የትግራይ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ችግሮቻቸውን በውይይት ይፍቱḷ

የትግራይ ሕዝብ እንደሁሉም ኢትዮጵያውያን ለሀገሩ ቀናኢ፣ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር ሟች፣ በነጻነቱ እና በሉአላዊነቱ የማይደራደር በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ሕዝብ ነው፡፡ በየዘመናቱም ወራሪዎችን አሳፍሮ በመመለስ እና ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር ደሙን በማፍሰስ እና አጥንቱን በመከስከስ ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ እንድትኖር የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡

ይሁን እንጂ ላለፉት 100 ዓመታት የትግራይ ሕዝብ ባልተገቡ ጦርነቶች ውስጥ እንዲያልፍ ተፈርዶበት ቆይቷል፡፡ በረባ ባልረባው በሚነሱ ጦርነቶች የተረጋጋ ህይወት እንዳይኖር እና ኑሮውንም እንዳያሻሽል ችግር ገጥሞት ቆይቷል፡፡

ከየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢዎች በባሰ መልኩ ትግራይ በርካታ ጦርነቶችን አስተናግዳለች፡፡ እነዚህ ጦርነቶች የትግራይ ወጣቶችን ህይወት ከመቅጠፍ ባሻገር ለትግራይ ሕዝብ ይዘው የመጡት በረከት ግን አልታየም፡፡ እነዚህ ጦርነቶች ልጆቹን ከማሳጣት እና ኑሮውን ሲኦል ከማድረግ ውጪ ያስገኙለት አንዳችም ፋይዳ የለም፡፡

ሆኖም ካለፉት ጉዳቶችና ጥፋቶች ባለመማር ዛሬም ትግራይን የጦርነት አውድማ ለማድረግ የሚዳዱ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን ዛሬም በየመድረኩ ግጭትን ሲቀሰቅሱ እየተሰሙ ነው፡፡ እነዚህ ግጭት ሰባኪዎች ከትናንቱ ባለመማር ዛሬም ትግራይን ለጦርነት ሕዝቧንም ለመከራ እና ለስቃይ ለመጣል ዳር ዳር ሲሉ እየተስተዋሉ ነው፡፡

ሆኖም ይህ ሁኔታ ግን አንድ ቦታ ማብቃት አለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ በሰላም የመኖር እና የማደግ መብት እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ብልጭ ድርግም የሚለው የሰላም ሁኔታ ተሻሽሎ ዘላቂነት ባለው ሁኔታ የሰላም አየር በክልሉ ሊነፍስ ይገባል፡፡ ክልሉ ለበርካታ ዘመናት ያህል በጦርነት የተጎዳ በመሆኑ የበርካታ መሠረተ ልማት እጥረት እና የምግብ ዋስትና ችግር የሚስተዋልበት ነው፡፡

ስለዚህ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ በትግራይ ጦርነት እና ግጭት የሚጠፋ ጊዜ፣ሀብት እና የሰው ህይወት መኖር የለበትም፡፡ ይህንን እውን ለማድረግ ደግሞ በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል፡፡

ለሁለት ዓመታት ያህል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል ሲደረግ የነበረው ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በፕሪቶርያ በተካሄደው የሰላም ስምምነት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን መሠረት አድርጎ ሉአላዊነትንና የግዛት አንድነትን እና ብሔራዊ ጥቅምን ባከበረ መልኩ እልባት አግኝቷል፡፡ ይህም ስምምነት ከትግራይ አልፎም ለመላ ኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋትን አስፍኗል፡፡

የፕሪቶርያው ስምምነት “በዘላቂነት የጦር መሳሪያ ድምጽ እንዳይሰማ ለማድረግ እና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመት የዘለቀው ግጭት እንዲቆም ተስማምተናል” ሲሉ የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት መስማማታቸው የሚታወስ ነው።

በወቅቱም በአንድ ድምጽ ግጭቱ ከፍተኛ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራዎችን አስከትሏል ካሉ በኋላ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጥቅም ከግምት በማስገባት የግጭቱን ምዕራፍ ከኋላችን ትተን “በሰላም እና በመቻቻል ለመኖር” ተስማምተናል ማለታቸው የሚታወስ ነው። ከዚህ ስምምነት በኋላም የፌዴራል መንግሥት ትግራይን መልሶ ለመገንባት ብዙ ርቀቶች ተጉዞ ውጤታማ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ ስለሆነም እንደ ፌዴራል መንግሥቱ ሁሉ በሕወሓት ፖለቲከኞችና ልሂቃን በኩል የተገባው የሰላም ቃል ሊጠበቅ ይገባል፡፡

የትግራይ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን ከጦርነት ይልቅ ሰላምን በመምረጥ ለሀገራቸው ውለታ ሊውሉ ይገባል፡፡ በረባ ባልረባው በሚነሳ ጦርነት እና ግጭት እየተሰቃየ ያለውን ሕዝብ መታደግ እና የሰላም አየር እንዲተነፍስ ማድረግ ከበሳል ፖለቲከኞችና ልሂቃን የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡

በዚህ ቅዱስ እሳቤ መሠረት ፖለቲከኞችና ልሂቃን በውስጣቸው ያሉትን ልዩነቶች በመግባባት፣ በመደጋገፍ፣ በሰላም እና የትግራይን ሕዝብ አንድነት በሚያረጋግጥ መልኩ ሊፈቱ ይገባል፡፡

ትግራይ ዛሬ የሚያስፈልጋት አንድነት እና ወንድማማችነት ነው፡፡ ትግራይ ለዘመናት ያህል በጦርነት የቆሰለች በመሆኗ ከዚህ በላይ ጦርነት እና ግጭትን የሚሸከም ትከሻ እንደሌላት በመገንዘብ በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ልሂቃን ችግሮቻችንን በውይይት የመፍቻው ጊዜ አሁን ነው!

አዲስ ዘመን ጥር 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You