ዜና ሐተታ
የጋሞዋ ቆላ ሙላቶ ቀበሌ ሴት አርሶ አደሮች እንደሁልጊዜው በአርሶ አደር ማሠልጠኛ ማዕከሉ ማልደው ተገኝተዋል። በእድሜ ገፋ ያሉት ቁጭ ብለው አፈር እየደቁ ያደቃሉ፤ ወጣቶቹ ደግሞ የላመውን አፈር ልክ እንደ እህል ይነፋሉ፤ ያበጥራሉ። ሌሎቹ ደግሞ እንደ ዱቄት የላመውን አፈር በተዘጋጀው የፕላስቲክ ከረጢት ሞልተው በአንድ መስመር ይደረድራሉ። ከፊሎቹ ደግሞ የለሙትን ችግኞች በመንከባከብ ሥራ ተጠምደዋል። ይህ ሥራ ታዲያ በቀበሌዋ በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ-ግብር ተጠቃሚ የሆኑ መሥራት የሚችሉ የአብዛኞቹ ነዋሪዎች የሚሳተፉበት ነው።
አፈሩን በዘነዘና መሰል ወፍራም እንጨት በመድቃት ሥራ ላይ ከተጠመዱት እናቶች መካከል ወይዘሮ ወተኬ ዋዳ አንዷ ናቸው። ምዕራብ አባያ ወረዳ ቆላ ሙላቶ ቀበሌ የተወለዱባትና ያደጉባት ቀዬ ብቻ ሳትሆን ተድረው ወግ ማዕረግ ያዩባትም ጭምር ናት። ከወጣትነት እስከ ጎልማሳነት እድሜያቸው ድረስ በላባቸው ሃብት ያፈሩት፤ ባላሰቡት ሁኔታ ተመልሰው ወደ ድህነት የገቡት፤ ክፉውን ደጉንም ያዩት በዚህችው ቀበሌ እንደሆነ ይናገራሉ።
አርሶ አደር ዋተኬ ባለቤታቸውን በሕይወት ካጡ በኋላ ስድስት ልጆቻቸውን የማሳደግ ኃላፊነት እርሳቸው ላይ መውደቁን ይገልጻሉ። ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ፤ ማሳቸውን እያሳረሱ ቤተሰባቸውን ያስተዳደሩ የነበሩት እኝሁ አርሶአደር፤ አንዲት ቀን ግን ኑሯቸውን ከድጡ ወደ ማጡ የሚያደርግ ክስተት ተከሰተ፤ ይኸውም በአካባቢያቸው ያለውና ግዛቱን እያሰፋ የመጣው አባያ ሐይቅ ሁለት ሄክታር የእርሻ መሬታቸውን እንዳልነበረ አደረገባቸው።
ጎርፉ የነበራቸውን ጥሪት ሁሉ ጠራርጎ ይዞባቸው በመሄዱ በቤታቸው የሚላስ የሚቀመስ ጠፋ፤ ልጆቻቸውንም የሚያሳድጉበት የገቢ አማራጭ አልነበራቸውምና የሰው እጅ ለማየት ተገደዱ። ይህንን ጊዜ ታዲያ የወይዘሮ ወተኬን ችግር የተረዳው የክልሉ መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበረ ባለው ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም እንዲካተቱ አደረገ።
የቤተሰባቸውን ቀለብ በመርሐ-ግብሩ ድጋፍ መሸፈን መቻላቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ወተኬ፤ ይሁንና ርዳታ አገኘሁ ብለው እጃቸውን አጣጥፈው አለመቀመጣቸውን፤ ይልቁኑም በየእለቱ ተሯሩጠው የሚያገኟትን ገንዘብ አጠራቅመው የንግድ ሥራ መጀመራቸውን ይገልፃሉ። ወላይታ ሶዶና ቦረዳ ከተባለ አካባቢ ድረስ ከአርሶ አደሮች ቅቤ ሰብስበው ወደ ከተማ ሄደው ይሸጣሉ፤ በዚህም የሚያገኙትን ትርፍ በመያዝ ለቤተሰቦቻቸው ቀለብ ይሸምታሉ። ልጆቻቸውንም ያስተምራሉ።
‹‹አሁን ላይ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ከረሃብ እና ከመታረዝ ወጥተናል፤ ልጆቼን እያስተማርኩኝ በመሆኑም ደስተኛ ነኝ›› የሚሉት ወይዘሮ ወተኬ፤ የሚያገኟትን ገንዘብ ዕቁብ እንደሚጥሉና ወደፊትም ሱቅ ለመክፈት ዕቅድ ያላቸው መሆኑን ያመለክታሉ። መንግሥት ብድር የሚያገኙበትን ዕድል ቢያመቻችላቸው ደግሞ እርሻቸውንም ሆነ ንግዳቸውን የማስፋፋት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ነው ያመለከቱት።
ይህ እቅዳቸው ከተሳካ ሙሉ ለሙሉ ከርዳታ የመውጣት ፍላጎት እንዳላቸው የሚናገሩት አርሶ አደሯ፤ ሌሎች ሴቶችም ከእርሳቸው ተሞክሮ በመውሰድ ከጠባቂነት ሊወጡ እንደሚገባ ያሳስባሉ። ‹‹ብዙዎቻችን ችግሩ ስለባሰብን እንጂ ተረጂ የሆንነው፤ ሁኔታዎች ቢመቻቹልን ራሳችንን መቻል እንፈልጋለን፤ እንደ እኔ ሌሎችም ሴቶች ከርዳታ መውጣት እንዳለባቸው ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ እናገራለሁ›› ብለዋል።
ወይዘሮ እታለም ፈልሃ ምዕራብ አባያ ቆላ ሙላቶ ቀበሌ ነዋሪ ናት። ሙዝ በመሸከም ሥራ ትተዳደር ነበር። ሆኖም እሷም ሆነ ባለቤቷ የሚያገኙት ገቢ አነስተኛ በመሆኑ የቤተሰባቸውን የምግብ ፍጆታ መሸፈን የዳገት ያህል ከብዷት እንደነበር ጠቅሳለች። በአካባቢያቸው ተግባራዊ በተደረገው የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ከታቀፈች ወዲህ ግን በአፈር ጥበቃ እና በችግኝ ልማት ሥራ በወር አንድ ሳምንት ብቻ በመሳተፍ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ብር ማግኘት በመቻሏ ከእጅ ወደ አፍ የሆነውን ኑሮዋን የደገፈላት መሆኑን ታስረዳለች። በተጨማሪም ሁለት ልጆችዋን ትምህርት ቤት ልካ እያስተማረች ትገኛለች።
የምታገኘውን ጥቂት ገንዘብ በመቆጠብ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በተጨማሪነት እየነገደች እንደምትኖር የምትገልፀው ወይዘሮ እታለም፤ የብድር አቅርቦት ቢመቻችላት ደግሞ የንግድ ሥራዋን ለማስፋፋት ማቀዷን ትናገራለች። ከዚህም ባሻገር በንግዱ በምታፈራው ጥሪት ከብት በማደለብ ሥራ መሠማራትና ኢኮኖሚዋን ወደ ላቀ ደረጃ የማሳደግ ሃሳብ ያላት መሆኑን ነው ያመለከተችው።
‹‹ከእንግዲህ ወደ ድህነት አልመለሰም›› የሚሉት ደግሞ የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ምሥራች ዳና ናቸው። እርሳቸውም ማሳቸው የአባያ ሐይቅ ሰላባ ከሆነባቸው የቀበሌዋ አርሶ አደር አንዷ ናቸው። በታታሪነታቸው በቀበሌዋ በአርዓያነት የሚጠቀሱት እኚህ ሴት ከጎርፉ በፊት ከሁለት ሄክታር በሚልቀው ማሳቸው እያመረቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ሥራ ወዳድና ጠንካራ በመሆናቸው ምክንያትም የቱንም ያህል ችግር ቢያጋጥማቸው ለርዳታ እጃቸውን ዘርግተው እንደማያውቁ፤ የቀበሌውም አስተዳደር በሚሰጡዋቸው የትኛውም ድጋፍ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ያስታውሳሉ።
ይሁንና ክፉ ቀን መጣና ጎርፉ ማሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ሲያወድምባቸው፤ ይህን ተከትሎም ጤናቸው በመታወኩ ከራሳቸው አልፈው ለሌላ የሚተርፉት እኚህ እናት፤ ችግሩ እየከፋባቸው በመሄዱ በልማታዊ ሴፍቲኔት መርሐ-ግብሩ ለመታቀፍ መገደዳቸውን ያመለክታሉ። ሆኖም ርዳታውን ብቻ መጠበቅ አዕምሯቸው አልቀበል ስላላቸው ከመርሐ-ግብሩ 20 ሺ ብር በብድር ወሰዱና እንጀራ የመጋገር ሥራ ጀመሩ። ሥራቸውን እያስፋፉ በመሄድ የቤተሰባቸውን የምግብ ፍላጎት ከማሟላት አልፈው የሳር ጎጃቸውን ወደ ቆርቆሮ ቤት መቀየር መቻላቸው ነው የነገሩን።
አሁን ላይ በአካባቢው ላሉ ምግብ ቤቶች ትኩስ እንጀራ በመሸጥ በሳምንት 500 ብር ዕቁብ ይጥላሉ፤ በቅርቡም ዕቁቡ ደርሷቸው ስለነበር አንዲት ላም ገዝተው ኑሯቸውን እየደጎሙ ሲሆን በቀረው ገንዘብ ደግሞ ከዕዳቸው ላይ 5ሺ 500 ብር መመለስ የቻሉ ሲሆን በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕዳቸውን ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና በማለት ይገኛሉ። አሁን ላይ ከልጆቻቸው ባሻገር በሚሠሩት ገንዘብ የቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑትን ባለቤታቸውን ገንዘብ ከፍለው መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲማሩ ድጋፍ ማድረጋቸውን ይገልፃሉ።
‹‹ከእንግዲህ ወደ ፊት እንጂ ወደ ኋላ አልመለስም›› የሚሉት ወይዘሮ የምሥራች፤ የእንጀራ ጋገራ ሥራቸውን የማስፋት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረው፤ ጎን ለጎንም እንደቀድሞው ሁሉ የእርሻ ሥራቸውን የመቀጠል ሃሳብ እንዳላቸው ይጠቁማሉ። ከወዳጆቻቸው ጋር በመምከር እንደጎመንና መሰል የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በስፋት በማልማት፤ ፍየልና ዶሮ አርብተው ለገበያ ለማቅረብ እቅድ ያላቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
በቀበሌው 141 አባወራ አደረጃጀት ውስጥ የሚገኙ 600 ነዋሪዎች የሴፍኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚዎች ናቸው። በቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ መርሐ-ግብር 52 ተጠቃሚዎች ብድር እንዲያገኙና ወደ ሥራ እንዲገቡ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ከእነዚም ውስጥ አስሩ ነፃ ብድር ያገኙ ሲሆን ቀሪዎች ሠርተው ከሚያገኙት ገንዘብ በረጅም ጊዜ የሚከፍሉበት ሁኔታ የተመቻቸላቸው መሆኑን ደግሞ የቆላ ሙላቶ ቀበሌ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘካሪያስ ሻንካ ነግረውናል።
ማሕሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም