በመዲናዋ የትራፊክ መጨናነቅን መነሻ ያደረጉት የመንገድ መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች

የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ በየጊዜው እየሰፋች እና በሕዝብ ቁጥርም በፍጥነት እያደገች ትገኛለች። ከተማዋ ከተለያዩ የሀገሪቷ ክልሎች እና ከተሞች ጋር የምትገናኝባቸው መንገዶች ቀደም ብለው ተሠርተዋል። መዲናዋ ምንም እንኳን ቀደም ብለው የተሠሩና ከተለያዩ ክልሎች ጋር የሚያገናኙ መውጫ መንገዶች ቢኖሩም አብዛኛዎቹ አሁን ካለው መጨናነቅ አንፃር የማይመጣጠኑ ናቸው። መንገዶቹ ከከተማዋ የማስተናገድ አቅም በላይ ስለሆኑም በተለይም መውጫዎች አካባቢ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቆች ይስተዋልባቸዋል።

በዚህ ምክንያት ተሽከርካሪዎች እና ነዋሪዎችም ለከፍተኛ እንግልት የሚዳረጉበት ሁኔታ አለ:: ወደ መዲናዋ የሚገቡና የሚወጡ ከባድ ተሽከርካሪዎች ለመንቀሳቀስ ሲቸገሩና የከተማዋ መግቢያዎች የአደጋ ስጋት ሲሆኑ ይታያል። ይህም የመዲናዋን ብሎም የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደኋላ የሚመልስ ነው። መንገዶቹ ደረጃቸውን ጠብቀው የመስፋትና አዳዲስ ማስተንፈሻዎችንም የሚፈልጉ ናቸው።

ይህንኑ ሁኔታ ለመቀየር የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከባለድርሻዎች ጋር በመሆን የአዲስ አበባ እና የሸገር ሲቲን ብሎም የተለያዩ የሀገሪቱን ክልሎች የሚያገናኙ መንገዶችን በከተማዋ የተለያዩ መውጫዎች እየገነባና የማስፋፊያ ሥራዎችንም እያከናወነ ነው፤ እንዲሁም ተጨማሪ ጥናቶችም እያደረገ ይገኛል። በተለይም ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ከዓለምገና-ቡታጅራ፣ ከአዲስ አበባ አምቦ፣ ከአዲስ አበባ ጎሃፅዮን፣ ከአዲስ አበባ ደብረብርሃን ያሉ ከከተማዋ መውጫ መግቢያ፣ ሸገር ሲቲ ከተሞች መገበያያዎች እና በፕሮጀክቱ የተካተቱ መንገዶች መካከል የሚገኙ ናቸው።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርም በከተማዋ መግቢያ እና መውጫዎች አካባቢ ያለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ታሳቢ በማድረግ በእነዚህ መውጫዎች እና መግቢያዎች ደረጃቸውን የጠበቁ የአዲስ የመንገድ ፕሮጀክት ሥራዎች እንዲሁም የማስፋፊያ መንገድ ግንባታዎችን እየሠራ ይገኛል። የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ከእነዚህ መንገዶች የተወሰኑ ሥራ ላይ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን ከሰሞኑ ለጋዜጠኞች ቡድን አስጎበኝቷል። የስታዲያ ኢንጂነሪንግ ሥራዎች አማካሪና ሲኒየር የሃይዌይ ኢንጂነር ሻሎም የኔነህ በአዲስ አበባ መግቢያ አካባቢዎች በሚከናወኑ እና ጥናት ላይ በሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢንጂነር ሻሎም እንደሚያስረዱት፤ አዲስ አበባ ትልቅ የኢኮኖሚ ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ከከተማዋ የሚወጡና የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ፈጥረዋል። ለዚህም በራዲያል የመንገድ ጥናት ፕሮጀክት አማካይነት ጥናት ተደርጓል። ከጥናቱ ጋር ተያይዞ በመዲናዋ መውጫዎች አካባቢ የተጀመሩ ግንባታዎች ያሉበትን ደረጃዎች ማየት ተችሏል። ጥናቱም የሚያካትታቸው የመጀመሪያው ʻኤ አንድ’ የተባለ መንገድ ከአዲስ አበባ ወደ ቢሾፍቱ የሚሄደው ነባር መንገድ ነው። እንዲሁም ከአዲስ አበባ ወደ አዳማ የሚሄደው የፍጥነት መንገድ አለ።

በተጨማሪም ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረብርሃን የሚሄደው ʻኤ ሁለትʼ ተብሎ የተያዘ መንገድ ሲሆን ከአዲስ አበባ በሱሉልታ አድርጎ ወደ ፍቼ የሚሄደው መንገድ ደግሞ ʻኤ ሶስትʼ መንገድ ተብሎ ተለይተዋል ይላሉ። ሌላኛው ʻኤ አራትʼ የመንገድ ፕሮጀክት ከአዲስ አበባ አምቦ የሚሄደው መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹ኤ አምስት አንድ የሚባለው ፕሮጀክት ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ጅማ የሚሄድ መንገድ ፕሮጀክት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ኤ አምስት ሁለት ከዓለም ገና ወደ ቡታጀራ የሚሄድ የትራንስፖርት መንገድ ነው። እነዚህም የመንገድ ፕሮጀክቶች በስታዲያ ኢንጂነሪንግ የመንገድ ጥናት የተካተቱ መንገዶች ናቸው›› በማለት ያብራራሉ::

የጥናቱ ዋና መሰረቱን በተመለከተ ኢንጂነር ሻሎም እንዳስረዱት፤ በመሬት ላይ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ምን እንደሆነ፤ መጨናነቁ ከምን የተነሳ እንደተፈጠረ ለማወቅ ትኩረት አድርጓል። በመሆኑም ከአዲስ የአበባ በሸገር ሲቲ በኩል አድርጎ ወደ ተለያዩ የሀገሪቷ ትላልቅ ከተሞች የሚሄዱ መንገዶች ላይ ያለው የመጨናነቅ ሁኔታ ከምን የተነሳ እንደተፈጠረም ይዳስሳል:: በምን መልኩ ደህንነቱ የተጠበቀ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴው የተስተካከለ ሁኔታ ለትራፊኩ መስጠት እንደሚቻል የመፍትሔ አማራጮችን አስቀምጧል።

በትራፊክ መጨናነቁ ምክንያት የሚቆሙ መኪናዎች መንገድ ላይ ተደርድረው የሚታዩ ከባድ መኪናዎች ሀገሪቷ ላይ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው የሚናገሩት አማሪዋ፤ ‹‹በትክክለኛ ፍሰቱ መሠረት ወደ መዲናዋ መግባት እና የፈለጉትን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማከናወን አለመቻላቸው የሀገሪቷ ኢኮኖሚው ላይ ያላው ተግዳሮት ላይ ጥናት ተደርጓል›› በማለት ያመለክታሉ። በጥቅሉ በጥናቱ መንገዱ ላይ ያሉ ተግዳሮቶች፣ የመንገድ ትስስሩ ምን እንደሚመስል፣ ለችግሮቹ ስትራቴጂዎች ተቀርጸዋል፤ እንዲሁም አካባቢያዊ እና ማህበራዊ ተፅእኖ ጭምር ተገምግመው መጠናቀቃቸውን ነው ያስገነዘቡት።

በሁለተኛው የጥናቱ ክፍልም በአንደኛው ክፍል የተለዩ ችግሮችን ተገቢነት ያላቸው የመፍትሔ አማራጮች መቅረባቸውን ጠቁመው፤ ከችግሮቹ መካከል ከአዲስ አበባ የሚወጡ የትራንስፖርት መንገዶች በጣም የተጣበቡ መሆናቸው፣ የአዲስአበባ ፍሰት እና ትልቅ ትራፊክ ተጠቅልሎ የሚወጣው በሁለት መስመር ብቻ መሆኑ እንደሆነ ያስረዳሉ። በተጨማሪም ተገቢ የሆነ የእግረኛ መንገድ የተሟላላቸው አለመሆናቸው የተለየ ችግር መሆኑን ይናገራሉ:: ‹‹እግረኛውም፣ ተሽከርካሪውም፣ ብስክሌተኛው ሁሉ ሰባት ሜትር ስፋት ያላትን መንገድ መከተላቸው ሌላኛው ዋነኛ ችግር ሆኖ የተለየ ነው›› ይላሉ::

እንዲሁም የመኪና ማቆሚያ አካባቢዎች በየቦታው ባለመኖራቸው በዚያችው መንገድ ላይ ከባድ ተሽከርካሪዎች ጭምር የሚቆሙ መሆኑ ትልቅ መጨናነቆችን መፍጠራቸውን ያስረዳሉ። መንገድ ላይ የሚሰሩ የተለያዩ አይነት የመንገድ ላይ ንግዶች ደግሞ መንገዶቹ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳላቸው ያስገነዝባሉ። ከዚህም ባሻገር በመንገድ ግንባታና ጥገና እንዲሁም የተለያዩ ህንፃ ግንባታዎች ወቅት እዛው መንገድ ላይ የሚደረጉ የግንባታ ቁሳቀሶች ጎልተው የወጡ የተለዩ ችግሮች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ኢንጂነር ሻሎም እንዳስታወቁት፤ ለእነዚህ ለተለዩ መጨናነቆች የፈጠሩ ችግሮች የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ መፍትሔዎች ተብለው ተለይተው የቀረቡ አማራጮችም በጥናቱ ተካተዋል። በአጭር ጊዜ መፍትሔም በተጨባጭ የሚታየውን ማስተካከል፣ ማፅዳት፣ የእግረኛ መንገዶቹን መሥራት፣ መጠገንና ተገቢ የሆነ የመንገድ ላይ ምልክቶችን መሥራት ናቸው። የአውቶቡስ መንገድ፣ የፓርኪንግ መስመሮች፣ የብስክሌትና የእግረኛ መንገዶችን ሰፋ አድርጎ መሥራት ይገኝበታል። እንዲሁም ነባር መንገዱን በራሱ አስፋፍቶ መሥራትና የተለያዩ መተላለፊያዎች ላይ ያሉ መጨናነቆችን ለማስቀረት፣ የተለያዩ የዲዛይን ማሻሻያዎችን በማድረግ መሥራት የመካከለኛ ጊዜ አማራጭ ሆኖ ተካቷል።

በሶስተኛነት ደግሞ የረጅም ጊዜ አማራጭ ሆኖ የተካተተው ከእነዚህ ማስፋፊያ መንገዶች ጋር ሰፊ ትላልቅ የሆኑ ትይዩ መንገዶችን መሥራት ነው። ከከተማው በውጪ በኩል በመሥራት ሁሉም አካባቢዎች ሊስተናገዱበት የሚችሉ ተጨማሪ ቀለበት መንገዶችንም በረጅም ጊዜ መፍትሔ አማራጭነት ተካተዋል። በረጅም ጊዜ እቅድ በከተማው በውጪ በኩል የሚሠሩት የአዋጭነት ጥናቱም ተግባራዊ ዲዛይኑም የተሰራላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ኢንጂነር ሻሎም እንደገለፁት፤ በጥናቱ የመካከለኛ ጊዜ መፍትሔ ላይ ከከተማው የወጡ ሳይሆን በከተማው ዙሪያ አካባቢ ናቸው። ለምሳሌ ከጣፎ አደባባይ አንስቶ ወደ ለገዳዲ የሚሄደው መንገድ ሰፋ ማድረግ ነው። በተመሳሳይ የማገናኘት ሥራዎች መሥራት ይገኝበታል። በዚህም ከዚህ ቀደም የተጠናቀቀው ከእንጦጦ አደባባይ ወደ ኮተቤ የሚሄደውን ከጣፎ አደባባይ ያለውን መንገድ ማገናኘት አንዱ ነው። ከኮተቤ እንጦጦ ማርያም ቀደም ብሎ የተሠራ መንገድ ጋር ማገናኘት፤ ከእንጦጦ ማርያም ደግሞ ወደ ጉለሌ እፅዋት ማዕከል ቀድሞ የተገነባ መንገድ ያለ በመሆኑ ያንን መሥራትን ያካተተ ነው። እነዚህ መንገዶች ትራፊኩ ከተማ ውስጥ ሳይገባ በዚያው በኩል ከደብረብርሃን የሚመጣን መኪና በተጠቀሱት መንገዶች በኩል አልፎ በሱሉልታ አድርጎ ወደ ባህርዳር አቅጣጫ መሄድ ያስችለዋል።

‹‹ከሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ የሚመጣውን ከሰሜን ምሥራቅ ጋር በቀላሉ መገናኘት የቻሉ መንገዶች ናቸው›› ያሉት አማካሪዋ፤ እነዚህም የመካከለኛ ጊዜ አማራጮች መሆናቸውን ይጠቁማሉ:: በአሁኑ ወቅት ዝርዝር ዲዛይን ላይ የሚገኝና ሁለተኛ ምዕራፍ ላይ መሆኑን ያመለክታሉ። በጥናቱ ሁለተኛ ምዕራፍ ደረጃ ላይ ያለው ʻኤ አንድʼ የተባለው ከአዲስ አበባ ቢሾፍቱ ትራንስፖርት መንገድ፣ ʻኤ ሁለት’ የተባለው ከጣፎ አደባባይ በለገዳዲ አድርጎ ኩራ ጅዳ ድረስ የሚሄደው መንገድ ዝርዝር ዲዛይን ጥናት ላይ የሚገኝ እንደሆነ ያስረዳሉ። ይህም 15 ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና ስፋቱ ደግሞ በ50 ሜትር እየተሠራ የሚገኝ እንደሆነም ይናገራሉ።

በተጨማሪም ʻኤ ሶስትʼ የመንገድ ፕሮጀክት ደግሞ ከሱሉልታ ፍተሻ ጣቢያ አንስቶ ወደ ሱሉልታ ከተማ የሚሄደው ሲሆን 20 ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመትና በ50 ሜትር ስፋት እየተሠራ የሚገኝ እንደሆነ ያመለክታሉ። ʻኤ አራትʼ ፕሮጀክት ደግሞ ከ18 ማዞሪያ አንስቶ በአሸዋ ሜዳ አድርጎ ኬላ ድረስ የሚሄድ ሲሆን 14 ነጥብ 73 ኪሎ ሜትር ርቀት ያለው መሆኑንና በ50 ሜትር ስፋት እየተሠራ የሚገኝ መንገድ መሆኑን ያስገነዝባሉ:: ከአዲስ አበባ ጅማ እና ዓለም ገና ቡታጀራ መንገድ ʻኤ አምስት አንድ’ እና ʻኤ አምስት ሁለት’ መንገዶች በጥናት ላይ የሚገኙ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

በተጨማሪም በከተማዋ ውስጥ የሚያልፈው ከእንጦጦ ማርያም ጉለሌ የእፅዋት ማዕከል የሚሄደው 4 ነጥብ 74 ኪሎ ሜትር እና 18 ነጥብ 5 ሜትር ስፋት ያለው መንገድ ነው። ከእንጦጦ ስፔስ ኦብዘርቫቶሪ እስከ ጫካ ፕሮጀክት የሚሄደውም 9ነጥብ1 ኪሎ ሜትር በ25 ሜትር ስፋት እየተሠራ የሚገኝ ነው። ከእንጦጦ ማርያም ፍተሻ ሳንሱሲ የሚሄደው መንገድም በጥናት ደረጃ ከጣፎ አደባባይ እስከ ማርያም ጋር የሚገናኘው መንገድ ነው። እንዲሁም ከፍተሻ ተነስቶ ሳንሱሲ ድረስ የሚሄድ መንገድ ጨምሮ በጥናት ላይ ያሉ መሆናቸውን ያብራራሉ። የመንገድ ግንባታ ሥራዎቹም በጥናቱ ምልከታ መሠረት እየተሠሩ መሆናቸውን ያስረዳሉ።

በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የመንገድ ሀብት ማኔጅመንት ምክትል ዋና አስተዳደር ኢንጂነር ዓለማየሁ አየለ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ መውጫዎች እየተከናወኑ የሚገኙና በቅርቡ ወደ ግንባታ ሥራቸው የሚገቡ መንገዶች ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅን የሚያስተነፍሱ መሆናቸውን ይናገራሉ። ከአዲስ አበባ ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መውጫ በሆኑት ዋና ዋና መንገዶች የሚገነቡ መሆናቸውን አመልክተው፤ ‹‹መንገዶቹም በመዲናዋ መግቢያ እና መውጫ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የመጣባቸው ናቸው። በዚህ ከቀጠለ ደግሞ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ መንገዶቹን ለመጠቀም ሙሉ በሙሉ ወደማይቻልበት ደረጃ የሚደርስ ነው›› ይላሉ።

በመሆኑም ከወዲሁ አስቀድሞ ለእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች መፍትሔ መፈለግ ተገቢ መሆኑን አስረድተው፤ በመዲናዋ መውጫ የሚገኙትን መንገዶች ማሻሻል እና የሚመጣውን የትራፊክ መጨናነቅ ጭምር ታሳቢ ያደረገ የመሸከም አቅም መጨመር እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ። ይህንን ማድረግ ካልተቻለም የሚመጣው የትራፊክ ችግር ከፍተኛ በመሆኑም በተለይ ከአዲስ አበባ ለገጣፎ፣ ከአዲስ አበባ በሱሉልታ በኩል ወደ ደጀን ጎሀፅዮን የሚሄደው መንገድ፣ ከ18 ማዞሪያ መናገሻ እስከ ሆለታ ድረስ የሚሄደው መንገድ ላይ በፍጥነት ማሻሻል ተገቢ በመሆኑ ሥራው እየተከናወነ ይገኛል።

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ መንገዶቹ ዲዛይናቸው ሲዘጋጅ ከጥራት አንፃር ታይተውና በግንባታ ወቅትም ክትትል የሚደረግባቸውና መንገዶቹ ለቀጣይ 20 ዓመታት አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው የተወሰኑ ናቸው:: የዛሬ 20 ዓመት የከተማዋ የትራፊክ መጨናነቅ ምን እንደሚመስል ዲዛይነሮቹ ከግምት አስገብተው የሚሠሩ ሲሆን ከ20 ዓመታት በኋላ ደግሞ ሁኔታዎች እየታዩ ማሻሻያዎች የሚደረጉባቸው ይሆናል:: በተጨማሪም መንገዶቹ ትክክለኛ የፕሮጀክት ማኔጅመንት አካሄድ ይዘው የሚሠሩ ሲሆን ከሚመለከተው ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ ሥራዎች ይሠራሉ።

ፕሮጀክቶቹን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ባለው ሂደት መብራት፣ ውሃ፣ ቴሌ ከመሳሰሉት ጋር በመቀናጀት ይሠራሉ፤ የዕለት ተዕለት ክትትል በማደረግ ፕሮጀክቶቹ በፍጥነት እንዲያልቁ የሚደረግ መሆኑን ይጠቁማሉ:: የመንገድ ግንባታዎችን ለማጠናቀቅ አጠቃላይ ሁለት ዓመት ያህል የሚፈጅ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግንባታ ሥራውን እያካሄደ ያለው ኮንትራክተሩ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መሆኑን፤ የዲዛይን አማካሪው ደግሞ ስታዲያ የኢንጂነሪንግ ሥራዎች አማካሪ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You