በሊቢያ አሸዋ ላይ…

እንደ መነሻ..

ሰንበት ነው:: ዕለተ እሁድ:: ብዙዎች የሚያርፉበት፣ በርካቶች ወደ ቤተ-ዕምነት የሚተሙበት ልዩ ቀን:: ዕለቱ ለብዙዎች መልከ ብዙ ሆኖ ይፈረጃል:: ዘመድ መጠየቂያ፣ ጉዳይ መከወኛ፣ ማረፊያና መዝናኛ ሆኖ:: ሰንበትን እንደ ልምዴ ለማሳለፍ ማለዳውን ከቤተክርስቲያን አጸድ ተገኝቻለሁ:: አይምሮዬ አሁንም ወደ አንድ ቦታ መለስ ቀለስ እያለ ነው::

ከቤት ወጥቼ መንገዴን እንደያዝኩ ያስተዋልኩት እውነት ውስጤን እየረበሸው ነው:: አዎ! በእግረኞች መስመር ላይ ዓይኖቼ አንዲት ሴትን በሚገባ አስተውለዋል:: ይህች እናት በሥፍራው መገኘቷ እንደ ብዙዎች ሰንበትን አክብሮ ቤተክርስቲያን ለመሳለም አይደለም:: የእሷ እውነት ከሌላ ጥግ ያደርሳል::

ወይዘሮዋ በሁለት እጆቿ ወጥራ የያዘችው ባለቀለም ፎቶግራፍ /ፖስተር/ በርቀት ቁልጭ ብሎ ይታያል:: በአጠገቧ የሚያልፉ በርካቶች ምስሉን ጠጋ ብለው ካዩ በኋላ የእጃቸውን ይጥሉላታል:: አንዳንዶቹ ደግሞ ድምጻቸውን አጉልተው ‹‹እግዜአብሔር ይማርልሽ ›› ይሏታል:: ስሄድ እንደዋዛ ያስተዋልኳት እናት በሃሳቤ ደጋግማ መመላለስ ይዛለች:: ይህ ስሜት በውስጤ ቦታ ቢይዝ ከአጸዱ ለመውጣት ወስኜ ተነሳሁ:: ከቤተክርስቲያኑ እምብዛም ያልራቀችው ሴት በቅርብ ርቀት ታየችኝ:: ውስጤ እፎይታ ሲያገኝ ተሰማኝ::

ጧፍና ቄጤማ የሚሸጡትን ወደ ኋላ ትቼ አጠገቧ ደረስኩና ሁኔታዋን አስተዋልኩ:: የተጎሳቆለው ፊቷ የዕንባ ጅረት ተመላልሶበታል:: የደረቀው አፏ እህል የቀመሰ አይመስልም:: እንደ ነገሩ ጣል ያደረገችው አዳፋ ነጠላ ቆሸሽ ካለ ልብሷ ተዳምሮ ቁስቁልናዋን አብሶታል:: ሁኔታዋ ከማሳዘን በላይ ሆነብኝ::

ፎቶግራፉ…

ያለአንዳች ድካም በእጆቿ ወጥራ ወደያዘችው ሰፊ ፖስተር አማተርኩ:: አሳዛኙ ፎቶግራፍ ከዓይኖቼ ቢገባ ይበልጥ ጠጋ ብዬ አስተዋልኩት:: በጸበል ቆይታ ያለ የሚመስል ወጣት ሁለት እጆቹን የኋሊት ታስሮ በደረቱ ተኝቷል:: በላዩ የተደረበለት አንዳች እራፊ ጨርቅ የለም:: ከፍና ዝቅ ብለው የተለጠፉት ምስሎች ተመሳሳይ ናቸው:: ሁሉም ስሜትን ይረብሻሉ:: በዕንባ ሳግ ይፈትናሉ::

ማለዳውን በአጠገቧ ሳልፍ የሰማሁት የመንገደኞች ቃል ትውስ አለኝ:: ‹‹እግዚአብሔር ይማርልሽ›› ሲሏት ነበር:: የእጄን ከጣልኩላት በኋላ እኔም ከልብ በሆነ ስሜት ‹‹እግዚአብሔር ይማርልሽ ›› ስል ተመኘሁ:: ይህን ብዬ ከማለፌ ግን አንድ ቃል ድንገት ወደኋላ መለሰኝ::

ወደሴትዬዋ ጠጋ ብዬ ያለችኝን በጥሞና ለመረዳት ሞከርኩ:: ምስጋናዋን ሳታቋርጥ በዕንባ እንደታጀበች ያስደነገጠኝን እውነታ በሲቃ አወጋችኝ:: ፎቶውን አይቼ የእግዜር ምህረትን የተመኘሁለት ወጣት የመጀመሪያ ልጇ ነው:: ምስሉ የሚያመለክተው ግን እኔ እንዳሰብኩት ጠበል ላይ ሆኖ አይደለም:: ይህ ወጣት የኋሊት ታስሮ የሚታየው በሊቢያ በረሀ አጋቾች እየተሰቃየ ነው::

እናት ይህን ታሪክ በመጠኑ ከነገረችኝ በኋላ ብዙ ማዳመጥ አልሆነልኝም:: ውስጤ ክፉኛ ተረበሸ፤ እንደምንም ዓይኔን መለስ አድርጌ ዳግም ፎቶው ላይ አነጣጠርኩ:: እውነታው እሷ እንዳለችኝ መሆኑን ለመረዳት አፍታ አልፈጀሁም:: ስሙን ከነአባቱ የነገረችኝ ወጣት ሊቢያ ነው በተባለ ምድረ ባዳ አሸዋ ላይ ተኝቶ እየተሰቃየ ነው:: ጠንካራው ጥቁር ገመድ እጅና እግሮቹን ክፉኛ ሰርስሯቸዋል::

ስቃዩን ለማወቅ፣ ስሜቱን ለመረዳት ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ በቂ ነው:: ይህ ሀቅ ደግሞ ዘጠኝ ወር ሙሉ አርግዛ በድካም ስቃይ ላሰደገች እናት ትርጉሙ ይለያል:: ውስጥ አንጀትን ዘልቆ የሚሰማው ስቃይ ከባለቤቱ አልፎ ለተመልካች ሁሉ ሕመሙን ያጋራል::

አሁንም ዓይኖቼ ከምስሉ አልተነሱም:: ወጣቱ የበረሀው እስረኛ በሀሩሩ ግለት የተቃጠለ ገላው ልብልብ ግንድ መስሏል:: ከንፈሮቹን ጨምሮ መላው አካሉ በጋለው አሸዋ ተለውሶ መከራውን እየመሰከረ ነው:: እንዳይንቀሳቀስ ሆኖ የተጠፈነገ አካሉ እንዲነካካ አልተፈቀደለትም:: ጀርባውን ወደብ አድርገው የተሳሰሩት እጅና እግሮቹ ለራሱ ባዕዳን ሆነዋል::

በእጅጉ ከረበሸኝ ጉዳይ ዓይኖቼን አንስቼ በሌላው ጎን ወደተለጠፈው አንድ ምስል አስተዋልኩ:: ወጣቱ ሊቢያ ከመሄዱ በፊት የተነሳው የቅርብ ጊዜ ፎቶ ነው:: አስቀድሜ ካየሁት ጋር ፈጽሞ አይመሳሰልም:: በጣም የሚያምርና በእጅጉ የሚያሳሳ ወጣት ከነወዘናው በዓይኖቼ አለፈ:: ጎስቋላዋ እናት ዕንባዋ ያለማቋረጥ ቀጥሏል:: በዘረጋችው ነጠላ ላይ የአቅማቸውን የሚጥሉላት አንዳንዶች ልክ እንደኔ ምስሉን አይተው ለልጇ ምህረትን ይመኛሉ::

በመጠኑ ያወጋችኝን ልብ ሰባሪ ታሪክ አንጠፍጥፌ መስማት ተስኖኛል:: ቦታውና ቀኑ ጠጋ ብሎ ለማውጋት አያመችም:: አጭር ቀጠሮ ለመያዝ ወሰንኩ:: እሷም በሃሳቤ ተስማምታ ቀጠሮዬን ተቀብላለች:: ከልብ ሰባሪው ታሪክ ጋር ወደቤቴ ስመለስ ሃሳቤ ሁሉ ከእናትና ልጅ ጋር ነበር::

ከቀናት በኋላ በሃሳቤ አብራኝ ከከረመችው እናት ጋር ዳግም ተገናኘን:: ዛሬም ከነጉስቁልናዋ ናት:: የሆነውን ሁሉ እስክትነግረኝ እየጠበኳት ነው:: ሰላም ስላት ጀምሮ መውረድ የጀመረው ዕንባዋ አልተገታም:: እንደምንም መለስ ብላ ተረጋጋች:: ዛሬም ከፍ ባለ ፖስተር የታተመው የልጇ አሳዛኝ ምስል ከእጇ ላይ ነው:: ማለዳውን አንስቶ ይዛው እንዳረፈደች ነገረችኝ:: ለአፍታ መንገደኞች ቀለል ሲሉ ወጋችንን ቀጠልን::

ከዓመታት በፊት…

ሀገሬ መኩሪያ /በፈቃዷ ስሟ የተቀየረ/ተወልዳ ያደገችው ምስራቅ ጎጃም ደብረማርቆስ ዙሪያ ነው:: ከዓመታት በፊት ቀዬ መንደሯን ትታ አዲስ አበባ መጣች:: ለዚህ ምክንያቷ ራሷን ለመለወጥ፣ ኑሮዋን ለማሻሻል ነበር:: ሀገሬ ጥቂት አይሉትን ጊዜ በሰው ቤት ሥራ ስታሳለፍ ከድካሟ ጀርባ የሚኖራትን ለውጥ እያሰበች ቆየች::

እሷ በላቧ ወዝ በጉልበቷ ድካም ያፈራችውን ጥሪት ማባከን አትሻም:: ነገ ሰው የመሆን ህልም አላትና ጥርሷን ነክሳ ለዓላማዋ ትኖራለች:: ከጊዚያት በኋላ ግን ይህን ትልሟን ከሚያቋርጥ አጋጣሚ ተገኘች:: ከአንድ ሰው ጋር ፍቅር መጀመሯ ሁሉን አስረስቶ ወደ ትዳር ዓለም አስገባት:: ሀገሬ እንዲህ መሆኑን አልጠላችውም:: የራሷ እመቤት፣ የባሏ ወይዘሮ መባሉን ወደዋለች::

ትዳር ከያዘች ወራት በኋላ የመጀመሪያ ልጇን ታቀፈች:: እጅግ የሚያምር የሚያሳሳ ህጻን የቤቱን ጎዶሎ በሙላት ቀየረው:: ሀገሬ የመጀመሪያ ልጇ በረከት ሁሉን አስረሳት:: ጠዋት ማታ ዓይን ዓይኑን እያየች ሰሰተችው:: አሁን እሱን በወጉ አሳድጋ ቁምነገር ማድረስን እያሰበች ነው:: ከቤት ኪራይ ያልዘለለው ኑሮዋ ቢፈትናትም ስለልጇ የማትሆነው የለም::

ጥቂት ዓመታት አለፉ:: የወይዘሮዋና የአባወራው ፍቅር እንደቀድሞው አልቀጠለም:: ትንሹ ልጅ ከፍ እንዳለ የተወለዱት ሁለት ልጆች የእናታቸው ኃላፊነት ብቻ ሆኑ:: አባወራው እየጠጣ መረበሹ፣ ማስቸገሩ የቤተሰቡን ሰላም ነሳ:: ሀገሬ ከባሏ ባትስማማ ትዳሯን ተናጋ:: የጥንዶቹ አለመስማማት መለያየት ፈጥሮ ፍቺ አስከተለ::

አባወራው ሶስት ልጆቹን ትቶ ከቤት ከወጣ ወዲህ ወይዘሮዋ ስለልጆቿ መኖር መታገል ያዘች:: ልብስ እያጠበች፣ በየቤቱ እየሠራች፣ የቤት ኪራይዋን፣ የወር ወጪዋን ልትሸፈን ታገለች:: ኑሮ ከነችግሩ እያንገዳገደ ዓመታትን አሻገራት:: ክፉ ደግ ባየችባቸው ልጆቿ ነገን አሻግራ እየቃኘች ተስፋዋን ሰነቀች::

የበኩር ልጅ …

ሁለቱ ልጆች በዕድሜ ቢያንሱም ትልቁ ልጇ ትምህርቱን አጠናቆ እንደ አቅሙ ይረዳት ይዟል:: ሀገሬ በኑሮና ችግር የጎበጠ ማንነቷ መቃናት ጀምሯል:: ትልቁ ልጇ ከእናቱ አልፎ ለታናናሾቹ ያስባል:: ተምሮ በተመረቀበት የቴክኒክ ሙያ ከሚያገኘው ገቢ የጎደለውን ሞልቶ ለራሱ መትረፍን አውቋል::

እናት ልጇ ደግና የዋህ መሆኑን ታውቃለች:: ሁሌም ከልፋቱ የሚያገኘውን ጥሪት ባያጠፋ ባያባክን ደስታዋ ነው:: እሱ ደግሞ የእናቱን ውለታ አይረሳም:: የተሻለ አግኝቶ፣ ከኪራይ ቤት ቢያወጣት፣ ውለታዋን በእጥፍ ቢከፍላት ይወዳል:: ይህ ሃሳቡ ሁሌም ከቅርብ ውሎ አያድርም:: አንዳንዴ ባሕር ቆርጦ፣ አየር ሰንጥቆ ይጓዛል::

ወጣቱ የእሱ እኩዮች ዛሬ የት እንዳሉ አሳምሮ ያውቃል:: ይህን ባሰበ ቁጥር የሚነሳሳው ልቡ በሃሳብ ከብዙ አድርሶ መልሶታል:: የባሕር ማዶ ኑሮ ፣ የፈረንጅ ሀገር ሕይወት ብዙዎችን እንደለወጠ አይጠፋውም:: ለእሱ ደግሞ ይህ አጋጣሚ ትርጉሙ ይለያል:: እሱ የእነሱን ዕድል ቢያገኝ ጎስቋላ እናቱን ከችግር ማለቀቅ፣ ዓላማው ነው:: ታናናሾቹን አስተምሮ፣ አልብሶና አሳምሮ ታሪካቸውን መቀየር ይመኛል:: እንዲህ ይሆን ዘንድ የእሱ ዋጋ መክፈል ግድ መሆኑን ካመነበት ቆይቷል::

በነሐሴ …

ቀኑን ሙሉ ሲዘንብ የዋለው ዝናብ ማምሻውንም ብሶበታል:: በየቤቱ በሥራ ስትባክን የዋለችው እናት ከነድካሟ ከቤቷ ደርሳለች:: ሁሌም እንደምታደርገው የቤት ጎዶሎዋን ለመሙላት ወዲያ ወዲህ እያለች ነው:: ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ ትልቁ ልጅ ከሚያገኘው ገንዘብ ጎኗን እየደጎማት ነው:: በተለይ ዓውደ ዓመት ሲመጣ የልጅነት ወጉን አይነሳትም:: በግ ዶሮውን፣ ጤፍ ቅቤውን ይላታል:: እንዲህ በሆነ ቁጥር ሁሌም የእናትነቷን ምርቃትና ምስጋና አትነሳውም::

ሀገሬ የልጇን ደግነትና አሳቢነት ባየች ቁጥር መጨረሻውን እያሰበች በደስታ ትፈካለች:: አንድ ቀን የሚደርስበትን ስታስብ ደግሞ ውስጧን ሰላም ይሰማዋል:: ይህኔ ደጋግማ ፈጣሪዋን ‹‹ተመስገን ›› ትላለች::

ዕለቱን በጊዜ ያልገባው ልጅ አሁንም ድምጹ የለም:: የእስከ ዛሬ ልምዱን የምታውቀው እናት ክፉኛ ተጨንቃለች:: እስካሁን አለመግባቱ እያሳሰባት ስልኩን ደጋግማ መደወል ያዘች:: ድምጽ አልባው ጥሪ አላገዛትም:: ጥቂት አሰብ አድርጋ ስለ ውሎው ወንድሞቹን ጠየቀች:: ጸጉራቸውን እንዲቆረጡ ብር ሰጥቶ ‹‹መጣሁ›› ብሎ መውጣቱን ነገሯት::

ምሽቱን የጀመረው ዝናብ ተግ ቢልም ተወዳጁ ልጅ ብቅ አላለም:: ሰዓቱ እየነጎደ ሌሊቱ እየገፋ ነው:: ጥቂት ቆይቶ የእጅ ስልኳ አቃጨለ:: ልጇ ነበር:: ሩቅ ቦታ እንዳለና መምጣት እንደማይችል ነግሯት ስልኩን ፈጥኖ ዘጋው:: ለወትሮው ይህ ዓይነቱ ልማድ የእሱ አይደለም:: ለምን እንዳደረጋው አልገባትም ተስፋ ሳትቆርጥ ጠበቀችው::

ደጅ ደጁን ስታይ፣ ኮቴ ስታደምጥ ያነጋችው እናት ወፎች ሲንጫጩ ከማለዳው ጋር ተፋጠጠች:: ደጉ ልጇ የሆነበትን ባታውቅም ረፋዱን ተስፋ አልቆረጠችም:: ለልጇ ማለፊያ ቁርስ አዘጋጅታ በር በሩን አየች:: ተናፋቂ ልጇ ድምፁ የለም:: ስልኳን አንስታ ደጋግማ ደወለች:: መልስ አልሰጣትም:: እንደተሳቀቀች፣ እንደተጨነቀች አንገቷን ደፍታ ዋለች::

‹‹ልጄን ያያችሁ››

ዋል አደር ሲል የሰፈር ጓደኞቹን አፈላልጋ ስለልጇ ጠየቀች:: ከእነሱ ሳይሆን ሰሞኑን ከሌሎች ጋር መታየቱን ነገሯት:: ስለእነሱ ሰምታ አታውቅም:: አድራሻ ስማቸውን አላገኘችም:: በእንባ ስትታጠብ፣ ደረቷን ስትደቃ ከረመች::

ሀገሬ ልጇ ከጠፋ ጀምሮ የአይምሮዋ ምስል ብዙ ነው:: ተገድሎ፣ ሬሳው ሲጣል ይታያታል:: ተደብድቦ እጅ እግሩ ተጎድቶ ሲመጣ ውል ይላታል:: ሁሌም በየቤተክርስቲያኑ ደርሳ ስታለቅስ፣ ስትማጸን ደግሞ ውስጧ ጸንቶ ይጠነክራል::

እነሆ! የነሐሴ አልፎ የመስከረም ወር ተተካ:: አዲሱ ዓመት ገብቶ አውደ ዓመቱ ሲነጋ ሀገሬ ደጉ ልጇን አሰበችው:: የዓመት በዓሉ ወግ፣ የምስጋና ምርቃቱ በረከት በዓይኖቿ ተመላለሱ:: እንደ ልማዷ እያነባች ‹‹ልጄ የት ነህ?›› ስትል ጮኸች፣ ተንከባለለች:: ዓውደ ዓመቱ መልኩን ሳይመስል ዕለቱ በድብርትና ሀዘን ተጠናቀቀ:: አዲሱ ዓመት አዲስ ነገር ያላሰማት እናት መስከረምን ጨርሳ የጥቅምት ወርን ተቀበለች:: ከወሩ አንድ ሳምንት ገፋ እንዳለ ለጆሮዋ የደረሰው የስልክ ጥሪ ግን በድንጋጤ የነበረችበትን አስረሳት:: የልጇ የደከመ ድምጽና ብርክ የሚያሲዘው ቁጣ አዘል ድምጽ የልጇን በሊቢያ በረሀ መታገት አረዷት::

ሊቢያ የት ነው? መታገትስ ምንድነው? ይህ ዓይነቱ ቃል ለምስኪኗ እናት ፍጹም ባዕድና አዲስ ነበር:: ጥቂት ቆይቶ በረሀብና ችግር የጠወለገውን፣ በድብደባና እንግልት የቆሰለውን ልጇን በምስል ቀርጸው አሳይዋት:: ስልኩን ከፍተው የሰለለ ድምጹን፣ የተዘጋ አንደበቱን አስደመጧት::

አጋች ተብዬዎቹ በዚህ ብቻ አልበቃቸውም:: የተጠየቀው አንድ ሚሊዮን ሶስት መቶ ሺህ ብር በተባለው ቀን ካልደረሰ ልጇን ሰይፈው እንደሚገድሉት አሰጠነቀቋት:: ለዚህ ማሳያም በረሀው ላይ እርቃኑን የኋሊት የፊጥኝ አስረው የሚያሳቃዩትን ፎቶ እያሳዩ አስፈራሯት::

ሀገሬ ይህን እውነት ካየች፣ ከሰማች ጀምሮ ቆጥራ የማትጨርሰውን ገንዘብ አንድ ብላ ልትጀምር በየሰው እግር ስር ወደቀች፣ በየቤተክርስቲያኑ ‹‹እርዱኝ›› ስትል ተማጸነች:: የገንዘቡን ብዛት የተረዳችው ብድር የጠየቀቻቸው ሰዎች መጠኑን በነገሯት ጊዜ ነበር:: ክፉኛ ብትደነግጥም ተስፋ አልቆረጠችም:: ስለልጇ እስትንፋስ በየቦታው ዞረች፣ ተንከራተተች::

ከጠዋት እስከ ማታ በዕንባ ታጥባ የምትለምነው ብር እስካሁን ቋት አልሞላም:: ብዙዎች ልጇ ጸበል ያለ ሲመስላቸው ‹‹ይማርልሽ›› ይሏታል:: በርካቶች ደግሞ ከተለመደው ልመና ፈርጀው በዝምታ ያልፏታል:: የገባቸው ጥቂቶች ከልብ አዝነው የእጃቸውን ይጥሉላታል::

እናት እስካሁን ለሶስት ተከታታይ ወራት ልጄን ‹‹አትርፉልኝ›› ስትል ተማጽናለች:: በእጇ የገባው ገንዘብ ግን ከሃምሳ ሁለት ሺህ ብር አላለፈም:: አንዳንዴ የሊቢያዎቹ አጋችና ደላሎች በስልክ ብቅ ብለው የልጇን ድምጽ ያሰሟታል:: ሁሉም አማርኛን ከአረብኛ አዛምደው ያወራሉ::

በሞት ሕይወት መሀል …

ድንገት ልጇን ባገኘችው ጊዜ ገንዘቡ ስንት ደረሰ ሲል ይጠይቃታል:: እውነቱን ሳትደብቅ ትነግረዋለች:: በቀና ልቦናው ‹‹አይዞሽ እናቴ በርቺልኝ›› ይላታል:: እንደ ቀድሞው ትንፋሹ ይሞቃታል፣ ጠረኑ ይናፍቃታል:: በዕንባ ሲቃ እያየችው ‹‹ ልጄ አለሁልህ›› ትለዋለች እናትና ልጅ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አያውቁም:: እሷ ከወዲህ፣ እሱ ከበረሀው ማዶ ባልሞተ መንፈስ ተስፋን ይናፍቃሉ:: በሞትና ሕይወት መሀል::

ከአዘጋጁ፤ ባለጉዳይዋን ለማነጋገር ወይም ለመርዳት ለምትፈልጉ 0965426293 ማግኘት ትችላላችሁ። ወይም መልዕክታችሁን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች በኩል ልታደርሱ ትችላላችሁ።

መልካምሥራ አፈወርቅ

አዲስ ዘመን  የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You