምትታወቀው::ማናለቦሽ ዲቦም ካሴት ለመሥራት ትፈለግ ነበርና ሙሉጌታ ዜማውን ሥራው እኔ ጎጃምኛውን፣ጎንደርኛውንና የምንጃሩን ግጥም ሠራሁ። ሌሎች ሁለት ገጣሚያን ተሳትፈው ሙሉውን ካሴት ሠራነው:: ይሁን እንጂ ካሴቱ ተጠናቆ ሊወጣ ሲል ከአእምሯዊ ንብረት ጋር በተያያዝ ሙዚቃ ማሳተም ተከለከለ:: የማናለቦሽን 12 ዘፈኖች ሙሉጌታ ለ2 ዓመት ተጠበበበት:: ከሁለት ዓመት በኋላ ሲፈቀድ ካሴቱ እንደ ከረሜላ በየመንደሩ ተቸበቸበ” በማለት ተስፋብርሃን ወደ ሙዚቃ ግጥም የተመለሰበትን ዘመን ያስታውሳል::
በጥበብ መፈወስ
የሙዚቃ ግጥም ደራሲና ተዋናዩ ተስፋብርሃን በሰዎች ዘንድ ብዙ ባይታወቅም ብዙዎችን አሳውቋል:: የአማርኛ የባህል ሙዚቃዎች ሲጠቀሱ እርሱ ከጀርባቸው እንዳለ በእርግጠኝነት ለመናገር ያስደፍራል:: በተለይ የበዓል ቀን በሚዲያ ከሚሰሙት 10 ሙዚቃዎች መካከል 7ቱ የእርሱ ግጥሞች ናቸው::
በእርሱ መንፈስ ተጸንሰው፤ በእርሱ ብእር ተከትበው በዜማ ተከሽነው ጥበብ ሆነው የገዘፉት ሙዚቃዎች ቁጥር ስፍር ቁጥር የላቸውም፤እንዲሁ በግርድፉ ከተሰሉ ሶስት ሺህ ይሻገራሉ:: በመደርደሪያው ውስጥ ተወሽቀው ገና ኳኩሎ ያላስዋባቸው ግጥሞቹም የዛኑ ያህል ብዙ ናቸው:: ዘመን ተሻግረው ዛሬም ደረስ የሚደመጡት ሙዚቃዎችን በማይነጥፈው ብእሩ አምጦ የወለዳቸው እርሱ መሆኑን እስኪዘነጋ ድረስ ዛሬም ድረስ የማያስታውሳቸው ሙዚቃዎች ጥቂት አይደሉም::
እንደ “ዓባይ ነጋ ጠባ ሀብቱን ያፈሰዋል፤ ጢስ አልባው ነዳጄ ብለው ምን ያንሰዋል”ን የመሰሉ ወቅታዊ ጉዳዮችንም በብእሩ አምጦ ወልዷቸዋል:: በተለይ በተለይ የተዘነጉትን ቱባ ባህላዊ ክዋኔዎች ፈልፍሎ እንደማውጣት የሚያስደስተው ሥራ የለም::
ከእነ ሙሉጌታ አባተ፣ ከእነ አበበ ብርሃኔ፣ ከእነ ዘላለም መኩሪያ ጋር የሠራቸው የሙዚቃ ግጥሞች ብዙዎች ተቋድሰዋቸዋል:: “እጅግ እጅግ፣አልሞትም፣ውሎየው ተጓዥ” ን የመሳሰሉትን ግጥም የሰጣት ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ አብዘቶ ያከብራታል። እንደእህቱ ይሳሳላታል:: ለሙያው ብቃትና ትልቅ አክብሮት ካላቸው ድምጻውያን መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይሰጣታል::
“አወይ ጊዜ ጊዜ ደራሽ” ሀመልማል አባተ፣ “ነጃ በለኝ ነጃ ታውቀዋለህና የፍቅርን ደረጃ” ብላ ግጥሙን በድምጿ ነፍስ የዘራችበት ሀና ሸንቁጤ፣ “ምስጋናው ደግ ነው” የሚለውና በርካታ የሙዚቃ ግጥሞች የሠራለት ይሁኔ በላይ፣ መስፍን በቀለ፣ ሻምበል በላይነህ፣አሸብር በላይ፣ማናለቦሽ ዲቦ፣መሀመድ አወል ሳልህ ሦስት አልበም ሙሉ፣ብርቱካን ዱባለ፣ገነት ማስረሻ፣ እንደልቤ ማንደፍሮ፣አምሳል ምትኬ፣ምናሉሽ ረታ፣ ሰማኸኝ በለው፣ግዛቸው ተሾመ፣አማረ መንበሩ እና ሌሎችም በርካቶች ይጠቀሳሉ::
ከአዳዲሶቹ እነ ሃናን አብዱን የመሰሉ የባህል ፈርጦች “አርከባስ፣አግራው፣እሪበል ወንዱ” የመሳሰሉ በቱባው ባህልና በጥበብ የበለፀጉ የሙዚቃ ግጥሞችን እንካችሁ ብሎናል::የትምወርቅ ጀምበሩ፣አህመድ ማንጁስ፣ሚሚ ሙሉቀን እና ለሌሎች በርካታ ድምጻውያን ከነጠላ ዜማ እስከ ሙሉ አልበም የእርሱን የመንፈስ ምጦችና የብዕር ጠብታዎች ተቀብለው ሙዚቃ አሰኝተዋቸዋል::
እንደ ሥራው የሚያከብረው መንግሥታዊ ተቋም ባያገኝም በሥራዎቹ የታወቁትና የተከበሩት ልክ እንደ ወላጅ አባታቸው ያከብሩታል:: እንደ አለመታደል ሆኖ በጥበብ ዙሪያ እውቅናና ሽልማት ከተሰጠ እርሱ እስከ መፈጠሩ የሚዘነጉትና እውቅናው ካለፈ በኋላ ይቅርታ የሚጠይቁት ብዙ ናቸው::
ለሀገሩ ያለው ፍቅር እዚህ ድረስ ነው አይባልም:: ለሀገራዊ ጥሪዎች ሁሉ ጎትጓች አይፈልግም፤ቀደሞ ነው ከፊት የሚሰለፈው::በተለይም “ወታደር ነኝ!” የሚለው የመከላከያ ሠራዊት መዝሙር ዛሬም ድረስ የሚኮራበት ሀገራዊ ሥራው ነው::
“በዓላማ የፀናሁ በጀግንነት ቁሜ
ድንበር የማስከብር ባጥንትና ደሜ”
ይህን መዝሙር ግጥም የጻፈው ተስፋብርሃን ዜማውን ደግሞ ዘላለም መኩሪያ ነው የሠራው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ሲመረቅ ፕሮዲዩሰሮቹ እርሱን አልጋበዙትም::ሲሸላለሙበትም እርሱን አላስታወሱትም::
ተስፋብርሃን አመስጋኝ ነው:: ነፍሱ ደስተኛ ናት፤ከጎደለው ይልቅ ባለው ነገር ያመሰግናል:: ለሙዚቃ የእድሜ ልክ አበርክቶው የሸለመው አካል ባይኖርም በሀገሩ ቅር ተሰኝቶና ተከፍቶ አየሁት የሚለው የለም፤ የሚሠራው ለእውቅና ባለመሆኑ እውቅናን አስቦትም አያውቅም::የእርሱ የጥበብ ፍሬዎች ብዙ በመሆናቸው በሥራዎቹ የሚያከብሩትም እነርሱ ስለሆኑ በጥበብ የወለዳቸው ሽልማቶቹ እንደሆኑ ያስባቸዋል::
ተስፋብርሃን (ኢንጅነር ባንጃው) የእድሜውን አብዛኛው ክፍል ያሳለፈው በሙዚቃ ግጥም ቢሆንም ብዙ ሰው የሚያውቀውና የሚያስታውሰው ለሦስት ወራት በሠራው ደምብ-5 በተሰኘው የቴሌቪዥን ድራማ መሆኑ ሁልጊዜም ይደንቀዋል:: በሬዲዮና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተከስቶም ብቃቱን አስመስክሯል:: ማተብ፣ የወደዱት፣ የከንፈር ወዳጅ፣ ጀምበር፣አሸንክታብ ፣አዲስ ሀገር…. የመሳሰሉትን ድራማዎችና የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችንም መጠቃቀስ ይቻላል:: አሁንም አዳዲስ የቴሌቪዥን ደራማዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል::
ቤተሰብ
የትዳር አጋሩን ያገኘው “አንች ወረተኛን” በፈጠረባት አስመራ ከተማ ነው:: በአስመራ ጎዳና ላይም መስከረም ታደሰ ጋር የፍቅር ቄጤማን ለአንድ ዓመት አካባቢ ቀጭተውባታል:: ልቡን ለእርሷ አስረክቦ ወደ ሞጆ ሲዛወር ቃላቸውን ጠብቀው እንደሚገናኙ እርግጠኞች ነበሩና ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመው ዳግም ተገናኝተዋል:: ቃሏን ጠባቂዋ መስከረም የችግር ጊዜ ፍቅረኛዋን ለመክዳት ድፍረት አልነበራትም፤ የቁንጅና ዘመኗ አላሳሳታትም፤የከበቧት ሁሉ በአይኗ አልሞሉላትም፤በውዝዋዜ ሙያዋ የተጓዘችባቸው በርካታ ሀገራት ልቧን አላሸፈቱትም፤ የዱባይ ወርቆች አይኗን አላጥበረበሯትም፤ ቃሏን ጠብቃ በፀአዳዋ አስመራ ጎዳናዎች ላይ አይኗ የገባውን ጥበበኛ ከማንም እና ከምንም ጋር አላወዳደረችውም::
ለጎኑ ማረፊያ የሚሆን ጎጆ እንኳን አለመኖሩ አላሳፈራትም:: “ምን አለው?” የሚለው የቤተሰብ ጥያቄም አላስጨነቃትም፤ቁሳዊ ሀብት ባይኖረውም በውስጡ ያለውን መክሊት ታውቃለችና ፍቅሩን አስቀድማ አብራው ለመሆን ከመወሰን ያገዳት አንዳች ነገር አልነበረም:: ፍቅሯን በትዳር አስራ አብራው ለመሆን ወስናለች፤ በውሳኔዋም የማትፀፀትበትን ፍሬ አፍርታለች። ሩታ ተስፋብርሃን እና ሃሌሉያ ተስፋብርሃንን የመሳሰሉ ልጆች ታቅፈዋል:: ለእርሱም የአይኑ ማረፊያ፣ሲደስት የደስታው ተጋሪ፤ ሲከፋው መፅናኛ የሆኑትን ልጆች ለቤቱ ድምቀት አግኝቷል።
ከጥበበኛ ወንድ ጀርባ ጥበበኛ ሚስት አለችና እርሱዋም ተወዳጅ ተወዛዋዥ በመሆኗ የጥበብ ምጡን ትጋራለታለች፤ተመስጦውን ታከብርለታለች፤በማንኛውም ሁኔታ ታበረታታዋለች፤ ታግዘዋለች:: ለሥራው ስኬት ከርሱ በላይ ትጨነቅለታለች፤ በሥራው ንዋይ ባይትረፈረፍላትም እንደ ልጆቹ መጠሪያው በሚሆኑት ከሦስት ሺህ በላይ የሙዚቃ ግጥሞቹ አብራ ትጠራባቸዋለች:: በእርሱ ሥራዎች የከበሩና የታወቁት እርሱን ሲያከብሩት አብራ ትከበርበታለች፤ሲመሰገንና ሲደነቅ አብራ እንደምትመሰገን ታውቃለችና ትኮራበታለች።
ምክረ ሃሳብ
ተስፋብርሃን ወግ አዋቂ ብቻ ሳይሆን ታሪክና ባህልንም ጠንቀቆ የሚረዳ ነው። አንባቢ ነው፤ በተለይም ታሪክ ነክ የሆኑ መጽሐፍት ተቀዳሚ ምርጫው ናቸው:: የጋን ውስጥ መብራትም አይደለም፤ ያወቀውን ለማሳወቅ ምክንያት አይፈልግም፤ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመተረክ ሌሎች እንዲጋባባቸው ያደርጋል::
“ገጣሚ ሁኜ የምቀጥል ከሆነ ሁልጊዜም አዳዲስ ነገሮችን በንባብ ማዳበር አለብኝ፤ ለተደራሲ የተሻለ ነገር ለመስጠት ሁልጊዜም የማህበረሰቡን የእውቀትና የስልጣኔ ደረጃ ባገናዘበ እውቀት መሙላት አለብኝ” የሚለው ተስፋብርሃን እለት በእለት የሆነ ነገር ሳያነብ አይተኛም::
ከዘመን ተጣልቶና ተኳርፎ መኖር ስለማይችል የዘመኑን እውቀቶች ከመቀበል ወደኋላ አይልም:: የሚሠሩትን ያበረታታል፤የሚያበላሹትንም ፊት ለፊት ይነቅፋል። ከ3ሺህ በላይ የባህል ሙዚቃዎችን ግጥሞች በመሥራቱ ለሀገሩ ያለውን ፍቅር እያዳበረለት እንደመጣ ይናገራል:: ዓሳ ከባሕር ወጥቶ በህይወት እንደማይኖር ሁሉ እርሱም ከሀገሩና ከባህሉ ርቆ መኖር እንደማይችል አረጋግጧል:: የጂኦግራፊ መምህር ይመስል የሀገሩን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ነጥብ በነጥብ ጠንቅቆ ያውቃቸዋል:: የዞን የወረዳና የቀበሌዎችን ስም ብቻ ሳይሆን የአየር ጠባያቸው ሳይቀር፣ወንዝና ሸንተረሩን፣ገዳማት መሰጂዱን፣ዘዬና ትውፊቱን አለባበስና አጊያጌጡን በሚገባ ያውቃል::የግጥሞቹ ይዘትም ከዚሁ የሚጨለፉ በመሆናቸው ለታሪክ ነገራና ለምስል ክሰታ አይቸገርባቸውም::
የወርቃማው ሙዚቃ ዘመን ፍሬ ነውና አሁን በሚያየውና በሚሰማው የሙዚቃ ሥራዎች አብዝቶ ያዝናል። “መነሻና መድረሻ የሌላቸው፣ባህልና ታሪክን የማይጠቅሱ፣ የማህበረሰቡን ስብዕናና ሥነ ምግባር የማያከብሩና የማይገነቡ ጥበባዊ ሥራዎችን እንደ ማየት አሳፋሪ ነገር የለም” የሚል እምነት አለው:: የአንድ ማህበረሰብ ባህሉንና ታሪኩን፣ትውፊቱንና እምነቱን የማያከብር ጥበብ “እርግማን ነው” ይለዋል:: መንግሥትም ሆነ የሙዚቃ ሙያ ማህበሩ ሙዚቃን ለማክበር የጥበቡን አመንጭዎች ማክበርና እወቅና መስጠት አለበት ይላል:: ከድምጻዊው እኩል ለሙዚቃ ግጥም ደራሲው፤ ለዜማ አውጪው እንዲሁም ለሙዚቀኛው በየደረጃው እውቅና መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ይገልጻል።
‹‹በአሁኑ ወቅት የሀገራችንን ሙዚቃ የሚዘውሩት በውጭ ሀገር ያሉ ሰዎች ናቸው:: እነርሱ የፈለጉትን እንጂ ጥበቡ የሚፈልገውን አይደለም የሚመርጡት፤ ለሀገራቸው ግብር እንኳን የማይከፍሉ ሰዎች እንዴት በሀገራችን ሙዚቃ ላይ ወሳኝ ይሆናሉ?›› በማለት ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ያደረገውን ቆይታ በሞጋች ጥያቄ ይቋጫል::
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን እሁድ የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም