– ባለትዳሮች በራሳቸው የዘር ፍሬ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ አገልግሎት እንዲያገኙ ተፈቅዷል
አዲስ አበባ ፤- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ የአተነፋፈስ ሥርዓትን ማቋረጥን የሚያካትተውን የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ በአንድ ተቃውሞ በዘጠኝ ድምፀ ተዓቅቦ አፀደቀ።
የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባሕል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡርቃ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ የአንድ ሕመምተኛ የልብ እና የመተንፈሻ አካላት የአሠራር ሥርዓት መመለስ በማይችልበት ደረጃ ሥራቸውን ሲያቆሙ። ወይም የአንጎል ሞት ሲረጋገጥ በመሣሪያ ላይ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓትን ሦስት አግባብነት ባላቸው ባለሙያዎች ውሳኔ ማቋረጥ እንደሚቻል ተቀምጧል።
ይህም ማለት በመሣሪያ ላይ የተመሠረተ የአተነፋፈስ ሥርዓትን ማቋረጥ የሚቻለው የልብና የአተነፋፈስ ሥርዓቱን መመለስ በማይቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱና የአንጎል ሞት መከሰቱ በሦስት ባለሙያዎች ሲረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል።
አንዳንድ ሰዎች ከአምስት ዓመት በላይ በመሣሪያ እየተነፈሱ አንጎል ሞቶ የሚቆዩበት አጋጣሚ አለ ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፤ ይህ ሊሆን የሚችለው ከውጭ በሚሰጠው ኦክስጅን አማካይነት እንጂ ሕመምተኛው ውስጥ ሕይወት ኖሮ አይደለም ብለዋል።
በዚህ አይነት ታካሚዎችን በሕክምና ተቋማት ማቆየት ለተቋማቱም፤ ለቤተሰቡም ጥቅም የሌለው በመሆኑ የተወሰነ መሆኑን ገልጸዋል። በምንም አይነት መልኩ ሕይወት የማሳጠር ሥራ የማይፈቀድ መሆኑንም አስቀምጠዋል።
በተጨማሪም አዋጁ ባለትዳሮች ከራሳቸው በተወሰደ የዘር ፍሬ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥነ ተዋልዶ የሕክምና አገልግሎት ለራሳቸው ብቻ ማግኘት እንደሚችሉም አስቀምጧል። በዚህ ረገድ ልገሳ እና የዘር ፍሬ መሰብሰብ ተግባራት ያልተፈቀዱ መሆኑም በአዋጁ ተደንግጓል።
ይህም ከማኅበረሰቡ ልማድ አኗኗርና ባሕል ጋር የተጣረሰ እንዳይሆን እንዲሁም እንደዚህ አይነት ሕጎች ሲወጡ ጥንዶችን ብቻ ሳይሆን የሚወለዱትንም ልጆች ከግምት ያስገቡ ሊሆኑ እንደሚገባ በመታመኑ ነው ብለዋል።
የጤና አገልግሎት አስተዳደር እና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ መፅደቅ ዘርፉ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታው ከሚጠይቀው እና ወቅቱ ከደረሰበት ደረጃ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ታስቦ መሆኑን ጠቁመው፤ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ደኅንነትና ፍትሐዊ ተደራሽነትን የሚያጎለብት አዳዲስ የጤና አገልግሎት ሥርዓቶች እንዲዘረጉ የሚፈቅድ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንዲሁም በጤና እና ጤና ነክ ተቋማትና ባለሙያዎች ላይ በአገልግሎት አሰጣጡ ዙሪያ በቂ ክትትልና ቁጥጥር እንዲኖር የሚያስችል እንደሆነ አመልክተው፤ አዋጁ በመማሪያ ሆስፒታሎች አካባቢ ባለው የተግባር ትምህርት እና የሕክምና አሰጣጥ ላይ ያጋጥም ለነበረው ችግር መፍትሔ የሚያስቀምጥና ለጤና አገልግሎት ሥርዓቱ ግልፅ የሆነ የሕግ ሽፋን የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 23 ቀን 2017 ዓ.ም