ዛሬ በሚጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 ከተካሄዱ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል በፓሪስ አስተናጋጅነት የተካሄደው ኦሊምፒክ በቀዳሚነት ይታወሳል:: ኦሊምፒክ በበርካታ ስፖርቶች ውድድር የሚካሄድበትና ተወዳዳሪዎችም በድንቅ ብቃት ለመፎካከር ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት መሆኑ ትልቅ ትኩረት ይሰጠዋል:: በመድረኩ ብቻም ሳይሆን በዓመቱ ከታዩ ኮከብ አትሌቶች መካከል አንዱ ደግሞ ኢትዮጵያዊው የማራቶን አትሌት ታምራት ቶላ ነው::
ከስፖርታዊ ውድድሮች በፈታኝነታቸው ቀዳሚ በሚል በሚቀመጠው ማራቶን ታምራት ቶላ የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ታሪክ አምስተኛው አትሌት ለመሆን ችሏል:: ይህ የሆነው ደግሞ የመድረኩን ክብረወሰን 2:06:26 በሆነ ሰዓት በማሻሻል ጭምር መሆኑ ክብሩን እጥፍ ያደርገዋል:: ይህንን የአትሌቱን ድንቅ ብቃት የተመለከተው የዓለም አትሌቲክስም ዓመቱን በተለያዩ ርቀቶች ከፋፍሎ ሲያስታውስ በማራቶን ለታምራት ተሳትፎና ብቃት ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል:: የ33 ዓመቱን ወጣት ድል ልዩ የሚያደርገው በቡድኑ በተጠባባቂነት ተይዞ ወደ ፈረንሳይ ካቀና በኋላ በአትሌት ሲሳይ ለማ ጉዳት ተተክቶ በመሮጥ ማሸነፉ ነው::
ታምራት ወደ ጎዳና ላይ ሩጫዎች ፊቱን ከማዞሩ አስቀድሞ በ10ሺ ሜትር ሀገሩን ወክሎ በበርካታ ውድድሮች ውጤታማ ነበር:: እአአ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው:: በፓሪስ ደግሞ ሁለተኛውን የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ሊያሳካ ችሏል:: በወቅቱ የነበረውን ሁኔታም ከዓለም አትሌቲክስ ድረገጽ ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት አስታውሷል:: ኮረብታዎች በሚበዙበትና ሞቃት በነበረው የአየር ሁኔታ እንዴት ክብረወሰን ሊያስመዘግብ እንደቻለ የተጠየቀው ታምራት ‹‹በፓሪስ እጅግ ከባድ ውድድር ቢሆንም በአእምሮዬ መሸነፍ እንደሌለብኝ ሳስብ ነበር:: ምክንያቱም ሀገሬ በመም ውድድሮች አንድም የወርቅ ሜዳሊያ ማሳካት አልቻለችም:: ማራቶን ደግሞ የመጨረሻው እድላችን በመሆኑ ያለኝን ሁሉ ለማውጣት ጥረት አደረግኩ›› ሲል መልሷል::
በውድድሩ ከ27ኛ እስከ 30ኛው ኪሎ ሜትር ያለው ርቀት ዳገታማ መሆኑ ፈታኝ ቢሆንበትም ታምራት ግን ሰዓቱን እያሰበ በመሮጥ ክብረወሰኑን ማሻሻሉ እንዳኮራውም ተናግራል:: ‹‹በአትሌቲክስ ፈታኝ ሁኔታዎች የስፖርቱ አካል ናቸው፤ ስለሆነም ሁሌም ለሀገራችን ውጤታማነት እንጥራለን›› ሲልም የብርታቱን ምክንያት ጠቁሟል:: እአአ በ2022 በዩጂን ዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ላይ ታምራት የወርቅ ሜዳሊያ በማራቶን ለሀገሩ ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው:: ቻምፒዮናውን ከኦሊምፒኩ ጋር ሲያነጻጽረውም በርካታ የማራቶን ስኬታማ አትሌቶች የተሳተፉበት መሆኑ ከባድ እንደሚያደርገው ተናግሯል::
‹‹በሪዮ ኦሊምፒክ 10ሺ ሜትር ነሐስ ካስመዘገብኩ በኋላ በቀጣዩ ዓመት የለንደን ዓለም ቻምፒዮና በማራቶን ተሳትፌ የብር ሜዳሊያ ነበር ያገኘሁት:: ዩጂን ላይ ደግሞ ወርቅ በማጥለቅ በማራቶን ችሎታዬን ማስመስከር ችያለሁ:: በዚህም እጅግ ደስተኛ ነበርኩ፤ ምክንያቱ ደግሞ ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኋላ ነው ለሀገሬ አሸናፊ የሆንኩት:: በ2023 በሆድ ህመም ምክንያት ማሳካት ባልችልም በፓሪስ ኦሊምፒክ ግን የበለጠውን ድንቅ ስኬት አግኝቻለሁ›› የፓሪስ ኦሊምፒክ ከመካሄዱ አስቀድሞ ከቡድኑ አባላት (ሲሳይ ለማ፣ ደረሰ ገለታ እና ቀነኒሳ በቀለ) ጋር ለሶስት ወራት ሲለማመድ የቆየው ታምራት በኦሊምፒኩ ባይሳተፍ ኖሮ ዝግጅቱ ለኒውዮርክ ማራቶን ይሆን እንደነበረም ያስታውሳል::
በተጠባባቂነት ተይዞ ውድድሩ ሁለት ሳምንታት ሲቀሩት ተወዳዳሪ እንደሚሆን ሲነገረውም ‹‹ደስተኛ ነበርኩ፤ ነገር ግን ለሲሳይ ሀገሩን የሚወክልበት ውድድር በመሆኑ ስሜቱ ቀላል ባይሆንም ተጎድቶ ከመሮጥ እኔ እንድሳተፍ ነበር የነገረኝ:: ወደ ውድድሩ ስጓዝም አስብ የነበረው ኬንያዊውን ኢሉድ ኪፕቾጌ እና ሌሎች ጠንካራ አትሌቶችን እንዴት መርታት እንደምችል ነበር:: ጠንካራ ልምምድ ማድረጌ እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ርቀቶች ወደፊት መውጣቴ ግን ማሸነፍ እንደምችል አረጋገጠልኝ:: አንጋፋው አትሌት ገዛኸኝ አበራ ማራቶንን ካሸነፈ በኋላ ላለፉት 24 ዓመታት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ማራቶን ወርቅ አላስመዘገበችም:: በመሆኑም ከረጅም ጊዜ በኋላ ተሳክቶልኝ ከአበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴ እና ገዛኸኝ አበራ ጋር ለመጠራት በመብቃቴ ደስተኛ ነኝ:: በኦሊምፒኩ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ለሀገሬ በማስመዝገብ ለሕዝቡ ደስታ ምክንያትም ሆኛለሁ›› ሲልም ሁኔታውን አብራርቷል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 22 ቀን 2017 ዓ.ም