
ኢትዮጵያ ሰፊ የድንጋይ ከሰል ክምችት ቢኖራትም፣ ይህን ሀብቷን ግን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጥቅም ላይ ማዋል ሳትችል ቆይታለች። ለኢንዱስትሪዎቿ በእጅጉ የሚያስፈልጋትን ይህን የድንጋይ ከሰል ለዘመናት ከውጭ ስታስገባ ኖራለች። ለእዚህም በዓመት ከ300 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታደርግ ስለመኖሯ መረጃዎች ያመላክታሉ።
ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን መንግሥት ገቢ ምርቶችን ለመተካት በቀየስው ስትራቴጂ የድንጋይ ከሰልን በሀገር ወስጥ ምርት በመተካት ላይ በትኩረት ተሰርቷል። በማኅበር የተደራጁም በኩባንያ ደረጃ ያሉም ፈቃድ ወስደው ወደ ልማቱ መግባታቸውን ተከትሎ የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ምርት መተካት የሚቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ምርቱን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካትም እየተሰራ ነው።
ከድንጋይ ከሰል ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር ለመፍታትም የድንጋይ ከሰል የሚያጥቡ ኩባንያዎች ግንባታዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል። ከእነዚህ አምራቾች መካከል አንዱ የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማህበር ነው።
አክሲዮን ማኅበሩ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በዳውሮ ዞን በተርጫ አካባቢ በድንጋይ ከሰል እጥበት ሥራ ለመሰማራት ፈቃድ ወስዶ ወደ ሥራ የገባው በ2014 ዓ.ም ነው።
ፋብሪካው በሰዓት 150 ቶን የድንጋይ ከሰል በማምረት የሀገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን ለማሟላት ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ሀገሪቱ ለድንጋይ ከሰል የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት እንዲሁም ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል ለመፍጠር እንደሚችልም ታምኖበታል።
ይህ በሀገሪቱ የመጀመሪያው የተባለ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ ባለፈው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ሥራ አስጀምሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ሥነሥርአት ላይ፤ ‹‹ዛሬ የተመለከትነው ልማት የሚያሳየው የተገለጠ አይንና የጠራ ሃሳብ ሲኖር ባጭር ጊዜ አገርን እንዴት መቀየር እንደሚቻል የሚያመላክት አቅም ኢትዮጵያ እንዳላት ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በሀገሪቱ ግብርናን በከፍተኛ ደረጃ የለወጠ፣ ምርትና ምርታማነትን ያሳደገ፣ ኢትዮጵያን ከድህነትና ከተረጂነት የሚያላቅቅ ምቹ ሁኔታ ስለመፈጠሩ በሁሉም ዘንድ በግልጽ ይታወቃል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሉ የዳውሮ ዞንም የዚህ ምቹ ሁኔታ ተጠቃሚ ሆኖ ቆይቷል። ዳውሮ በቱሪዝምና በማዕድን እምብዛም አይታወቅም ነበር። በቱሪዝም ረገድ የዳውሮ ንጉስ የካዎ ሀላላ አሻራ ያረፈበት የሀላላ ኬላ ግንብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ኩራት መሆን የሚገባው ታላቅ ሥራ ነው። ይህ ሀብት ባለቤት አልባ ሆኖ ለብዙ ዘመናት ተዘንግቶ ቆይቷል።
የካዎ ሀላላ ኬላን በተለየ ሁኔታ እንድናደንቅ ካደረጉን ምክንያቶች አንዱ ግንባታው 48 ዓመታትን የፈጀ መሆኑ ነው። ትውልድ ከትውልድ እየተቀባበለ ሰርቶታል። በአንድ ዘመን ተጀምሮ ያለቀ ፕሮጀክት አይደለም፤ አባቶች አቅደው ጀምረው ልጆች ተከትለው የጨረሱት ነው።
ይህን ማስታወስና በዓለም ሕዝብ ዘንድ እንዲታይና እንዲታወቅ ማድረግ መቻላችን ክልሉና ዞኑ ከፍተኛ የቱሪስት መስህብ እንዳላቸው ከሚያሳዩ ጅምር ሥራዎች መካከል አንዱ ነው፤ ይህ ማለት ግን ሌላ ሥራ የለም ማለት አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በቅርቡ በጋምቤላ ክልል የዲማ የወርቅ ፋብሪካ ተመርቋል። አሁን ደግሞ በዳውሮ ዞን ተርጫ አካባቢ ይህን የመሰለ የድንጋይ ከሰል ማምረቻ ፋብሪካ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በዚህ መንገድ ተሰርቶ ወደ ማምረት ሥራ ተሸጋግሯል።
‹‹ይህም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አፍሰን ወደ አገር ውስጥ ስናስገባ የነበረውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እንዲሁም በድንጋይ ከሰል ያለንን ሰፊ አቅም በቀጣይ ደግሞ ወደ ውጭ ለመላክ ዕድል ይሰጠናል›› ሲሉ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ፋብሪካው በሀገር አቀፍ ደረጃ ድንጋይ ከሰል የማምረት አቅምን ከማሻሻል ባሻገር ለበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል ይፈጥራል፣ ሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ ስታስገባ የኖረችውን የድንጋይ ከሰል በማስቀረት ምርቱን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የበኩሉን ሚና ሊጫወት ይችላል።
የደቡብ ምዕራብ ክልል በማዕድን ሀብት የበለጸገ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአካባቢው መዋዕለ ነዋያቸውን ሥራ ላይ ማዋል ለሚፈልጉ ሁሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም አስታውቀዋል። የግሉ ዘርፍ ወደዚህ አካባቢ መጥቶ ተጨማሪ ፋብሪካዎች እንዲገነባም ጥሪ አቅርበዋል። ጅማንና ሚዛንን ጨምሮ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ጠቁመው፣ በአካባቢው ያለውን ለሸክላ የሚሆን ቀይ አፈር በመጠቀም የሸክላ ሥራ መስራት እንደሚቻልም አስታውቀዋል። በተወሰነ ደረጃ ያለውን የኖራ/ላይም/ሃብትም ጥቅም ላይ ለማዋል መጠነኛ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መሰራት እንደሚቻልም አመልክተዋል። ይህን በማድረግ ቢያንስ የአካባቢውን ፍላጎት መመለስ እንደሚቻልም ገልጸዋል።
ለልማት ወሳኝ የሆኑ ፖሊሲ፣ ወሳኝ የሆነ ሰላም፣ ወሳኝ ተባባሪና ደጋፊ ሕዝብ ያለበት አካባቢ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ከማዕድን ፋብሪካዎች በተጨማሪ ሌሎች ኢንዱስትሪዎችን እውን በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ብዝሃ ዘርፍ የሚባል ሃሳብ በዚህ አካባቢ ዕውን ማድረግ እንደሚቻል አስታውቀዋል። ይህም የሕዝቡን የኑሮ ደረጃ እንደሚያሻሽል፤ አገሪቱን ከደህንነት እንደሚያላቅቅ፣ እንደ ሀገር የታሰበውን ብልጽግና ለመጨበጥ እንደሚያስችል አመልክተው፣ ባለሀብቶች ወደዚህ አካባቢ መጥታችሁ ኢንቨስት አድርጉ በማለት ከአደራ ጭምር አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ የክልሉ ሕዝብ የአካባቢውን ሰላምም መጠበቅ ይኖርበታል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ትልቅ አለው። ታይቶ አይጠገብም፤ በመልከዓምድሩ፣ በአየር ሁኔታው በከርሰምድር ሃብቱ በተለየ መንገድ ተባርኳል።
ይህን በረከት ማውጣት እንዲቻል በውስጣችን ያለው ሰላም በእጅጉ አስፈላጊ ነው ሲሉም አመልክተው፣ ሰላማችሁን ለመጠበቅ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በከፍተኛ ትብብርና በቅንጅት ስሩ ሲሉም አስገንዝበዋል። በአካባቢው የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የጋምቤላና ኦሮሚያ ክልሎች እንዳሉም ጠቅሰው፣ ከእነሱ ጋር ተባብራችሁ ብትሰሩ ሰፊ ገበያ ማግኘት እንደሚቻል፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመልማትና ለማደግም እንደሚያግዝ አስታውቀው፣ ‹‹ሰላማችሁን ጠብቁ ሲሉ አስገንዝበዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የበርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች መኖሪያ ነው። ሁላችንም የሰው ዘርና ወንድማማች ስለሆንን በሚያለያዩን ጉዳዮች ሳይሆን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ተባብረን የአካባቢያችንን ሰላም ጠብቀን ልማትን ልናፋጥን ይገባል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
‹‹በክልሉ ዳውሮ ዞን መዋዕለ ንዋዩን አፍስሶ የሚከስር የለም›› ሲሉም ጠቅሰው፣ በክልሉ መዋዕለ ነዋያቻውን ሥራ ላይ ላዋሉት የኢቲ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር ባለቤቶች ምስጋና አቅርበዋል፤ ፋብሪካው ውጤታማ እንዲሆንም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋልም ብለዋል።
የማዕድን ሚኒስትሩ ሃብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) በበኩላቸው በዚሁ ወቅት የተመረቀውን ፋብሪካ ጨምሮ በዚህ ዓመት ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ የሚገቡ አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ምርቱን በመተካት የውጭ ምንዛሪን ለማስቀረት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት የታጠበ የድንጋይ ከሰል ከውጪ ስታስገባ እንደነበርም አስታውሰዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በአይነትም፣ በብዛትም ሆነ በጥራት በርካታ የማዕድን ሀብት ቢኖራትም፤ ይህንን ሀብት አውጥታ ስትጠቀም አይስተዋልም። ዘርፉ በዓለም ላይ የቆየና እየተሰራበት ያለ ቢሆንም በሀገራችን ደግሞ አዲስ ዘርፍ ነው። ከለውጡ በኋላ በማዕድን ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶት አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ መደረጉ አበረታች ለውጦችን እያመጣ ይገኛል።
ሀገሪቱ ካሏት በርካታ አይነት ማዕድናት መካከል አንዱ የድንጋይ ከሰል ነው። የድንጋይ ከሰል በብዙ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ይገኛል። የድንጋይ ከሰል በከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በተለይ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ጥቅም ላይ ይውላል። ‹‹እኛ የድንጋይ ከሰል እንደ ሌሎች አገራት ለኢነርጂ አንጠቀም። በዓለም ላይ ከ40 በመቶ በላይ የሆነ ኢነርጂ በድንጋይ ከሰል ይሸፈናል። እኛ በአብዛኛው የምንጠቀመው በሃይድሮ ኢነርጂ የሚመነጭ ኃይል ነው›› ብለዋል።
ቀደም ሲል ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በድንጋይ ከሰል አቅርቦት እጥረት ሲቸገሩ እንደነበር አስታውሰው፣ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ለማምጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥር ይገጥም እንደነበርም ገልጸዋል።
በዚህ ላይ የድንጋይ ከሰል በሚመጣባቸው አገራት ላይ ችግር ሲከሰት የሲሚንቶ ፋብሪካዎቹ ማምረት የሚችሉበት ሁኔታ ያጋጥም እንደነበርም አስታውሰዋል። የድንጋይ ከሰል ሀብቱ እያለን ከውጭ ለምን እናመጣለን የሚል አቋም በመያዝ የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ወደ ማምረት መገባቱን አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ በአገሪቱ የድንጋይ ከሰል በተለያየ መንገድ በአነስተኛ ደረጃ ይመረታል። ይህ ምርት ግን የሚፈለገውን ያህል የሀገር ውስጥ ፍላጎትን የሚያሟላ አልነበረም። ሲሚንቶ ፋብሪካዎች የሚፈልጉትን የጥራት ደረጃ ያለማሟላት ይስተዋል ነበር። ለእዚህ ደግሞ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ አስፈልጓል። ይህ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ የመጀመሪያ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካ የተተከለ እውን የተደረገውም ይህን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት የአራት የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎችን ግንባታ አጠናቆ ወደ ሥራ በማስገባት የሀገር ውስጥ ፍጆታ ሙሉ ለሙሉ መሸፈን እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ፋብሪካዎቹ በሙሉ አቅማቸው መሥራት ሲጀምሩ በዓመት ኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል በተጨማሪ እስከ 400 ሺህ ቶን ትርፍ ማምረት ይችላሉ። በቅርቡ ተመርቆ ሥራ የጀመረው ፋብሪካም በዓመት 450 ሺህ ቶን ያለቀለትና ጥራት ያለው የድንጋይ ከሰል ያመርታል። ይህም የሀገሪቱን 25 በመቶ የድንጋይ ከሰልን ፍላጎት የሚሸፈን ነው። የሀገር ውስጥ ፍጆታ ሙሉ ለሙሉ መሸፈን ከተቻለ ደግሞ ቀሪውን ወደ ውጭ ለመላክ ይሰራል።
በሀገሪቱ ከወርቅም በላይ የአገርን ኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ መቀየር የሚችሉ በርካታ የማዕድን ሀብቶች እንዳሉ ጠቅሰው፣ በእነዚህ ላይ ሁሉ መስራት እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።
‹‹የማዕድን ዘርፉ የኢኮኖሚ ምሰሶ ከተባሉ አምስት ዘርፎች አንዱ ነው። ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት የማዕድን ሀብቱ ስላለ ነው›› የሚሉት ሚኒስትሩ፤ ‹‹በዘርፉ ሀብት ካለ ኢኮኖሚያችንን በዚህ ላይ የማናደርግበት ምንም አይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም፤ ባላደገ ግብርናና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ብቻ ከመወሰን በመውጣት ባለን በርካታ የማዕድን ሀብት ተጠቅመን ሀብት ማመንጨት እንችላለን››ብለዋል።
ይህ ዘርፍ ለኢኮኖሚው ዋና ከሚባሉት ምሰሶዎች አንዱ ሆኗል ማለት ደግሞ ራሱን የቻለ ፖሊሲ፣ ስትራቴጂና የሕግ ማሕቀፍም አሉት ማለት እንደሆነም አስታውቀዋል። ዘርፉ በባሕሪው ከፍተኛ የሆነ ቴክኖሎጂ፣ ኢንቨስትመንት እንደሚጠይቅ አመልክተው፣ ማበረታቻና ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈልግ ገልጸዋል። ከላይ እስከታች ያለው የመንግሥት መዋቅር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ በዚህ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት እንዲደረግ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
በተለይ በታዳጊ ሀገራት ማዕድን ለማውጣት ዋንኛ ተግዳሮት የሚሆነው ምን ያህል የማዕድን ክምችት አለ የሚለውን መለየትና ማወቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ የማዕድን ዳታ በማግኘት ላይ ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ባለፉት ስድስት ወራት ተግባራዊ በተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። እስካሁን በማዕድን ዘርፉ የሚገኘው ገቢ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሆኖ አያውቅም። ይህ አሀዝ በተያዘው በጀት ዓመት በግማሽ ዓመቱ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን እየደረሰ ነው። ይህም ውስን ሀብቶችን ኤክስፖርት በማድረግ የተገኘ ስኬት መሆኑን ጠቅሰው፣ ብዙዎቹ ማዕድናት ገና እንዳልተነኩ ገልጸዋል።
ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ያለባቸውን ከፍተኛ የሆነ የኃይል እጥረት ለመፍታት፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች በሀገር ውስጥ ከተገነቡ በኋላ የተፈጠረውን የድንጋይ ከሰል ፍላጎት ለመመለስ ከውጭ ይመጣ የነበረውን የድንጋይ ከሰል ምርት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በከበሩ ማዕድናትና በሌሎች ማዕድናት ዘርፍም እንዲሁ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ፣ በዘርፉ ከኤክስፖርት፣ ከተኪ ምርት እና ከሥራ እድል ፈጠራ አንጻር አበረታች ለውጦች ማምጣት ተችሏል ብለዋል።
የማዕድን ሥራ የረጅም ዓመት ኢንቨስትመንት እንደሚፈልግ ተናግረው፣ ውጤቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይታይ ገልጸዋል። ‹‹ፈጥነን፣ ልምዶችን ወስደን ትኩረት ሰጥተን ከሰራን ግን በአጭር ጊዜ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ ሊደግፍ የሚችል ኢንቨስትመንት ነው›› ሲሉ ተናግረዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም