አዲሱ የግብርና ፖሊሲ እንደ ፍኖተ ካርታ

የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ለሀገራዊ ኢኮኖሚው የአንበሳውን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል። በአረንጓዴ ዐሻራና በሌማት ትሩፋት የተጀመሩ ሥራዎች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በቂ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የእንስሳት ተዋፅኦ ምርት ለገበያ እንዲቀርብ ማስቻላቸውን፤ አዲሱ የግብርና ፖሊሲም በዘርፉ እየተመዘገበ የሚገኘውን ስኬት ይበልጥ ያሰፋዋል ተብሎ ይታመናል።

በተለይም የግብርና ባንክ በማቋቋም ጭምር አርሶና አርብቶ አደሩ መሬትና የተፈጥሮ ሀብቱን በማስያዝ የገንዘብ ብድር አገልግሎት የሚያገኝበት ዕድል እንዲፈጠር የሚያደርግ፤ የገጠር ግብርናን መዋቅራዊ ሽግግር በማሳለጥ የኢትዮጵያን የዕድገት ርዕይ ለማሳካት ቁልፍ መሳሪያ መሆኑን፤ ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ አዋጅና ሌሎች መመሪያዎች በማዘጋጀት የገጠር ግብርና ሽግግርን ለማሳለጥ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝም እየተገለጸ ይገኛል።

በአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሠረት በ2030 ዓ.ም የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር በማረጋገጥ በገጠር መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣትና ለሀገር ብልፅግና ጉልህ ሚና የሚጫወት ሆኖ የማየት ርዕይ ተሰንቋል። ነባሩ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከ20 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየ ሲሆን ሚያዝያ 17/2016 ዓ.ም የተሻሻለው ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወሳል።

አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መዘጋጀቱ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የግብርና ምርትና ምርታማነት እድገትን በማረጋገጥ፤ ለሀገራዊ ሥርዓተ ምግብ መሻሻል እንዲሁም የምግብ ዋስትናና የምግብ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ዘላቂ አጠቃቀም እንደሚያሳድግም፤ ፖሊሲው ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ፤ አርሶ አደሩ መሬቱን ተጠቅሞ የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኝና የገጠሩን ሕዝብ የአኗኗር ዘይቤ ለማሻሻል መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ በስፋት እየተገለጸ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ዕምቅ ሰብዓዊና ተፈጥሮዓዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም፣ ያለፉት ሥርዓቶች ይከተሏቸው የነበሩ የተዛባ የልማት ፖሊሲዎችና ሌሎች መዋቅራዊ ችግሮች ምክንያት የግብርናው ዘርፍ ሌሎቹን ዘርፎች ይዞ በመነሳት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት ማራመድና አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ብሎም አጠቃላይ ሕዝቡን ከድኅነት አላቆ ተጠቃሚ ማድረግ የሚችልበት ሁኔታ አልተፈጠረም ነበር:: ይህም ሆኖ የግብርናው ዘርፍ በሁሉም ሥርዓቶች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንትና የ85 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የኑሮ መተዳደሪያ ሆኖ የመሪነቱን ሚና ሲጫወት ቆይቷል::

በ1983 ዓ.ም. የደርግ አገዛዝ በነፍጥ ከተገረሰሰ በኋላ ሀገሪቱ ከዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንድትሸጋገር ተደርጓል:: በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ማሕቀፍ ውስጥም ሕዝቡን ከድኅነትና ከኋላቀርነት እንዲሁም ሀገሪቱን ወደ ብልፅግና ጐዳና የሚያሸጋግሩ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተነድፈዋል:: ከተነደፉት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ውስጥም በ1994 ዓ.ም. የተዘጋጀው ግብርናንና ገጠሩን ማዕከል ያደረገ የልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ወይም ግብርና መር ኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ አንዱና ዋነኛው ነው:: ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያረጋግጥ፣ በየደረጃው ያለውን ሕዝብ ከልማቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ሀገራችንን ከተመጽዋችነት የሚያላቅቅና የዳበረ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲገነባ የሚያስችል ነው:: የዚህ ፖሊሲና ስትራቴጂ ስኬታማነት የሚወሰነውም ያለንን መሬትና ጉልበት በስፋትና በላቀ ደረጃ እንዲሁም ያለንን አነስተኛ ካፒታል በቁጠባ መጠቀም ስንችል እንደሆነ ፖሊሲው ላይ በግልጽ ተቀምጧል:: ፖሊሲው ከፀደቀ በኋላም ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጎና የጋራ መግባባት ተፈጥሮ ወደ ሥራ ተገብቷል:: ፖሊሲውንም በመንግሥትና በሕዝቡ የጋራ ጥረት ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ እጅግ በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል::

ስለሆነም ባለፉት 23 ዓመታት በግብርናው ዘርፍ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል:: ግብርና ለሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ምንጭና የሀገሪቱን ዜጎች ከድኅነትና ከኋላቀርነት በማላቀቅ ወደ ተሻለ የኑሮና የብልፅናግ ጎዳና እንዲያመሩ የሚያደርግ ዓብይ ዘርፍ ነው:: ይህ ዘርፍ የተጣለበትን ሀገራዊ አደራ ተረክቦ መተግበር ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት ዕምቅ አቅሞቻችንን በስፋትና በላቀ ደረጃ ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል:: በየትኛውም የግብርና ልማት ዘርፍ የምናከናውናቸው ተግባራት ዋነኛ ግብ የሰብልን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ዘላቂነትና ቀጣይነት ያለው የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ነው:: ከዚህም አልፎ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪና ለውጭ ገበያ ጥራት ያለው ምርት በሚፈለገው መጠንና ዓይነት ማምረት የሚቻለው ለዚህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ሲቻል እንደሆነ እውን ነው::

በዋና ዋና ሰብሎች (ብርዕ አገዳና ጥራጥሬ ሰብሎች) በ1983 ዓ.ም. ተገኝቶ የነበረው ምርት መጠን 52 ሚሊዮን ኩንታል የነበረ ሲሆን፣ ይህ የምርት መጠን የግብርና ገጠር ልማት ፖሊሲው ተነድፎ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት በ1992 ዓ.ም. 88.9 ሚሊዮን ኩንታል ደርሶ ነበር::

ፖሊሲው ተነድፎ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ በኋላ በ2004 ዓ.ም. የምርት መጠኑ 231 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል፡፡ የምግብ ሰብሎችን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ሀገራችንን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ እየተደረገ ባለው የግብርና ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ተግባር ሲሆን፣በመጀመሪያዎቹ አራት የGTP ዓመታት ትኩረት ተሰጥቶ ከተከናወኑ ቁልፍ ተግባራት መካከል አንዱና ዋንኛው ነው፡፡

በሰብል ልማት በተለይም የመኸር ሥራችን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻው ዓመት ሲሆን፣ በዚህም መሠረት የ2006 ዓ.ም. እና የ2007 ዓ.ም. መኸር የማዕከላዊ ስታትስቲክሰ ኤጀንሲ የቅድመ ትንበያ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዋና ዋና ሰብሎች በምርታማነትና ምርት ዕድገት የዝቅተኛውን የዕድገት አማራጭ ግብ ለማሳካት ተችሏል፡፡ ይህም የአነስተኛ አርሶ አደሩ የሰብል ልማት 26.7 ሜትሪክ ቶን ለማድረስ ታቅዶ የበልግ ምርትን ሳይጨምር የ2007 የመኸር የቅድመ ምርት ትንበያ መረጃ መሠረት 26.8 ሜትሪክ ቶን ምርት እንደሚገኝ ያመላክታል፡፡ ይህ የምርት ጭማሪ ተጨማሪ መሬት በማልማት የታቀደው 12.1 ሚሊዮን ሔክታር ሲሆን፣ የቅድመ ምርት ትንበያ መረጃ 12.5 ሚሊዮን ሔክታር እንደደረሰ ያሳያል፡፡

በምርታማነት ረገድ 22 ኩንታል በሔክታር ለማድረስ ታቅዶ 21.4 ኩንታል በሔክታር እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡ በዚህም አጠቃላይ የሰብል ምርት ዕቅዱን ያሳካን ሲሆን፣ በምርታማነት ረገድ 97.3 በመቶ በመሬት ደግሞ የዕቅዱን 103 በመቶ ማከናወን እንደተቻለ ያሳያል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የተጠናከረ ቅድመ ዝግጅት በማድረግና የነበሩንን የክህሎት ክፍተቶች በመገንዘብ በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በተሻሻሉ የሰብል ፓኬጆች ላይ በመስጠትና የተግባራትን አፈጻጸም በተደራጀ መልክ በኮማንድ ፖስትና በክላስተር ደረጃ በመከታተል ጠንካራ ግብረ መልስ በመስጠቱ ነው፡፡

በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራዎች ረገድም ስንመለከተው የተፋሰስና የመስኖ ልማት ሥራዎች በተደራጀ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ተከናውኗል፡፡ የተለያዩ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ የተካሄደባቸው የማኅበረሰብ ተፋሰሶች ሽፋን በ2002 ዓ.ም. ከነበረበት ከ3.77 ሚሊዮን ሔክታር ወደ 7.8 ሚሊዮን ሔክታር ማድረስ ሲሆን፣በGTPው አራት ዓመታት 16.285 ሚሊዮን ሔክታር ማድረስ ተችሏል፡፡ ይህም በዕቅዱ ዘመን ከሚደረስበት በ7.8 ሚሊዮን ሔክታር ወይም በ140 ከመቶ በብልጫ ከዕቅድ ዘመኑ ከአንድ ዓመት ቀድሞ መፈጸም ተችሏል፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከተው ሰፊው የኅብረተሰብ ተሳትፎ ቢሆንም፣ በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ ለሥራው ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራቱ የተገኘ ውጤት ነው፡፡

በተመሳሳይ የአነስተኛ ዘመናዊ መስኖ ግንባታ የተካሄደበት መሬት ስፋት በ2002 ዓ.ም. ከነበረበት 853.1 ሺህ ሔክታር በ2007 በጀት ዓመት 1.85 ሚሊዮን ሔክታር ማድረስ ሲሆን፣ የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ወደ ሥራ በገባባቸው ተመሳሳይ አራት ዓመታት አፈጻጸም በአንድ ዙር ብቻ የለማው መሬት 2.08 ሚሊዮን ሔክታር ደርሷል፤ ይህ አፈጻጸም በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ከሚደረስበት ግብ ቀድሞ መድረስ መቻሉን ያሳያል፡፡ ይህ ከላይ የተገለጸው ውጤት የሚያሳየን ግብርና አንድን ሀገር የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ለተለያዩ ምርቶች ጥሬ ዕቃ ለማቅረብ እንዲሁም የግብርና ምርት ውጤቶችን ለፋብሪካዎች በማቅረብ ለሀገር ፍጆታም ሆነ ለውጭ ሀገር የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት የሀገርን ኢኮኖሚ በፍጥነት ማሳደግ ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ሰፊ ቆዳ ስፋት ያለውና የተለያየ የአየር ንብረትን የታደለች ሀገር ናት፡፡ ይህ የአየር ንብረት የተለያዩ ዓይነት ሰብሎችን ቅመማ ቅመምንና ፍራፍሬዎችን ማምረት እንድትችል አድርጓታል፡፡ የግብርና መር ፖሊሲ ደግሞ ይህን የታደለችውን ተፈጥሯዊ ሀብት በአግባቡ በመጠቀሟ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን እንድታስመዘግብ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ መንግሥት የግብርና መር ፖሊሲን በሀገሪቱ ተግባራዊ መደረጉ ስትራቴጂያዊ እይታን ያረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህም ምስክር የሚሆነን ይላል የግብርና ሚኒስቴር በቅርቡ ሀገራችን ድህነትን ከመቀነስ ረገድ ከጥቂት የዓለማችን ሀገሮች አንዷ ሆና መሸለሟ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) በቅርቡ ባደረገው ግመገማም ሀገራችን ኢትዮጵያ ፍጹም ስኬታማ ሆነው ከተመረጡት 25 ሀገሮች መካከል አንዷ መሆኗን ተከትሎ በ150ኛው የፋኦ ካውንስል መደበኛ ስብሰባ ላይ የተለየ ፕሮግራም በማዘጋጀት ሮም በሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤቱ ዕውቅና በመስጠት ሽልማት ያበረከተ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ተጨማሪም በሀገራችን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማረጋገጥና በየደረጃው ያለውን ሕዝባችን ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የተነደፈው የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂ ትክክለኛ መሆኑን ውጤታማ ከሆኑ የልማት ጀግና አርሶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ከለውጡ ወዲህ ደግሞ በበጋ መስኖ፣ በኩታ ገጠም ግብርና፣ በሜካናይዜሽንና ኤክስቴንሽን በተሠሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል። ሰላሙ ቢረጋገጥ ደግሞ ምርታማነትን ከዚህም በላይ በእጥፍ ድርብ ማሳደግ ይቻላል።

በ2016/17 መኸር 20 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኖ ከዚህም እስካሁን 505 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል። በመኸሩ ከ608 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ የእስካሁኑ ውጤትም ከዕቅድ በላይ ምርት እንደሚገኝ አመላካች ነው። በምርት ዘመኑ በመኸር፣ በመስኖና በበልግ ከስንዴ ልማት 340 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዷል። በ2017 የበጋ መስኖ ስንዴ 4 ነጥብ 27 ሚሊየን ሄክታር መሬት በማረስ 173 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው እስካሁን 3 ነጥብ 41 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል።

በዚህም ከመኸሩ እስካሁን 101 ሚሊየን ኩንታል የስንዴ ምርት መገኘቱን ጠቅሰው በሩዝ ምርትም 1 ነጥብ 65 ሄክታር መሬት ታርሶ 48 ሚሊየን ኩንታል ምርት ተገኝቷል። በአትክትልና ፍራፍሬ ልማትም ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ገቢ እየተገኘ መሆኑን የኢዜአ ዘገባ ያስታውሳል፡፡

በነገራችን ላይ የአዲሱ የግብርና እና ገጠር ልማት ፖሊሲ ርዕይ በ2030 ዓ.ም ግብርናን በማሻገር በገጠር መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ለሀገር ብልፅግና ጉልህ ሚና ተጫውቶ ማየት ነው። የአዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ መሠረታዊ ለውጥ የሚባሉት የተሻሻለ የግብዓት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ የገጠር የሰው ኃይል ወደ አገልግሎት እና ኢንዱስትሪ ማሸጋገር፤ የእርሻ መሬት ጥምርን ማጠናከር፣ የተሻሻለ የመሬት ባለቤትነት እና የመብቶች ሥርዓት መዘርጋት፤ የሴክተሩን የካፒታል ፍሰት ለመጨመር በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ ሽርክናን ማስፋፋት እና ማጠናከር፤ ከፍተኛ ምርታማነት ያለው የቴክኖሎጂ ማላመድን ለማሳደግ ከግሉ ሴክተር ጋር መሥራት፤ ሥነ-ምህዳር እና የምርት ሥርዓቶች ማጣጣም እና ቁልፍ የእሴት ሰንሰለቶችን በዲጂታል የገበያ ማስተዋወቅ ናቸው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ተስፋ የሚያሰንቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በዚያ ሰሞን በፓርላማው ተገኝተው እንዲህ ይገልጹታል።

በበጋ መስኖ እንኳ ከስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ሄክታር በትንሹ ሶስት መቶ ሚሊየን ኩንታል ስንዴ በዚህ ዓመት ይመረታል። በዚህ ሳይወሰን ሰሊጥ ለውዝ አኩሪ አተር ቦሎቄ ቀድሞ ከነበረን በእጅጉ አድጓል። ሰሊጥ ድሮ ከምናመርተው ከእጥፍ በላይ እየተመረተ ነው። በሁመራ አካባቢ የሚታወቀው ሰሊጥ በወለጋ አካባቢ በስፋት ማምረት ተችሏል። ቦሎቄም በተለይ ለውዝ በሀረርጌ አካባቢ በጣም በስፋት የተመረተ ሲሆን ለውዝ ብቻ ከአምስት ሺህ ሄክታር በላይ ማምረት ተችሏል። እነዚህ በግብርና ዘርፍ የመጡ ውጤቶች ያገኘናቸውን ድሎች ጠብቀን ስንሰራ እና የገጠሙንን ድካሞች አርመን፤ አርቀን እያስፋፋን መሄድ ብንችል አሁንም ሰፊ መሬት በጣም ሰፊ ውሃና የሰው አቅም ስላለን የማደግ እድሉ በጣም ሰፊ ነው።

በዚህ ረገድ በተለየ መልኩ ሥራ የሚፈልገው ማዳበሪያን በተመለከተ ነው። እስካሁን በጅምላ አንድ አይነት ማዳበሪያ እንገዛና ለሁሉም መሬት የምንጠቀመው የተቀራረበ ማዳበሪያ ነበር። በዚህ ዓመት እንደ መሬቱ ጸባይ ማዳበሪያ ለማቅረብ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ሥራውን ስንጀመር የምርጥ ዘር አቅማችን በጣም ውስን ነበር። ምርጥ ዘር አልነበረንም በስንዴ እና በበቆሎ መቶ በመቶ ባልላችሁም በምርጥ ዘር ከፍተኛ እድገት እየመጣ ነው። ተጨማሪ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም።

መስኖና በበጋ የማምረት አቅማችንም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ማሸነሪና ፓምፕ መጠቀመም ጨምሯል። ማሽነሪም ፤ ምርጥ ዘርም፤ ማዳበሪያም ተጨማሪ ሥራ ይፈልጋሉ። እነዚህን በመሥራት ሁለት ቁልፍ ተግባራት ከፊታችን እንደ ፈተና ይጠብቁናል። አንደኛ ጥራት፤ ሁለተኛ አምራችነትን ማሳደግ ይገባል። ቡና ጥራት ላይና ምርታማነት ላይ ሥራ ይፈልጋል። ስንዴም ጥራትና ምርታማነት ላይ ሥራ ይፈልጋል። ይህም ማለት በአንድ ሄክታር አርባ ኩንታል የምናገኝ ከሆነ አርባ አምስት ማድረስ ይቻላል ማለት ነው። ማለትም መሬት ሳይጨመር ባለበት ላይ ምርትን ለማሳደግ ተጨማሪ ሥራ ይጠበቃል። በድምሩ ግብርና ስድስት ነጥብ አንድ በመቶ እድገት በማረጋገጥ ስምንት ነጥብ አራት በመቶ ለማደግ ያለንን ጥረት ለማሳካት አጋዥ ሆኖ የሚቆም ይሆናል። ይህ ሴክተር እንደተለመደው ትልቅ እምርታ የመጣበትና ወደፊትም ተስፋ የሚጣልበት ነው።

ሻሎም ! አሜን ።

በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You