
አዳማ፡– ብልፅግና ፓርቲ የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ ተረድቶና ለይቶ ወደ ሥራ መግባት መቻሉ ስኬታማ እንዳደረገው የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ አብዲ አስታወቁ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አራት ዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግር በፈጸሙ ከ80 ሺ በላይ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ርምጃ መወሰዱን አመለከቱ፡፡
አቶ አወሉ አብዲ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳስታወቁት፤ ብልፅግና ወደ ሥልጣን ሲመጣ ባለፉት ዘመናት በነበሩ መንግሥታት ይነሱ የነበሩ የሕዝብ ጥያቄዎችን በአግባቡ ተረድቶ እና ለይቶ ከሕዝብ ጋር ተወያይቶ ወደ ሥራ በመግባቱ ስኬታማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በሕዝብ ሲነሱ ከነበሩ ጥያቄዎች ውስጥ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር፤ የእውነተኛ ፌዴራሊዝም ጥያቄ አንዱ እንደነበር ጠቁመው፤ ጥያቄውን በመመለስ እውነተኛ ፌዴራሊዝም መተግባር ተችሏል ብለዋል፤ በተለይም አዳዲስ ክልሎች ተዋቅረው ራሳቸውን ማስተዳደር መቻላቸው ለፓርቲው ትልቅ ድል እንደሆነ አመልክተዋል።
ቀደም ሲል በነበረው ሥርዓት በሞግዚት ይተዳደሩ የነበሩ ክልሎች በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን ችለውና ሕዝባቸውን አስተባብረው በራሳቸው የመልማት ሂደት ውስጥ ገብተዋል፤ ይህም ለፓርቲው ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የፖለቲካ ምህዳር ሰፍቷል። ቀደም ሲል የሀገሪቱ ዜጋ ሆነው የራሳቸውን አመራርና ኃላፊ ለመምረጥ እድሉ ያልነበራቸው ክልሎች ነበሩ። ኢህአዴግ ጉባኤውን ሲያካሂድ ይመጣሉ፤ የአጋርነት መልዕክት ያስተላልፋሉ። የመመረጥ ሳይሆን የመምረጥ መብትም እንኳ የሌላቸው ነበሩ።
ዛሬ ግን ይህ የዳር ፖለቲካ ቀርቶ ወደመሃል የመምጣት እድል በሰፊው ተፈጥሯል። ይህ ብልፅግና ፓርቲ የሚኮራበት ሌላኛው ድሉ ነው ያሉት አቶ አወሉ፣ ቀደም ሲል አጋር ተብለው ከነበሩ ክልሎች የተወከሉ ዛሬ የፓርቲያችን ምክትል ፕሬዚዳንት መሆን ችለዋል፤ ይህ ፓርቲያችን ምንጊዜም የሚኮራበት ትልቅ ድል ነው ብለዋል።
ብልፅግና በኢኮኖሚው ላይ የሠራቸው የገዘፉ ሥራዎች ስኬታማ እንዳደረጉት የጠቆሙት አቶ አወሉ፤ ፓርቲው ሀገር ሲረከብ ደመወዝ መክፈል የማይቻልበት፤ መድኃኒትም ሆነ ነዳጅ መግዛት ያልተቻለበት፤ የውጭ ምንዛሪ ክምችትም ስጋት ውስጥ ገብቶ የነበረበት፤ በጥቅሉ ሀገር ሀገር ሆና የመቀጠል ደረጃዋ ተሟጥጦ ያለቀበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ይህንን ችግር ለመቀልበስ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርም በመቅረጽ ብዝሃ ኢኮኖሚ ሥራ ላይ እንዲውል በማድረግ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ለውጥ እንዲመጣ ማድረግ ችሏል። የስንዴ ልመና ታሪክ ተቀይሯል። በአሁኑ ወቅት ስንዴ አምርተን ለራሳችን ፍጆታ አውለን ወደ ውጭ ሀገር መላክ ጀምረናል። ይህ ትልቅ የታሪክ እጥፋት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ብልፅግና የታጠቁ የፖለቲካ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሀገር ቤት እንዲገቡ፤ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ አድርጓል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም፤ የሽግግር ፍትህ እውን እንዲሆን እየተሠራ ነው። የዜጎች አንድነትና ትብብር እንዲፈጠር አድርጓል። በብልፅግና የተሠሩ ሥራዎች በብዙ መልኩ 20 እና 30 ዓመታት ያስቆጠሩ ፓርቲዎች ከሠሩት ሥራ ይልቅ ሀገርንና ሕዝብን መጥቀም ያስቻለ እንደሆነም አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ባለፉት አራት ዓመታት ኦሮሚያ ክልል ላይ ብቻ ከ80 ሺ በላይ የመልካም አስተዳደርን የጣሱ አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ርምጃ መወሰዱን ያስታወቁት አቶ አወሉ፤ ከርምጃዎቹ መካከልም የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው፣ ከነበሩበት የሥራ ደረጃ ዝቅ ብለው እንዲሠሩ፣ ከሥራ ቦታ እንዲነሱ፣ እንዲሰናበቱና ለሕግ እንዲቀርቡ መደረጋቸውንም ገልጸዋል። ይህ በራሱ አንድ ትልቅ ርምጃ ነው ሲሉ አመልክተዋል።
አዲስ የቀበሌ አወቃቀር በመፍጠር አገልግሎት ወደ ሕዝብ እንዲቀርብ እና እንዲሳለጥ አድርጓል። የአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ዋና ዓላማና ተልዕኮ ሕዝቡ ከመኖሪያ አካባቢው ሳይርቅ እዛው በአካባቢው አገልግሎቱን እንዲያገኝ ታስቦ የተሠራ ነው ሲሉ ጠቅሰው፤ በዚህም ትልቅ ለውጥ መምጣት እንደቻለ ተናግረዋል።
አሁንም ቢሆን የሕዝብ ሮሮና ጩኸት አለ። አሁንም በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ ችግሮች አሉ፤ አመራር ቢሮ ያለመገኘት፣ በተቀመጠ አቅጣጫ አለመሥራትና ፈጣን አገልግሎት ያለመስጠት ሁኔታዎች አሉ። ይንንም እየገመገምን በየጊዜው ተከታትለን ርምጃ የምንወስድ ይሆናል። በዚህም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ የፓርቲያችን ቁጥር አንድ አጀንዳ ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ “ከቃል እስከ ባሕል” በሚል መሪ ሃሳብ ከጥር 23 እስከ 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም መካሔዱ ይታወቃል።
የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወሉ ጋር ያደረግነውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በወቅታዊ አምድ ገጽ ስድስት ጀምሮ ማንበብ ይችላሉ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ጥር 29 ቀን 2017 ዓ.ም