ባለብዙ ዘርፉ የንግድ ሰው

የዛሬው የስኬት አምድ እንግዳችን በግሉ ዘርፍ ጤና አገልግሎት ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረከቱና በተለይ የሀገሪቱን የጤና ምርመራ ሥራ በማዘመን ረገድ ስማቸው ጎልቶ የሚነሳ ግለሰብ ናቸው፡፡ እንግዳችን አቶ ዳዊት ኃይሉ ይባላሉ፤ የውዳሴ ግሩፕ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የተወለዱትና ያደጉትም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ፍልውሃ በሚባለው አካባቢ ነው፡፡

እንደ ማንኛውም ልጅ ዶክተር ወይም አውሮፕላን አብራሪ መሆን የልጅነት ሕልማቸው ነበር፡፡ ወላጅ አባታቸው የፋርማሲ ባለሙያ መሆናቸው ሀኪም የመሆን ዝንባሌ ይበልጥ አንዲያድርባቸው ማድረጉን ያስታውሳሉ፡፡

ይሁንና የሁለተኛ ደረጃ ውጤታቸው ከሕክምናው ይልቅ የንግድ ትምህርት ለመማር የሚያስችላቸው ሆኖ ተገኘ፤ እናም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንግድ ሥራ ኮሌጅ ገብተው በአካውንቲንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ። በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በሶሶሎጂ ትምህርት መስክም (የማኅበረሰብ ጥናት) ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንደያዙ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የመመደብ እድል ቢኖራቸውም የግላቸውን ሥራ መስራት ይሹ ስለነበር የምደባ ምዝገባ ቅፅ መሙላቱን ተውት፡፡ ይህን ሀሳባቸውን አሁን ለደረሱቡት ደረጃ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቷን ለሚናገሩላት ለያኔዋ ጓደኛቸውና ለአሁን ባለቤታቸው አጫወቱ፡፡ በወቅቱ ደግሞ ወደ ትዳር ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ ስለነበር አዋጭ ነው ባሉት የሥራ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት አብረው መከሩ፡፡ በአቅራቢያቸው ያለውን ምቹ እድል ሲያማትሩም የሀገር ባህል እቃዎች ሽያጭ ላይ ቢሰማሩ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመኑ፡፡ እናም በባለቤታቸው ስም ውዳሴ የሀገር ባሕል እቃዎች የሚል ሱቅ ከፈቱ፡፡

‹‹ይህንን ሥራ ስንጀምር በእጄ የነበረው ስድስት መቶ ብር፣ ባለቤቴ ደግሞ ሁለት መቶ ብር ብቻ ነበር›› ሲሉ የሚያስታውሱት አቶ ዳዊት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከፊታቸው ያለው ሰርግ ደግሞ ሌላ ውጥረት ፈጥሮባቸው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ለሰርጋቸው ያሰቡትን አነስተኛ ገንዘብ ይዘው ከሰርጋቸው አንድ ወር አስቀድሞ የሀገር ባሕል እቃ መሸጫ ሱቃቸውን መክፈታቸውን ይጠቅሳሉ።

ሰርጋቸውን ቀለል ባለ መንገድ ለማካሄድ አስበው እንደነበር የሚናገሩት እንግዳችን፤ ይሁንና ጓደኞቻቸውና ቤተዘመዶቻቸው ትብብር አብዛኛው ወጪያቸው እንደተሸፈነላቸው ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም ለሰርጋቸው የተሰጣቸውንም የገንዘብ ስጦታ ለከፈቱት የንግድ ተቋም አዋሉት፡፡

‹‹ይህንን ሥራ ስንጀምር ሱቃችን በጣም የሚያምር ቢሆንም በገንዘብ እጥረት ምክንያት ብዙ እቃ አልነበረውም›› የሚሉት አቶ ዳዊት፤ ከባለቤታቸው ጋር በመመካከርም ከሌሎች ተመሳሳይ ሥራ ከሚሰሩ ድርጅቶች እቃ በማምጣትና በመሸጥ ኮሚሽን እያገኙ የገንዘብ አቅማቸውን ማሳደግ ውስጥ ገቡ፡፡

ይህ አይነቱ የንግድ ዘዴ በወቅቱ ያልተለመደ ቢሆንም እንደ እድል ሆኖ በርካታ ነጋዴዎች በሃሳባቸው ተስማምተው እቃቸውን ለአቶ ዳዊትና ባለቤታቸው መስጠት ጀመሩ፤ እነ አቶ ዳዊትም ሸማቹን የሚስቡበት የተለየ ዘዴ በመፍጠርና ጠንክረው በመስራት የደንበኞቻቸውን መጠን በአጭር ጊዜ ከፍ ማድረግ ቻሉ፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ የሱቆቻቸውን መጠን ከአንድ ወደ ሦሥት እስከ ማሳደግ ደረሱ፤ አልፎ ተርፎም የሀገር ባሕል አልባሳትና ቁሳቁስን ወደ ውጭ እስከ መላክ ድረስ አቅማቸውን አጎለበቱ፡፡

ገበያው እየሰፋና ተፈላጊነታቸው በከፍተኛ መጠን እያደገ ሲመጣም የራሳቸው ሸማ ሰሪዎች በማደራጀት ለቱሪስቶች የሚሆኑ የባሕል አልባሳትን እስከ ማስመረት ደረሱ፡፡ ምርቱንም በወቅቱ ብዙዎች ደፍረው በማይገቡበት የመረጃ መረብ ግብይት ሥርዓት (ኦንላይ ቢዝነስ) ዘርግተው ማስተዋወቅና መሸጥ ቀጠሉ፡፡ በዚህም በርካታ ደንበኞችን በማፍራት የገቢ አቅማቸውን ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ ቻሉ፡፡

አቶ ዳዊትና ባለቤታቸው ይህ ሥራ ምንም እንኳን ትርፍ እያገኙበትና እየሰፋ ቢመጣም፣ አንድ ቀን ተመልሶ ሊቀዘቅዝ እንደሚችል በማሰብ ጎን ለጎን ተጨማሪ የሥራ መስክ ላይ ለመሰማራት ቆርጠው ተነሱ፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ እየመከሩ ሳለም አንድ ከውጭ የመጣ ጓደኛቸው በውጭ ሀገር በጤናው ዘርፍ ዲያግኖስቲክስ ሕክምና (የውስጥ ደዌ ምርመራ) አዋጭ እንደሆነ፤ ይህንን ሥራ ወደ ኢትዮጵያ ቢያመጡ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይመክራቸዋል፡፡

እንግዳችን አቶ ዳዊት ግን በአባታቸው ምክንያት ለጤናው ዘርፍ ቅርብ ቢሆኑም በኢትዮጵያ ደረጃ እምብዛም በማይታወቀውና በቴክኖሎጂ በሚደገፈው በዚህ የጤና ምርመራ ሥራ ቢሰማሩ ‹ልንከሰር እንችላለን› የሚል ስጋት አደረባቸው፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ያለው የኃይል መቆራረጥ ችግር፤ የቴክሎጂና መለዋወጫ መሳሪያዎችና የባለሙያ አለመኖር ጉዳይ እነ አቶ ዳዊትን ብዙ አሳስቧቸውም ነበር፡፡ ይሁንና ‘ደፋርና ጭስ መውጫ አያጣም’ የሚለውን የአበው ብሂልን ተከትለው በዘርፉ ለመሰማራት ተስማሙ፡፡

ስለዘርፉ ካማከራቸው ሰው ጋር ሽርክና በመፍጠር አንዲት የሲቲስካን መሳሪያ በመያዝ ሥራውን መጀመራቸውን የሚያስታውሱት አቶ ዳዊት፤ በወቅቱ ማሽኑ በሀገር ውስጥ ባለ ሌላ የጤና ተቋም ያለመኖሩ ብቸኛ ሆነው በመቅረብና በዘርፉ አዲስ እምርታ ለማምጣት ቀን ከሌሊት መስራት ቀጠሉ፡፡ እንዳሰቡትም ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ በመስራትና በማሽኑና በሚሰጠው አገልግሎት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ከሰሩ በኋላ የድርጅታቸውን አገልግሎት በመሻት ወደ ድርጅቱ የሚሄደው ሕብረተሰብ ቁጥር እያደገ መጣ፡፡

በእዚህ መሀል የሥራ አጋራቸው ሥራውን ትቶ ወጣ፤ እነ አቶ ዳዊትም ድርጅቱን ሙሉ ለሙሉ በመረከብ ሥራቸውን አስፋፉ፡፡

ውዳሴ ዲያግኖስቲክስ ማዕከልን እንደከፈቱ በርካታ ተግዳሮቶች አጋጥመዋቸው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ዳዊት፣ በተለይም በወቅቱ የሲቲስካን አገልግሎት በጣም ውድ እንደሆነ በማሰብ ሕብረተሰቡ ወደ እነሱ ለመምጣት ስጋት እንደነበረበት ይጠቅሳሉ፡፡

በተቃራኒው ግን ማንኛውም ታካሚ ሙሉ ምርመራ በማድረግ ለራጅ፣ ለአልትራሳውንድና መሰል ምርመራዎች በተናጠል ከፍተኛ ውጪ እንደሚያወጣ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ጥቂት የማይባለው ሰው ልዩነቱን ባለመረዳት ማሽኑ አዲስ በመሆኑ ምክንያት ይሸሽ እንደነበር፤ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልም እንዳልነበር ጠቅሰው፣ በዚህ ሁሉ ምክንያት የሲቲስካን ምርመራ የሚያዙ በጣም ጥቂት እንደነበሩ ያነሳሉ፡፡

አቶ ዳዊት እንደ ሀገር ያለውን የግንዛቤ ችግር ለመፍታት ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መስራት የግድ ሆኖባቸው እንደነበርም ይገልጻሉ፤ በዚህ ሥራም የበርካቶችን አመለካከት መቀየር መቻላቸውን ያመለክታሉ፡፡

ይህን ተከትሎ የኅብረተሰቡ ፍላጎት እየጨመረ ከመምጣቱም በላይ ከድርጅታቸው አቅም በላይ ሆኖ እንደነበርና በአንድ ማሽን ብቻ በሚፈለገው ልክ አገልግሎት መስጠት ተቸግረው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በቀጠሮ ወደ ማስተናገድ ገብተው የነበረበት ወቅትም ነበር፡፡

በመሆኑም ያላቸውን ጥሪት ሰብስበው ተጨማሪ ማሽን ለመግዛት አሰቡ፤ ይሁንና ባለቤታቸውን ማሳመን በራሱ ትልቅ ፈታና ሆኖባቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ። ‹‹ባለቤቴ ‘መኖሪያ ቤት ሳይኖረን እንዴት ተጨማሪ ማሽን እንግዛ ትላለህ’ ብላ ብዙ ተሟገተችኝ፤ በኋላም ከብዙ ንግግር በኋላ የማሽኑ መገዛት ለድርጅታችን ማደግ ወሳኝ መሆኑን አምና በእኔ ሃሳብ ተስማማችና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውንና 16 ስላይስ ያለውን ሲቲስካን አስመጣን›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡

አዲሱ ማሽን ሲመጣ ደግሞ ውዳሴ ስሙ ከስራው ጋር አብሮ እንደ ተስፋፋ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም ሳይወሰኑ ‘ኤም.አር.አይ’ የተባለውን ሌላውን ዘመናዊ ማሽን ገዝተው የምርመራ አቅማቸውን በከፍተኛ ደረጃ አሳደጉ። በሂደትም በአቅምም ሆነ በሚሰጡት አገልግሎት ስፋት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሌሎች ማሽኖችን በመጨመርና የራሳቸውን ሕንፃ በመስራትም አገልግሎታቸውን ይበልጥ እያሳደጉ መጡ፡፡ በድርጅታቸው የሚሰሩ ሰራተኞችንም ቁጥር በእጅጉ አሳደጉ፡፡

‹‹ይህንን ሥራ ስንጀምር ስምንት ሰዎች ብቻ ነበር የቀጠርነው፤ አሁን ላይ ውዳሴ ዲያግኖስቲክ ማዕከል ብቻ ለ500 ሰዎች የሥራ እድል ፈጥሯል›› የሚሉት የስኬቱ እንግዳችን፤ ከማዕከሉ ባሻገር አኮ ቡና፣ ጆርጎ አካዳሚ የተባለ ትምህርት ቤት ፣ ፍቱን ቴክኖሎጂ ሶልዊሽንስ የተባለው የቴክኖሎጂ ተቋም እንዲሁም ሞአ ኮንሰልታንሲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ሴንተር የተባለ የማማከርና ማሰልጠኛ ተቋም ጭምር በመክፈት በንግዱ ዓለም ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

አክለውም ‹‹አኮ ቡና ብቻውን በኢትዮጵያ ውስጥ 11 ቅርንጫፎች አሉት፤ ዱባይ ላይም የአኮ ቡና ኢትዮጵያዊ ሬስቶራንት ከፍተናል›› ይላሉ፡፡ ውዳሴ ዳያግኖስቲክስ አሁን የራሱን ሆስፒታል እየገነባ መሆኑን ያስረዳሉ። በአምስቱም የውዳሴ ግሩፕ እህት ድርጅቶች ውስጥ ከአንድ ሺ 200 በላይ ሰራተኞች የሥራ እድል እንደተፈጠረላቸውም ያመለክታሉ፡፡

በቀጣይም የሁሉንም ድርጅቶቻችን አገልግሎት የማስፋትና የማጠናከር፤ በተለይም ለሀገርና ለሕዝቡ መፍትሔ የሚያመጡ ሥራዎችን የመስራት እቅድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዚህም ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ዓላማ ይዘው እየተጉ ይገኛሉ፡፡

አቶ ዳዊት ድርጅታቸው ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በርካታ ሥራዎችን እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡ በተለይም አቅም ለሌላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በነፃ የሕክምና አገልግሎት በመስጠትም ስሙ ጎልቶ እንደሚነሳ ተናግረው፣ ‹‹ምንም እንኳን ከምናገኘው ገቢ 20 በመቶውን ለበጎ አድራጎት ሥራ የማዋል እቅድ ቢኖረንም አንዳንድ ጊዜ ከዚያም በላይ በመሆን ሥራችን ላይ ጫና የሚፈጥርበት ሁኔታ አለ›› በማለትም ነው ማኅበራዊ ኃላፊነትን ስለመወጣቸው ያስታወቁት፡፡

እንግዳችን በተሰማረቱበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ የመሆናቸውን ምስጢር ሲናገሩም ‹‹እያንዳንዱ ቢዝነስ ራሱን የቻለ ሰፊ መንገድ አለው፤ እነዚህ ሰፋፊ መንገዶች በሂደት የሚመጡና ራሳቸውን የቻሉ አዙሪቶችም ያላቸው ናቸው፤ የሁሉንም ፈታኝ ነገሮች ማለፍ ይጠበቃል›› ይላሉ፡፡

በተለይ የፋይናንስ እጥረት፣ የልምድ ማነስ፣ ቶሎ ተቀባይነት አለማግኘትና መሰል ችግሮችን በፅናት መጋፈጥ ወሳኝ ነገር መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ድርጅቱ አቅሙ ሲሰፋ ደግሞ ፈጣን እድገት የሚያመጣው አዙሪት ሌላው ማነቆ እንደሆነ ተናግረው፤ ድርጅቱ ባደገ ቁጥርም የዚያኑ ያህል ወጪው የሚበዛና ተንቀሳቃሽ ገንዘብ የሚያጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ወጪ በእቅድ መምራት እንዳለበትና በአቅም መኖር እንደሚያስፈልግም ያብራራሉ፡፡

በሌላ በኩል የትኛውን ሥራ ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችል ፅኑ እምነትም እንደነበራቸውና ይህም አሁን ለደረሱበት ስኬት ወሳኝ ሚና እንደነበረው ይናገራሉ፡፡ ‹‹በአንድ ሥራ ላይ ለመሰማራት የግድ በሙያው የሰለጠነ ሰው መሆን አይጠበቅም፤ ዋናው የራዕይ መኖር፤ ሀገሪቱ ምን እንደምትፈልግ፣ ገበያው ምን ቢሰሩ አዋጭ ሊሆን እንደሚችልና ለማኅበረሰቡ የሚጠቅመውን ማወቁ ነው›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የታሰበው ሥራ ማህበረሰቡን የሚጠቅም እስከሆነና ፍላጎት እስካለ ድረስ ማንም ሰው ስኬታማ የማይሆንበት ምክንያት እንደሌለ ያስገነዝባሉ፡፡ ይሁንና አንድ ድርጅት ስኬታማ ሆነ ማለት ትርፋማ ሆነ ማለት ላይሆን እንደሚችል ጠቅሰው፤ ውጤቱ መለካት ያለበት ካስቀመጠው ግብ አንፃር መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ትምህርት መሰረት እንድንይዝ እድል ይሰጠናል፤ ሥራ ግን የሚፈልገው ክሕሎትን፤ ዝቅ ብሎ የመስራት ተነሳሽነትን፤ ሁሉንም በእኩል የማገልገል ትህትናን፤ ነገሮችን በቅንነት ማየትን፤ አርቆ ተመልካች መሆንን ነው፤ ከተሰጠው ሥራ አልፎ መስራት እንዲሁም ታማኝ መሆንን የሚጠይቅ ነው›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

ከሰርተፍኬት ጋጋታ ይልቅ ዘመኑ ከሚጠይቀው አንፃር ቴክኖሎጂን በአግባቡ የመጠቀም አቅምን መጠቀም ወሳኝ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ከዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተመርቀው የወጡ በርካታ ወጣቶች በሙያቸው ሥራ በመፈለግ ጊዜያቸውን ከማባከን ይልቅ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉና ሥራን ሳይንቁ እንዲሰሩ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን  ጥር 24 2017 ዓ.ም

Recommended For You