ዛሬ ብዙዎችን ወደኋላ ስለሚያስቀረውና ከህልማ ቸው ደጃፍ እንዳይደርሱ እንቅፋት ስለሆነው ፍርሃት ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት ወድጃለሁ። ለመሆኑ ‹‹ፍርሃት›› ምንድነው? ይህን ስሜት ለእድገታችንና ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ በምናደርገው ጉዞ ላይ እንቅፋት እንዳይሆን እንዴት መቆጣጠር እንችላለን? በእነዚህና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገን የመፍትሔ ሃሳቦች ላይ እንደሚከተለው እንመክራለን።
ፍርሃት ተፈጥሯዊ ነው
ፍርሃት ሁላችንም የሚያጋጥመን ነገር ነው። የተለመደና የሕይወት አንዱ ክፍል ነው። ብዙ ወጣቶች በሚሰማቸው ፍርሃት የተነሳ ስሜቱን መቋቋም ሊያቅታቸውና እንደ ከባድ ሸክም ሊሰማቸው ይችላል። ፍርሃት አዳዲስ ነገሮችን ከመሞከር ወይም ግብ ላይ እንዳትደርስ ሊከለክልህ አሊያም እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል።
ፍርሃት ብዙ ዓይነት ነው። አንድን ሥራ ወይም አዲስ እቅድ ብንሞክር ‹‹ውድቀት ሊያጋጥመን ይችላል›› ብሎ መፍራት፣ በሰዎች በቀላሉ ልንተች እንደምንችል በማሰብ ፍርድን መፍራት ወይም ያልታወቀን ፍርሃት ሊሰማን ይችላል። በዚህ ምክንያት ፍርሃትህ የሚፈልገውን ሕይወት ከመኖር ሊያግድህ ይችላል።
ይህ ሰዋዊ ስሜት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ልንቆጣጠረውና በቀላሉ ለምንፈልገው የሕይወት ግብ ራሳችንን ልናዘጋጅበት የምንችለው ነው። ከፍርሃት መላቀቅ፣ ድፍረትን እና በራስ መተማመንን ማዳበር ትችላለህ። ይህ ጉዞ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም በትናንሽ ርምጃዎች እና ተከታታይ ጥረት ማሳካት የምትችለው ነው።
በራስ መተማመንና ድፍረት
ድፍረት ያለ ፍርሃት መኖር አይደለም። ፍርሃትን መጋፈጥ እና ማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ አልፎ ወደፊት መሄድ ማለት ነው። በራስህ ስትተማመንና ተግዳሮቶችን የመወጣት ችሎታህ እንዳለህ ስታምን በቀላሉ የምትፈልገውን ማድረግ ትችላለህ። ድፍረት እና በራስ መተማመን ህልምህን ለማሳካት ይረዳሃል። የመጀመሪያው ርምጃ ፍርሃትህን መረዳት ነው። “የምፈራው ምንድን ነው?” ብለህ ራስህን ጠይቅ። ፈተና መውደቅ፣ በሕዝብ ፊት መናገር ወይም አዲስ ንግድ መጀመር ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ ፍርሃት የሚመጣው መጥፎውን ውጤት በማሰብ ነው። ግን ብዙ ጊዜ ይከሰታል ብለህ የምታስበው መጥፎ ውጤት አይደርስም፤ ፍርሃትህ ግን ለውስጥህ የሚነግረው እርሱን ነው። ይህንን መረዳትህ ወደ ድፍረት የሚወስደውን የመጀመሪያ ርምጃ እንድትወስድ ይረዳሃል።
እዚህ ጋር አንድ ምሳሌ ላንሳልህ። በቅርብ የማውቀው ወዳጄ ነው፤ አዲስ አበባ የሚኖር ወጣት፤ ዓለም ይባላል። ለዚህ ጽሑፍ ስል ስሙን ቀይሬዋለሁ። ዓለም ሁልጊዜ የራሱን የዳቦ ቤት ንግድ መጀመር ይፈልጋል። የራሱን ሥራ የመሥራት የረጅም ጊዜ እቅድ ነበረው። ነገር ግን የሚፈልገውን ለማድረግና ለማሳካት ዓመታት ወሰደበት፤ መነሻ ገንዘብ አልነበረም ያጣው፤ ፍርሃት ነበር ወደኋላ የሚጎትተው።
ለብዙ ጊዜ በቤተሰቦቹ እና በጓደኞቹ ፊት የራሱን ንግድ ቢጀምር ስለሚያጋጥመው ኪሳራና ወድቀት ሲያወራና ሲያመነታ ነበር። ለዓመታት አደጋውን ብቻ ያስብ ስለነበር፤ ይህም በጣም ስላስፈራው በማይወደው የሙያ ዘርፍ ውስጥ ተቀጥሮ ሲሠራ ቆይቷል። አንድ ቀን ግን ዓለም ፍርሃቱን ለመጋፈጥ ወሰነ። የዳቦ ቤት ንግዱን በትንሹ ጀመረ። በቤት ውስጥ መጋገር እና ለጎረቤቶች በመሸጥ ነበር። ያኔ የስኬት ጉዞውን አንድ ብሎ ጀመረው። ከጊዜ በኋላ በራስ የመተማመን ስሜቱ እያደገ ሄደ፤ ቀስ በቀስ ሱቅ ከፍቶ ንግድ ሥራውን አላመደ። አሁን ዓለም የተሳካ የዳቦ ቤት ንግድ ላይ ተሰማርቶ ይገኛል። ዛሬ ላይ ከእርሱ አልፎ ሌሎችም ህልማቸውን እንዲከተሉ ያነሳሳል።
ፍርሃትን የማሸነፍ መንገድ
በራሳችን የማመን ድፍረትን መገንባት በትንሽ ድርጊቶች ይጀምራል። ፍርሃትህን በቀላል መንገዶች በመቃወምና ውስጥህን በማሳመን መጀመር ትችላለህ። ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት ቦታ ለመናገር ከፈራህ ለጓደኛህ አስተያየትህን ለማካፈል ሞክር። ከእርሱ ጋር ማውራትን ሃሳብህን በስፋት መግለፅ ላይ አተኩር። ‹‹የምትጀምረው ንግድ አሊያም ትምህርት አይሳካልኝም›› ብለህ ውድቀትን ከፈራህ፣ ደህንነቱ በተጠበቀ ከባቢ ውስጥ ትንንሽ ርምጃዎችን ውሰድ። እነዚህ ትናንሽ ርምጃዎች ፍርሃትህ የሚመስልህን ያህል ከፍተኛ አደጋ እንደማያመጣብህ እንድትረዳ የማድረግ አቅም ይፈጥሩልሃል። ፍርሃትህን በተጋፈጥክ ቁጥር ጠንካራ ትሆናለህ። ቀስ በቀስም በራስ መተማመንህ እየተሻሻለ ይመጣል።
ሌላው አስፈላጊ ርምጃ ስለ ፍርሃት ያለህን አመለካከት መቀየር ነው። ፍርሃትን እንደ መጥፎ ነገር ከመመልከት ይልቅ ለማደግ እንደ እድል አድርገህ ተመልከተው። ፍርሃት ብዙውን ጊዜ አዲስ ወይም አስፈላጊ የሆነ ርምጃ ልትወስድ ስትል በውስጥህ የሚፈጠር ተፈጥሯዊ ጠባይ ነው። ፍርሃት ለብዙ ጊዜ ከቆየህበት ከምቾትህ ከባቢ ለመውጣትህ ምልክት ነው። ለምሳሌ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችውን ሃናን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ሃና በአደባባይ መናገር ትፈራ ነበር። ነገር ግን የዩኒቨርሲቲ የውይይትና የክርክር ክበብን ስትቀላቀል ፍርሃቷን ለማሻሻል እንደ እድል ተጠቀመችበት። ከጊዜ በኋላ በራስ የመተማመን መንፈሷ በአስደናቂ ሁኔታ ተቀየረ፤ አልፎ ተርፎም ሽልማቶችን ማሸነፍ በመድረኮች ላይ አነቃቂ ንግግሮችን በማድረግ ተወዳጅ ሆነች። አንተም ከዚህች ወጣት ብዙ የምትማረው ነገር ይኖራል።
ሁሌም ዝግጁ ሁን
ፍርሃት ያለ መዘጋጀት ውጤትም ነው። ስለዚህ በምታደርገው ነገር ሁሉ ቀድመህ በምትዘጋጅበት ጊዜ በራስ መተማመንህ ያድጋል። ፈተናን ከፈራህ ጠንክሮ ማጥናት እና ያለፉ ጥያቄዎችን መለማመድ ይኖርብሃል። የሥራ ቃለ መጠይቆችን ከፈራህ ከጓደኛህ ጋር ተለማመድ። ይህን ማድረግህ ዝግጁነት እንዲሰማህ ይረዳሃል፤ ፍርሃትህም ይቀንሳል። ትናንሽ ጥረቶች እንኳን አስፈላጊ መሆናቸውን ተገንዘብ። ለምሳሌ የነፃ ትምህርት ዕድል ማመልከት ብትፈልግ ጥያቄህ ውድቅ እንዳይደረግ ፍርሃት ሊፈጠርብህ ይችላል። በመሆኑም ማመልከቻውን ከማስገባትህ በፊት ቀድመህ መዘጋጀት ይኖርብሃል። መምህሮችህን ማማከር፤ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲፅፉልህ ማድረግና ለፈተናዎች መዘጋጀት ይኖርብሃል። በመጨረሻ ማመልከቻውን ብታስገባ የሚያስጨንቅህ ነገር አይኖርም። ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ቀድመህ መዘጋጀትህ በራስህ እንድታምንና ሁሌም ደፋር እንድትሆን ያደርግሀል።
ከሚያበረታቱህ ጋር ወዳጅነት መመሥርት
በራስ መተማመንህን ሊያሻሽሉልህና ሊደግፉህ በሚችሉ ሰዎች ራስህን መክበብ አስፈላጊ ነው። በአንተ የሚያምኑ ጓደኞች እና ቤተሰቦች ፍርሃትህን አሸንፈህ ዓላማህን እንድታሳካ ሊረዱህ ይችላሉ። አንተ ዝቅ የማለትና የራስ መተማመን ችግር ሲገጥምህ ጠንካራ ጎኖችዎን ሊያስታውሱህና ሊያበረታቱህ ይገባል። ከዚህ በተቃራኒ ሆነው ራስህን እንድትጠራጠር ካደረጉ ከእነዚህ አሉታዊ ስሜት ከሚፈጥሩብህ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ከማሳለፍ መቆጠብ ይኖርብሃል። ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች መራቅ ብቻ ሳይሆን ለዓላማህ የሚቀርቡና አንተነትህን የሚቀበሉ ሰዎችን ፈልገህ መቅረብ ይኖርብሃል። ይህንን ማድረግ የቻሉ በርካታ አትሌቶች፣ ሙዚቀኞች እና ሥራ ፈጣሪዎች ስኬትን ማግኘት ችለዋል፤ ፍርሃታቸውን ተጋፍጠው አሸንፈዋል። እነዚህ ሰዎች በዝቅታ ጊዜያቸው ወቅት የወሰዱትን ርምጃ ማጥናትህ ለወደፊት ጠንካራ አንተነት ግንባታህ ሊረዳህ ስለሚችል በጥልቀት አጥናቸው።
ከውድቀትህ መማር
ካለፈው ውድቀትህ እና ሽንፈትህ መማር ድፍረትና በራስ መተማመንህን ለመገንባት ሌላኛው ቁልፍ መፍትሔ ነው። ውድቀት የተፈጥሮ የሕይወት አንዱ ክፍል ነው። የማይሠራ አይወድቅም። ካለፈው ጥረቶችህና ውድቀቶችህ ጠቃሚ ትምህርቶችን መውሰድ ትችላለህ። ውድቀትን ከመፍራት ይልቅ ወደ ስኬት የሚወስድ አንድ ርምጃ አድርገህ ቁጠረው።
እዚህ ጋር አንድ ምሳሌ ለማንሳት እንሞክር። በትንሽ መንደር ውስጥ የሚኖር አንድ ገበሬን ተመልከት። መልካም ሰብልን ለማፍራት አዲስ ዘር በመሬቱ ላይ ለመዝራት ቢሞክርና በመጥፎ የአየር ሁኔታ ምክንያት ምርቱን ቢያጣ ይህ ሰው ዳግም ጥረቱን ላለመቀጠል ምክንያት አይሆንም። ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ከስህተቱ ተምሮ የእርሻ ዘዴውን ማስተካከልና እንደገና መሞከር ይገባዋል። በቀጣዩ ወቅት፣ የተሳካ ምርት አግኝቶ ለጎረቤቶቹ ካለፈው ስህተት በመማር የተሻለ ውጤት ማምጣቱን ማሳየት ይችላል። ከዚህ ምሳሌ መገንዘብ የምንችለው አንድ ጊዜ ሞክረን አልተሳካልንም ማለት የውድቀት መጨረሻ እንዳልሆነ ነው።
አሉታዊ ውድድር ውስጥ አትግባ
አንዳንድ ጊዜ ፍርሃት የሚመጣው ራስን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ነው። “ከእኔ የበለጠ ብልህ ናቸው” ወይም “ተጨማሪ እድሎች አሏቸው” ብለህ በማሰብ በራስ መተማመንህ እንዲሸረሸር በር ትከፍታለህ። ነገር ግን የሁሉም ሰው ጉዞ የተለየ መሆኑን ማወቅ አለብህ። ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን በራስህ መንገድና መፍትሄዎች ላይ ማተኮር ይገባሀል። ለምሳሌ በልብስ ስፌት ወይም በአንድ ሌላ ዘርፍ አዲስ ሙያ እየተማርክ ከሆነ ሌሎች ከአንተ የተሻሉ ቢሆኑ ልትጨነቅና በራስ መተማመን ልታጣ አይገባም። ልምምድህን በራስህ አቅምና የችሎታ ልክ መቀጠል አለብህ። በዚህ ጊዜ በራስ መተማመን የሚገነባው በንፅፅር ሳይሆን ሳታቋርጥ በለውጥ ላይ በማተኮር መሆኑን ትገነዘባለህ።
መዳረሻህን ቀድመህ ገምት
ከፍርሃት ለመላቀቅ ሌላኛው መንገድ ስኬትን በዓይነ ሕሊናህ መመልከት ነው። ዓይንህን ጨፍነህ ግብህን በርግጠኝነት እንደምታሳካው አስብ። ልትወስዳቸው ስለሚገቡ ርምጃዎች እና በሂደቱ ድል ስለምታደርጋቸው ተግዳሮቶች በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ይህ እይታህ የበለጠ ዝግጁነት እንዲሰማህ እና ፍርሃት እንዲቀንስ ያደርጋል።
ለምሳሌ በባሕር ዳር አካባቢ የምትኖር ወጣት ነህ እንበል። የቡና መሸጫ ለመክፈት ፈልገህ ይሆናል። በዚህ ሥራ ውስጥ ብትገባ ‹‹ላይሳካልኝ ይችላል›› የሚል እሳቤ በውስጥህ በፍርሃት መልክ ተፈጠረ። ነገር ግን ቀድመህ ሥራውን ከመጀመርህ በፊት ሱቅህን፣ ደንበኞችህን እና መፍጠር የምትፈልገውን ድባብ በዓይነ ሕሊናህ ለማየት ሞክር። ይህ በውስጥህ የተፈጠረው አዎንታዊ ምስል በድፍረት ወደ ንግድ ሥራው እንድትገባ በርግጠኝነት ያግዝሃል። መልካምና ቀና አስተሳሰብ በውስጥህ እንዲኖር ያደርጋል።
በመጨረሻም ይሄን አድርግ
በማመስገን ላይ ስታተኩር ፍርሃት ይቀንሳል። ምስጋና ጥንካሬህን እና ያለህን ክህሎት ያስታ ውስሃል። ለእያንዳንዱ ቀን የምታመሰ ግንባቸውን ምክንያቶች ፃፍ። ይህ ቀላል ልማድ አስተሳሰብህን ሊለውጥ እና በራስ የመተማመን ስሜት እንድታዳብር ሊረዳህ ይችላል። ድፍረት ለድርጊትህ አጋዥ መንገድ እንጂ መድረሻ እንዳልሆነ አስታውስ። ፍርሃትህን በተጋፈጠህ ቁጥር አንድ ርምጃ ወደፊት ትሄዳለህ። ከጊዜ በኋላ እነዚህ ትናንሽ ርምጃዎች ይጨምራሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ወጣቶች ፍርሃት የሚፈጥሩ ፈተናዎች ይገጥሟቸዋል። ነገር ግን አንተ ፍርሃት ከህልምህ ሊያግድህ አይገባም። ንግድ ለመጀመርም፣ ትምህርት ለመከታተል ወይም ለምታምንበት ነገር ሁሉ በድፍረት ለመቆም ከፍርሃት የመላቀቅ ኃይል አለህ። ትንንሽ ርምጃዎችን ውሰድ፣ በራስህ እመን፣ እና በአዎንታዊ ሃሳቦችና ተጽዕኖዎች ውስጥ ለመቆየት ሞክር። ሞክረህ ትማርበታለህ እንጂ የውድቀትህ መጀመሪያ እንዳልሆነ አስታውስ። በጊዜ እና ጥረት ህልምህን ለማሳካት ድፍረትን እና በራስ መተማመንን መገንባት ትችላለህ። ወደ ድፍረት የሚወስደው መንገድ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ግን ደግሞ ውጤቱ ያማረና ዋጋ ያለው ነው። ፍርሃትን አሸንፈህ የምትኮራበትን ሕይወት መፍጠር ትችላለህ። እንዳታቆም፤ ወደፊት ተራመድ!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም