“ፀጋዎቻችንን በአግባቡ አውቀን እንዳንጠቀምባቸው የነጠላ ትርክት እሳቤ ሳንካ ሆኖብናል” – ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) በብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ

አዲስ አበባ፦ ሀገራዊ ፀጋዎቻችንን በአግባቡ አውቀን እንዳንጠቀምባቸው የነጠላ ትርክት እሳቤ ሳንካ እንደሆነብን የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ገለጹ። በጋራ የተገነቡ እሴቶችና ታሪኮች ሁሉንም በሚያግባባ፣ በሚያስተሳስርና በሚያቅፍ መንገድ ለኢትዮጵያ ብልፅግና መጠቀም እንደሚገባ አመለከቱ።

ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳመለከቱት፤ ሀገራዊ ፀጋዎቻችንን በአግባቡ አውቀን እንዳንጠቀምባቸው ነጠላ ትርክት ተግዳሮት ሆኗል፤ ትርክቱ የሌሎችን ወደ ጎን በመተው፤ አንዳንድ ጊዜም የሌሎችን በማጠልሸት ስለ ራስ ብቻ ማሰብ፤ የራስን ብሔር ወይም የራስን ሃይማኖት ብቻ በማቀንቀን ላይ የተመሠረተ ነው::

በጎሳ፤ በዘር፤ በአካባቢ፤ በሃይማኖት ላይ የሚያጠነጥን ትርክት የመገንባት ፍላጎት የያዘ፤ የሌሎችን መብት የሚጋፋና ሌሎችን የማያቅፍ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው፤ እሳቤው አሁን ላይ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለመገንባት እየተደረገ ላለው ጥረት ትልቅ ፈተና መሆኑን አመልክተዋል ::

“እኔ የሚለው ነጠላ ትርክት ራሱ በሁለት ጫፎች የተከፈለ ነው:: ግቡም አጠቃላይ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው:: ለኢትዮጵያ ሀገር ግንባታም አይበጅም:: የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋ፣ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እንቅፋት የሚሆን የተቃርኖ ትርክት ነው” ብለዋል ::

ነጠላ ትርክት ሁለት መልክ እንዳለው ያመለከቱት ኃላፊው፤ የመጀመሪያው ፍጹማዊ አንድነትን የሚከተል፤ ኢትዮጵያን አንድና አንድ አድርጎ የሚያይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሃሳብ ልዩነቶችን፣ የሃይማኖት ልዩነትን፣ የብዝኃ ብሔር ማንነትን ሁሉ የማይቀበል ፤በሁሉም ነገር አንድ መልክ ብቻ ያላት ኢትዮጵያ የመመልከት አባዜና ዝንባሌ ያለው ስለመሆኑ አመልክተዋል::

ሁለተኛው ፍጹም ልዩነትን የሚሰብክ ነው:: የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጋራ ተጋምደው የኖሩበትን ሁኔታ የማይቀበል፤ ፍጹም ልዩነትን የሚፈልግ፤ እኔ ራሴን እችላለሁ ብሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን መስተጋብርና ትስስር ለማቋረጥ የሚፈልግ ትርክት እንደሆነ ጠቁመዋል::

በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሕዝቦች የጋራ የሆነ ታሪክ አላቸው:: የጋራ የሆነ ዐሻራ አላቸው:: የጋራ የሆነ እሴት አላቸው፤ እነዚህ በጋራ የገነባናቸውን እሴቶችና ታሪኮች ሁሉንም በሚያግባባ፣ በሚያስተሳስርና በሚያቅፍ መንገድ ለኢትዮጵያ ብልፅግና መጠቀም ይገባል፤ ለዚህ ደግሞ ይህንን የሚሸከም የወል ትርክት ያስፈልጋል ብለዋል።

እኔ በሚለውና እኛ በሚለው መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ:: እኔ የሚለው ሌሎችን ያገላል:: አግላይነት አለው:: እኛ የሚለው የወል ትርክት አቃፊነት አለው:: ሌሎችን የሚያቅፍ ነው:: ሁሉን የሚያቅፍ ነው:: “ከኔ በላይ ላሳር” የሚል አይደለም:: ከኔ በላይ ማን አለ? የሚል አይደለም:: ወይም ለራስ ከፍተኛ ቦታ በመስጠት ሌላውን የሚያንኳስስ የትረካ ስልት እንዳልሆነም ጠቁመዋል ::

የወል ትርክት ሁሉም የራሱ የሆነ ፀጋ አለው ብሎ የሚያምን፤ ሁሉን እኩል የሚመለከት፤ ሁሉን የሚያሰባስብ ፤ በሀገረ ግንባታ ውስጥ ሁሉም የራሱ አበርክቷል አለው ብሎ የሚያምን፤ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የሁሉም ነች:: ሁላችንም በጋራ ያቆየናት፣ የጠበቅናት፣ ሁላችንም መስዋዕትነት የከፈልንላት ሀገር ናት ብሎ የሚያምን እንደሆነም አስገንዝበዋል ::

ከብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ሰማ ጥሩነህ (ዶ/ር) ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ሙሉ ቃል በገጽ 6 ተመልከቱ::

አዲሱ ገረመው

አዲስ ዘመን ጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You