ጦርነት ውድመት እንጂ…

ጦርነት ሰው በላ ነው። ጦርነት ባለበት ውድመት እንጂ እድገት አይታሰብም። ከጦርነት ሽንፈት እንጂ ድል የለም። ጦርነት ሺዎችን የሚበላ፤ ሚሊዮኖችን የሚያፈናቅል፤ ቢሊዮን ብሮችን እንደቀልድ ዶጋ አመድ የሚያደርግ፤ ሕጻናትን ያለወላጅ የሚያስቀር እናቶችን ጧሪ እና ቀባሪ የሚያሳጣ ክፉ ደዌ ነው።

ይኸው ሐቅም ዛሬ ጦርነት እና ግጭት ባለባቸው የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተመለከትነው ነው። ለዚህ አባባላችንም ከአማራ ክልል በላይ አስረጂ ማግኘት አይቻልም። አማራ ክልል በግጭት አዙሪት ውስጥ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ጥፋቶች እና ውድቶች ታይተዋል። ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፤ ተማሪዎች ቤት ውለዋል፤ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች በግጭቱ ስለተጎዱ ተገቢውን ሕክምና መስጠት ተስኗቸዋል። በዚህም የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች ወደ ኋላ ተመልሰዋል።

በአማራ ክልል ግጭት ከተከሰተ ወዲህ ከ4ነጥብ7 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል። በርካታ ታዳጊዎች እንደእኩዮቻቸው ተምረው ነገን በተስፋ ከማየት ይልቅ ቤት ለመዋል እና የከብት እረኛ ለመሆን ተገደዋል። ታዳጊ ሴቶችም ለጠለፋ፤ ካለእድሜ ጋብቻ እና አለፍ ሲልም ለአስገድዶ መድፈር ተጋልጠዋል።

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ሰሞኑን ይፋ እንዳደረገውም ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ አስፈልጓል። ለአብነትም በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከ400 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ቢሮው ገልጿል፤ በአጠቃላይ በክልሉ ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች ወደ አገልግሎት ለመመለስ 112 ቢሊዮን ብር ያስፈልጋል።

በሌላም በኩል የክልሉ ጤና ቢሮ እንደገለጸውም፤ በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት የጤና ሥርዓቱን በእጅጉ ስለጎዳው ጠፍተው የነበሩ በሽታዎች ጭምር እንደአዲስ መታየት ጀምረዋል። ጦርነቱ በፈጠረው እክል ምክንያት አራት ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ደግሞ የጤና አገልግሎት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሆነው ተገኝተዋል።

ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ የክልሉ የአደጋ ስጋት ቢሮ ይፋ እንዳደረገውም አሁን ላይ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። ከዚህ ውስጥ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ያህሉ አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው።

ይህ ሁሉ የሰላም እጦት ያመጣው ጣጣ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀግንነቱን ያህል ሰላም ወዳድም ነው። በየትም ሥፍራ ቢኖር፣ የትኛውንም እምነት ቢከተል፣ በተለያዩ ቋንቋዎች ቢገለገል፣ ባሕሎቹና ልማዶቹ ቢለያዩም ለሰላምና አብሮነት ሰፊ ቦታን ይሰጣል። ሰላም የእሴቶቹ አንዱ መገለጫ ነው።

ይህም ሆኖ ከዚህ የኢትዮጵያውያን ባሕል ባፈነገጠ መልኩ ፍላጎታቸውን በነፍጥ ማሳካት የሚፈልጉ ቡድኖች እየተበራከቱ መጥተዋል። ከውይይት ይልቅ ነፍጥ ማንሳት የሚቀናቸውና ሰላም ወዳዱን ሕዝብ የሚረብሹ፤ አብሮነቱን የሚያውኩ፤ የኢትዮጵያን መረጋጋትና ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ ቡድኖች እዚህም እዚያም አቆጥቁጠዋል።

እነዚህ ወገኖች በሚፈጥሩት ሁከትና ብጥብጥም ልማት ተደናቅፏል፤ የሰዎች ወጥቶ መግባት ተስተጓ ጉሏል፤ አለፍ ሲልም የሀገር ሕልውናንም አደጋ ላይ ወድቋል። ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ ተጠምደው ይታያሉ።

እነዚሁ ኃይላት ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የሀገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ለሀገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ ሳይቀር በቁሙ ሲዘርፉ ተስተውለዋል።

እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት ስለሚቀናቸው የማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕዝቡን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ። በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳለፍ ተገዷል።

ከዚህ ድርጊታቸው የሚያስቆማቸው የፀጥታ ኃይል ሲመጣ ደግሞ ግብረ አበሮቻቸውን ሰብስበው በሰፊው ስም የማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ይገባሉ። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ለብሶ ታላላቅ ድሎችን የተጎናፀፈውን ጀግና የመከላከያ ሠራዊታችንንም በማጠልሸትም ኢትዮጵያን ለማሳነስም በቀቢጸ ተስፋ ሲሯሯጡ ይታያሉ ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡ እጅግ በጣም ሰላማዊና ለሕግ ትልቅ ትኩረት ስለሚሰጥ ለአመፅና ለብጥብጥ ሥፍራ የለውም እንጂ የእነዚህ አካላት ድርጊት ሀገርን የማፍረስ ዓላማ ጭምር ያለው መሆኑ አደገኝነቱ ከሚገመተው በላይ እንደሆነ ከማንኛውም ሀገሩን ከሚወድ ዜጋ የተሰወረ አይደለም ።

መንግሥት በሆደ ሰፊነት በጥፋት ተልዕኮ ላይ ያሉ የጥፋት ቡድኖች ወደ ሰላም እንዲመለሱ በተደጋጋሚ ጥሪ አድርጓል። በምክክር እና ውይይት አሉ የሚባሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ የምክክር ኮሚሽን አቋቁሞ ወደ ተግባር ከገባ ከሁለት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል።

ከጦርነት ግጭት ይልቅ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባሕልም እንደሀገር ሊጎለብት ይገባል። የሥልጣኔም አንዱ መለኪያም ይኸው ነውና። በኢትዮጵያ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ውስጥም ሆነ በሌሎች መስኮች የተሰማሩ ወገኖች፣ ለውይይት ቅድሚያ መስጠት አለባቸው።

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተጋረጡ በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት። የሀገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ ለመነጋገርና ለመደማመጥ ጊዜ መስጠት አለባቸው። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የኑሮ ውድነት አለ። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተካሄደው ጦርነት አላገገምንም፤ ሥራ አጥነት አሁንም አሳሳቢ ነው ነው፤ አሁንም ከድህነት ያልወጣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ አለ።

ስለዚህም እነዚህን ችግሮች ለመሻገርና የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሰላም ወሳኝ ነው። ሰላም ለማምጣት ደግሞ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሣሪያ ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ ቁጭ ብሎ የመነጋገር እና የመወያየት ባሕል ማዳበር ይገባል።

አሊሴሮ

አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You