
አዲስ አበባ፡- የትግራይ ልሂቃን ሕዝቡን ከስጋት፤ እናቶችን እንቅልፍ ከማጣት፤ ወጣቶችን ደግሞ ከስደት ለማዳን እንዲሠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ፡፡ ልዩነታቸውን በመግባባትና የትግራይ ሕዝብን አንድነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲፈቱ ጠየቁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ለክልሉ ልሂቃን እና ለትግራይ ሕዝብ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው በአቀረቡት ምክረ ሃሳብ የትግራይ ሕዝብ ሀገሩን የሚወድ፣ ሰላም፣ እፎይታና ሥራ ወዳድ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የትግራይ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የመንግሥትን ምንነት በሚገባ የሚያውቅና ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመሆን ሀገረ መንግሥት የመሠረተ ሕዝብ መሆኑን አመልክተው፥ ሀገረ መንግሥት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜም ከባድ ዋጋ በመክፈል ሀገረ መንግሥት ያፀና ነው ብለዋል ።
ለዚህም ድርቡሽ፣ ግብፅ፣ ጣሊያን በኋላ ደግሞ በምዕራብ፣ ምሥራቅና ሰሜን ለመጡት ወራሪዎች ለክብሩና ለሀገሩ ሉዓላዊነት ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመተባበር መታገሉንና መስዋዕትነት መክፈሉን ጠቁመዋል።
የትግራይ ሕዝብ ትንሽ ሰላም ባገኘበት ወቅት፡- በንግድ፣ እርሻ፣ ሥነ ሕንፃ፣ ጥበብ እና ቴክኖሎጂ ዘርፎች የሠራቸው አስደናቂ ተግባራት መኖራቸውን አመልክተው ÷ ሕዝቡ በፈተና የማይናወጥ መንፈሰ-ጠንካራ ሕዝብ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
መጥፎ አጋጣሚ ሆኖ በተለይ ባለፉት 100 ዓመታት በተለያዩ አጋጣሚዎችና በተለያዩ ምክንያቶች፣ በተለይ ደግሞ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ባጋጠመ አለመግባባት የትግራይ መሬት የጦርነት ዓውድ፤ የትግራይ ሕዝብ ደግሞ የጦርነት ሰለባ መሆኑን ገልፀዋል።
ምክንያቱ የፈለገ ይሁን መነሳት ያለበት ጥያቄ፥ “ባለፉት 100 ዓመታት በተደረጉት ጦርነቶች የትግራይ ሕዝብ ያገኘው ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፀጥታዊ ትርፍ አለ ወይ? ምንስ ከሰረ?” ብሎ መጠየቅ ተገቢ እንደሆነ አመልክተው÷ በዚህ ወቅት አንድ ልባም ትግራዋይ ልሂቅ፥ “ትግራይና ሕዝቧ ከጦርነት ያገኙት ነው ወይስ ያጡት የሚበዛው?” ብሎ መጠየቅና መልስ ማግኘት እንደሚገባው መክረዋል።
የተደረጉ ጦርነቶች ብቸኛ አማራጭ ነበሩ ወይ? ሌላ መፍትሔ አልነበረም ወይ? ከዚህ በኋላስ ጦርነት እንዳይነሳ ምን መደረግ አለበት? የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረብ ተገቢ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የትግራይ ሕዝብ የትላንት ቁስሉ ሳይሻር፣ ገና አሁንም ሰላምና እፎይታ አግኝቶ ሠርቶ እንዳይገባና እንዳያለማ በፍራቻና ጭንቅ የጦርነት ወሬ እየኖረ መሆኑ አሳዛኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እንደዚህ ዓይነት አደጋን እንዴት መፍታት ይቻላል የሚለው በእርጋታ መነጋገር የሚያስፈልገው ጉዳይ እንደሆነም አመልክተዋል።
በፖለቲካ፣ ንግድ፣ ፀጥታ፣ አካዳሚ፣ ሚዲያና ሌሎች ዓውዶች ያሉትን የትግራይ ልሂቃንና መላው የትግራይ ሕዝብ እስካሁን የተከፈለው ዋጋ ይበቃል፣ ከጦርነት የሚገኝ ትርፍ የለም በማለት መጀመሪያ በውስጣቸው ያለውን ልዩነት በመግባባት፣ በመደጋገፍ፣ በሰላምና የትግራይ ሕዝብን አንድነት በሚያረጋግጥ የሠለጠነ መንገድ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም ከፌዴራል መንግሥት ይሁን ሌሎች ኃይሎች ጋር ያሉትን ልዩነቶች በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በመግባባት ለመፍታት ዝግጁ እንዲሆኑ÷ በፌዴራል መንግሥት በኩል፥ በሁሉም ጉዳዮች ለመነጋገር እና የሃሳብ ልዩነት እንደ ልዩነት በመውሰድ በሚያግባቡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰላም መሥራት የሚያስችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ መገንዘብ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም