
– የዓለም የገንዘብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ነው
አዲስ አበባ፦ ለረጅም ጊዜ የቆዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመሻገር የለውጥ ሥራዎቻችንን በጠንካራ ትኩረት እና ባለቤትነት በመያዝ ቆራጥ፣ ሁሉን አቀፍ እና ታሪካዊ ርምጃዎችን ወስደናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት ፤ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስታሊና ጂኦርጂዬቫ በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት ጉብኝት እንኳን ደህና መጡ ብለዋል።
አይኤምኤፍ ለኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራማችን የሚያደርገውን የቀጠለ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ የእርስዎንም የግል ጥረት እና አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ዋጋ እንሰጠዋለን ሲሉም ገልጸዋል።
በአይኤምኤፍ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ታላላቅ የድጋፍ መርሃ ግብሮች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም በሀገር በቀል ርዕይ እና የለውጥ አጀንዳ ላይ የተመሠረተ የእድገት እና የልማት ህልሞቻችንን በሚገባ ቀርጾ የያዘ ነው ብለዋል።
ለረጅም ጊዜ የቆዩ የማክሮ ኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመሻገር የለውጥ ሥራዎቻችንን በጠንካራ ትኩረት እና ባለቤትነት በመያዝ ቆራጥ፣ ሁሉን አቀፍ እና ታሪካዊ ርምጃዎችን ወስደናል ሲሉም አክለዋል።
በፕሮግራሙ እስካሁን የታዩ ውጤቶችም ቀና እና አበረታች ናቸው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው። እየተካሄዱ ያሉ የትግበራችን ሥራዎችም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት፣ እድገትን ማፍጠን፣ የዜጎች ኑሮ ደረጃን ማሻሻል ሲሆኑ በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን ማስቻል ናቸው ብለዋል።
በተያያዘ ዜና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ብሄራዊ ቤተመንግሥት ሙዚምንና ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልንና ብርሃን የዓይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤትን ትናንት ጎብኝተዋል።
በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት ዋና ዳይሬክተሯ ፤ ቀደም ብሎ ከገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል። እንዲሁም ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከልንና ብርሃን የዓይነ ሥውራን አዳሪ ትምህርት ቤትን ጎብኝተዋል።
ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር በኢትዮጵያ ስላሉ የንግድ እና ኢኮኖሚ እድሎች ሃሳቦችን እንደሚለዋወጡም ተገልጿል። የዋና ዳይሬክተሯ ጉብኝት አይኤምኤፍ ኢትዮጵያ ለማይበገር እና ዘላቂነት ያለው ጠንካራ የኢኮኖሚ ዕድገት ለምታደርገው ጥረት ያለውን የድጋፍ ቁርጠኝነት የሚያመላክት እንደሆነም ነው የተመላከተው።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ዋና ዳይሬክተሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሺዴ፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ እና የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ እ.አ.አ ከ2019 ጀምሮ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋምን በማኔጂንግ ዳይሬክተርነት በመምራት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን የካቲት 2 ቀን 2017 ዓ.ም