«የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የፓርቲያችን ቁጥር አንድ አጀንዳ ሆኖ የሚቀጥል ነው» አቶ አወሉ አብዲ

አቶ አወሉ አብዲ የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር

ብልፅግና ፓርቲ ዋና መሪ ሃሳቡንከቃል እስከ ባሕልየሚለውን አድርጎ ባለፉት ሶስት ቀናት ጉባዔ ማካሄዱ የሚታወቅ ነው። ፓርቲው በጉባዔው ማጠናቀቂያም ስምንት ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

በአቋም መግለጫው ዘላቂና አዎንታዊ ሰላም ማስፈንና ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነትን እውን ማድረግ ላይ እንደሚሠራ አሳውቋል። አዲስ ዘመንም በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ላይ በመመሥረት የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ከአቶ አወሉ አብዲ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሮ አቅርቧል።

አዲስ ዘመን፡ብልፅግና እንደ መንግሥትና ገዥ ፓርቲ በኢትዮጵያ ያስመዘገባቸው አበይት ስኬቶች ምን ምን ናቸው?

አቶ አወሉ፡የብልፅግና ስኬቶችን ከመጥቀሴ በፊት በመጀመሪያ ለውጥ ለመምጣቱ ዋና ገፊ ምክንያቶችን ምን ነበሩ? ለሚለው ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ይመስለኛል። ለለውጡ ገፊ ምክንያቶች ከሚባሉት አንደኛ መጠነ ሰፊ የሕዝብ ቅሬታዎች ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ የእኩልነት፣ የነፃነት፣ የኢኮኖሚ፣ የማንነት፣ የዴሞክራሲ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ይገኙበታል።

ባለፉት ጊዜያት የነበሩ መንግሥታት በሕዝብ ሲነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን ለይተው ለመመለስ የነበራቸው ተነሳሽነት ሆነ ቁርጠኝነት በጣም ዝቅተኛ ነበር። ለምሳሌ የአጼ ኃይለሥላሴን ዘመን ብንወስድ የሕዝቡ ጥያቄ የነበረው አንደኛ ሕዝባዊ መንግሥት ይቋቋም የሚል ነው፤ ሁለተኛው የመሬትና የኢኮኖሚ ሲሆን፣ ሶስተኛው ደግሞ የማንነት ጥያቄ ነበር። እነዚህን ጥያቄዎች ሥርዓቱ መመለስ አልቻለም፤ እንኳን ሊመልሳቸው ቀርቶ ሊሰማቸውም አልወደደም። በወቅቱ “እኛ ከእግዚአብሔር የተሾመን ነን!” በሚል ራሳቸውን ሰይመው ስለነበር የሕዝብን ጥያቄ አዳምጠው የመመለስ ፍላጎቱ አልነበራቸውም።

የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት በኃይል ከተገረሰሰ በኋላ የመጣው የደርግ መንግሥት ነው፤ የደርግ መንግሥትም የተጠየቀው እነዚያ ሶስቱን ጥያቄዎች ነበር፤ ደርግም ለመመለስ የሞከረው አንዱን ሲሆን፣ እሱም መሬት ለአራሹ የሚለውን ነው። እሱንም ቢሆን በአዋጅ ደረጃ ከመለሰ በኋላ ወደ ተግባር ሲገባ ሕዝብ ያመረተውን ምርት በኮታ መልክ ሲሰበስብ እንደነበር የሚታወስ ነው። የዴሞክራሲንና የማንነትን ጥያቄ ግን ያለፈው ደፍጥጦ ነው።

ጥያቄዎች ሳይመለሱ ሲቀር የተማሪውም ሆነ የሕዝቡ እንቅስቃሴና ተቃውሞ እንዲሁም ሰልፉም እየበዛ ሄደ። ጥያቄዎቹ ባለመመለሳቸው የትጥቅ ትግል ተበራክቶ ነበር። በወቅቱ ወያኔ፣ ሻዕቢያ፣ ኦነግ፣ ኦብነግን ዓይነት የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚና መሰል ጥያቄ ያነገቡ ኃይሎች በየቦታው የትጥቅ ትግል ያካሂዱ ነበር።

ደርግ በዚህ መልኩ ከተገረሰሰ በኋላ ኢህአዴግ መጥቶ ሥልጣኑን ተቆጣጠረ። ይሁንና እሱም ያመጣው ለውጥ የለም። የተነሱትን የሕዝብ ጥያቄዎች መመለስ አልቻለም። በርግጥ ኢህአዴግ ክልል በማደራጀት የማንነት ጥያቄን ለመመለስ ሙከራ አድርጓል። እሱም ቢሆን ክልል ማደራጀት እንጂ አውነተኛ ፌዴራሊዝም መፍጠር አልቻለም። በወቅቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ነበሩ፤ ሞትና መፈናቀልም ነበር። በተለይም ራሳችንን በራሳችን የማስተዳደር መብታችን ይከበር የሚሉ ጥያቄዎች ጎልተው ይደመጡ ነበር። ኢህአዴግም ቢሆን ትርጉም ባለው መልኩ ለዴሞክራሲ እና ለማንነት ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጠም።

ክልሎች ይተዳደሩ የነበረው በሞግዚት ነበር። የሚዲያ ነፃነትም የታፈነ ነበር። የፖለቲካው ምህዳር ምቹ ባለመሆኑ ወደ ብጥበጥ የተገባበት ሁኔታ ነበር። እነዚህ ጥያቄዎች ለለውጡ መምጣት አንደ ገፊ ምክንያት መሆን ችለዋል። የለውጡ መምጣት አይቀሬ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሕዝባዊም ነበር። ለውጡ የፓርቲም ጭምር ነበር።

የሀገራችን ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ገብቶ ነበር፤ ሀገር ሊበተን ጥቂት ጊዜ ቀርቶት የነበረ ወቅት ነው። የሀገራችን ኢኮኖሚ ዜሮ ደረጃ የመጣበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። የውጭ ምንዛሬ የለም ማለት ይቻልም ነበር። የዓባይ ግድብን ጨምሮ የአምራች ኢንዱስትሪ ግንባታ ፕሮጀክቶች ችግር ውስጥ ገብተው ነበር።

የኢኮኖሚ፣ የሰላም እጦት፣ የዴሞክራሲ ችግር፣ እራስን በራስ የማስተዳደር ችግር፣ የማንነት ጥያቄ ለለውጡ መምጣት ተጠቃሽ ገፊ ምክንያቶች ነበሩ። ከዚህ ጎን ለጎን ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ነበሩ። በጥቅሉ ለውጡ በሚካሔድበት ጊዜ ብዙ ሀገራዊ ተግዳሮቶች ነበሩ።

ብልፅግና ወደ ሥልጣን ሲመጣ ጥያቄዎቹን በአግባቡ ለይቶና ከሕዝብ ጋር ተወያይቶ ወደሥራ መግባቱ ስኬታማ አድርጎታል። በዚሁ መንገድ ከሠራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ወይም እውነተኛ ፌዴራሊዝምን ሥራ ላይ ማዋል ነው።

ጥያቄው የሕዝብ ነበር፤ የእውነተኛ ፌዴራሊዝም ጥያቄ የነበራቸው ክልሎች ነበሩ። በተለይም በደቡብ ክልል አካባቢ ጥያቄው ሰፊ ነበር። ሲዳማ ይሄ ጥያቄ ነበረውና ለመመለስም ጥረት ተደርጓል። ሌሎችም የክልል እንሁን ጥያቄዎች በተመሳሳይ ምላሽ እንዲያገኙ ተደርጓል።

ይህ ሥራ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን በትክክል የተተገበረበት ስለሆነ ብልፅግና የሚኮራበት ነው። አዳዲስ ክልሎች ተዋቅረው ራሳቸውን ማስተዳደር መቻላቸው እንደ አንድ ድል አድርገን የምንቆጥረው ተግባር ነው።

ሁለተኛውና ዋናው ነገር ቀደም ባለው ጊዜ በክልል ተደራጁ የተባሉ ሌሎችም ክልሎች አደረጃጀታቸው እውነተኛ ፌዴራሊዝም ላይ የተመሠረተ አልነበረምና፤ የሚተዳደሩት በሞግዚት ነበር። በአሁኑ ወቅት እሱ ቀርቶ ክልሎች ራሳቸውን ችለውና ሕዝባቸውን አስተባብረው በራሳቸው የመልማቱን ሂደት ተያይዘዋል። ይህ ለፓርቲው እንደ ትልቅ ድል የሚቆጠር ነው።

ሶስተኛ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ምህዳር መስፋቱ ነው። ቀደም ሲል የዚህ ሀገር ዜጋ ሆነው ሳሉ የራሳቸውን አመራርና ኃላፊ ለመምረጥ እድሉ ያልነበራቸው ክልሎች ነበሩ። ለምሳሌ አጋር የነበሩት ሱማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ እንዲሁም ጋምቤላና ሐረሪ ክልሎችን መጥቀስ ይቻላል።

ይህ ማለት ከሩዋንዳው ፓትሪዮቲክ ፓርቲ ከቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ወይም ከደቡብ አፍሪካው ኤኤንሲ የተለዩ አይደሉም። ኢህአዴግ ጉባኤውን ሲያካሂድ ይመጣሉ፤ የአጋርነት መልዕክት ያስተላልፋሉ። የመመረጥ ሳይሆን የመምረጥ መብትም ያልነበራቸው ነበሩ።

ዛሬ ግን ይህ የዳር ፖለቲካ ቀርቶ ወደ መሃል የመምጣት እድል በሰፊው ተፈጥሯል። ይህ ብልፅግና ፓርቲ የሚኮራበት ሌላኛው ድል ነው። ብልፅግና ለውጬዋለሁ   ብሎ አፉን ሞልቶ ከሚናገራቸው አንዱና ትልቁ ይህ ነው። ቀደም ሲል አጋር ተብለው ከነበሩ ክልሎች የተወከሉ ዛሬ የፓርቲያችን ምክትል ፕሬዚዳንት መሆን የቻሉ አሉ። ይህ ፓርቲያችን ምንጊዜም የሚኮራበት ትልቅ ድል ነው። እኩልነትን በተግባር ያረጋገጠ ብቸኛ ፓርቲ ቢኖር ብልፅግና ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ለውጡን ለማደናቀፍ እና ለመበተን ጥረት ሲደረግ ነበር። ብልፅግና ይህን ማስቀረት ችሏል። ሌላው ኢኮኖሚው ላይ የተሠሩ ሥራዎች የገዘፉ ናቸው። የብልፅግና ፓርቲና መንግሥት ሀገር ሲረከብ ደመወዝ መክፈል የማይቻልበት፤ መድኃኒትም ሆነ ነዳጅ መግዛት ያልተቻለበት ሁኔታ ላይ ነበር። የውጭ ምንዛሬ ክምችት ሥጋት ውስጥ ገብቶ የነበረበት ጊዜ ነበር፤ በጥቅሉ ሀገር ሀገር ሆና የመቀጠል ደረጃዋ ተሟጥጦ ያለቀበት ወቅት ነበር።

ይህንን እውነታ ለመቀልበስ በመጀመሪያ ደረጃ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በመቅረጽ ብዝሀ ኢኮኖሚ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ችሏል። የስንዴ ልመና ታሪክ ተቀይሯል። በአሁኑ ወቅት ስንዴ አምርተን ለራሳችን ፍጆታ አውለን ወደ ውጭ ሀገር መላክ ጀምረናል። ይህ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው።

ከዚህ በተጨማሪ አረንጓዴ ዐሻራ ላይ በሰፊው ሥራ ተሠርቷል። ቡና፣ ሩዝ፣ ወርቅ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ የኮሪዶር ሥራዎች በአግባቡ እየተሠራባቸው ያሉ ሥራዎች ናቸው። ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በስፋት እየተሠራ ነው። በምርጫ ሕዝባዊና ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዲመረጥ ተደርጓል። በዲፕሎማሲውም መስክ በዚያው ልክ ከተሠራባቸው ሥራዎች ውስጥ የሚነገርለት ሥራ ነው፤ ይህ ትልቅ ድል ነው ማለት ይቻላል።

በተለይም በዲፕሎማሲው ረገድ ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገራት በሚል ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ላይ ተሠርቷል። ከጎረቤት ሀገሮች ጋር ያለን ግንኙነት እንዲሻሻል ተደርጓል።

የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል። የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ ተደርጓል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል። የሽግግር ፍትህን እውን ለማድረግ እየተሠራ ነው። የዜጎች አንድነትና ትብብር እንዲፈጠር ተደርጓል።

እውነት ለመናገር በብልፅግና የተሠሩ ሥራዎች በብዙ መልኩ 20 እና 30 ዓመታት ያስቆጠሩ ፓርቲዎች ከሠሩት ሥራ ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን መጥቀም ያስቻለ ነው። ሊነገርላቸው የተገቡ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል።

አዲስ ዘመን፡የብልፅግና ፓርቲ ሕዝብን ያማረሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በምስለ ተገልጋይ አጥንቶ በርካታ ጉድለቶችን መለየቱ ይታወቃል፤ ግኝቱን ተመርኩዞ የወሰደው ማስተካከያ ምንድን ነው?

አቶ አወሉ፡በነገራችን ላይ አንደኛው ጉባኤችንም ትኩረት አድርጎ ያስቀመጠው አቅጣጫ አንዱ መልካም አስተዳደርና አገልግሎት የማሻሻል ሥራን ነው፤ በሁለተኛው ጉባኤም በተመሳሳይ መንገድ አቅጣጫ ተቀምጦለታል።

ፓርቲያችን ሰው ተኮር ነው፤ እያንዳንዱ የምናደርጋቸው ነገሮች ሁሉ ሕዝብን ማዕከል ማድረግ አለባቸው የሚል የጸና እምነት የተያዘባቸው ናቸው። መንግሥትም ያለው እምነት ይኸው ነው።

ከመልካም አስተዳደር አኳያ ያሉት ችግሮች ምንድን ናቸው? በሚል ችግሮችን የመለየት ሥራ ፓርቲያችን ሠርቷል። የመልካም አስተዳደር ጉዳይ በሀገርም በክልልም ደረጃ ቁጥር አንድ የፖለቲካ አጀንዳ እንዲሆን ብልፅግና ይፈልጋል።

በየደረጃው ያለው አመራር አገልግሎት ሰጪ አመራር እንዲሆን አቅጣጫ ተቀምጧል። ለዚህ የሚሆኑ አሠራሮች ተዘርግተዋል፤ ስታንዳርዶች ወጥተዋል፤ አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆኑ ተደርጓል። በባለጉዳይ ቀን ቢያንስ አመራሮች በሳምንት ሶስት ጊዜ ቢሮ እንዲውሉ ተደርጓል። ሚዲያዎቻችንም የሕዝብ ድምጽ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በዚህ ልክ ለውጥ አምጠተናል ወይ ከተባለ፤ በጸጥታ ላይ፣ በኢኮኖሚ ላይ፣ በዲፕሎማሲ ላይ፣ ከተረጂነት ለመላቀቅ ባደረግነው ትግል እና ባገኘነው ውጤት ልክ ውጤት አላገኘንም። አሁንም ድረስ ሌብነቱ አለ። ሰውን ማመላለሱ አለ፤ አድርባይነት አለ፤ ስታንዳርዶችን ያለመጠበቅ ሁኔታ አለ። ግልጽ ሆኖ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ያለመሥራት ችግር አለ። ይህን ገምግመናል። ችግሩንም ለይተን በብዙ አመራሮች እና ሠራተኞች ላይ ርምጃ ወስደናል።

ባለፈው አራት ዓመታት ውስጥ ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ከ80 ሺ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ርምጃ ወስደናል። ከሥራ ቦታ አንስተናል፤ እንዲሰናበቱም አድርገናል። ለሕግ አቅርበናል። ከደረጃ ዝቅ አድርገናል። ይህ አንድ ትልቅ ርምጃ ነው ማለት ይቻላል።

ከዚህም በላይ ደግሞ በተለይ አዲሱ የቀበሌ አወቃቀር ወደታች እንዲወርድ አድርገናል። ይህ ሁሉ አገልግሎትን ወደ ሕዝብ ከማቅረብና የተሳለጠ ከማድረግ አንጻር የሚታይ ሥራ ነው ። የቀበሌም አዲሱ አደረጃጀት ዋና ዓላማና ተልዕኮ ሕዝቡ ከመኖሪያ አካባቢው ሳይርቅ እዛው በአካባቢው አገልግሎቱን እንዲያገኝ ታስቦ የተሠራ ነው። በዚህም ትልቅ ለውጥ መምጣት ችሏል።

ይሁንና አሁንም ቢሆን የሕዝብ ሮሮና ጩኸት አለ። አሁንም በአገልግሎት አሰጣጡ አመራር ቢሮ ያለመገኘት ሁኔታ አለ። በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አሁንም ፈጣን አገልግሎትን ያለመስጠት ሁኔታዎች አሉ። ይህንንም እየገመገምን በየጊዜው ተከታትለን ርምጃ የምንወሰድ ይሆናል። ምክንያቱም የመልካም አስተዳደር ሁኔታ የፓርቲያችን ቁጥር አንድ አጀንዳ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡ከሁለተኛው የብልፅግና ጉባኤ በኋላ ፓርቲው ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራባቸው አንኳር ጉዳዮች ምን ምን ይሆናሉ?

አቶ አወሉ፡ብልፅግና ከሁለተኛው ጉባኤ በርከት ያሉ ውሳኔዎችን እና አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ ሰላምን ማረጋገጥና ማጽናት ነው። ለውጡን ለማደናቀፍ ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። ለውጡን የሚቃወሙ ኃይሎች የበላይነትን የለመዱና የዘረፉ ኃይሎች ናቸው።

እነዚህ ኃይሎች ከውስጥም ከውጭም በጋራ ሆነው በመደራጀት ለውጡን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ነገር ግን በሕዝብ የጋራ ርብርብ ጥረታቸው ሊመክን ችሏል።

ሁለተኛው ሪፎርም ከተደረገባቸው ዘርፎች ዋነኛው እና ቀዳሚው የሴክተር ሪፎርም ነበር። ለውጡ ራሱ የሕዝብ ከመሆኑ አንጻር ከሕዝቡ ጋር በመሆን እኩይ አስተሳሰብ ያላቸውን አካላት ዓላማቸውን ማምከን ተችሏል።

በአራቱም አቅጣጫ የታጠቁ ኃይሎች አሉ። በምሥራቁ በኩል አልሸባብ፣ ሰሜኑ የሚታወቅ ነው፤ በሰሜን ምሥራቅ ጽንፈኛው ፋኖ አለ ፣ ኦሮሚያ ውስጥም ሸኔ አለ። እነዚህ ኃይሎች ከውስጥ እስከ ውጭ በጋራ ሆነው በመደራጀት ለውጡን ለመቀልበስ ተንቀሳቅሰዋል።

ሰላም የማምጫ አንዱ መንገድ የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ መሥራት ነው፤ በዚህ በኩል ረጅም ርቀት ተሄዶበታል። ለዚህ ፈቃደኛ ባልሆኑት ላይ የሰላም ማስከበር ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም አንጻራዊ ሰላም ተገኝቷል። ከዚህ በኋላ ይህን ሰላም ማጽናት ያስፈልጋል። ዜጎቻችን በሰላም ወጥተው በሰላም መግባት መቻል አለባቸው።

ሌላው ከልማት አንጻር የተቀመጠ አቅጣጫዎች አሉ። ከሁሉ በላይ ዋናው አጀንዳ ልማት ነው። የተያዘው አቅጣጫ ቢኖር ይህን በደንብ አጠናክረን መቀጠል አለብን የሚል ነው። የጀምርነው የግብርና ልማት አለ። በምግብ ምርት ራስን የመቻል አቅጣጫ አለ። የተለያዩ ኢንሼቲቮች አሉ። ኢትዮጵያ ታምርት በሚል የተጀመረ ኢንሼቲቭ አለ። እነዚህን ሥራዎች ሳናሰልስ አሁን እየሠራን ባለው ልክ መሥራት ይጠበቅብናል፤፡

በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቁን፤ አምስተኛ ኢኮኖሚ ገንብተናል፤ ኢኮኖሚያችን ከምሥራቅ አፍሪካ አንደኛ፣ ከሰብ ሰሃራ ደግሞ ሶስተኛ ኢኮኖሚ ነው። በ2024 ኢትዮጵያ የአፍሪካ ብልፅግና ተምሳሌት ትሆናለች የሚለውንና በ2040 ደግሞ የዓለም የብልፅግና አርዓያ ትሆናለች የሚል ርዕይ አስቀምጠን እየሠራን ነው። ይህንንም እናሳካዋለን። ለዚህ ደግሞ በጣም ጥሩ የሆኑ ጅምሮችና ምልክቶች አሉ። ይህን አጠናክረን እንቀጥላለን።

ሶስተኛው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው፤ በዘርፉ የሚሰሙ ሮሮዎችና ጩኸቶች አሉ። ከዚህ አልፎ ቁጣዎችም አሉ፤ ይህን ማስተካከል አለብን። ለዚህም ቴክኖሎጂን በአግባቡ መጠቀም አለብን። በተቀመጠው አቅጣጫ የማይሠሩ ካሉ ርምጃ መውሰድ አለብን የሚል አቅጣጫም አለ።

አዲስ ዘመን፡በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል የሰላም ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ቀጣይ ሥራዎችስ ምንድን ናቸው?

አቶ አወሉ፡በመጀመሪያ ነገሮችን አንጻራዊ በሆነ መልኩ ማየት ይኖርብናል። በነገራችን ላይ በአሁኑ ወቅት ዓለም ጦርነት ላይ ይገኛል። የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት የሁለቱ ሀገሮች ጦርነት ብቻ አይደለም። ምዕራቡና ምሥራቁ ጎራ ለይቶ ዩክሬንን የጦር አውድማ አድርጎ እየተፋለመ ነው።

ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ መካከልም ሊፈነዳ የደረሰ የጦርነት አዝማሚያ አለ። በቻይና እና በታይዋን መካከል ተመሳሳይ የሆነ ምናልባትም አንድ ቀን ብቻ የቀረው ጦርነት አለ። በእስራኤልና ፍልስጤም በኩል ያለው ሁኔታ የሚታይ ነው። በሶሪያም ሆነ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ያለው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። ከሁለትና ሶስት ወር በፊት ኬንያ አካባቢ የነበረው ነገር የሚዘነጋ አይደለም። በአጠቃላይ ዓለም ጭንቅ ላይ ናት ማለት ይቻላል።

የእኛም ከዚህ የተለየ አይደለም። የእኛን የተለየ የሚያደርገው ነገር ቢያንስ ጦርነትን አስቀርተነዋል። የተያዘው ዓላማ ሀገርን ማተረማመስና ማፍረስ ነበር። ሌላው ቀርቶ በሀገራችን ሰሜኑ አካባቢ የተደረገው ጦርነት ከዚህ የተለየ አልነበረም ። ቢያንስ ሕዝብ ብዙ እንዳይፈናቀል እና ንብረትም ብዙ እንዳይወድም አድርገናል።

ካርቱምን ስናይ በአሁኑ ወቅት ወድማለች ለማለት ያስደፍራል። በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ትግራይ፣ አማራ እና አፋር የተደረገ ጦርነት ቢኖርም፤ የሕልውና ዘመቻው ኃላፊነት በተሞላበት ሁኔታ የተካሄደ በመሆኑ ብዙ ውድመቶችን ማስቀረት አስችሏል።

በኦሮሚያ ደግሞ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ወለጋ አካባቢ፣ ወደ መሃል ሀገር ደግሞ ሰሜንና ምዕራብ ሸዋ አካባቢ፣ ምሥራቅ ደቡብ ሸዋና አርሲ አካባቢ፣ ሁለቱ ጉጂና ቦረና አካባቢ ብዙ ጦርነቶች ነበሩ። ጦርነቶቹን ወድመት እንዳያስከትሉ፣ ተፈናቃይ እንዳይበዛ ፣ ከተፈናቀለም በቶሎ ወደ አካባቢው የሚመለስበትን ሁኔታን ባመከለ መልኩ መቀልበስ ተችሏል። እየተዋጋን፤ እየሞትን እና እየቀበርን ልማቱን ማስቀጠል ተችሏል።

በጦርነት ወቅቶች የግብርና ግብዓት እንዳይቋረጥ፣ ማሕበራዊ አገልግሎቶች፤ የጤና፣ ትምህርት፣ የሕዝብ አገልግሎት እንዳይቋረጥ የማድረግ ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህ ዙሪያ ተሳክቶልናል ብለን መናገር እንችላለን።

እኛ ከሰላሙ አኳያ ተሳክቶልናል ብለን እንወስዳለን፤ ብዙዎቹ ለሰላም ጥሪው ምላሽ በመስጠታቸው ጠመንጃቸውን አስቀምጠዋል። በዚህም ጥሩ ውጤት ተገኝቷል። የኦሮሚያ ሰላም በአሁኑ ሰዓት ከውጭ እንደሚወራው አይደለም፤ በርግጥ መንገራገጩ አለ። የተወሰኑ ግጭቶችም አሉ። አንዳንድ ተላላኪና ጸረ ሰላም ኃይሎች መንገድ ላይ የሆኑ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ንጹሃን ዜጎች ላይ የሽብር ተግባር ይፈጽማሉ፤ ይግድላሉ፤ ይዘርፋሉ፤ ያፍናሉ፤ ያግታሉም።

ነገር ግን ቅንጅት በመፍጠር የሕዝባችንን ደኅንነት ከማረጋገጥ አንጻር ትርጉም ባለው ደረጃ ለውጥ ማምጣት እየቻለን ነው። በቅርቡ ደግሞ የቀረው ሥራ የሚስተካከል ይሆናል። በዚህም ኦሮሚያ ሙሉ በሙሉ ሰላም ትሆናለች።

አዲስ ዘመን፡ኢትዮጵያን ከተረጂነት በማላቀቅ ወደ ታላቅነቷ ለመመለስ በኦሮሚያ ደረጃ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ምን ይመስላሉ?

አቶ አወሉ፡እውነት ለመናገር ተረጂነት ውርደትን የሚያከናንብ ነው። በሌላ ሀገር መረዳት ማለት ሀገራዊ ውርደት ነው። ምክንያቱም በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር ሰፊ መሬት አለን። በገጸ ምድርና በከርሰ ምድር በቂ የሆነ ውሃ አለን። ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ የምትባል ሀገር ነች። ሌሎች ሀገሮችን ኬንያን፣ ሶማሊያን፣ ግብጽን ጨምሮ ውሃ የምናቀርብላቸው እኛ ነን።

ከዚህ በተጨማሪ የአየር ጸባዩ ምቹ፣ 13 ወር ሙሉ ፀሐይ የሚወጣባት ሀገር ስንዴ ስትለምንና ስንዴ ስትገዛ ማየት ውርደት ነው። ብልፅግና ይህን ዓይነቱን ነገር ለውጧል፤ ለመለወጥም ከያዛቸው ወርቃማ ከሆኑ ፖሊሲዎች አንዱ ይህ ነው።

ሰው እጅ እግር እያለውና በሀገሩ ምቹ የሆነ መሬትና ውሃ እያለ ለሴፍትኔት የሚሰለፍበት ሁኔታ አለ። ይህን ዓይነቱ አመለካከት ዝቅጠትና ውርደትን ካለመጠየፍ የሚመጣ ነው። ይህን አመለካከት ለመቀየር በመንግሥት በኩል ጥናት ተደርጎ ወደታች እንዲወርድ ተደርጓል። የውርደትን ታሪክ ለመቀየር፤ የልማት አቅሞቻችንን በሙሉ አሟጠን መጠቀም አለብን በሚል ተነሳሽነትን ወስደን ወደሥራ ገብተናል። በዚህም ስኬታማ ተግባራትን አከናውነናል።

የመጀመሪያ ሥራችን የልየታ ነው፤ በሴፍትኔት ውስጥ የሚረዳው የኅብረተሰብ ክፍል እውነት ትክክለኛ ተረጂ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለውን ስናጠና እና ስንለይ ከ70 በመቶ በላይ በየወሩ ተረጂ ነኝ ብሎ የሚሰፈርለት በትክክል ተረጂ ያልነበረውን አካል አግኝተናል። ምክንያቱም ይህ 70 በመቶው የኅብረተሰብ ክፍል መሬት፣ ሀብትና ጤንነት ያለው ፤ መሥራት የሚችል መሆኑን አጣርተን የደረስንበት ነው።

ሴፍቲኔት በመሠረቱ ከተረጂ ሕዝብ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም። በመሐል ካለው ሌባ አመራር ጋር የሚነካካ ጭምር ነው ። ከነዳጅ፣ ከውሎ አበል ጋር በተያያዘ ለችግር የተጋለጠ ነው። ለዚህም ነው ማን ነው ሴፍትኔትን እየተጠቀመ ያለው በሚል የልየታ ሥራ ለመሥራት የተገደድነው።

በፕሮግራሙ ከታቀፉ ከ70 በመቶ በላይ ሰዎች ከፕሮግራሙ እንዲወጡ ተደርጓል። አለ አግባብ እየተጠቀሙ ያሉትንም የለያቸው ሕዝቡ ራሱ ነው። በዓመት ከ30 እስከ 40 ኩንታል ምርት ድረስ እያመረተ የሚያስገባ ሰው ሁሉ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ሆኖ ተስተውሏል። ይህን በማስቆሙ በኩል የተሳካ ሥራ ተሠርቷል።

ሁለተኛው ደግሞ በየጊዜው ድርቅ ሆነ ጎርፍ ይከሰታል። ወረርሽኙም እንዲሁ ይመጣል። ለዚያ ዓይነት አደጋዎች መዘጋጀት የግድ ነው። ለመዘጋጀት እንደ ክልል የቡሳ ጎኖፋ ሥርዓት አቋቁመናል። ሕዝቡ በዚህ ሥርዓት ውስጥ በፍላጎቱ እንዲሳተፍ፤ አነስተኛ የገንዘብ መዋጪ እንዲያደርግ እየተሠራ ነው።

ሌላው ዝም ብሎ የተቀመጠ መሬት አለ፤ እሱ መታረስ አለበት። መሬቱን የማረስ አቅጣጫ ተከትለናል። ባለፈው ዓመት 43 ሺ ሄክታር መሬት ለማረስ አቅደን ከተማሪዎች ምገባ ጋር በተያያዘ ከሞላ ጎደል ከ 15 ሺ ሔክታር በላይ መሬት ለማረስ ችለናል። በአሁኑ ወቅት ምርቱን እየሰበሰብን ነው። በዚህም ችግርን በራሳችን አቅም የመጋፈጥ አቅም መፍጠር እየቻልን ነው።

ትልቅ ሕዝብና ታላቅ ሀገር ሆነን በድህነት ምክንያት እጃችን እንዲጠመዘዝ መፍቀድ የለብንም። ሌሎች እጃችንን ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ ከሆነ ሉዓላዊነታችን ይገፈፋል። የምንለምን ከሆነ ደግሞ ለማኝ ሲጀመርም ክብር የለውም፤ አይኖረውምም። የምንለምን ከሆነ የምናዋርደው የሀገራችንን ክብር ነው። ይህን መቀየር አለብን። በዚህ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ችለናል።

በአሁኑ ወቅት ሰው ተፈናቅሎ በየቦታው እንዳይኖር ለማድረግ በኦሮሚያ ደረጃ በብዙ ተሞክሯል። ቀደም ሲል በክልሉ የነበረው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃይ ነበር ፤ በአሁኑ ወቅት ወደ 987 ሺ አካባቢ የሚደርስ ተፈናቃይ ወደቀዬው እንዲመለስ ተደርጓል። መሬት እንዲያርስና የራሱን ሕይወት እንዲመራ እየተደረገ ነው።

በተለይ ቆላማ የሆነ ቦታ እና ሁልጊዜ ድርቅ የሚያጠቃው አካባቢ ላይ መለስተኛ ግድቦች ሠርተናል፤ ውሃ በመያዙ ልማት ተጀምሯል። ከሞላ ጎደል በራሳችን አቅም ራሳችንን ለመቻል ጥረት በማድረግ ላይ ነን።

እንደ ከዚህ ቀደሙ ችግር መጥቶ ጠራርጎ የሚወስደን ዓይነት ሁኔታ ላይ ሳይሆን መመከት የሚያስችለንን አቅም ገንብተናል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የከብት መኖ የማዘጋጀት ሥራ ተሠርቷል። ድርቅ እንኳ ቢከሰት ሁለትና ሶስት ዓመት ማቆየት የሚያስችል መኖ አዘጋጅተናል። በየዞኑና በየወረዳው የራሳችን ማከማቻ እንዲኖረን ጥረት ተደርጓል። ይህ በእኛ በኩል ትልቅ ለውጥ ነው ብለን ወስደናል።

ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር የተደረገው ጥረት በተለይ ደግሞ ከኢኮኖሚ ሪፎርሙ ጋር ተያይዞ ትልቅ ለውጥ መምጣት ችሏል። በአሁኑ ወቅት ከእራሳችንም አልፈን ሌሎችንም እየረዳን እንገኛለን።

ለአብነት ያህል ለትግራይ ክልል ከጦርነቱ በኋላ በርካታ ድጋፍ አድርገናል። በጎፋ የመሬት መንሸራተት ወቅት እንዲሁ ያደረግነው ድጋፍ ከፍተኛ ነው። ሌሎች በርካታ ድጋፎችንም በማድረግ ላይ ነን። ከጎረቤት ክልሎችም ጋር ያለን አጋርነት ይበል የሚያሰኝ ነው።

አዲስ ዘመን፡ከለውጡ ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በጤና፣ በትምህርት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃ፣ በመንገድና በሌሎች መሠረተ ልማቶች ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎች ምን ይመስላሉ ?

አቶ አወሉ፡ከመሠረተ ልማት አንጻር እንደሚታወቀው ሪፎርማችን ብዝሀ ኢኮኖሚ ነው። ከሞላ ጎደል የሕዝብ ጥያቄ ያለባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም ውስጥ ውሃ፣ መብራት፣ መንገድ፣ የትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ጤና ኬላ፣ ሆስፒታል እና ሌሎችም አሉ። እነዚህ መገንባታቸው ብቻ ሳይሆን ግብዓትም ጭምር የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ምክንያቱም ሆስፒታል ወይም ትምህርት ቤት ተገንብቶ ግብዓት የማይኖራቸው ከሆነ ትርጉም አይኖራቸውም።

በኦሮሚያ ላይ ትኩረት ያደረግነው ሰው መቅጠሩን ማቆም ነው። ስለሆነም በደመወዝ ክፍያ የሚያልቅ ነገር የለም። በሌላ በኩል ኢኮኖሚው ላይ ጥሩ የሚባል ሥራ ሠርተናል። ይህን በማድረጋችንም ገቢያችን ተሻሽሏል። ለምሳሌ ከአምስት ዓመት በፊት ለውጡ የተጀመረ አካባቢ የኦሮሚያ ክልል ገቢ ወደ 14 እና 15 ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር። ዛሬ ላይ ግን የኦሮሚያ ክልል ገቢ ወደ 205 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል።

ይህ ሲሆን አንድም የደመወዝ ጭማሪ አላደረግንም። አንድም የውስጥ እድገት አልፈቀድንም። ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቁንን የመኪና ዓይነት ጥያቄዎችን ማስተናገድ አቁመናል። ስለዚህ ትኩረት ያደረግነውና ገንዘቡን ያዋልነው ለሕዝብ አገልግሎት ነው።

የመጀመሪያው የለውጡ ሁለተኛ ዓመት አካባቢ ያስመረቅነው ወደ አራት ሺ ፕሮጀክቶችን ነው። በዚህ ውስጥ የውሃ፣ መብራት ፕሮጀክቶችም አሉ፤ ሁለተኛ ዓመት ላይ ያስመረቅነው ወደ 11 ሺ ነበሩ፤ ሶስተተኛው ዓመት ላይ ደግሞ 20 ሺ አካባቢ ፕሮጀክት ናቸው። አራተኛው ዓመት ላይ ወደ 19 አካባቢ ናቸው። ባለፈው ዓመት ደግሞ ወደ 20 ሺ ፕሮጀክት ያስመረቅን ሲሆን፣ በጥቅሉ ከ75 ሺ ፕሮጀክቶች በላይ ተመርቀው ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት ሆነዋል። ፕሮጀክቶቹ በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶችና የሕዝብን አቅም በመጠቀም እውን ያደረግናቸው ናቸው።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ መሟላት የተገባቸውን ሁሉ ያሟሉ ከ17 ሺ በላይ መዋዕለ ሕፃናት ተገንብተዋል። እነዚህን ትምህርት ቤቶች የገነባናቸው በሕዝብ አቅምና ጉልበት ነው። ከዚህ በተጨማሪ የድሃ እናቶችን ቤት አድሰናል። ሁሉም ሠርቶ መብላት የማይችል በመሆኑ የማዕድ ማጋራት ጉዳይም አለ። በዚህ መስክ የሠራናቸው ሥራዎች ትልቅ ስኬት ናቸው ተብለው የሚወሰዱ ናቸው።

ብዙዎቻችን እንደምናውቀው ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶችን ለመሥራት ሲታሰብ ይደረግ የነበረው በየቦታው የመሠረት ድንጋይ እያስቀመጡ መሄድ ነበር። በአሁኑ ወቅት እንደ እሱ ዓይነት ታሪክ በብልፅግና ዘመን ተቀይሯል። ብልፅግና የሚያደርገው የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጥ ሳይሆን ሥራውን አጠናቅቆ ሪቫን መቁረጥ ነው።

እንዲያው በብልፅግና ባሕል ፕሮጀክት ሲጀመር ንግግርም የለም። አሁን ያለን ፖሊሲ በፕሮጀክቶችም ሆነ በሕዝብ መሠረተ ልማት ግንባታ ላይ እያደረግን ያለነው ሥራውን አጠናቅቀን ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እንጂ “ልገነባ አስቤአለሁ፤ ልጀምር ነው፤ ጀምሬልሃለሁ” የሚሉ ነገሮች በብልፅግና ተቀባይነት የላቸውም።

በዚህ ረገድ ብልፅግና ታሪክ ቀይሯል ማለት ይቻላል። በርካታ ሥራዎችን መሥራትም ችሏል። ከሞላ ጎደል ፕሮጀክቶች ላይ የሠራናቸው ሥራዎች ጥሩ ናቸው የሚባሉ ቢሆኑም፤ አሁንም ከሕዝብ ፍላጎት አንጻር ገና ብዙ ርቀት መጓዝ አለብን ብለን እናምናለን።

በሌላ በኩል ደግሞ የግንባታ እቃዎች የዋጋ ንረት አለ። እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹ የግንባታ እቃዎች የሚመጡት ከውጭ ነው። በተለይ ደግሞ የዩክሬንና ራሽያ ጦርነት የዓለም የኢንዱስትሪ ምርቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጥሯል። የኮሮና ቫይረስ በተከሰተበት ወቅትም እንዲሁ ኢንዱስትሪዎችን በአግባቡ እንዳያመርቱ ጫና ፈጥሮባቸው ቆይቷል። ከዚህ የተነሳ የምርት አቅርቦት ውስንነቶች ነበሩ።

አጋጣሚ በመጠቀም መክበር የሚፈልጉ አንዳንድ ራስ ወዳድ ነጋዴዎችን አሉ። ከዚህ አንጻር ከዋጋ ንረት አኳያ ጎልተው የወጡ ችግሮች አሉ። በኮንትራክተሮች ደረጃም ሆነ በመንግሥት በኩል የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ውስንነት ታይቶባቸዋል። ከተጠናቀቁም በኋላ የጥራትም ችግር የሚታይባቸው አሉ። እነዚህን እየተከታተልን የእርምት ርምጃዎችን እየወሰድን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡በኦሮሚያ የገጠር ኮሪዶር ልማቱ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ብዙ ከተሞች መግቢያ ላይ ግንባታዎች ቢፈርሱም ሥራ አልተጀመረም፤ ይህ ለምን ሆነ?

አቶ አወሉ፡የኮሪዶር ልማት ከመንግሥት ዋና ዋና ግቦች መካከል የሚጠቀስ ነው። የመኖሪያ አካባቢዎቻችንን ምቹ እና ጽዱ የማድረግ ዓላማ ያለው ነው። መንገዶቻችንን ሰፋ ሰፋ የማድረግ ዓላማ ያነገበ ነው። አዲስ አበባን ከወሰድሽ ደግሞ የአፍሪካ መዲና እና የዓለም አቀፍ የዲፕሎማት መቀመጫ የሆነች እና በርካታ ኤምባሲዎችም የሚገኙባት ከተማ ነች። ከምንም በላይ ደግሞ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ዋና ከተማ ነች።

ከተማዋ በጨለማ የተዋጠች፣ ቆሻሻ አብዝቶ የሚስተዋልባት፣ ለመግለጽ የሚያስቸግር ድህነት ውስጥ ያሉ ብዛት ያላቸው ዜጎች የሚገኙባት በመሆኗ አንገት የሚያስደፋ ነው። ይህን መቀየር አለብን በሚል ሰፊ ሥራዎች ሠርተናል። ተስፋ ሰጭ ስኬቶችም እያስመዘገብን ነው።

በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከጨለማ ወጥታ ወደ ብርሃን ተሻግራለች። ይህ የሆነው በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሃሳብ አመንጪነት ነው። ሃሳብ ማመንጨት ብቻ ሳይሆን የሚተገበር እቅድ አውጥተው ራሳቸው 24 ሰዓት እየተከታተሉ እየሠሩ እና እያሠሩ ያስመዘገቡት ውጤት ነው።

ከአዲስ አበባ በመማር በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች ተሞክሮው እንዲሰፋ በመደረግ ላይ ነው። ከዚህ በፊት ይህን ዓይነት አስደናቂ ሥራ ልምድ ለመቅሰም ይኬድ የነበረው ወደሌላ ሀገር ነበር። ዛሬ ግን በዚሁ በሀገራችን ዋና ከተማ አዲስ አበባ ላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን አስበው፣ ሠርተው በማሠራት የሀገራዊ ስኬት ታሪክ አካል መሆን ችሏል።

በዚህ ሥራ ሌላው ተጠቃሹ ጉዳይ የሥራ እድል ፈጠራ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሥራው በሚሠራበት ጊዜ የድሃ ድሃ የተባሉትን የኅብረተሰብ ክፍሎችም ቦታ ማስያዝ ተችሏል። በዚህ ውስጥ ልማት አለ፤ መንገዶችንም ለትራፊክ ፍሰት የማመቻቸት ጉዳይንም ያካተተ ነው።

እድገት ሲባል የሀገርን ገጽታ ከፍ ማድረግ ነው። እውነተኛ እንዲሆን ማድረግም ጭምር ነው። በአሁኑ ወቅት ከዚህ አንጻር ሲታይ ርግጠኛ ነኝ አዲስ አበባ ከአፍሪካ ካሉ ከተሞች ምርጥ እና ቁጥር አንድ ከተማ እንደሆነች መናገር የሚከብድ አይሆንም። ይህ ደግሞ ከብልፅግና ትሩፋቶች መካከል አንዱ የኮርዶር ልማት ያመጣው ሥራ ነውና በዚህ እንኮራለን።

የኮሪዶር ልማቱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ከሕዝብ ጋር ውይይት ማድረግ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ከዚያ አካባቢ ያለውን ሕዝብ ማንሳት ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ምትክ ቦታ መስጠት፤ በዚያም ሥፍራ መኖር የሚያስችላቸውን አመቺ ሁኔታን መፍጠር፣ መንገድ መጥረግና ወደ ግንባታ መግባት ነው። በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያም እየሠራን ያለነው የማፍረስ ሥራ ሳይሆን የግንባታ ሥራ ነው።

በዚህም በጅማና አጋሮ የተከናወኑ የኮሪዶር ልማት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው። በአሁኑ ወቅት የኮሪዶር ልማቱ በሸገር ከተማ ተጀምሯል። አዳማ አካባቢም የተጀማመሩ ነገሮች አሉ። አንዳንድ ወደኋላ በመቅረት የሰነፉ ከተሞች አሉ። እነርሱንም ወደሥራው እያስገባን ወደግንባታ ምዕራፍ የተሸጋገርንበት፤ ምናልባትም በተቻለ መጠን ክረምቱ ሳይገባ የጀመርነውን የኮሪዶር ልማታችንን ከሞላ ጎደል የምናጠናቅቅበት ደረጃ ላይ እንገኛለን። በዚህ ደረጃ ከጨለማ ወደ ብርሃን በማሸጋገር ሂደት ላይ ነን። ለዚህም በጣም ጠንክረን እየሠራን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡ሌብነትንና ብልሹ አሠራርን ማስወገድ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ኃላፊነት እንደሆነ ተጠቅሷል፤ በዚህ ጉዳይ ቁርጠኝነቱ እስከየት ድረስ ነው?

አቶ አወሉ፡በመጀመሪያ ደረጃ ቁርጠኝነት የሚባለው የሚጀምረው ከየት ነው? በመጀመሪያ ጉዳዩን አጀንዳ ከማድረግ ነው። የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የብልፅግና ዋና ምናልባትም ከሰላምና ከልማት ቀጥሎ ሶስተኛው ትልቁ አጀንዳ ነው።

ጉዳዩን አጀንዳ እና ፖሊሲ የማድረግ ነው። አሠራር የመዘርጋት ነው። በየጊዜው ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ነው። በየደረጃ ያሉ ጉዳዮችን የማረም ነው። ርምጃ የመውሰድ ነው፤ ይህን ለይተናል። በቁርጠኝነት እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች ውስጥ አንዱ እንዳልኩሽ የመልካም አስተዳደር ሥራ ነው።

ሕዝብን የሚያማርሩ ሌቦችን፣ ቢሮ የማይገኙትን፣ ተገኝተው የሚጠበቅባቸውን የማይሠሩትን፣ ውሳኔ የማይሰጡትን፣ የሕዝብን ቅሬታ የማያዳምጡትን፣ አዳምጠውም ምላሽ የማይሰጡትን አመራሮች፣ ሠራተኞችና ፈጻሚዎች የመለየት ሥራ በተለያየ መንገድ ተጠቅመን ሠርተናል።

በዚህ ሂደት ሚዲያዎችን ተጠቅመናል፤ ሕዝብንም አሳትፈናል። እንዲያርሙና እንዲታረሙም እድልም ሰጥተናል። በዚህ ውስጥ ሁሉ አስቀድሜ እንደጠቅሱት፤ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ከ80 ሺ በላይ በሚሆኑ አመራሮች እና ፈጻሚዎች ላይ ርምጃ ወስደናል። በአሁኑ ወቅት ግን እንደባለፈው ዓይነት አካሔድ ብቻ የምንሔድ አይሆንም። ትንሽ ቆንጠጥ የሚያደርግ ርምጃ የሚወሰድ ይሆናል። የሚወሰደው ርምጃ ጠበቅ ያለ ይሆናል። የጉባዔያችንም አቅጣጫ አንዱ ይኸው ነው። በቀጣዮቹ ዓመታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የሚሠራበት ጉዳይ ነው። ከዚህ አንጻር ያለው ቁርጠኝነት በጣም ከፍ ያለ ነው። ከግማሽ መንገድ በላይ ሄደናል፤ ቀሪውን ደግሞ በተሻለ ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ ድፍረትና ወኔ የምናስተካክለው ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡በኦሮሚያ ክልል በወረዳ ደረጃ የነበረው የመንግሥት አወቃቀር ወደ ቀበሌ አደረጃጀት ወርዷል ይህ አደረጃጀት ከመልካም አስተዳደር አኳያ ያስገኘው ውጤት እንዴት ይገለጻል?

አቶ አወሉ፡ይህ የመንግሥት አወቃቀር ብዙ ጠቀሜታ ያለው ነው። መዋቅር የሚከፈለው በፌዴራል፣ በክልል፣ በየዞን፣ በወረዳና በቀበሌ ነው። የቀበሌውን መዋቅር በአግባቡ ማጠናከርና ወደሥራ እንዲገባ የማድረግ ኃላፊነትና ሥልጣንን ወደታች የማውረድ ሥራ ነው ።

ቀደም ሲል በወረዳ ደረጃ የነበረውን አደረጃጀት በአሁኑ ወቅት ወደ ቀበሌ አውርደናል። ይህን ማድረጋችን በአራት ነገር ተጠቃሚ አድርጎናል። አንደኛው ለሰላም ጠቀሜታው የጎላ ነው። የቀበሌ አመራሮች የተሰጣቸው ተልዕኮ ከሕዝቡና ከሚሊሻዎች ጋር ሆነው የቀበሌውን ሕዝብ ሰላም የመጠበቅና የማስጠበቅ ነው። በዚህም ከፍተኛ የሆነ ለውጥ መመዝገብ ችሏል። አሁን የተገኘው አንጻራዊ ሰላም የቀበሌ መዋቅር እስከ ሕይወት መስዋዕት ከፍሎ የሠራቸው ናቸው ።

ሁለተኛውና ዋናው ተልዕኮ መልካም አስተዳደር ነው። ሕዝቡ ከቀዬው ርቆ ሳይሄድ አገልግሎት ማግኘት ይገባዋል። አንድ የቀበሌ ነዋሪ መታወቂያ ለማውጣት ወረዳ መምጣት አይኖርበትም። ጉዳይ ካለው ለማስፈጸም ወደ ወረዳው በመምጣት የትራንስፖርት ወጪ ማውጣትም ሆነ ጊዜውን ማቃጠል አይኖርበትም።

ወረዳ ድረስ ሔዶ አመራሩን ቢሮ ስለማያገኝ አድሮ ጉዳዩን ለማስፈጸም የሚያወጣው ወጪ ሊኖር ይችላል፤ ከዛም አልፎ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰገ አንዳንድ ሌባ አመራር ለአገልግሎቱ ጉቦ እንዲከፍል ሊጠይቀው ይችላል፤ የቀበሌ መዋቅር ያንንም ለማስቀረት የሚረዳ ነው።

የቀበሌ አመራሩ ማለትም የመዋቅሩ ተልዕኮ ልማት ነው፤ ልማቶች የሚሠሩት ቀበሌ ላይ ነው። የበጋ ስንዴ ሆነ የተለያዩ ኢንሼቲቮች የሚተገበሩት ቀበሌ ላይ ነው። አረንጓዴ ዐሻራም የሚተገበረው ቀበሌ ላይ ነው። ለዚህም በእያንዳንዱ ቀበሌ ላይ ሰባት ሰባት የችግኝ ማፍያ ጣቢያ እንዲኖር ተደርጓል።

የገበያ ትስስርም ሆነ ሎጂስቲክ እንዲሁም ሕዝብን በማስተባበር በሕዝብ ጉልበት የሚሠሩ ሥራዎች ያሉት ቀበሌ ላይ ነው። በመሆኑም መዋቅሩ ያለው ተልዕኮ ትልቅ ነው። የተገኙ ውጤቶችም ከፍተኛ ናቸው። በሕዝብ ዘንድም ተቀባይነት አግኝቷል ።

አዲስ ዘመን፡በኦሮሚያ ክልል ከግብር ግመታ እና አሰባሰብ ጋር በተያያዘ የሚሰሙ ቅሬታዎች አሉ፤ በዚህ ላይ ምን የሚሉት ነገር አለ? አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የሕዝቡ ቅሬታ እያደመጠ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አወሉ፡– ያነሳሽው ጥያቄ ልክ ነው፤ ከግብር ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች አሉ፤ የቅሬታዎቹ መነሻ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ ሌቦች ናቸው። እነዚህ አካላት ይስርቃሉ፤ ጉቦ ይጠይቃሉ። ያልተገመተውን ገምተናል ይላሉ። በውስጥ ያለው ምስቅልቅል ብዙ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ግብር ከፋዩ ዘንድም የሚታይ ችግር አለ። እኛ እንደ ሀገር ግብር መክፈል አልለመድንም። ልምዱም ሆነ ልምምዱ ገና ነው። የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ብናይ ካላቸው ጥቅል ሀገራዊ ምርት (ጂዲፒ) አኳያ የግብር አከፋፈላቸው ሲሰላ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚሰበስቡ ሀገሮች አሉ። ወደ እኛ ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ሲመጣ ግን ገና በቅጡ አራት በመቶ እንኳ መድረስ አልቻልንም። ገና ሁለትና ሶስት በመቶ ላይ ነን። ስለዚህ ግብር የመክፈል ልምምዱ ላይ ወደኋላ የቀረን ነን።

ነገር ግን መንግሥት የሚያወጣው አቅጣጫ ተከትሎ ያንን ከማስፈጸም ይልቅ የራሳቸውን ጉዳይ ሕዝቡ ላይ ለመጫን የሚሯሯጡ አሉ። እነሱን እየለየንና እየገመገምን መሔድ አለብን እንጂ እንደተባለው አሁን ያለው ግብር ጫናው በዝቶ አይደለም። ችግሩ የተፈጠረው የአሠራር ሥርዓት ክፍተቶች በመኖራቸው ነው።

ሌላው ቀርቶ አንዱ ከተማ ከሌላው ከተማ ጋር ሲነጻጸር በግብር አጣጣሉ አይመሳሰልም። እሱን ወደ አንድ የማምጣት እና ግልጽነት የመፍጠር ሥራዎች ይቀሩናል። እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግሥት ችግሩን ገምግመን የማስተካከል ሥራ መሥራት አለብን የሚል አቅጣጫ አስቀምጠን እየሄድንበት ነው።

አሁን ባለው እውነታ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ከግብር በሚጠበቀው ያህል ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም። የመጀመሪያው ችግር መሰብሰብ የነበረበት ግብር አልተሰበሰበም። ለዚህም ግብር መክፈል የማይፈልጉ ግብይትን በደረሰኝ የማያከናውኑ በርካታ ናቸው። ገዥውም አይጠይቅም፤ ሻጩም አይሰጥም። ከዚህ የተነሳ የሕዝብና የሀገር ጥቅም ችግር ላይ ይወድቃል።

ይህንን ሀገራዊ ችግር ለመሻገር የግብር አከፋፈል ባሕላችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል። ቅሬታዎች እየቀደሙ ያሉትም ለዚሁ ነው። እነሱን ተከታትለንና ገምግመን የምንደርስበትን ማስተካከያ ለሕዝቡ የምናሳውቅ ይሆናል።

አዲስ ዘመን፡ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ አወሉ፡እኔም አመሰግናለሁ።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You