ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ገና ያልተነካ ብዙ ሀብት እንዳላት ጥናቶች ያመላክታሉ። እነዚህን ሀብቶች በምን ያህል መጠን፣ የት የት አካባቢ እንዳሉ አጥንቶ በማወቅና በመለየት ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ግን ብዙ እንዳልተሠራም እንዲሁ ይጠቁማሉ፡፡
ሀገሪቱ ለማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ዘርፉ በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት እድገት ለማስመዝገብ በዋናነት ከተያዙት አምስት ዘርፎች አንዱ እንዲሆን ተደርጓል፡፡
ይህን ተከትሎም የማዕድን ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ፣ የክልል ማዕድን አደረጃጀቶች፣ ባለሀብቶች በማዕድናት ላይ ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ የማዕድን ሀብትን አውጥቶ በመጠቀም በኩልም እንዲሁ ለውጦች መታየት ጀምረዋል፡፡ ለትላልቅ ኢንዱስትሪዎች በኃይል ምንጭነት የሚያገለግለውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ማምረት መጀመሩ፣ ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ እንደ ግራናይት ያሉትንም በሀገር ማምረት መቻሉ፣ ኩባንያዎች በወርቅ ልማት እየተሰማሩ ያሉበት እንዲሁም የወርቅ ምርት እየጨመረ ያለበትም ይህንኑ ከሚያመለክቱት መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
የማዕድን ሀብቱን ከዚህም በላይ ለመጠቀም በቅድሚያ ጥናትና ምርምር ማድረግ የግድ ይላል። ይህ ሥራ በተለያዩ ተቋማት የሚከናወን ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳሉ፡፡
ተቋማቱ ዘርፉ በእውቀትና በብቃት እንዲመራ ለማድረግ የሰው ኃይል ከማሰልጠን ባሻገር በጥናትና በምርምር የተደገፉ ሥራዎች በመሥራት የሀገሪቱ ማዕድናት የትና በምን ያህል መጠን እንደሚገኙ፣ አልፎም ተርፎ የማዕድናቱን ባህሪያት ጭምር ለመለየት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ተቋማቱ በየአካባቢያቸው ባሉ የማዕድን ዓይነቶችና በማዕድናቱ የክምችት መጠን ላይ ለብቻቸውም፣ ከክልል ማዕድን መሥሪያ ቤቶችና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን ጥናትና ምርምሮች እንደሚሠሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል አንዱ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው፤ ዩኒቨርሲቲው በማዕድን ዘርፉ በርካታ ተግባሮችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በተለይ ከአማራ ክልል የማዕድን ቢሮ ጋር በመተባበር በክልሉ ማዕድናት ላይ ጥናት በማካሄድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠረ ስለመሆኑ ከዩኒቨርሲቲው የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የሥነ ምድር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አቶ ውለታው ሙሉአለም እንዳስታወቁት፤ ዩኒቨርሲቲው በምርምርና በማስተማር ዘርፍ አንጋፋ እንደመሆኑ በማዕድን ዘርፉም ምርምሮችንና ጥናቶች ያደርጋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በማዕድን ዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ጥናትና ምርምር ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ከክልሉ ማዕድን ቢሮ ጋር በመተባበር ውጤታማ የምርምር ሥራዎች እየሠራ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ለዚህም አብነት ሲጠቅሱ፤ በዩኒቨርሲቲው በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች ( ቋራ፣ ጃዊ፣ ስማዳና ጃን አሞራ) የሥነ ምድር ካርታ ትንተናና የማዕድን ሀብት ሥርጭት ለ1፤50000 /አንድ ለሃምሳ ሺ/ በሆነ ስኬል አጥንቶ የተገኘውን ውጤት ለማዕድን ቢሮው ማስረከቡን ይገልጻሉ፡፡
በእነዚህ ወረዳዎች ከተደረጉ ጥናቶች ናሙና ተወስዶ የማዕድን አመላካቾች መገኘታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በቋራ ወረዳ የብረት ማዕድን መገኘቱን ጠቅሰው፤ ይህን የብረት ማዕድን በተመለከተ ሰፋ ያለ ጥናት ተካሂዶ የተገኘውን አበረታች ውጤት ክልሉም እንዲያወቀው መደረጉን አስታውቀዋል። ዘንድሮም በጠለምትና አዲአርቃይ ወረዳዎች የማዕድናት ጥናት እያደረገ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በማስተማርና በምርምር ግንባር ቀደም በመሆኑ በማዕድናት ላይ የሚያከናውናቸውን የጥናትና ምርምር ተግባሮችንም አጠናክሮ ቀጥሏ። በዩኒቨርሲቲው በሚደረጉ የበጀት ድጋፎች በተለያዩ ወረዳዎች በተካሄዱ ሜጋ ጥናቶች የማዕድን ክምችቶችን ለመለየት ተችሏል፡፡ በጋይት አካባቢ የኦፓል እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች ደግሞ የሌሎች ማዕድናት ሀብቶች ስለመኖራቸው አመላካቾች ታይተዋል፡፡
የሥነ ምድር ካርታ ጥናት ሲካሄድ በየወረዳው ያሉ የማዕድናት ሀብቶች ሥርጭት ምን ይመስላል? የት ወረዳ ላይ ምን ዓይነት ማዕድን ይገኛል? የሚሉት ተለይተዋል፡፡ በመሆኑም በየወረዳዎቹ አንድ ማዕድን ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ዓይነት ማዕድናት እንዳሉ ማወቅ ተችሏል፡፡
የብረት፣ የወርቅ ፣ የኦፓልና የሌሎች ማዕድናት ጥናቶችም እንደሚካሄዱ ጠቅሰው፤ ጥናቶቹ በዩኒቨርሲቲው በጀት ብቻ ሳይሆን ከክልሉ ማዕድን ሀብት ቢሮ ጋር በመተባበር ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ያካሄደው የቋራ ወረዳን የብረት ማዕድን ጥናት ብቻ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ በአዲአርቃይና ጠለምት ወረዳዎች ላይም እንዲሁ በወርቅ ማዕድን ላይ ጥናት መካሄዱን አመልክተዋል። ማንኛውንም የማዕድን ሀብት ያጠቃለለ ጥናት እየተሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በወረዳዎች በተሻለ ደረጃ ጥናት ስናካሂድ ከፍተኛ ክምችት ያለውን የማዕድን ዓይነት ለይተን እናሳወቃለን የሚሉት የዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ፤ ይህም በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ያለውን የማዕድን ክምችት አውቀው እንዲሠማሩ ለማስቻል ይረዳል ብለዋል፡፡
ጥናቶቹ የሀገሪቱ አቅም በሚፈቅደው መሠረት በማዕድን ዘርፉ ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንደሚያስችሉ ይጠቁማሉ፡፡ ለእዚህ አብነት ጠቅሰው ሲያብራሩም፣ በቋራ ወረዳ የተገኘውን የብረት ማዕድን አመልክተዋል፡፡ በወረዳው ከፍተኛ ክምችት ያለው የብረት ማዕድን መገኘቱን ጠቅሰው፣ ለዚህም ተጨማሪ ጥናቶች መደረጋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲውም በማዕድናት ዙሪያ በራሱ በጀት ጥናት እንደሚያካሂድ ተናግረው፣ በማንኛቸውም ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት በሚውሉ የማዕድናት ዓይነቶች ላይም ጥናት ማካሄዱንም ጠቅሰዋል፡፡
እሳቸው እንዳሉት፤ በግራናይት ማዕድን ላይም እንዲሁ ጥናት ተካሂዷል፤ በኦፓል ማዕድናት ክምችት በኩልም በታች ጋይንት እንዲሁም በሰሜን ጎንደር የተለያዩ አካባቢዎችም ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በሚመደበው በጀት ለአንድ ዓመት በሚካሄዱ ጥናቶች ለኮንስትራክሽን ግብዓት በሚውሉ ማዕድናት ላይ ጥናት ተካሂዷል፤ አብዛኛዎቹም የጥናት ውጤቶች ታትመዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በማዕድን ላይ ከሚያከናውናቸው ሥራዎች ጎን ለጎን በሥነ ምድር ትምህርት ክፍል ደግሞ የመሬት መንሸራተት አደጋዎችንና ውሃን፣ በተመለከተ ይሠራል፡፡
የአማራ ክልል በቆዳ ስፋታቸው በሀገሪቱ ከሚታወቁ ክልሎች አንዱ እንደ መሆኑ ዩኒቨርሲቲው በባለፉት ዓመታት ባካሄዳቸው የጥናትና ምርምር ሥራዎች ሁሉንም በማካለል ተደራሽ ማድረግ አልቻለም፤ አሁንም ገና ጥናት ላይ ያሉም አሉ፡፡ በሌሎችም ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁ ጥናቶች እየተደረጉ ስለሆነ የሥነ ምድር ካርታ ጥናት ገና እየተሠራ ነው፡፡ በተጠኑት ወረዳዎች ላይ ግን የተሻለ የማዕድን ሀብት ክምችት ያለ ስለመሆኑ አመላካቾች መኖራቸው አስታውቀዋል፡፡
እንደ አቶ ውለታው ማብራሪያ ፤ በክልሉ በጥናቱ እንደተመላከተው የብረትና ኦፓል ማዕድናት ከፍተኛ ክምችት አለ፡፡ አሁን በመሥራት ላይ ባሉትም ጥናቶችም እንዲሁ ልክ ባለፉት ጊዜያት እንደተካሄዱት ጥናቶች በወርቅ ማዕድንም ተስፋ ሰጪ አመላካቾች መኖራቸው ታውቋል፡፡ እንደ ግራናይት፣ ማርብል ዓይነት ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውሉ ማዕድናትም በብዛት እንዳሉ ጥናቶቹ ያመላክታሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተያዘው በጀት ዓመት የሁለት ወረዳዎችን ፕሮጀክቶች እየሠራ ይገኛል። ፕሮጀክቶቹን እስከ መጪው ሰኔ ወር ድረስ ያጠናቅቃል፡፡ በአንደኛው ፕሮጀክት በጠለምት ወረዳ የሥነ ምድር ካርታ ትንተናና የማዕድን ሀብት ሥርጭትን ለማሳየት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው፤ በሁለተኛው ፕሮጀክት ደግሞ በአዲአርቃይና አካባቢው የሚካሄደው የወርቅ ክምችት ፍለጋ ሥራ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ የሚደረገው ጥናት እንደተጠናቀቀ ውጤቱ ይገለጻል፡፡
በክልሉ ማዕድናት ላይ ጥናቶች ሲካሄዱ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሙ ጠቅሰው፣ አንዱ ተግዳሮት ጥናት በሚካሄድባቸው ቦታዎች አልፎ አልፎ የሚያጋጥመው የጸጥታ ችግር መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ ጥናቱ የሚካሄድበት አካባቢ ለትራንስፖርት አመቺ ላይሆን እንደሚችል ተናግረው፣ ብዙ ርቀት በእግር መጓዝን ሊጠይቅ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ በዚህ ላይ የጸጥታ ስጋት ሲታከል እንደልብ ተንቀሳቅሶ ናሙናዎች ለመሰብስብ አዳጋች የሚሆንባቸው ጊዜያት እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ በተቻለ መጠን ሥራዎች ሳይቋረጡ እንዲቀጥሉ በማድረግ እንደሚሠራም ያስረዳሉ፡፡
የመሠረተ ልማት ችግር ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ በእግር በመጓዝ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ ያመላክታሉ፡፡
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የክልሉን ማዕድናት ጥቅም ላይ ለማዋል ዋናው ተግዳሮት ማዕድናትን በሚገባ አለማወቅና አለመጠናታቸው መሆኑን አመላክተው፣ የክልሉን የቆዳ ስፋት የሚመጥኑ ሥራዎች እንደሚያስፈልጉም ተናግረዋል፡፡ አሁን በተጀመሩ ሥራዎች ጥሩ ለውጦች እየመጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ የክልሉ ማዕድን ቢሮ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ጥሩ ሥራዎች እየሠራ ነው፤ ይህም አበረታች ለውጦችን እያመጣ ይገኛል፡፡ በሥነ ምድርና በማዕድን ዘርፍ ያለው ሀብት የተሻለ ሆኖ እነዚህ ሀብቶች አለመጠናታቸው ክፍተት ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን ላይ በማዕድን ዘርፉ በርካታ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ናቸው፡፡
ዩኒቨርሲቲው ከክልሉ ጋር መሥራቱን አጠናክሮ በመቀጠል ከእስካሁኑም በበለጠ እንደሚሠራም ይገልጻሉ፡፡ በዩኒቨርሲቲው በጀት ላይ ተመሥርተው የሚሠሩ ሥራዎችንም በማጠናከር ጥናቶች በማድረግ በማዕድን ዘርፍ የበኩሉን ኃላፊነት ለመወጣት በሰፊው አቅዶ እየሠራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
እሳቸው እንደሚሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ጊዜያት በሥነ ምድር ትምህርት ዘርፍ በማዕድን ዘርፍ መሥራት የሚችሉ ብዛት ያላቸው ተማሪዎችን እያሰለጠነ በማስመረቅ የዘርፉን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም እንዲሁ የሰው ኃይል በማሰለጠን ብቁ ያደርጋሉ፡፡
ይሁን እንጂ ይህንን አቅም አደራጅቶ የሥራ እድል በመፍጠርም ሆነ በተለያየ መልኩ ወደ ተግባር የማስገባት ችግር እንደሚታይ ጠቁመዋል፡ በማዕድን ዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት ጎልቶ የሚታይ ክፍተት አለመሆኑንም ጭምር አመልክተዋል፡፡
አቶ ውለታው እንዳስታወቁት፤ የማዕድን ዘርፉን በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ በማድረግ ላይ ግን ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡ ማዕድናትን ለማጥናት፣ ለመለየትና ለማልማት የሚጠቅሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በእጅጉ አስፈላጊ ናቸው፡፡
ጥናቶች ሲካሄዱ የሚሰበሰቡ ናሙናዎች ምርመራ የሚደረገው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ባሉ ቤተሙከራዎች /ላብራቶሪዎች/ ነው። ሁሉም የሚሰበሰቡ ናሙናዎች ሀገር ውስጥ ባሉ ቤተሙከራዎች /ላብራቶሪዎች/ እየተሠሩ አይደለም፤ ይህም የዘርፉ ሌላው ዋንኛ ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በማዕድን ሚኒስቴር ፣በጂኦሎጂካል ኢንስቲ ትዩት እና በዩኒቨርሲቲዎች በኩልም የጂኦሎጂ ቁሳቁስ ያልተሟሉበት ሁኔታ እንዳለም ጠቁመው፤ እነዚህ ቁሳቁስ በሀገር ውስጥ ባለመኖራቸው የተነሳ የተወሰኑ ናሙናዎች ወደ ውጭ ሀገር በመላክ የሚሠሩበት ሁኔታ መኖሩን ያመላክታሉ። እነዚህን ናሙናዎች ውጭ ሀገር ልኮ ለማሠራት የሚወጣው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲው ናሙናዎችን የሚፈትሽበት የራሱ ላብራቶሪ እንዳለው ጠቅሰው፣ ሁሉንም ናሙናዎች ለመፈተሽ የሚያስችል አቅም እንደሌለው ተመራማሪው አመልክተዋል፡፡ እንደ ሀገር ሲታይ ያሉት ላብራቶሪዎች ሁሉንም ናሙናዎች እዚሁ ለመፈተሽ የሚችሉ አይደሉም ያሉት ተመራማሪው፣ የተወሰኑ ናሙናዎችን ወደ ውጭ ልኮ ማሠራት የግድ ይሆናል ይላሉ፡፡
ዩኒቨርሲቲውም ሆነ የሚመለከታቸው አካላት እነዚህን ላብራቶሪዎች ለማሟላት ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ አሁን ላይ ለዩኒቨርሲቲው ላብራቶሪ አስፈላጊ ማሽኖች ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ወደ ውጭ ተልከው የሚሠሩ ናሙናዎችን በሀገር ውስጥ ለመሥራት የሚያስችሉ ማሽኖችንን ማሟላት ቢቻል፣ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ያስችላል የሚሉት ተመራማሪው፤ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ጥር 30 ቀን 2017 ዓ.ም