አዲስ አበባ፡- ዳግመኛ የተወለደው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያ ታሪክ ማሳያ ድርሳን ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ምረቃ ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል፡፡
ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ የብሔራዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ምረቃ ሥነ ሥርዓት ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ ታሪካዊና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ ዕድሳት የተደረገለት ብሔራዊ ቤተመንግሥት የኢትዮጵያ ታሪክ ማሳያ ድርሳን ነው፡፡ ይህንን ቤተ መንግሥት የማደስና የማስዋብ ተግባር የሚደነቅና ሀብትን በአግባቡ የመጠቀም አዲስ ልምምድ ነው ብለዋል፡፡
ቤተ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ውጣ ውረድና ፍሰት ጎላ ብሎ የሚታይበት ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ይህን ታሪካዊ ቤተ መንግሥት በአማረና ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ መታደሱ ታላቅ ሀገራዊ ኩራትን የሚያላብስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ቤተ መንግሥቱ ዘመናዊነትን የተላበሰና ታሪካዊ እንደሆነ ገልጸው፤ ቤተ መንግሥቱን የማደስና የማዘመን ብቻ ሥራ ሳይሆን የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ይህን ታሪካዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት የተደረገለት መሆኑን አውስተው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ አንዱ አካል የሆነው ብሔራዊ ቤተ መንግሥትን በማደስ ለትውልድ እንዲተላለፍ የማድረጉ ተግባር የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል፡፡
ቤተ መንግሥቱ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁለተናዊ ዕድገትና ታሪክ የተቀየሰበት፣ ዲፕሎማሲና የነፃነት ብርሃን መፈንጠቁን የታየበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ለዚህ ታሪካዊ ቤተ መንግሥት ዕድሳት ድጋፍ ላደረገው የፈረንሳይ መንግሥትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል::
በ1948 ዓ.ም እንደተገነባ የሚነገርለት ብሔራዊ ቤተ መንግሥት በውስጡ በርካታ የሀገር ታሪካዊ ቅርሶች ይዞ እንደሚገኝ ተገልጿል:: ከእነዚህ መካከልም የንጉሣውያን ቤተሰቦች ይጠቀሙባቸው የነበሩ አውቶሞቢሎች፤ የስጦታ ዕቃዎች፣ ዘውዶች፣ ዙፋኖችና ንጉሡ የሚጠቀሙባቸው ባቡሮች ይገኙበታል:: እነዚህ ቅርሶችን ሕዝብ እንዲጎበኛቸውም ቤተ መንግሥቱ ታሪካዊና ባሕላዊ ይዘቱን ጠብቆ ከማደስ ባሻገርም የተሽከርካሪዎች መካነ ርዕይ ተገንብቷል:: ግቢውን በአረንጓዴ ልማት የማሳመር፣ ፋፋቴዎችንና ኩሬዎችን ያካተቱ ሥራዎች ተከናውነዋል:: ብሔራዊ ቤተ መንግሥቱ ከ27 ሄክታር መሬት በላይ ላይ ያረፈ እንደሆነ ታውቋል፡፤
የብሔራዊ ቤተመንግሥት እድሳት የታሪክ እና የባሕል ቅርሳችንን ጠብቆ ለማቆየት የምናደርገው ጥረት ከፍ ያለ ርምጃ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጀመረው የእድሳት ተግባር አሁን አንድነት ፓርክ ከሆነው ከታላቁ ቤተመንግሥት ጀምሮ ይህን ትዕምርታዊ ስፍራ እንደገና ለታላቅ አገልግሎት እንዲሰናዳ በማድረግ ቀጥሏል። ብሔራዊ ቤተመንግሥት አሁን የሕዝባችንን ጽናት፣ ጥበባዊ አቅምና ርዕይ ግዘፍ ነስቶ የሚታይበት የሀገራዊ ጉዟችን ዋቢ ሆኖ ይታያል። የቀደመ ግዝፈቱን እና ውበቱን በመመለስ ያለፈ ታሪካችንን እናከብራለን። ለትውልዶችም የኩራትና የተነሳሽነት ዘላቂ ተምሳሌት አኑረናል ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል::
ጌትነት ምሕረቴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 21 ቀን 2017 ዓ.ም