
አዲስ አበባ፡- የፀደቀው አጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ የመምህርነት ሙያን የሚያስከብር፣ የትምህርት ጥራት ጉድለትን የሚቀርፍ እና የተማሪዎችን የሞራል ልዕልና የሚያሳድግ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትላንትናው እለት ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ጉባኤ የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅን አፅድቋል።
በምክር ቤቱ የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) የውሳኔ ሀሳቡን ባቀረቡበት ወቅት እንዳብራሩት፤ የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጁ የመምህርነት ሙያን የሚያስከብር፣ የትምህርት ጥራት ጉድለትን የሚቀርፍ፣ የተማሪዎችን የሞራል ልዕልና ከፍ የሚያደርግ እና ትምህርትን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዝ ነው። በተጨማሪም አዋጁ ሴት መምህራንን በብዛት ለማፍራት እና ወደ ትምህርት አመራርነት ለማምጣት ልዩ ድጋፍ ያደርጋል።
አዋጁ የትምህርት ቤቶችን አደረጃጀት የሚያስተካክል እና በሥርዓተ ትምህርት አካሄድ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የነበረውን ክፍተት የሚያጠብ እንደሆነ ሰብሳቢው ገልጸዋል።በመሆኑም በሀገር ውስጥ የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች እና የውጭ ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ቢሮዎች ጋር በቅርበት እንዲሠሩ የሚያስችልና የመማር ማስተማር ሂደቱ የሀገሪቱን እሴት ጠብቆ እንዲካሄድ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የአስተማሪነት ሙያ እንዲከበር በሂደትም የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ለመስጠት ረቂቅ አዋጁ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። አዋጁ በተፋጠነ ዝውውር መርሑ ፈጣን የአዕምሮ እድገትና የመማር ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች የትምህርት ካላንደሩን ሳይጠብቁ ከክፍል ወደ ክፍል ዝውውር እንዲያደርጉ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል።በተፋጠነ የትምህርት አሠራሩም በመደበኛው ትምህርት መርሐ-ግብር ተጠቃሚ ያልሆኑ ልጆች፣ ከእድሜያቸው ጋር ተስማሚ በሆነ ሥርዓተ-ትምህርት ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት በፍትሐዊነት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱን የሚመለከቱ ሕጎችና ደንቦች በተበታተነ መልኩ በሥራ ላይ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ የአጠቃላይ ትምህርት አዋጁ መፅደቅ እነዚህን ችግሮች የሚፈታ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጥናት ተሳታፊ እንደነበሩ አስታውሰው፤ በቀጣይ አዋጁን መሠረት አድርገው በሚዘጋጁ መመሪያዎችና ደንቦች ላይም ተመሳሳይ ተሳትፎ የሚያደርጉ ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የአጠቃላይ ትምህርት ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1368/2017 ሆኖ በሁለት ተቃውሞ፣ በአሥር ድምፀ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም