
ከተረጂነት መላቀቅ ሉዓላዊነትን ማስከበር ነው
የትግራይ ሕዝብ ያለፉትን ረጅም ዓመታት በጦርነት ውስጥ አሳልፏል። የጥይት ድምጽ እና የአረር ሽታ ለረጅም ጊዜ አብሮት ኖሯል። ልጆቹን በጦርነት ገብሯል። ሀብት ንብረቱን በጠራራ ፀሐይ አጥቷል። በዚህም ምክንያት ልማት ሳይሆን ድህነት ፣ እድገት ሳይሆን ጉስቁልና እጣ ፋንታው ሆኖ ኖሯል። ይሄ ሁሉ ችግር የሚፈራረቅበት የትግራይ ሕዝብ ወዶና ፈቅዶ አይደለም። አሁንም ሆነ ቀደም ሲል ሕዝቡ የሚፈልገው ሰላም እና ልማት ነው። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሁሉ አንድነትን ነው። ልጆቹን አስተምሮ፣ አሳድጎ መዳርና ወግ ማዕረግ ማየትን ይፈልጋል። በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስክ ስኬታማ ሕዝብና ክልል እንዲሆን ይመኛል። የሕዝቡ ዕድገት የክልሉ፣ የክልሉ ልማት የሕዝቡ ነውና ለዚህ የሚሆነውን ሰላም ይናፍቃል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ የፈለገውንና የተመኘውን መሆን አልቻለም። አሁንም በጦርነትና ጦርነት ቆስቋሽ አስተሳሰቦች ስጋት ውስጥ ነው።
በተለይም የትግራይ ሕዝብን ለተጎሳቆለ ኑሮና ሕይወት የዳረገው 100 ዓመታት ጀምሮ የተደረገ ጦርነት ነው። ሕወሓት ከፌዴራል መንግሥት ጋር በነበረው አለመግባባት በተከሰተው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹ የጥይት ሲሳይ ሆነዋል። ለቁጥር የሚዳርግ የሚቆጠር ሀብት ንብረቱ ወድሟል። ከእዚህ ጋር ተያይዞ በሕዝቡ ሥነልቦና ላይ የተፈጠረው ተጽዕኖም ዛሬም ድረስ ከአዕምሮው የወጣ አይደለም። አሁንም ይሄ ቁስሉ ሳይሽር ሌላ ስጋት ላይ ወድቋል። እናቶች እንቅልፍ አጥተዋል፤ ወጣቶች ስደትን ምርጫቸው አድርገዋል።
የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ሕዝቡ እፎይ ብሎ የሰላም ውሃ መጠጣት ሲጀምር እና የተጎነጨውን ውሃ አጣጥሞ ሳይጎነጭ አሁንም ጦርነት ቀስቃሽ ንትርኮች እየተባባሱ መምጣታቸው ሕዝቡን ይበልጥ አሳዝኖታል። ለዳግም ሥነልቦና ቀውስ እየዳረገውም ይገኛል። ይሄንኑ ስሜቱን በአደባባይ በመውጣትም ጦርነት በቃን! የምንፈልገው ሰላም ነው! ልማት ነው ሲል በተደጋጋሚ ድምጹን አሰምቷል። አዎ! የትግራይ ሕዝብ እውነት አለው። እስከመቼ በጥይት አሩር እያረረ ይኖራል። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሰላም መኖር የትግራይ ሕዝብ የሁልጊዜም ፍላጎት ነው። ስለሆነም በሰላም የመኖር መብቱ ሊጠበቅለት እና ለሚያሰማው የሰላም ጥሪ ጆሮ ሊሰጠው ይገባል።
ከጦርነት ያተረፈ ማንም የለም። ከዚህ ቀደም ከተካሄዱት ጦርነቶችም የትግራይ ሕዝብ አላተረፈም። ከጦርነት ያተረፈው ነገር ቢኖር ልጁን ትምህርት ቤት መላክና ማስተማር አለመቻልን ነው። ታሞ የሚታከምበት ሆስፒታልና መድኃኒት ማጣትን ነው። እንደልብ ወጥቶ ወርዶ ፣ ለፍቶ ሠርቶ ኑሮውን መቀየር አለመቻልን ነው። እንደልቡ ተንቀሳቅሶ መነገድ አለመቻሉን ነው። እናም የትግራይ ሕዝብ የጦርነትን አስከፊነት ከማንም በላይ ያውቀዋል። ሳይወድ በግድ የኖረበት ረጅሙን ሕይወቱን በሰቀቀን ያሳለፈበት ነውና። የጦርነትን ዳፋ በሚገባ ስለሚገነዘብም የማንንም የጦርነት ነጋሪት መስማት አይፈልግም። ሰላም ስጡን! ሲል አደባባይ የወጣው ለዚህ ነው። ስለሆነም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የዚህ ሕዝብ የሰላም ጥሪ ሊሰማ ይገባል።
ሕዝቡ ዛሬ ነገ ችግር ይፈጠር ይሆን ብሎ በስጋት ላይ ይገኛል። ተረጋግቶ መኖር ብርቅ ሆኖበታል። ይሄ ሁሉ የችግር ጋጋታ የጦርነት ጉሰማ የሚካሄደው የግል ጥቅማቸውን ለማስፈጸም በሚፈልጉ ጥቂት ልሂቃን መሆኑ ግልጽ ነው።
“ጅራፍ ራሱ ገርፎ …” እንዲ ልሂቃኑ ትናንት የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ እንዲደረግ ሥራ ሲጀመር እንቅስቃሴውን ሲያደናቅፉና በሌላ በኩል ደግሞ ስምምነቱ ተግባራዊ አልተደረገም ብለው ሲከሱ የነበሩ ናቸው፤ አሁንም በክልሉ ሰላም እንዳይሰፍን በተለያየ መልኩ አመጽ ቀስቃሽ ፣ ሕዝብ ከፋፋይ እኩይ ሥራና ሴራ ላይ ተጠምደዋል። በየመግለጫዎቻቸው ጦር ቀስቃሽ እሩምታዎችን እያወረዱ ይገኛሉ። ይሄ ሕዝቡን እየረበሸ ነው። ሕዝብን አንድ ጊዜ ማታለል ይኖራል፤ሁለት ሦስት ጊዜ ማታለል ግን አይቻልም። ሕዝብ ግጭት እና ጦርነትን እንቢ፤ በቃኝ! ሲል ማድመጥና መተግበር አመዛዛኝ ህሊና ካለው አካል የሚጠበቅ ነው፡፡ በእውነትም የትግራይ ሕዝብ ጦርነት፣ መከራና ስቃይ በቃው ሊባል ይገባል። ሰላሙን አግኝቶ ንጹህ አየር መተንፈስ አለበት።
በየትኛው የፖለቲካ አስተሳሰብ ውስጥ የሃሳብ አንድነት ይኑር ብሎ ማለት አይቻልም። የተለያዩ ሃሳቦችና አስተሳሰቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ልዩነቶች ሊመጡ፣ አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ይሄ ተፈጥሯዊ ነው። ነገር ግን ማንኛውንም ልዩነት በሰለጠነ መንገድ፣ በመነጋገር እና በመወያየት መፍታት ይቻላል። ስለሆነም የትግራይን ሕዝብ እወዳለሁ የሚል ሁሉ የሕዝቡን የሰላም ጥሪ ሊሰማ እና ሊተገብር ግድ ይላል!
ብሌን ከ6 ኪሎ
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከበዓለ ሲመታቸው እለት ጀምሮ የተለያዩ አነጋጋሪ ውሳኔዎችን እያሳለፉ ቀጥለዋል። ከእያንዳንዱ የፕሬዚዳንቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ውሳኔዎች ጀርባም አሜሪካውያንን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ሀገራትንና ሕዝቦችን በአሉታዊም ይሁን አዎንታዊ መንገድ ተፅዕኖ ማሳደሩ ግልፅ ነው። ምክንያቱም ሀገሪቱ አሜሪካ ነች።
ፕሬዚዳንቱ በተለየ ትኩረት አድርገው እየወሰዱ የሚገኙት የተለያየ ምጣኔ ሀብታዊ ውሳኔ በርካታ ሀገራት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጎጂ ሲሆኑ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እየታዘብን እንገኛለን። ትራምፕ በጎረቤታቸው ካናዳ ላይ ሳይቀር የጣሉት የንግድ ታሪፍ እንኳን እንደ አፍሪካ ላሉ ታዳጊ ሀገራት አቅም ለፈጠሩ የአሜሪካ ተናጋጅ ሀገራትም ስጋት መደቀኑ አልቀረም።
ትራምፕ የኃያሏን ሀገር በትረ ሥልጣን ከጨበጡ ገና አንድ ወር እንኳን ሳይሞላቸው አሜሪካንን ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት እንድትወጣ አድርገዋል። ይህ በቃ ሳይሉም በዩ ኤስ ኤድ አማካኝነት አሜሪካ ለተለያዩ ሀገራት የምትሰጠው ርዳታ እንዲቋረጥ አድርገዋል። ይህ ውሳኔ የአሜሪካንን የረድኤት እጅ የሚጠብቁ በርካታ ዜጎች ላላቸው እንደ አፍሪካ ላሉ ሀገራት ተፅዕኖው ቀላል አይደለም። በዚህም ምክንያት ሰብዓዊ ርዳታዎች የሚቋረጡባቸው ብዙሃን ስጋት ቢያድርባቸው አይገርምም።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ የአሜሪካንን ለዘመናት ተዘርግተው የኖሩ የረድኤት እጆች እንዲታጠፉ ማድረግ ብዙ ሰዎችን ሊጎዳ እንደሚችል ቢታመንም የራሱ አዎንታዊ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችልም ማየት ይቻላል። የተፅዕኖውን አሉታዊ ጎን ተቋቁሞ ወደ መልካም አጋጣሚ የመለወጥ የቤት ሥራው ግን የእኛ የአፍሪካውያን ይሆናል። ለዚህም አደጉ የሚባሉ ሀገራት በተለይም አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት ትራምፕ ከፀጥታና ወታደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የወሰዱት ርምጃ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ወደ መልካም አጋጣሚ ለመቀየር እየተንቀሳቀሱ የሚገኙበትን መንገድ ልንኮርጅ ይገባል።
ርግጥ ነው የትራምፕ ውሳኔ ለእኛ የአፍሪካውያን የሰብዓዊ ረድኤት ጉዳይ፣ ለአውሮፓውያን ደግሞ የፀጥታና ወታደራዊ ጉዳይ በመሆኑ ተፅዕኖውን ለየቅል ያደርገዋል። ትራምፕ አሜሪካ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት(ኔቶ) የምታወጣውን ብዙ ገንዘብ ልትቀን ወይም ልታስቀርና ከአባልነቱም ልትወጣ እንደምትችል ደጋግመው ዝተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አውሮፓዎች በዚህ ረገድ ለጦር ድርጅቱ መዋጯቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ከመግለፅ ባሻገር ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙ መናገር የጀመሩት ገና ነጩ ቤተመንግሥት ሳይገቡ ነበር። የአውሮፓ ሕብረት ይህ በአህጉሪቱ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንደሚኖር ቢያውቁም አልተደናገጡም። አውሮፓ በወታደራዊ ጉዳይ ላይ የአሜሪካንን እጅ ሳትጠብቅ ራሷን ለመቻል መልካም አጋጣሚ ይሆናታል በሚል እምነት ቆም ብለው እንዲያስቡ ነው ያደረጋቸው። ለዚህም እንደ ፈረንሳይና ጀርመን የመሳሰሉ ሀገራት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
አፍሪካ አውዱ ቢለያይም ከአውሮፓውያኑ ሊማሩ የሚችሉት ነጥብ አለ። ያም የአሜሪካንን ምፅዋት ተስፋ አድርጎ ከመጠበቅ ይልቅ በምግብና መድኃኒት በመሳሰሉ ጉዳዮች ራስን ለመቻል ተግቶ መሥራት ነው። እውነት ነው አፍሪካ አሁን ያለችበት ሁኔታ የአሜሪካንን ረድኤት አሽቀንጥራ የምትጥልበት አይደለም። ያንን ላድርግ ብትል የሚከፈል ዋጋ ይኖራል። መጥፎውን አጋጣሚ መቀየር አይቻልም። የሚቻለው ነገር የሚኖረውን ህመም ቻል አድርጎና ጥርስን ነክሶ ራስን ለመቻል መነሳሳትና ለዚያም ጠንክሮ መሥራት ነው።
የረድኤት እጆች አንድ ቀን መታጠፋቸው አይቀርም። አፍሪካውያን እስከ መቼ የሰው እንጠብቃለን? የሚል ቁጭት ሊያድርባቸው ይገባል። ምፅዋት አዙሪት ነው፣ መቼም አይለቅም። በሄዱበት የሚከተል ክብረ ነክም ነው። ለዚህ ከወር በፊት የነበረን አንድ አነጋጋሪ ጉዳይ ማስታወስ ይቻላል።
በኢትዮጵያ በ1977ቱ ድርቅ ለተጎዱ ዜጎች ተቀንቅኖ ድጋፍ የተሰበሰበበት ‘Do they know its Christmas?’ ሙዚቃ በቅርቡ ዳግም መለቀቁን ተከትሎ ብዙዎችን ማስቆጣቱ ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ በርካታ ሰዎች “የኢትዮጵያን አሁናዊ የልማት ጉዞ ያላገናዘበ ገጽታን የሚያበላሽ ተረክ” ነው ሲሉም የሙዚቃውን ዳግም መለቀቅ ተችተዋል። አሁን ያለው የኢትዮጵያ እውነት በአርአያነት የሚጠቀስ ፈጣን እድገት እንጂ ሚሊየኖች የሚያልቁበት የረሀብ ታሪክ እንዳልሆነም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል። ሙዚቃው የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ያቃለለና ሰዋዊነትን ዝቅ የሚያደርግ ተረክ የያዘ ነው ተብሎ በብዙዎች ተተችቷል።
የሀገር ሉዓላዊነትና ክብር መገለጫው ከተረጂነት መውጣት ነው። ተረጂነት እንደ አዙሪት ነው። ተረጂነት ከዓመት ዓመት የርዳታ እጅ ለመጠበቅ ይዳርጋል። ተረጂ ሀገራት ጥገኛ ይሆናሉ። የረጂዎች ታዛዥና ተጎታች የመሆን ፈተና ላይ ይወድቃሉ። ክብራቸውን ያጣሉ። እንዲህ ዓይነት ውርደት፣ ለአፍሪካ አይመጥንም። ለየትኛውም ሀገር ቢሆን፣ የርዳታ አዙሪት ጥሩ አይደለም። በጭራሽ መታሰብ የለበትም።
አፍሪካ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ ትልልቅ ሀገርን የያዘች ታላቅ አህጉር ናት። በተለይም ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን ታሪክ ባለቤት ናት። በዓለም ታሪክ ሕልውናቸውን አስጠብቀው በነፃነት መዝለቅ የቻሉ ሀገራት ቢበዛ ከአምስት አይበልጡም። ኢትዮጵያ ከእነዚህ ውስጥ የምትጠቀስ ናት። ለአፍሪካ የነፃነት ፋና ለመሆን የበቃች ሀገር ናት። በሕዝብ ብዛት ከዓለም 10ኛ ናት። የተረጂነት አዙሪት በፍጹም ለኢትዮጵያ አይመጥንም። ከተረጂነት ጋር አብሮ የሚመጣ የታዛዥነትና የተጎታችነት ውርደት እንደነውር መቆጠር አለበት። “ውርደት ከኢትዮጵያ ባሕል ጋር አይሄድም” የሚል የቁጭት ስሜት በሕዝብ ዘንድ መፈጠር አለበት።
የሕዳሴ ግድብን ለማስተጓጎልና ለማስቆም ብዙ ዘመቻ ተካሂዶብናል። በኢትዮጵያ ላይ እየተደራረበ የመጣባትን የውጭ ጫና እንዲሁ እንደዘበት የምንረሳው አይደለም። ኢትዮጵያውያንን ምንኛ እንዳስቆጣቸው እናስታውሳለን። በኛው ዘመን በኛ ትውልድ ላይ የተካሄደ ዘመቻ ነው። የራሳችን ታሪክ፣ የእያንዳንዳችን ትዝታ ነው። ያኔ ክፉኛ አንገብግቦናል። አንገሽግሾናል። ዛሬም ይከነክነናል። “የሕዳሴ ግድብ ግንባታን አቋርጡ፤ አለበለዚያ ርዳታ እንከለክላለን!” የሚል ማስፈራሪያ ሊዋጥልን ይቅርና መታሰቡ ራሱ ይተናነቀናል።
በተረጂነት ሰበብ የሚመጣ የውጭ ጫና ምን ያህል እንደሆነ ከእኛ በላይ የሚያውቅ የለም። ሀገራዊ ጸጋዎቻችንን እንዳናለማ፣ ሠርተንና ገንብተን እንዳናድግ አስሮ የሚይዘን ከሆነ ዘላለም “ተረጂ” ሆኖ ከመቅረት ውጭ ምን አማራጭ ይኖረናል? ተረጂነት ተረጂነትን ይወልዳል የሚባለውም ለዚህ ነው። “ተረጂነት ይብቃ” ብለው በጥሰው ሰብረው ካልተላቀቁ፣ እውነትም “አዙሪት ነው” ያስብላል። በርዳታ ሰበብ የውጭ ጫናዎችን አሜን ብለን ከተቀበልን ተስፋችንን ከማጨለም አይመለስም። ሀገራችን ታዛዥና ተጎታች እንድትሆን ከተገደደች፣ እንዴትስ “ሀገር አለን” ብለን በሙሉ ልብ እንናገራለን?
የተረጂነት ጣጣ ብዙ ነው። ሁሉንም ነገር ይነካል። የሕልውና ፈተና ይሆናል። በኑሮ የመሻሻል ተስፋን ያጨልማል። የኢኮኖሚ እድገትንና የሀገር ብልፅግናን አሰናክሎ ያስቀራል። የሀገር ሉዓላዊነትን ያሳጣል። የሀገርና የሕዝብ ክብርን ያዋርዳል። በተረጂነት ሳቢያ የሚመጡ አደጋዎች ኢኮኖሚን፣ ፖለቲካን፣ ባሕልን ሁሉ የሚያበላሹ ናቸውና።
ተረጂነት ያስጠቃል፤ ያስደፍራል፤ ያዋርዳል። ከተረጂነት የመላቀቅ ጉዳይ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳችን መሆን ያለበትም በእነዚህ ምክንያቶች ነው። ተስፋችን መጨለም የለበትም። ለልጆቻችን ተረጂነትንና የዕዳ ሸክም ማውረስ የለብንም። የሀገራችንና የሕዝባችን ክብር መታደስ አለበት። ሀገራችን ከተረጂነት በመላቀቅ ወደ ብልፅግና መጓዝ አለባት። ደግሞም ትችላለች። እንደምትችልም ከራሳችን ልምድና ከራሳችን የስኬት ጅምሮች መማር እንደማይከብደንም።
ፈተናዎችን በራሳችን አቅም ተቋቁመን መሻገር እንደምንችል በኮቪድ ወረርሽ ወቅት አይተናል። ያኔ የዓለም ኢኮኖሚ እንደተናጋ ሁላችንም እናውቃለን። የብዙ ሀገራት ኢኮኖሚ አሽቆልቁሏል። በኢትዮጵያ ግን፣ ወረርሽኙን ከመከላከልና ከመቋቋም ጎን ለጎን፣ ኢኮኖሚያችንም እንዲያድግ በጥበብና በትጋት ስለጣርን ተሳክቶልናል።
በኮቪድ ምክንያት የዓለም አየር መንገዶች ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ሲወድቁ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግን በርካታ የመፍትሔ አማራጮችን በመጠቀም ውጤታማ ሆኗል። ይህም ብቻ አይደለም። ወረርሽኙን ከመከላከል ባሻገር ለዘለቄታው የሚጠቅም መንገድ የጤና ተቋማትን አቅም ለማሳደግ ተችሏል።
ኢትዮጵያ ችግሮችን በራሷ አቅም ተቋቁማ ወደ ተሻለ ከፍታ ማደግ አያቅታትም። የሕዳሴ ግድብ ግንባታን በሚመለከት በኢትዮጵያ ላይ የደረሰባት ከባድ የውጭ ጫናም ሁለት ነገሮችን ያስተምረናል። በአንድ በኩል፣ በዓለም ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከባድ የውጭ ጫናዎችን ተቋቁመን፣ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ ተከራክረን የማሸነፍ አቅም እንዳለን አሳይተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በተረጂነት ሳቢያ የሚመጣ የውጭ ጫና የቱን ያህል አደገኛና የቱን ያህል ቅስም ሰባሪ ሊሆን እንደሚችል በዚሁ አጋጣሚ ታዝበናል። የሕዳሴ ግድብን ለማስቆም የተካሄደ ዘመቻ፣ የኢትዮጵያን ቅስም ለመስበር የተደረገ ሙከራ ነው ማለት ይቻላል። ለዚያውም የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በብድር ወይም በርዳታ የሚካሄድ አይደለም። እንደዚያ ቢሆንማ፣ ከመነሻውም ርዳታና ብድሩ አይገኝም። በሆነ ተዓምር ርዳታ ተገኝቶ የግድብ ግንባታ ቢጀመርም፣ የትም አይደርስም ነበር። ርዳታው ተቋርጦ፣ የግድብ ግንባታው ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር። ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የምትገነባው ስለሆነ ነው፣ “የሀገር ምኞት” በተግባር “የሀገር እውነት” ወደመሆን እየተሸጋገረ የመጣው።
እንዲያም ሆኖ ከብዙ ፈተና አላመለጠም። በውጭ ርዳታ የሚካሄድ ፕሮጀክት ባይሆንም፣ ከውጭ ጫና አልዳነም። ለምን? ኢትዮጵያ ተረጂ ሀገር ስለሆነች በውጭ ተጽዕኖ እጇን መጠምዘዝ እንችላለን ብለው ስላሰቡ። “በደካማ ጎኗ እንግባባት” ብለው ነው የተረባረቡባት። “ለግድብ ግንባታ ባይሆንም ለሌላ ለሌላ ነገር ርዳታ ትፈልጋለች። ርዳታ እንቀንሳለን፤ ከፈለግንም እናቋርጣለን” ብለው የማስፈራራት ቀዳዳ አግኝተዋል።
እንዳሰቡት ቢሳካ ኖሮ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት ይቅር የማንለው ከባድ የታሪክ ቁስል ይሆንብን ነበር። ትልቅ የታሪክ ስብራት በደረሰብን ነበር። ፊት ለፊት የመጡ ወረራዎች ሳይበግሯት አሸንፋ መልሳለች። ወረራው እጅግ ሲከፋም “አሻፈረኝ” ብላ፣ እጅ ሳትሰጥና በባርነት ሳትንበረከክ ነፃነቷን አስከብራለች። ነገር ግን አንድ እውነት እንድንገነዘብም ያስገድደናል። ተረጂነት ያስደፍራል፤ ያስጠቃል፤ ለውርደት ያጋልጣል። ታዲያ ምን እስኪመጣብን፣ ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው? እስከ መቼስ ነው የርዳታ እጅ የምናየው? ለምንስ ነው ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፈው?
በርግጥ “ተረጂነት ውርደትን ያመጣል” ሲባል፣ በአደጋ ጊዜ ያገዙንን ሰዎች ለማጣጣል አይደለም። ኢትዮጵያ ታመሰግናለች። የኢትዮጵያ መንግሥትም ከማመስገን ወደኋላ አይለም። ክብር የሚያውቅ ሀገር ውለታ ቢስ አይሆንም። ኢትዮጵያ ደግሞ ክብር ታውቃለች። ታሪኳ ነው። ባለውለታዎቿን ታመሰግናለች።
ነገር ግን “ተረጂ” ሆና ለመቅረት አይደለም። በጭራሽ! ተከባብሮ መተጋገዝ መተባበር መልካም ነው። ኢትዮጵያም በተለያዩ ጊዜያት የራሷን ድጋፍ እንዳበረከተች ሁሉ። በበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ኃይል ተሰማርተዋል። ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የተላበሱና የአፍሪካዊ ወዳጅነትን የሚያስፋፋ አገልግሎት ሰጥተዋል።
አሜሪካ የሽብር ጥቃት በደረሰባት ጊዜ ኢትዮጵያ አጋርነቷን አሳይታለች። ኢትዮጵያውያን ደቡብ ኮሪያ ድረስ ሄደው መስዋዕት ከፍለዋል። ወደ ኮንጎም ተሰማርተዋል። በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ በሥልጠና ረድታለች። በዓለም መድረክ ዋና አለኝታ ሆናላቸዋለች። እንዲህ ዓይነት የመደጋገፍ ተግባር መልካም ነው። ከመከባበር ጋርም ይሄዳል። አንዱ ሀገር የሁልጊዜ ረጂ፣ ሌላኛው ሀገር የሁልጊዜ ተረጂ ከሆነ ግን መከባበርን ያጠፋል።
ተረጂነት በጊዜ ካልተገታ፣ “ጌታና አሽከር” ለመፍጠር ይጠቀሙበታል። በወዳጅነት ምትክ የበላይነትና የበታችነት ስሜትን ያቀነቅኑበታል። ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱን ውርደት እንደማትቀበል በተደጋጋሚ አሳይታለች። ሁነኛውና አስተማማኙ መፍትሔ ግን፣ ችግሮችን በራሷ አቅም ተቋቁማ በመሻገር የሚገኝ መፍትሔ ነው። ከተረጂነት በመውጣት ነው የውጭ ጫናዎችን ሙሉ ለሙሉ ማምከን የሚቻለው።
እንዲያውም ከረጂነት ወጥታ ወደ ብልፅግና ስትሸጋገር፣ ለወዳጅነት የሚፈልጓት፣ የሚያከብሯትና ከጎኗ የሚቆሙ ይበረክታሉ። በጠላትነት ስሜት ክፉ የሚያስቡባት ደግሞ ሃሳባቸውን ይለውጣሉ። ለጥቃት ሊሰነዘሩ የነበሩ እጆችም ይሰበሰባሉ።
ከተረጂነት የመላቀቅ ሃሳብ ዙሪያ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል እንዲህ ዓይነት መሠረታዊ መግባባትና የጋራ ጽኑ ዓላማ በውይይት እየተፈጠረና በውይይት እየዳበረ መሄድ አለበት። ከተረጂነት መላቀቅ ለኢትዮጵያ የሉዓላዊነትና የሀገር ክብር ጉዳይ ነው በሚለው የጋራ አቋም ላይ ሙሉ እምነት ሊኖረን ይገባል።
የውጭ ኃይሎች የሚደፍሩት ሳይሆን የሚያከብሩት ሀገር፣ የሚያከብሩት ሕዝብ እንሆናለን ለጠላትነት የሚያስቡት ሳይሆን ለወዳጅነት የሚፈልጉት። ደካማ ጎን አይተው ጥቃት የሚሰነዝሩበት ሳይሆን፣ “ጠንካራ ነው፤ ለምንም አይበገርም፤ የሚቃጡበትን ያሳፍራል” ብለው ይጠነቀቃሉ። “ኢትዮጵያ የሚያከብራትን ታከብራለች” ብለው የሚተማመኑባት ጠንካራ ሀገር ትሆናለች። ክብሯም ይታደሳል። በኛ ዘመን የኢትዮጵያን ክብር ማዋረድ የለብንም።
“ከተረጂነት ወደ ምርታማነት፣ ከዕዳ ወደ ምንዳ” እንዲሉ ነው። ከተስፋ ብርሃን ወደ ተጨባጭ ብርሃን መሸጋገር ይቻላል። ይህም ብቻ አይደለም። ካወቅንበትና ከሠራንበት፣ ሀገራችን ዕምቅ ጸጋ የበዛላት ሀገር ናት። በሀገራችን በየአካባቢያችን የሚገኙ ጸጋዎችን ወደ ብልፅግና ልንቀይራቸው እንችላለን። በአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት የምንሆንበት ጊዜም ሩቅ አይሆንም። ያን ጊዜ ተረጂነት ታሪክ ይሆናል። በችግር ጊዜ በቀና ልቦና የረዱንን የምናመሰግንበት ትክክለኛው መንገድም፣ ከተረጂነት በመውጣትና ራሳችንን በመቻል ነው። ከራሳችን አልፈን ወደ ብልፅግና ስንጓዝና ሌሎችን የመርዳት አቅም ሲኖረንም ነው “ውለታ ከፋይ” የምንሆነው።
ስንዴን ኤክስፖርት ማድረግ ማለት በቀላሉ እጇ የማትጠመዘዝ ኢትዮጵያን መገንባትና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ማለት ነው። የሀገር ሉዓላዊነትና ክብር ሲባል አንደኛው መገለጫ ከተረጂነት መውጣት ሲሆን ይህም የሚረጋገጠው ውስጣዊ አቅም በመፍጠር ነው።
ኢትዮጵያ ፀጋዋን ተጠቅመን ከተረጂነት መላቀቅ በእጅጉ ያስፈልገናል። ውጤት እያስመዘገብን የምንገኝበትን የግብርና ምርታማነታችንን በማሳደግ ሀገራዊ ለውጡን በፅኑ መሠረት ላይ መገንባት ያስፈልጋል። በስንዴ ልማት ላይ እየተመዘገበ የሚገኘው ውጤት በሀገሪቱ አዲስና ልዩ የሉዓላዊነት መሠረት በኢትዮጵያ እየተጣለ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ይሰጣል።
እንደ ሀገር ከምናመርተው የስንዴ ምርት ውስጥ የተወሰነውን ወደ ውጭ መላክ ማለት፤ በቀላሉ እጇ የማይጠመዘዝ ኢትዮጵያን መገንባትና ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው። እንደ ሀገር ወደ ውጭ ስንዴ የመላክ ጥቅም ዶላር ማግኘት ብቻ አይደለም። የተወሰደው ርምጃ በኢትዮጵያም ስንዴን ከራስ ፍላጎት ባሻገር ወደ ውጭ መላክ ይቻላል የሚለውን አቅም ለመላበስ ጭምር ነው።
የሀገራችንን እምቅ አቅም እና ፀጋ ገና አልተጠቀምንም። ግን ጀምረናል፣ ወደ ተሟላ አቅም በመለወጥ ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት ያስፈልጋል። በደም መሰዋዕትነት የተረጋገጠውን የሀገር ነፃነት በላባችን እና በጥረታችን አሟልተን የዚህ ትውልድ ታሪክ ሠሪዎች መሆን ይገባናል።
ብሌን ከ6 ኪሎ
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም