
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የተመድ የሥነ ሕዝብ ፈንድ (ዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤ) በጋራ በመሆን ‹‹ወጣት የሰላም ባለቤት›› በሚል መሪ ቃል ሀገር አቀፍ የወጣቶች ሰላምና ደህንነት ጉባኤ በያዝነው ሳምንት አካሂዷል። በኮንፍረንሱ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች የዩ ኤን ኤፍ ፒ ኤ ተወካይ የተገኙ ሲሆን ከተለያዩ ክልሎች የተወከሉና ከሲቪክ ማህበራት የተወጣጡ ወጣቶች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል። በእለቱም ወጣቶቸ ሰላምን በማስፈን ውስጥ ያላቸውን ሚና በተመለከተ የተለያዩ መልዕክቶች የተላለፉ ሲሆን የፓናል ውይይትም ተካሂዷል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አሕመድ በሰላም ዙሪያ ወጣቶች ያላቸውን ሚና፣ ለሀገር የሚበረክቱትን አስተዋጽኦ እና ያላቸው ተሳትፎ ምን መምሰል አለበት በሚል እና ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ ስለሚገኛቸው ሥራዎች በመድረኩ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል። በዛሬው የወጣቶች ገጻችን በመድረኩ ላይ የተነሱ ሃሳቦችንና ተሳታፊ ከነበሩ ሁለት ወጣቶች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አዘጋጅተነዋል።
የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወይዘሮ ሙና አሕመድ በንግግራቸው የወጣቶች የሰላምና ደህንነት አጀንዳ አድርጎ ለመመካከር፣ ሰላም የሰፈነባት እና የበለፀገች ኢትዮጵያን በወጣቶች ንቁ ተሳትፎ እውን ለማድረግ መሰባሰብ በራሱ ለዘላቂ ሰላም ያለንን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የጉባኤው መሪ ሃሳብ “ወጣት የሰላም ባለቤት” ስንል ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ ሁሉም የማህበረሰብ አካላት ድርሻ ያላቸው ቢሆንም የሀገር ባለቤት የሆኑት ወጣቶች ዋነኛ የሰላም ባለቤት ራሳቸው መሆናቸውን በመገንዘብ ግጭቶችን በመከላከል፣ በመፍታት እና በዕርቀ ሰላም ሂደት ውስጥ የሚጫወቱት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በማመንም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።
ጉባኤው ወጣቶች በሀገር ግንባታ ውስጥ የሚጫወቱትን ወሳኝ ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ፣ ለኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም እና ደህንነት ብሔራዊ የድርጊት መርሐ-ግብር ዝግጅት መሠረት የሚጥል መሆኑንም ጠቅሰዋል። ይህም ወጣቶች በሰላም ግንባታ፣ በግጭት መከላከል እና በማህበራዊ መስተጋብር ላይ ያላቸውን ወሳኝ ሚና ለማጠናከር ያለንን ሀገራዊ ቁርጠኝነት የሚያረጋገጥ ነው።
በመሆኑም ወጣቶችን በማብቃት፣ ድምፃቸው እንዲሰማ በማድረግ እና በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ወጣቶች ለሰላም የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲደግፉና ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ተገቢ ነው።
ለዚህም መንግሥት ፖሊሲ፣ የሕግ እና የአሠራር ሥርዓቶችን በመቅረጽ እንዲተገበሩ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ሚኒስትሯ የወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማጎልበት የሚያስችል እንዲሁም አዎንታዊ የወጣቶች ልማትን መሠረት ያደረገ ብሔራዊ የወጣቶች ፖሊሲ የማሻሻያ ሥራ፣ ወጣቶችን በሥነ-ምግባር በማነጽ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ብሔራዊ የወጣቶች የዜግነት አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ እንዲሁም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል ያደረገ ዜጋ መፍጠርን ርዕዩ ያደረገ ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ረቂቅ ፖሊሲ አዘጋጅቷል። እነዚህም የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የመንግሥትን ቁርጥ ኝነት ማሳያ ናቸው።
በመድረኩ ላይ በየዓመቱ በኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ወጣቶች ሰላምን ለማረጋገጥ በሚከናወን ተግባር፤ በሰላም ግንባታና ግጭትን በመከላከል፣ በአካባቢ ደህንነት፣ በሰላም ጥበቃ እንዲሁም የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም ተግባር እየተሳተፉ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጸዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወጣቶችን ማብቃት ላይ ያተኮሩ በርካታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ሚኒስትሯ የገለጹ ሲሆን በተለይም የግጭት መንስኤ የሆኑት የተሳትፎ ዕድሎች፣ ኢ-ፍትሃዊነት፣ ሥራ አጥነት፣ የስብዕና ግድፈት፣ ማህበራዊ መገለል እና የመሳሰሉ ችግሮችን ካልተፈቱ ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ እንደማይችል በመገንዘብ በሥራ ፈጠራ፣ በስብዕና ግንባታ፣ በማህበራዊ አገልግሎቶች፣ የወጣት አደረጃጀቶችን በማጠናከር፣ ወጣቶች የውሳኔ ሰጭነት ሚናቸው እንዲጎለብት በመደገፍ እንዲሁም ወጣቶች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ ለወጣቶች ዕድሎችን ለመፍጠር በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የወጣቶች ቁጥርና አቅም በመጠቀም ለዘላቂ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት ለማሳየት ከሀገራዊ ፖሊሲዎች እና ከዓለም አቀፍ ማሕቀፎች፤ ለአብነትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 2250 ጋር በተጣጣመ መልኩ ወጣቶች በግጭት አፈታት እና ሰላምን ለማጎልበት በሚደረጉ እንቅስቃስዎች ውስጥ ቁልፍ ባለድርሻ እንዲሆኑ ለማስቻል የወጣቶች፣ ሰላም እና ደህንነት ብሔራዊ የድርጊት መርሐ-ግብር በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች። ይህ የድርጊት መርሐ-ግብር በወጣቶች ዙሪያ ያሉ ልዩ ፈተናዎችን እና እድሎችን ለመፍታት የሚያስችል ማሕቀፍ ነው።
እናንተ ወጣቶች የሕዝባችን የልብ ትርታ ናችሁ። ጉልበታችሁን፣ ዕውቀታችሁን እና የፈጠራ ችሎታችሁን የኢትዮጵያን ብልፅግና፣ እና ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ተጠቀሙበት። እናንተ የሰላም ባለቤቶች እንደመሆናችሁ እንቅፋቶችን የማፍረስ፣ የተዛቡ አመለካከቶችንና ትርክቶችን የማረም፣ በመወያየትና በመመካከር ችግሮችን የመፍታት እና የሰላም ድልድዮችን የመገንባት ኃይል አላችሁ። ስለሆነም ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ የምታደርጉት እያንዳንዱ ርምጃ የብልፅግና ጉዞአችንን ስኬታማ ያደርገዋል።
በመጨረሻም ሰላም የግጭት አለመኖር ብቻ እንዳልሆነ እናስታውስ። የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የተሳትፎና የተጠቃሚነት እድሎች መኖር ጭምር እንጂ። ይህ ጉዞ የሁላችንም ማለትም የመንግሥት፣ የልማት አጋሮች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የግሉ ሴክተር እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የወጣቶችን የጋራ ጥረት የሚጠይቅ ነው።
በመሆኑም የልማት አጋሮቻችን እና ባለድርሻ አካላት የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በጋራ በማረጋገጥ ወጣቶች እንዲበቁ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያለንን ቁርጠኝነት እናረጋግጥ። በወጣቶች ላይ ኢንቨስት እናድርግ፤ ለሁሉም ሰላምና ብልፅግና የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት በጋራ እንሥራ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የወጣቶች የሰላምና ደህንነት የድርጊት መርሐ-ግብር መዘጋጀት ሀገራችን ወደ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ለምታደርገውን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ነው። ለዚህ ታላቅ ርምጃ ሁላችሁንም በንቃት እንድትሳተፉ ጅምሩ ወደ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲሸጋገር ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ከዚህ ኮንፈረንስ የሚገኙ የውይይት ግብዓቶችና ምክረ-ሃሳቦች ለድርጊት መርሐ-ግብሩ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ርግጠኛ ነኝ።
ወጣት ዘላለም አለምባይ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክትል ፕሬዚዳንት እና የአማራ ክልል ወጣቶች ምክር ቤት ሥራ አስፈጻሚ ነው። ዘላለም ወጣቶች ለሰላም ያላቸውን ሚና በመረዳት የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ ኮንፍረንስ ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር መካሄድ ያለበት እና የሚበረታታ መሆኑን ገልጿል።
የሰላም አለመኖር እንደ ዘላለም ላሉ ወጣቶች እና እሱ በሚኖርበት ክልል ካለው ነባራዊ ሁኔታ በርካታ ወጣቶች እና ቤተሰቦች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉበት የእለት ተእለት እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን አዳጋች የሆነበት መሆኑን የገለጸው ዘላለም በጉባኤው ላይ የተነሱ መሰል የውይይት መድረኮች ወደታችኛው ማኅበረሰብ ወርደው ከወጣቶች ጋር የመወያያና ሃሳብ መለዋወጥ የሚያስችል መድረክ እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል።
ወጣቶች ያላቸው ቁጥር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የሕዝብ ቁጥር የሚይዝ መሆኑ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በመድረኩ ላይ የተገለጸ ሲሆን ወጣቶች ያላቸውን አቅም ለመጠቀም እና በሀገራቸው ሊያመጡት የሚችሉትን ውጤት በተመለከተ በወጣቶች እና በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ላይ ባሉ ባለድርሻ አካላት መካከል ምን ክፍተቶች አሉ ምንስ መደረግ አለባቸው በሚል ዙሪያ ዘላለም ላነሳንለት ጥያቄ የራሱን ምላሽ ሰጥቷል። ‹‹ወጣቶች ከሚይዙት ሰፊ ቁጥር ባሻገር በርካታ የተማረ የሰው ኃይል የምንላቸው ወጣቶች ናቸው። እንደ ሀገር ከሚያስፈልገው ባለሙያ እና ወጣቶች ያላቸውን ሙያ እንዲያዳብሩ በማድረግ እና በማብቃት ረገድ ውስንነቶች ይታያሉ። በመሆኑም የተማረውን እምቅ አቅም ያለውን የወጣት ክፍል ወደ ምርታማነት በመቀየር ሀገር በሚፈለገው ልክ በዜጎቿ ለውጥ እንድታመጣ ወጣቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሠራ ይገባል። ›› ዘላለም ይህ ሃሳብ እውን እንዲሆን እና ወጣቶች ትኩረት ተሰቷቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሌሎች ማኅበረሰብ ክፍሎች ድርሻ ጭምር መሆኑንም ገልጿል።
ወጣቶችን በማብቃት ረገድ ሁሉንም የራሱን ሚና መወጣት እንደሚገባው ያነሳው ዘላለም በመንግሥት ደረጃ ወጣቶችን ማብቃት ላይ ያተኮሩ ፖሊሲዎችን ቀርጾ ወደሥራ መግባት እንደሚያስፈልግ ጠቁሟል። በተጨማሪም እንደ ዘላለም ገለጻ ወጣቶችን ማብቃት ሥራ እድል መፍጠር ላይ ያተኮሩ ውይይቶችም ሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች በመገናኛ ብዙሃን ከሚሰጣቸው ሽፋን በዘለለ ወደታች ወርዶ የወጣቶችን ጥያቄ፣ ፍላጎት በመረዳት ወጣቶችን በአቅማቸው እንደየክህሎታቸው እና የሥራ ዘርፋቸውን በመመልከት የሚታይና የሚጨበጥ ሥራ መሠራት እንደሚገባው ወጣት ዘላለም አጽንኦት ሰጥቷል።
በመድረኩ ላይ ወጣቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ እያካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በምን መልኩ ሊጠቀሙበት እንደሚገባ የተገለጸ እና የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ተገኝተዋል። ወጣቶች በዚህ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ላይ ያላቸው ሚና በተመለከተ ዘላለም የራሱ ሃሳብ አለው ‹‹ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለሀገራችን እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ነው። በመሆኑም ወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል እንደ ሀገር አጀንዳ ተደርገው ሊነሱ ይገባል የሚላቸው ጉዳዮችን ወደፊት ይዞ በመቅረብ ማንሳት ይጠበቅበታል።››
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ያለው አፈጻጸም እንደየክልሉ እንደሚለያይ የገለጸው ወጣት ዘላለም ወክሎ የመጣበት የአማራ ክልል ላይ በተሳትፎ ረገድ ላይ ያሉ ውስነቶች ላይ አስተያየት መስጠቱን አስታውሶ ወጣቱ ያለውን ጥያቄ የችግሮች መንስኤዎችን ከታች ወርዶ መሥራት እንደሚገባ ጠቁሟል። የተደላደለች ሀገር ወደቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር ስለሚያስችል በአግባቡ መጠቀም ይገባል።
ሌላኛው በጉባኤው ላይ ተገኝቶ ሃሳቡን ሲያንጸባርቅ የነበረው ወጣት ከድር አብዱልሽኩር ነው። ከድር ሁለተኛ ዲግሪውን ያጠናቀቀው (በፒስ ኤንድ ሴኩሪቲ) ሲሆን በአሁን ሰዓት በመምህርነት ሙያ በማገልገል ላይ ይገኛል። እንዲሁም ከአፍሪካ ወጣቶች ሰላምና ደህንነት የኢትዮጵያ ኔትዎርክ ኦፕሬሽን ክፍል ውስጥ በበጎ ፍቃደኝነት ያገለግላል። ሰላምን ማስፈን እና ማስጠበቅ የሚለው ሃሳብ በብዛት ከጸጥታ አካላት ጋር መያያዙ ስለሰላም ያለን እይታ ላይ መስተካከል የሚገባው ነው ብሎ ያምናል። ‹‹ሰላምን አብዛኛውን ጊዜ ከጦርነት አለመኖር ጋር ብቻ እንመለከተዋለን። የጦርነት አለመኖር ብቻውን ግን ሙሉ በሙሉ የሰላም መስፈንን አያረጋግጥም። ደህንነት፣ የተረጋገጠ የሥራ እድል እና ሌሎች የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን አብሮ የያዘ ነው፡›› የሚለው ከድር ያለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ስለሰላም የሚሰጠው ትርጓሜ ከጦር መሳሪያ በዘለለ መሆኑን ጠቅሷል።
ወጣቶች ያላቸውን አቅም አሟጠው ተጠቅመው የሚሠሩበት እና የሚያድጉበት፣ ሃሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት እድል ሲፈጠር በሀገራቸው ተስፋ ያደርጋሉ፤ በሀገራቸውን ተስፋ የሚያደርጉ ወጣቶች ደግሞ ለተሻለ ነገር የሚሠሩ እንጂ በመጥፎ ተግባር ላይ የሚሠማሩ አይሆኑም የሚል ሃሳብ አለው።
ያለንበት ወቅት ሀገራችን ቀጣዩን የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ለማካሄድ በመሰናዳት ላይ ትገኛለች። ከድር ወጣቶች የሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆኑ ገንቢም ጭምር ናቸው ያለ ሲሆን ጉባኤው ለወጣቶች ትኩረት የሚሰጥ መሆን እንደሚገባው አንስቶ ወጣቶች ሃሳባቸውን ለመግለጽ እና መብታቸውን ለማስከበር ንቁ ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው እና አስተሳሰባቸውን በዚህ መልኩ መቀየር እንደሚገባም አስታውሷል።
በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች ላይ በሕፃናትና ሴቶች ላይ ለሚደርሱ ጥቃቶች ለመከላከል ወጣት ወንዶችም በጋራ መቆም እንደሚገባቸው ገልጾ ሰላም አካታች እና የሁሉም መሆን ስለሚገባው እንደ ሀገር ያለንን ልዩነት ለመልካም ነገር በመጠቀም የጋራ የሚያደርጉን ነገሮች ላይ በመሥራት ሰላማችንን ማስጠበቅ እንችላለን።
ከድር የወጣትነት እድሜ ሁሉም አካል ሊጠቀምበት የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሶ ወጣቶች ጊዜያቸውን አለአግባብ ከሚያጠፉበት ነገር ይልቅ ለሕይወታቸው መሠረት የሚሆን ተግባር ሠርተው እንዲያልፉ ቤተሰብ ያለውን ወሳኝነት ይገልጻል። ‹‹መንግሥት የምንለው የማኅበረሰብ ውጤት ሲሆን ማኅበረሰብ ደግሞ የቤተሰብ ውጤት ነው። በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት የሚያርቁበት መንገድ ለነገ ማንነታቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ስላለው ቤተሰብ ላይ ማተኮርም ጥሩ ዜጋ ማፍራት ላይ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል። ››
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም