እስራኤል በተኩስ አቁም ጉዳይ ውይይት የሚያደርግ ቡድን ወደ ኳታር ልትልክ ነው

እስራኤል በተኩስ አቁም ጉዳይ ውይይት የሚያደርግ ቡድን ወደ ኳታር ልትልክ መሆኑን ገለጸች። እስራኤል በጋዛ ተኩስ አቁም ስምምነት ቀጣይ አተገባበር ዙሪያ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን ወደ ኳታር ለመላክ እየተዘጋጀች መሆኗን የጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ቢሮ አስታውቋል።

እስራኤል እና ሀማስ በደረሱት ለስድስት ሳምንታት በሚቆየው የመጀመሪያ ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት መሠረት ታጋቾች በፍልስጤማውያን እስረኞች ተለውጠው የተለቀቁ ሲሆን፤ በሁለተኛው ዙር ድርድር ደግሞ ጦርነቱን በዘለቄታዊነት ያስቆመዋል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል ተብሏል።

ሀማስ ስምምነቱ ተግባራዊ በሆነበት የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ታጋቾችን የለቀቀ ሲሆን፤ እስራኤል እስከ እድሜ ልክ እስራት ፍርደኛ የነበሩ በርካታ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለቃለች። ከተለቀቁት የእስራኤል ታጋቾች ውስጥ አምስቱ ሴት እስራኤላውያን ወታደሮች ናቸው። በሁለተኛው ዙር ድርድር ሀማስ በእጁ ያሉትን ሁሉንም ታጋቾች እንዲለቅና እስራኤል ደግሞ ከጋዛ ጠቅልላ እንድትወጣ ንግግር ይደረጋል ተብሏል።

ሀማስ እስራኤል ከጋዛ ለቃ እንድትወጣና ዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ የሚፈልግ ሲሆን፤ እስራኤል በአንጻሩ ሀማስን ጨርሶ ማጥፋት የዘመቻ ግቧ እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወሳል።ሀማስ ጥቅምት እኤአ 7 ቀን 2023 በደቡብ እስራኤል ድንበር ጥሶ በመግባት አንድ ሺህ 200 ሰዎችን ከደገለ እና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ ነበር ሀሰማስና እስራኤል ወደ አጠቃላይ ጦርነት መግባታቸው ይታወቃል።

አዲስ ዘመን ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You