አገልግሎቱ በተያዘው በጀት ዓመት አንድ ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ

አዲስ አበባ፡- ከሐምሌ እስከ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 443 ሺህ 147 ጉዳዮችን አስተናግዶ አንድ ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት አስታወቀ::

የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዓለምእሸት መሸሻ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ ሰነዶችን ከሕግና ከሞራል ጋር የማይጻረሩ መሆናቸውን እያረጋገጠ የመመዝገብ አገልግሎት ይሰጣል:: ከሐምሌ 2016 እስከ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ 443 ሺህ 147 ጉዳዮችንና 719 ሺህ 073 ተገልጋዮችን አስተናግዷል:: በዚህም አንድ ነጥብ 25 ቢሊዮን ብር ሰብስቦ ለመንግሥት ገቢ አድርጓል ብለዋል::

በበጀት ዓመቱ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ከአገልግሎቱ የሚወጡ ሰነዶች ‹ሴኪዩሪቲ ፊቸር ያላቸውና ኤሌክትሮኒክስ ማኅተም እንዲያርፍባቸው በማድረግ በቀላሉ ተመሳስለው የማይሠሩ ሰነዶችን በመስጠት ላይ ይገኛል:: ከክልሎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የበይነ መረብ ትስስር በመፍጠር ሐሰተኛ ሰነዶችን ለመከላከልና ባለጉዳዮችን ከአንዱ ተቋም ወደሌላው እንዳይጉላሉ ማድረግ የሚያስችል አሠራርም መዘርጋት መቻሉን አብራርተዋል:: ይህም የተገልጋዩን ጊዜ፣ ሀብትና ጉልበት ብክነት ማስቀረት አስችሏል ::

ከዚህም በተጨማሪ ተገልጋዮች ወደ ተቋሙ ከመምጣታቸው በፊት ቀጠሮ መያዝ የሚችሉበትን አሠራር ለመዘርጋት የሙከራ ትግበራ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ በተሠሩ የሪፎርም ሥራዎች ተገልጋዩ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት አገልግሎት እያገኘ ነው:: ክፍያዎች የሚከናወኑትም በኤሌክትሮኒክስ መንገዶች ነው:: ይህም የተቋሙ ተገልጋዮች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ማስቻሉን ጠቅሰዋል::

ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጎን ለጎን የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ አዲስ አበባ በሚገኙት 16 ቅርንጫፎቹ እያከናወነ ነው ያሉት አቶ ዓለምእሸት፤ በበጀት ዓመቱም ከ44 ሺህ በላይ ዜጎችን ለዲጂታል መታወቂያ መዝግቧል ነው ያሉት::

ከኅዳር አንድ ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ማንኛውም አገልግሎት ፈላጊ ወደተቋሙ ለአገልግሎት ሲመጣ ዲጂታል መታወቂያ መያዝ እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል::

በቀጣይነትም የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና የተገልጋዮችን እርካታ ለመጨመር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚው አቶ ዓለምእሸት መሸሻ ጠቁመዋል::

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You