
አንድን ሀገርና ሕዝብ ለመግለጽ ከሚጠቅሙ መሠረታዊ መገለጫዎች መካከል ባሕልና ቅርስ፣ ቱሪዝምና ኪነ ጥበብ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነኚህን መገለጫዎች ለኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያበረክቱት የሰው ልጅ እሴቶች ዋነኞች ናቸው፡፡
ቱሪዝም ማለት ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ ወጣ ብለው ለመዝናናት፣ ስለአንድ አካባቢ ለማወቅ፣ ለማጥናት፣ ለሥራ ጉዳይ በሄዱበት እግረ መንገድ ጉብኝት የሚያደርጉበትም ሊሆን ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ የሚጎበኙ ታሪካዊና መንፈሳዊ ቦታዎች፣ ብሔራዊ፣ ባሕላዊና ሕዝባዊ በዓላት፣ አስደናቂ የተፈጥሮ ሥፍራዎችንና እንስሳት አሏት፡፡
ኢትዮጵያ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደ አቅሟ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ተፈጥሯዊ እና ሌሎችም ጎብኚዎችን ሊስቡ የሚችሉ የቱሪዝም ሀብቶቿን በማስተዋወቅ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጉላት ጥረት እያደረገች ነው። በአስደናቂ ታሪኳ፣ በተለያዩ መልከዓ ምድሮች እና ህያው ባሕሏ የጉዞ መዳረሻ ሆና ይበልጥ እንድትቀጥል በቱሪዝም መሠረተ ልማት እየታደሰች ትገኛለች።
ከድንጋይ ከተጠረቡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ጀምሮ እስከ ጥያ ትክል ድንጋይ፣ ከሶፍ ዑመር ዋሻ እስከ ጎንደር የነገሥታት ግንቦች፣ ከአክሱም ሐውልት እስከ ሐረር ግንብ፣ ከራስ ዳሽን እስከ ዓለማችን ዝቅተኛው ሥፍራ ዳሎል፣ የሰው ልጆች በሁለት እግራቸው መራመድ የጀመሩበት፣ የኤርታ አሌ የሚንተከተክ እሳት እና ሌሎችም አያሌ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና አካባቢያዊ ቅርሶች እና ምልክቶች በጉያዋ የያዘች ሀገር ናት።
በዚህ ረገድ በተለያዩ ዘርፎች የታደለች ከመሆኗ ባሻገር በርካታ የቱሪስት መሰህቦችን በዓለም ደረጃ ለማስመዝገብ ችላለች። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርሶች መዝገብ ውስጥ የተካተቱ በርካታ የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች አሏት። ቅርሶቹ ከአክሱም ሐውልቶች እስከ ታችኛው ኦሞ ሸለቆ ድረስ የተንጣለሉ ናቸው።
ከዚህም መካከል የላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተክርስቲያናት፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የፋሲል ግቢ እና የጎንደር ሐውልቶች፣ አክሱም፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የጢያ ትክል ድንጋዮች፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ፣ የሐረር ጀጎል ጥንታዊ ከተማ፣ የኮንሶ መልክዓ ምድር፣ መስቀል፣ ፍቼ ጫምበላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ ጥምቀት፣ የጌዴኦ ባሕላዊ መልክዓ ምድር፣ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ተመራጭ ከሚያደርጓት ነገሮች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት ‹‹ገበታ ለሀገር›› እና ‹‹ገበታ ለትውልድ›› በሚል መሪ ሃሳብ የተለያዩ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተገነቡ ይገኛሉ። በተጨማሪም በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወኑ የሚገኙ የኤርፖርት ማስፋፊያዎች ለዚህ አንፀባራቂ ምሳሌ ናቸው። በአዲስ አበባ እና ክልሎች የተጀመሩ የኮሪደር ልማቶችም እንዲሁ። በኢትዮጵያ እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ ግድቦች እና የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ለቱሪዝም መዳረሻ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘላቂ ኃይል ለማቅረብ ይረዳሉ።
ለመሆኑ እነዚህ ታላላቅ ፕሮጀክቶችና መዳረሻዎች ካለፈው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር እንዴት ይታያል? ለዘርፉስ ይዘውት የመጡት እምርታ ምን ይሆን? በቀጣይስ መሠራት የሚገባው ምንድን ነው? ስንል የዘርፉን ባለሙያዎች ጠይቀናል፡፡
ካነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች አንዱ የቱሪዝም ሀብት ልማት ባለሙያው አቶ ቃለዓብ በላቸው ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በ1960ዎቹ ገደማ በግሉ ዘርፍና በንጉሳዊ ሥርዓት የለሙ ታሪካዊም ሆነ ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ሀብቶች የነበሩ ሲሆን፤ ነገርን እነኛን ከመጠቀም ባለፈ በተቀናጀ መልኩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ከማስፋፋት እና ከማልማት አንጻር ውስንነቶች ይታዩ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በመላ ሀገሪቱ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተቀርጸው በመሠራት ላይ መሆናቸው ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት አዲስ እይታን የሚፈጥር ነው፡፡
በመሆኑም ይላሉ ባለሙያው፣ የቱሪዝም ዘርፉ ሀገሪቱ ያላትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ከመቅረፍ አንጻር የራሱን ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማልማት በሥፍራው ለሚገኙ የአካባቢው ማህበረሰቦች የመሠረተ ልማት እድገትን በመደገፍና የሥራ እድልን በመፍጠር ጠቀሜታዎችን በመስጠት ላይ መሆኑ እሙን ነው፡፡
ፕሮጀክቶቹ የአካባቢና ቅርስ ጥበቃ፣ የማህበረሰብ ተሳትፎ፣ የአቅም ግንባታ እና የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶችን ያካትታሉ። እንዲሁም የኢትዮጵያን የበለጸገ የባሕል ትሩፋት በመጠበቅ የግሉ ሴክተር በመነቃቃት የማያቋርጥ እድገትን ያበረታታል ሲሉ ያክላሉ።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተሠሩ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንዳሉ ያስታውሳሉ፤ በ“ገበታ ለሸገር”፣ በ“ገበታ ለሀገር” እና በ“ገበታ ለትውልድ” በተሰኙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ማልማት መቻሉን ያስረዳሉ፡፡
በ“ገበታ ለሸገር” እና በ“ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት የለሙት የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ተጠናቅቀው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙና በ“ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት ደግሞ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተጨማሪ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን የማልማት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ ስለሺ፤ አውሮፕላን ማረፊያ በሌለባቸው የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ትንንሽ አውሮፕላኖችን የሚያሳርፍ እና የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ መከናወኑን ይናገራሉ።
የፕሮጀክቶቹ መገንባት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ቁጥር በመጨመርና የቆይታ ጊዜያቸውን በማራዘም የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ የሚያስችል ነው። ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ማህበራዊ መስተጋብርን ለማጠናከር፣ የሀገሪቱን ገጽታ ለመገንባት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የቱሪስት መዳረሻ ቦታ ባለቤት እንድትሆንም የሚያደርጋት መሆኑን አቶ ስለሺ ያብራራሉ።
የተሠራው ሥራ የቱሪዝም ሥራ መዳረሻን ማስፋፋትና ሀገር ማስተዋወቅ ብቻ አይደለም የሚሉት አቶ ስለሺ፤ የቱሪስቶችን ፍላጎት በማሟላት የቆይታ ጊዜያቸውን ለማራዘም እና ወደ ኢትዮጵያ ለመሳብ ጥረት እየተደረገ ነው ይላሉ።
እንደ አቶ ስለሺ ገለጻ፤ “የገበታ ፕሮጀክቶች” መገንባት የሀገሪቱን ገጽታ በእጅጉ ቀይሯል። ለበርካቶችም የሥራ ዕድል በመፍጠር እንጀራ ሆኗል። ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ጉልህ ሚና ከማበርከት ባለፈ ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ያደረገ ሲሆን፤ የፕሮጀክቶቹ በአጭር ጊዜና በጥራት መገንባት የይቻላል መንፈስን በመላ ኢትዮጵያውያን አሳድሯል።
ቱሪዝም በመንግሥት ትኩረት ከተሰጣቸው አምስቱ የኢኮኖሚ አቅጣጫዎች መካከል አንዱ መሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ፍጹም ገዛኸኝ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በሌሎች ባለድርሻ አካላት አማካኝነት የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማስፋፋት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው እድገት ግብዓት በመሆናቸው የሚደነቁ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ፣ በባሕልና በሰው ሠራሽ የተሠሩ በርካታ መስህቦችና የቱሪዝም መዳረሻዎቿ ያላት በመሆኑ ተመራጭ ሀገር ናት፡፡ መስህቦች በራሳቸው ዝም ብለው ቢቀመጡ ትርጉም የማይኖራቸው በመሆኑ እነኚህን መስህቦች በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ በሰፊው እየተከናወነ መሆኑን አቶ ፍጹም ይናገራሉ፡፡ ለዚህም በአሁን ወቅት እየተከናወኑ የሚገኙ የመዳረሻ ልማት ሥራዎች ለአስጎብኚ ድርጅቶች መልካም እድሎችን የፈጠሩ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ከ288 በላይ አስጎብኚ ማህበራትን ያቀፈ ሲሆን፣ እያንዳንዱ ማህበራት በሥራቸው በርካታ ባለሙያዎችና ሠራተኞችን ቀጥረው እያሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከቱሪዝም ሚኒስቴርና ከክልል ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር ሙያዊ ድጋፎችንና አስተያየቶች በመስጠት ተቀራርበን እየሠራን እንገኛለን ሲሉ አቶ ፍጹም ይጠቁማሉ፡፡
ቱሪዝም የውጭና የሀገር ውስጥ ተብሎ ለሁለት የሚከፈል ሲሆን፣ የውጭ ቱሪዝም በርካታ የውጭ ምንዛሬ የሚገኝበት ነው ያሉት አቶ ፍጹም፤ እንዲሁም የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን በማስፋፋት ዜጎች ስላላቸው ባሕል፣ ቅርስና ትውፊት አውቀው ማክበርና መቀበል እንዲችሉ በማድረግ ዜጎች ቅርሶቻቸውንና ባሕላቸውን አውቀው እንዲጠብቁ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
የቱሪዝም ዘርፉ መጠናከር ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመክፈት፣ የሀገርን ኢኮኖሚ በመደገፍና ከቱሪስቱ የሚገኘውን ገቢ በዜጎች መካከል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ እንዲሁም የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና የባሕል ሽግግሮች እንዲኖሩ እድል የሚሰጥ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ እንደሚናገሩት፤ መንግሥት የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ምሰሶዎች አንዱ አድርጎ የቱሪዝም ዘርፉ ላይ በስፋት እየሠራበት ይገኛል። በዚህም ራሱን ችሎ በሚኒስትር ደረጃ እንዲቋቋም ከማድረግ አንስቶ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ እስከ ማድረግ የደረሱ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች ከለውጡ በኋላ ተከናውነዋል። ኢትዮጵያ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት የሀገር ገጽታን እየቀየሩ ያሉ ሪዞርቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ተደብቀው የነበሩ እምቅ የመስህብ ሥፍራዎችን፣ መልከዓ ምድሮችን፣ ፓርኮችን እና ታሪካዊ ቦታዎችን እየገለጠች ትገኛለች።
ከዚህ በፊት በመሠረተ ልማት እጦት ከተጓዦች ተደብቀው የቆዩትን መንፈስን የሚያድሱ የመስህብ ሥፍራዎችን፣ መልከዓ ምድር፣ እጅግ የተለዩ አዕዋፍና ዕጽዋትን በትስስሩ በተፈጠሩ ዕድሎች ለጎብኚዎችና አሳሾች በቀላሉ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታን እየፈጠሩ ነው። የቱሪዝም መሠረተ ልማት መስፋፋት ለጎብኚዎች ተደራሽነትና ደህንነትን ያበረታታል፤ የቱሪስቶችን እንቅስቃሴ ቀላል ያደርገዋል። የመንገድ መሠረተ ልማት እና የአየር ማረፊያዎችን በማሻሻል በውጭ እንግዶች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ጉዞን ቀላል እንዲሆን ያስችላል።
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሀብቷ ከአፍሪካ ግንባር ቀደም ከሆኑት ሀገሮች አንዷ እንደሆነች ቢነገርም፤ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እያገኘች አለመሆኗ ይታወቃል። የቱሪስት መዳረሻዎችን በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅና ማልማት አለመቻሏ ደግሞ ለዘርፉ መቀንጨር በምክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ የቱሪስት መዳረሻዎች ከማስተዋወቅ አንጻር በሀገር ውስጥ እና ከዚህ በፊት ተቋርጦ በነበረው በጀርመን፣ በእንግሊዝ እና በተለያዩ የዓለም ሀገራት በቱሪዝም ሚኒስቴር እና በግሉ ዘርፍ በኩል የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል። እንዲሁም የሀገሪቱን የቱሪስት ቦታዎች በሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ከማስተዋወቅ ባለፈም የብራዚል፣ የሩሲያ፣ የቻይና እና የሌሎች ሀገራት ሚዲያዎች እንዲጎበኙና እንዲያስተዋውቁ ተደርጓል። የቢዝነስ ለቢዝነስ ትስስሮች፣ ኤግዚቢሽኖችንና ሌሎች የማስተዋወቂያ ፕሮግራሞች መከናወን ችለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ከምትታወቅባቸው በተጨማሪ በርካታ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎች ስላሏት አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ብቻ ተንጠልጥሎ የነበረውን የቱሪዝም ገበያ ወደ አፍሪካ ለማምጣት በትኩረት እየተሠራ ይገኛል፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከማስተዋወቅና ከመዳረሻ ልማት በተጨማሪ “የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት” የቱሪዝም መረጃ የሚያዝበት ሥርዓት (ሲስተም) ያበለጸገ ሲሆን፤ በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ላይ አጠቃላይ መረጃዎችን ለማቅረብ እንዲያስችል ተደርጎ የተዘጋጀው የቱሪዝም የሳተላይት አካውንት ማስጀመር መቻሉንንም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሳተላይት አካውንት በዘርፉ የነበረውን የተደራጀ መረጃ ውስንነት በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም አስረድተዋል፡፡
አቶ ስለሺ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪዝም አቅም ቢኖራትም በቱሪዝም መሠረተ ልማት ማበልጸግ ባለመቻሏ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች። ከለውጡ በኋላ ግን መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ በሰጠው ትኩረት ከአምስቱ የሀገር በቀል የሪፎርም አጀንዳዎች ውስጥ በማካተት ዘርፉን ለማሳደግ እየተሠራ ነው፡፡ የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችን የማድረግ፣ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ የመተግበር፣ የከተሞችን የቱሪዝም ብራንድ የማዘጋጀት፣ በዘርፉ የግሉን ሴክተርና የውጭ ባለሀብቶችን ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማበረታት ሥራ ተሠርቷል፡፡
የቱሪዝም ሀብት ልማት ባለሙያው አቶ ቃለዓብ የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም የገለጡ ፕሮጀክቶች መሠራታቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተበሰሩት የገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር፣ ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ገጽታን በመሠረታዊነት እየቀየሩ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ከመሀል ሀገር እየሰፉ ራቅ ወዳሉ የመስህብ ሥፍራዎች፣ መልከዓ ምድርና ፓርኮችን በመሠረተ ልማቶች በማስተሳሰር አዳዲስ የቱሪስት እድሎችን እንዲከፈቱ መደላድል እየፈጠሩ እንደሚገኙም ያመለክታሉ፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ትልልቅ ሥራ ያከናወናች ቢሆንም ቀሪ የቤት ሥራዎች አሉ። በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ በቀዳሚነት የምትጠቀስ ሀገር ናት፡፡ ይሁን እንጂ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ ገና ብዙ ማድረግ የሚጠበቅባት እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ ከቱሪዝም ልማቱ ጋርም ተያይዞ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የዘመነ አገልግሎት ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በቂ የቱሪዝም ሀብት እያላት የመሠረተ ልማት ግንባታውም እያደገ የዘመነ አገልግሎትን በተሻለ መንገድ ማቅረብ ባለመቻሉ የሚደርሰው ኪሳራ ከፍተኛ በመሆኑ ኪሳራውን ለማካካስ በዘርፉ ተጠቃሽ ከሆኑ ሀገራት ልምዶችን በመቅሰም የቱሪዝም አገልግሎት ዘርፉን ማዘመን ይገባል።
በአሁን ወቅት ያደጉ ሀገራት በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመታገዝ አገልግሎቶችን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በዘርፉ የተማረ የሰው ኃይል አስፈላጊ በመሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቁ የሰው ኃይል ከማፍራት አኳያ በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በቱሪዝም ዘርፉ የሚመቻቹ አገልግሎቶችን ከውጭ ከሚመጡ ቱሪስቶች በተጨማሪ የሀገር ውስጥ ዜጎችም እንዲጠቀሙ በማድረግ የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ለማበረታታት መሠራት ያስፈልጋል፡፡ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በሚገባ በማስተዋወቅ ረገድም በየወቅቱ የሚነሱ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት፤ ሀገሪቱ ያላትን ሀብቶች በሚገባ መጠቀም እንድትችል ወቅታዊ የሰላም ሁኔታው ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ቱሪስት ወደ አንድ አካባቢ ለመዝናናት፣ መረጃ ለመፈለግ፣ ለማጥናት፣ አንዳች አስደናቂ ነገር ለማየት እንዲመጣ ታሪካዊና መንፈሳዊ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቶችን ብሔራዊ፣ ባሕላዊና ሕዝባዊ በዓላት አከባበርን በሰፊው ማስተዋወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡
ቃልኪዳን አሳዬ
አዲስ ዘመን ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም