
በ1970ዎቹ ከአደግሁባት ፍኖተ ሰላም ከ20 ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት በምትገኘው ቡሬ ከተማ የግብርና ሜካናይዜሽን ማዕከል ነበር። እንዲሁም ከከተማችን በቅርብ ርቀት የብር ሸለቆ ዘመናዊ የእርሻ ልማቶች አሉ። የላይ ብርና የታች ብር እርሻ ልማቶች። በትራክተር የሚያርሱ የሚከሰክሱ፤ የሚዘሩ፣ ምርጥ ዘር የሚጠቀሙ፣ በመስመር የሚዘሩ፣ ፀረ ተባይ መድኃኒት በአነስተኛ አውሮፕላን የሚረጩ፣ ሲደርስ በኮምባይነር ምርት የሚሰበስቡ ዘመናዊ እርሻዎች አሉ።
በእነዚህ እርሻዎች አፍንጫ ስር ያሉ አርሶ አደሮችም ሆኑ በቡሬ ሜካናይዜሽን ማዕከል በቅርብ ርቀት የሚገኙ አርሶ አደሮች ግን በበሬ የሚያርሱ፣ በሰው ኃይል የሚዘሩ፣ የሚያርሙ፣ የሚኮተኩቱ፣ ሲደርስ በማጭድ የሚሰበስቡ፤ በቁም እንስሳት የሚያበራዩ ነበሩ። ዛሬም በቅጡ ከዘመናዊ ሜካናይዜሽን ጋር አልተዋወቁም። ሆኖም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይበል የሚያሰኙ ጅምሮችን እያየሁ ነው።
የግብርናው ዘርፍ ባለመዘመኑ ከዝናብ ጥገኝነት ጋር ተደምሮ ለብዙ ዘመናት በሚፈለገው ልክ ምርታማ ሳይሆን ቆይቷል:: ይህን እውነታ ለመለወጥ የግብርና ሜካናይዜሽን የአነስተኛ አርሶና አርብቶ አደር ግብርናን በማዘመን፣ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር፣ ጥራትን በማሻሻል እንዲሁም ቅድመና ድህረ ምርት ብክነትን በመቀነስ ላይ ያለውን ከፍተኛ ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለፉት ስድስት ዓመታት የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች አቅርቦትና አገልግሎት አሰጣጡን በልዩ ሁኔታ በማሻሻልና ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘሁት መረጃ ያትታል::
የግብርና ሜካናይዜሽን ስንል በግብርናው ዘርፍ የሰው ጉልበትን በማሽነሪዎች እና በመሣሪያዎች በመተካት መጠቀም ሲሆን የእንስሳት ኃይል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ ነዳጅን ወይም ታዳሽ ኃይል መጠቀምን ሊያካትት ይችላል። ቴክኖሎጂው ጉልበት፣ ጊዜንና ወጪን ከመቆጠብ አንጻር ትልቅ ሚና አለው:: ከዚህም አንጻር የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች እንዲስፋፉ እና አገልግሎቱ አርሶ አደሩ ጋር ተደራሽ እንዲሆን በቅድመ ምርት፣ ድህረ ምርት፣ የመስኖ እና የእንስሳት ቴክኖሎጂዎች ላይ በሰፊው እየተሠራ ይገኛል::
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ አቶ እሸቱ ሁንዴ እንደገለጹት፤ በግብርናው ዘርፍ ከሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ መፈቀድ ለዘርፉ መዘመን አስተዋጽኦ አበርክቷል:: መንግሥት ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ከፈቀደ በኋላ በርካታ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ገብተዋል፤ እየገቡም ይገኛሉ::
አርሶ አደሩ በስፋት ቴክኖሎጂውን እንዲጠቀም ዕድል በመፈጠሩ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ይገኛል ያሉት አቶ እሸቱ፣ በርካታ ማሽነሪዎች በዓይነትና በመጠን ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ መሆናቸውን ጠቅሰው ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪዎችም እየተፈጠሩና የኪራይ አገልግሎትም እየተበራከተ መሆኑን፤ በግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ ግብርና ተግባራዊ በተደረገባቸው አካባቢዎች ምርታማነታቸው እየጨመረ እንደሆነና በ2016/17 ዓ.ም የምርት ዘመንም አርሶ አደሩ ምርቱን በነዚህ ቴክኖሎጂዎች ታግዞ እየሰበሰበ እንደሆነም ተናግረዋል:: ለዚህ እመርታ የዘርፉ ያለፉ ስድስት ወራት አፈጻጸም በአብነት ሊነሳ ይችላል።
በአጠቃላይ በአስር ዓመቱ ስትራቴጂ እቅዳችን አሁን ካለንበት 20ሺ ትራክተር ወደ 65 ሺህ፣ ኮምባይነር ከ2700 ወደ 15 ሺህ ማድረስ እንዲሁም አርሶ አደሩ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተወካዩ አቶ እሸቱ ሁንዴ ገልጸዋል:: ግብርናውን ከማዘመን ጋር በተያያዘ በተለይም በደቡብ ኮሪያ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚገነባው የግብርና ሜካናይዜሽን የልህቀት ማዕከል አሁን ላይ ግንባታው ተጠናቆ ማሽነሪዎችን ማስገባት ላይ ሲገኝ ማዕከሉ ሲጠናቀቅ የቴስት፣ የዲዛይን፣ የጥገና እንዲሁም የሥልጠና ማዕከል ሆኖ አገልግሎት በመስጠት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ ይጠበቃል::
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) የተቋሙን ያለፉትን ስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት በዚህ ሰሞን ሲገልጹ፤ በዓመቱ ከ6 ነጥብ 1 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ እቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑን እና በግማሽ ዓመቱ በሁሉም የምርት ዓይነቶች ጥሩ ውጤት ተመዝግቧል። በምርት ዘመኑ በሦስቱም ወቅቶች በሁሉም የሰብል ዓይነቶች፣ በሆርቲካልቸር እና በጥጥ 30 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት እየተሠራ መሆኑን፤ በግማሽ ዓመቱ በበልግ እና በመኸር በሁሉም የምርት ዓይነቶች 793 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰው፤ በመስኖ ልማት በስንዴና በሆርቲካልቸር ዘርፎች ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
እንዲሁም ከቡና ምርትም በ2017 ዓ.ም እስከ አሁን ድረስ 908 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን፤ በእንስሳት ልማት እና በሌማት ትሩፋትም በዕቅዱ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃም አበረታች ዝግጅት መደረጉን፤ በአጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ እና የምግብ ዋስትናን ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎች በጥሩ አፈጻጸም ላይ መሆናቸውን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተም ከባለፈው ምርት ዘመን የተረፈ 3 ሚሊዮን ኩንታል መኖሩን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፥ አዲስ ተገዝቶ የገባ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል መድረሱ፤ ይህም ለመስኖ ከበቂ በላይ መሆኑን፤ ለበልግና ለመኸር በሂደት እንደሚገባ ተናግረዋል። የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን፤ የሚታረስ መሬት፣ በሜካናይዜሽን፣ በግብርና ኤክስቴንሽን፣ የኮሜርሻል ኩታ ገጠም እርሻ እና በሌሎችም የሚሠሩ ሥራዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን፤ የምርጥ ዘር አቅርቦትን በተመለከተ እስከ አሁን ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ መዘጋጀቱን፤ የቡና ምርት ወጪ ንግድ አሁን ከተገኘው በተጨማሪ በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ በመሥራት ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት በፖሊሲዎች፣ በስትራቴ ጂዎች፣ በሕግ ማሕቀፎች እና በመዋቅር ማሻሻያዎችን በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን፤ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በፖሊሲዎች፣ በስትራቴጂዎች፣ በሕግ ማሕቀፎች እና በመዋቅር ማሻሻያዎችን በማድረግ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን፤ በ2016/17 ምርት ዘመን የመኸር እርሻ 20.4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም 608 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅና እስካሁንም 505 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን፤ በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን ገልጸዋል።
የመኸር ስንዴ ምርትን በተመለከተ ሚኒስትር ዴኤታው እንደተናገሩት በ2011/12 የምርት ዘመን በ1.74 ሚሊዮን ሄ/ር መሬት በማልማት 48 ሚሊዮን ኩ/ል ምርት ተገኝቷል:: በ2016/17 የምርት ዘመን ወደ 3.52 ሚሊዮን ሄ/ር መሬት በማሳደግ 155 ሚሊዮን ኩ/ል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እስከሁን 101 ሚሊዮን ኩ/ል መሰብሰብ መቻሉን፤ በ2017 ዓ.ም በበጋ ወቅት 4.27 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ በማልማት 173 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ እስካሁን 3 ነጥብ 42 ሚሊዮን ሄክታር በዘር መሸፈኑን፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ባላቸው የፍራፍሬ ተክሎች ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት በ2011/12 ምርት ዘመን 90.01 ሚሊዮን የነበረውን ችግኝ በየዓመቱ በማሳደግ በ2016/17 ምርት ዘመን 540 ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኞችን በማዘጋጀት ማልማቱን ገልፀዋል::
ባለፉት አራት ዓመታት ምርትና ምርታማነትን ከሚያሳድጉ ተግባራት መካከል የተሻሻሉ አሠራሮችና የግብርና ሜካናይዜሽን በመጠቀም የተሠሩ ሥራዎች ዋንኞቹ ናቸው:: አርሶ አደሮቻችን ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ የእሴት ሠንሠለቱን ተከትለው፣ የማሳ ዝግጅትና የክስካሶ፣ በውስን ቦታዎችም ቢሆን የዘር መዝሪያ በብዛት ስለሌለ፣ የርጭትና የእንክብካቤ አገልግሎት፣ የአጨዳ የመውቂያና የፍልፈላ፣ ከውቂያ ቦታ ምርት የማጓጓዝ ሥራ በተቀላጠፈ ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎቶችን በኪራይ እንዲያገኙ በማድረግ የግብርና አጠቃቀማቸውን እንዲያሳድጉ የተቀናጀ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ይደረጋል::
በዚህም የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለመስጠት በማኅበር የተደራጁ የቴክኖሎጂው ባለይዞታዎች፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ የግል ባለሀብቶች፣ መንግሥታዊ የሆነ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪ ድርጅት፣ በ10ሩ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጪያ ማዕከላት፣ በሥራቸው የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ያደራጁ የአርሶ አደር ዩኒየኖች የግብርና ሜካናይዜሽን የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ የተደራጁ ወጣቶች፣ ለአጎራባቾቻቸው የኪራይ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ሰፋፊ እርሻ ያላቸው ባለሀብቶች፣ በተናጠልና በቡድን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የመሣሪያ ባለቤቶች እንዲሳተፉ ይደረጋል::
በተጨማሪም የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማሳለጥ የተደራጁ የዲጂታል ፕላት ፎርሞች አገልግሎት ፈላጊንና አገልግሎት ሰጪን በመረጃ ቋት በማደራጀት አገልግሎቱን የሚያገኙበትና ክፍያውንም ለአጠቃቀም ቀላል በሆነ የዲጂታል መተግበሪያ አማካኝነት የሚፈፅሙበት አሠራር ተጠናክሮ እንዲስፋፋ ሥራ በመሠራት ላይ ይገኛል:: በምርት ዘመኑ እማወራ አርሶ አደሮች የተለየ ትኩረት ተሰጥቷቸው በመረጃ ቋት ተይዘው በአገልግሎት ሰጪዎች የቅድሚያ ትኩረት አግኝተው አገልግሎቱን እንዲጠቀሙ ይደረጋል::
የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት አሰጣጡ ከባሕላዊ አሠራሩ ጋር ሲነፃፀር፣ የመሬትና የሰውን ምርታማነት እንዲሁም የሌሎች ግብዓቶች ብክነት በማስወገድና ወጪን በመቀነስ ከሄክታር የሚገኘውን ምርታማነትን ማሳደግ፣ በአጨዳና በውቂያ የሚፈጠረውን የምርት ብክነትና የጥራት መጓደልን ማስወገድ፣ በገበያ ተወዳዳሪና ተፈላጊ ዋጋውም ከፍተኛ የሆነ ምርት ለፍጆታ፣ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እና ለውጭ ገበያ የማቅረብ ዕድል መስፋት፣ የአርሶ አደሮችን ድካም መቀነስ፣ በተለይም የሴቶችን እንግልት ማስወገድ፣ ለጉልበት ሥራ ያልደረሱ ሕፃናትን ከግብርና ሥራ ማውጣትና በትምህርታቸው እንዲያተኩሩ በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በጥራትና በብዛት በማምረት የሀገራችንን ምጣኔ ሀብት ማሳደግ ነው::
የግብርናውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ሜካናይዜሽን ትልቁን ሚና ይጫወታል:: የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋት ግብርናን ለማዘመንና የምርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ግብርናውን ለማዘመን በሚደረገው ርብርብ ሜካናይዜሽን ከሌሎች የግብርና ግብዓቶች ጋር ተዳምሮ ለዘርፉ እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው::
ሜካናይዜሽን ለግብርናው ዘርፍ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ከግምት በማስገባት በጀርመን የልማት ትብብር (ጂአዜድ) እና በግብርና ሚኒስቴር በጋር የግብርና ሜካናይዜሽን ሥራዎች ላይ ያተኮረ የግብርና ሜካናይዜሽን ለባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች Agricultural Mechanization for Small holder farmers/AMS ፕሮጀክት በመተግበር ላይ ይገኛል:: ፕሮጀክቱ ከሚያደርጋቸው ድጋፎች አንዱ ለባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች ማነቆ የሆኑ የግብርና ሜካናይዜሽን ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የፈጠራ ሥራዎችን በገንዘብና በቴክኒክ መደገፍ ነው::
በዚህ መነሻነት የአርሶ አደሩን ችግር የሚፈቱ የተለያዩ የግብርና ሜካናይዜሽን የፈጠራ ባለቤቶችን ለማበረታታት ፕሮጀክቱ የገንዘብና እውቅና ሽልማት አበርክቷል:: የግብርና ሜካናይዜሽን የፈጠራ ባለቤቶቹ ከምርምር ተቋማት፣ ከግብርና ሙያ ኮሌጆች፣ ከዩኒቨርሲቲዎች እና ከግል ድርጅቶች እንዲሁም በግል ደረጃ የተውጣጡ ናቸው::
ፕሮጀክቱ የግብርና ሜካናይዜሽንን የመስፋፋት ማሕቀፍ ማሻሻል ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለፁት የፕሮጀክቱ ቡድን መሪ ፓስካል ካውምቡዞ (ዶ/ር) የአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮችን ምርታማነት ለማሳደግ የግብርና ሜካናይዜሽን ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል:: በግብርና ሜካናይዜሽን የፈጠራ ባለቤት የሆኑትን በገንዘብና በቴክኒክ መደገፍ አንዱ ሥራ መሆኑንም ተናግረዋል::
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን አማካሪ አቶ ታምሩ ሀብቴ በበኩላቸው፤ በዘርፉ የፈጠራ ባለቤቶችን በገንዘብ መደገፍና እውቅና መሰጠቱ ሥራው ወደ መሬት እንዲወርድና የፈጠራ ባለቤቶቹ የሜካናይዜሽን ልማቱን የሚደግፉበትን መንገድ ለማመቻቸት እንደሚያስችል አብራርተዋል:: የግብርና ሜካናይዜሽን ፈጠራ ባለቤት በመሆን የገንዘብ ድጋፍና እውቅና ማግኘታቸው ሥራውን ወደ አርሶ አደሩ ለማውረድ እንደሚያስችላቸውና የተሻሻሉ፣ ውጤታማና ተደራሽ የሆኑ የግብርና ሜካናይዜሽኖችን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያግዛቸው ተሸላሚዎች አመልክተዋል:: በሽልማቱ 11 የተለያዩ የግብርና ሜካናይዜሽን ፈጠራ ባለቤቶች እውቅናና ሽልማት ያገኙ ሲሆን ለእያንዳንዱ በአማካኝ እስከ 3 ሚሊዮን ብር ሽልማት ተሰጥቷቸዋል::
በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ አንዱ የግብርናው የጀርባ አጥንት ነው:: ዘርፉ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት በሰብል ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት፣ በዕፅዋት ጥበቃ እንዲሁም በግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ላይ ያተኮሩ ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል::
በግብርና ሚኒስቴር የእርሻና ሆርቲካልቸር ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ ዘርፉ የሰብል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እንደ ሀገር የተጣለውን የምግብና ሥነ-ምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ የሥራ ዕድልን የመፍጠር፣ የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ምርት የመተካት፣ የውጭ ምርቶችን አቅርቦት በመጨመር የውጪ ምንዛሪ ግኝትን የማሳደግ እና የኢንዱስትሪ ፍላጎትን የማርካት ግቦችን ለማሳካት በትኩረት እየሠራ ነው::
የሆርቲካልቸር ልማት በያዝነው የ2016/17 ምርት ዘመን እስካሁን ድረስ በመኸር ልማት 1,706,540 ሄ/ር በማልማት 210,962,604.64 ኩ/ል ምርት ማሰባሰብ መቻሉን እንዲሁም በበጋ መስኖ 752,010.41 ሄ/ር ለማልማት ታቅዶ 880,629.34 ሄ/ር መልማቱንና ከዚህም 100,350,150 ኩ/ል ምርት እንደሚጠበቅ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት የሆርቲካልቸር ልማትን በክላስተር ከማልማት አኳያ ጥሩ ጅማሮ ያለ መሆኑን፤ በያዝነው የበጋ መስኖ ልማት በክላስተር ከማልማት አኳያ ከለማው 880,629.34 ሄ/ር የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ውስጥ 38,844.88 ሄ/ር በክላስተር መልማቱን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
አትክልትና ፍራፍሬን በክላስተር ከማልማት አንፃር ሰፊ እንቅስቃሴ ካላቸው ክልሎች ውስጥ ሲዳማ ክልል 45.3 በመቶ በክላስተር በማልማት አንደኛ ሲሆን የደቡብ ኢትዮጵያና የትግራይ ክልሎች እንደቅደም ተከተላቸው በሆርቲካልቸር ክላስተር ልማት የተሻለ አፈፃፀም እንዳላቸው ገልጸው ሁሉም ክልሎች አትክልትና ፍራፍሬን በክላስተር የማልማት ሥራን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል::
ሆርቲካልቸርን በክላስተር ማልማት ለአርሶ አደሮች የግብዓት አቅርቦትን ለማሻሻል፣ የኤክስቴንሽን አገልግሎት በወቅቱና ወጥነት ባለው መልኩ ተደራሽ ለማድረግ፣ ለገበያ ብሎ ለማምረትና የገበያ አማራጭ ለመፍጠር እንዲሁም ምርትን ከሚያቀነባብሩ ኢንዱስትሪዎች ጋር ለማስተሳሰር ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን በአጠቃላይ ምርትና ምርታማነትን ያሳድጋል::
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም