ዜና ትንታኔ
የኅትመት ሚዲያ በዲጂታል ሚዲያ እንደተተካ እና አሁን ላይ የኅትመት ሚዲያ ፋሽኑ እንዳለፈበት ተደርጎ ይነገራል:: ሁሉንም ሰው የዲጂታል ሚዲያ ተጠቃሚ አድርጎ በማሰብ ‹‹በዚህ ዘመን ጋዜጣ ማን ያነባል?›› ሲባል ይሰማል:: ለመሆኑ የኅትመት ሚዲያ ዘመን የሚሽረው ነው? ዲጂታል ሚዲያ የኅትመት ሚዲያን መተካት ይችላል?
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት መምህር ናትናኤል ዮሐንስ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን የሚባሉ የሚዲያ አይነቶች እንደመጡ ‹‹የኅትመት ሚዲያ አለቀለት›› ተብሎ ነበር:: ዳሩ ግን ብዙ የምርመራ ዘገባዎች የተሠሩት በጋዜጦችና መጽሔቶች ነበር:: ሬዲዮና ቴሌቪዥን ብርቅ በነበሩባቸው ዘመናት የኅትመት ሚዲያዎች መዳከም ብቻ ሳይሆን ይቀራሉ የሚል ስጋት ሁሉ ነበር፤ ዳሩ ግን የኅትመት ሚዲያ እነሆ ቀጥሏል:: የኅትመት ሚዲያው፤ ከሬዲዮ በኋላ ከ130 ዓመታት በላይ፣ ከቴሌቪዥን በኋላ ከ90 ዓመታት በላይ እነሆ አሁን ድረስ ተመራጭ ሆኖ እየሠራ ይገኛል::
መምህር ናትናኤል እንደሚሉት፤ የኅትመት ሚዲያው በሳይንሳዊ ባሕሪው አሁንም ይቀጥላል:: ሰዎች በተረጋጋ ቀልብ ጥልቅ ግንዛቤ የሚያገኙት ከኅትመት ሚዲያ ነው:: በአውሮፓና አሜሪካ ሀገራትም አሁንም ጋዜጣ አለ:: በተለይም እንደ ኢትዮጵያ የንባብ ባሕል ደካማ በሆነበት የኅትመት ሚዲያው ሊዳከም ሳይሆን ሊጠናከር እንደሚገባውም ያሳስባሉ::
‹‹ጥናቶች እንደሚያሳዩት የኅትመት ሚዲያ ለጤናም ተመራጭ ነው›› ያሉት መምህር ናትኤል፤ በተለይም አዋቂ ሰዎች ለዓይንና ለጭንቅላት ጤንነት የኅትመት ሚዲያዎችን እንደሚመርጡ ከጥናትም በአካባቢ ከማየትም ማረጋገጥ ይቻላል ነው ያሉት ::
እንደ መምህር ናትናኤል ገለጻ፤ የዲጂታሉ ዓለም የኅትመቱን ያህል አይታመንም:: አመሳስሎ ለመሥራት ቀላል ነው:: አንድን ጋዜጣ አስመስሎ ማሳተም አልተለመደም፤ የዲጂታሉ ዓለም ግን አመሳስሎ ለመሥራትና ሐሰተኛ መረጃ ለማሰራጨት ምቹ ሆኗል:: የዲጂታሉ ፕላትፎርም ታሪክን ሰንዶ ለማስቀመጥም አስተማማኝ አይደለም:: ለአያያዝና ለአገልግሎት ምቹ ቢሆንም በአንድ አጋጣሚ ሊጠፋ የሚችል እንደሆነ ያብራራሉ::
አስተማማኝ የሆኑት ሬዲዮና ቴሌቪዥን በመጡበት ዘመን ያልተዳከመው የኅትመት ሚዲያ በዲጂታሉ ዓለም ሊበለጥ እንደማይገባም ያሳስባሉ::
ከ16 ዓመታት በፊት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2008-2009 ሮይተርስ ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ‹‹የበይነ መረብ ዕድሎችና ፈተናዎች ለኅትመት ሚዲያ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው ጥናት፤ የአውሮፓን ዕለታዊና ሳምንታዊ ጋዜጦች ከዘረዘረ በኋላ ‹‹የኅትመት ሚዲያ ዕድገት አይኖረውም፤ በፍፁም ግን አይሞትም›› ይላል:: የኅትመት ሚዲያው ስጋት የተደቀነበት ቢሆንም እያከሸፈና እየተሻገረ ስለሚሄድ የረጅም ጊዜ ራዕይ እንደማይኖረውም ይገልጻል::
ከዚህኛው ጥናት ከሁለት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2010 በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ‹‹የኅትመት ሚዲያ የወደፊት ዕጣ ፋንታ›› በሚል በተሠራ ጥናት ደግሞ፤ እንዲያውም አዳዲስ ጋዜጦች እየተጀመሩ እንደሆነ ይገልጻል:: ይህኛው ጥናት እንደሚለው፤ አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮች በመጡ ቁጥር የኅትመት ሚዲያው ይፈተናል ብሎ መስጋት አዲስ ነገር አይደለም፤ የኒውዮርክ ታይምስ አርታኢ በአንድ የሎንደን ጉባኤ ላይ ‹‹ከዚህ በኋላ ማሳተሙን ልናቆም እንችላለን›› እስከማለት ደርሶ እንደነበርም ይገልጻል:: ያም ሆኖ ግን የኅትመት ሚዲያዎች ቀጥሏል::
የሪፖርተር ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዮሐንስ አንበርብር በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጠው አስተያየት፤ የኅትመት ሚዲያው በዲጂታል ሚዲያ ይተካል አይተካም የሚለው ጥናት የሚፈልግ ሆኖ፤ የዲጂታል ሚዲያው ግን የደኅንነት ስጋት ያለበት ነው:: የበይነ መረቡ ዓለም በአንድ አጋጣሚ ስህተት ወይም ሆን ተብሎ በሚደረግ ጥቃት ሊጠፋ የሚችል ነው:: የተሠሩ ሥራዎችና የተሰነዱ ሰነዶች ሁሉ ሊጠፉ ይችላሉ:: ኅትመትን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል መተካት በምዕራቡ ዓለምም ተሞክሮ ያልተሳካ ነገር ነው፤ ወደ መደበኛው የኅትመት አማራጭ ተመልሰዋል ነው ያለው::
የዲጂታል ሚዲያው ታማኝነት የለውም በሚሉ ሀሳቦች የማይስማማው ጋዜጠኛ ዮሐንስ፤ በጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባር ከተሠራ እና ተቋማዊ ታማኝነትን ከገነባ ዲጂታል መሆኑ ብቻውን አጠራጣሪ እንደማያደርገው ይናገራል:: የኅትመት ሚዲያን በዲጂታል መተካት ማለት፤ በኅትመት ሚዲያው ተቋማዊ ማንነትን የገነቡ አካላት የሚያስተዳድሩት ስለሚሆን የታማኝነት ችግር ስጋት አይሆንም፤ ችግሩ ግን የበይነ መረቡ ዓለም ብቻውን አስተማማኝ አለመሆኑ ነው:: ስለሆነም ሁለቱንም ማስኬድ እንደሚገባ ጋዜጠኛ ዮሐንስ ያሳስባል::
እንደ ጋዜጠኛ ዮሐንስ አስተያየት፤ የበይነ መረቡ ዓለም በተደራሽነት የኅትመት ሚዲያን ብቻ ሳይሆን የብሮድካስት ሚዲያዎችንም ቀድሟል:: በዚህም ምክንያት ሪፖርተር ጋዜጣን ጨምሮ የሀገራችን የሚዲያ ተቋማት የዲጂታል ሚዲያ አማራጭ አላቸው:: ከዘመኑ ጋር መሄድ ስለሚያስፈልግ የዲጂታል አማራጭ መጠቀም የግድ ይሆናል:: በተለይም በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የኅትመት ጉዳይ አስቸጋሪ ስለሆነ ከተደራሽነት ስፋት አንፃር ዲጂታል ሚዲያውን መጠቀም አስገዳጅ መሆኑን ይናገራል::
ጋዜጠኛ ዮሐንስ እንደሚለው፤ በኢትዮጵያ አዲስ የኅትመት ሚዲያ ለመጀመር የማይታሰብ እየሆነ ነው:: እንኳን አዲስ መጀመር ነባሮችም እየተፈተኑ ነው:: ሪፖርተር ጋዜጣ ለ30 ዓመታት ያህል የቆየ እና ተቋማዊ ማንነት የገነባ ስለሆነ ማስታወቂያ ስለሚያገኝ እንጂ ጋዜጣ ከመሸጥ የሚያገኘው ገቢ የለውም:: የጋዜጣው ማሳተሚያ ዋጋ ከጋዜጣው መሸጫ ዋጋ በላይ ነው፤ ከስሮ ነው የሚሸጠው:: ይህ ሁኔታ ባለሙያዎች ወደ ዲጂታሉ አማራጭ ብቻ እንዲሄዱ ያደርጋቸዋል ሲል ያብራራል::
መንግሥት ለኅትመት ሚዲያ ግብዓቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ የገለጸው ጋዜጠኛ ዮሐንስ፤ ተቋማዊ ኃላፊነት ላላቸው እና ተጠያቂነታቸው ግልጽ ለሆነ የሚዲያ ተቋማት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሐሰተኛ መረጃዎች የሚያሰራጩ የዲጂታል ሚዲያዎችን እንቅስቃሴ እንደሚገድብ ያሳስባል::
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም