‹‹በመልካምነት የሰዎችን ሕይወት ማቅናት እንችላለን›› – ሰዓሊና የሥነ ጥበብ መምህር ዓለም ጌታቸው

ሰዓሊ ናት፤ የህፃናት መጻሕፍት ደራሲም ጭምር። ትውልድ በሥነ ምግባር ታንጾ ያድግ ዘንድ ብርታት ለመሆን ያላትን ለማካፈል ትተጋለች። ‹‹ዓለም የሥነ ጥበብ ማዕከል›› የተሰኘ የስዕል ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በመክፈት ለዓመታት እያስተማረች ትገኛለች። ‹‹አብረን›› የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅትም አቋቁማ በመልካም ምግባር ላይ ተሰማርታለች። በርካታ የስዕል ኤግዚቢሽኖችን በጋራና በግል አዘጋጅታለች። ይህቺ ሴት ሰዓሊ ዓለም ጌታቸው ትባላለች።

በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለፈለገ ሰላም የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ‹‹ነገን ዛሬን እንሳል›› በሚል ርእስ የአካል ጉዳተኞችን የሚገጥማቸውን አስቸጋሪ ሕይወት በጥበብ ለታዳሚያን ለማሳየት ችላለች። ዛሬ እዚህ ለመድረሷ ትናንት በብዙ ትግል ውስጥ ልታልፍ የግድ ነበር። ዓለም ገና በ12 ዓመቷ ነበር ለአካል ጉዳት የተጋለጠችው። ይህ አጋጣሚ አበረታት አንጂ ተስፋ ለመቁረጥ ምክንያት አልሆናትም። የዝግጅት ክፍላችን የዓለም የሕይወት መንገድ ለትውልድ አንዳች እውነት እንደሚገልጥ በማመኑ እንግዳችን እንድትሆን ጋብዟታል። መልካም ቆይታ!

ትውልድና እድገት

ለብዙዎች የብርታትና ምሳሌ የሆነች ሰዓሊና የሥነ ጥበብ መምህር ዓለም የተወለደችው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በጎንደር አዘዞ ነው። አባቷ ኢንስፔክተር አቶ ጌታቸው ወርቁ ትውልዳቸው አዲስ አበባ ይሁን እንጂ በውትድርና በሜካኒክነት ይሠሩ ስለነበር ከባለቤታቸው ጋር ተዋውቀው ትዳር የመሠረቱት በጎንደር ነው። በውትድርና ግዳጅ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር የግድ ነውና ታዳጊዋ ገና በህፃንነቷ ቤተሰቦቿን ተከትላ ወደ ኤርትራ መሄድ ነበረባት። አባቷ የተበላሹ ወታደራዊ አውሮፕላኖችን ጨምሮ የሜካናይዝድ መሳሪያዎችን በመጠገን የሚታወቁ ሜካኒክ መሆናቸው አንድ ቦታ ተቀምጦ ቤተሰቡ ሕይወትን እንዲመራ እድል የሚሰጥ አልነበረም።

በዚህ ምክንያት ቤተሰቦቿ ዓለምን በድጋሚ ወደ አያቶቿ ለመመለስ አስገደዳቸው። አያቷ ነበሩ ወደ ኤርትራ አቅንተው ብዙም ሳትቆይ በሰባት ዓመቷ ወደ ጎንደር ይዘዋት የተመለሱት። ዓለም በልጅነቷ ዝምተኛ ነበረች። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዘውትራ ትሄድ ነበር። ከተፈጥሮ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ነበራት፤ ለቤት እንስሳት በተለይ ለድመት ልዩ ፍቅር አላት፤ አትክልቶችን መትከልና መንከባከብም እንዲሁ የልጅነት ልዩ ዝንባሌዋ ነበር። ለጥበብ ቅርብ እንድትሆንና ስስ ልብ እንዲኖራት ይህ ዝንባሌዋ መሠረት ነበር። ነገር ግን ዝምተኛ መሆኗና ይበልጥ ከቤት እንስሳት ጋር ቅርበት መፍጠሯ በቤተሰቦቿ እምብዛም አይወደድላትም ነበር።

ሰዓሊና መምህር ዓለም በጎንደር ቀያምባ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሶስት ዓመታት ተምራለች። ኤርትራ በቆየችባቸው ዓመታት ቤት መኻ የሚባል ትምህርት ቤት ገብታ ነበር። ከሌሎች ተማሪዎች በተለየ የስዕል ልዩ ዝንባሌ ነበራት። የደረጃ ተማሪ ባትሆንም ጎበዝ ከሚባሉ መካከል ነበረች። በተለይ መምህሮቿ በብላክ ቦርድ ላይ የሚሳሉ ማስተማሪያዎችን እንድትሠራ ያበረታቷት ነበር። በቀያምባ ለተከታታይ ሶስት ዓመት በዚህ ተግባሯ ቀጥላ ልዩ እውቅናን አትርፋበታለች።

‹‹የስዕል ተሰጥኦዬን የወረስኩት ከአባቴ ነው። ኤርትራ በነበርኩበት ወቅት ስዕል ብቻ ሳይሆን መጻሕፍትንም እንዳነብ ያበረታታኝ ነበር›› ትላለች፤ አባቷ ለጥበብ ቅርብ እንደነበሩና የእርሳቸውን ፈለግ እንደተከተለች በመግለጽ። እርሳቸው ግን ቤተሰብ ለመምራትና ሀገርን ለማገልገል በሌላ የሙያ መስክ ላይ በመቆየታቸው ልክ እንደ እርሷ ለጥበብ ቅርብ አልሆኑም።

ዳግም ወደ ኤርትራ-ያልታሰበው አጋጣሚ

ሰዓሊ ዓለም ወደ ኤርትራ ዳግም ተመልሳ ከወላጆቿ ጋር መኖር የግድ አላት። አያቶቿን ተሰናብታ ከስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን አቋርጣ ወደ አስመራ አቀናች። ጊዜው የደርግ ወታደር ከኤርትራ አማፂያን እና ከወያኔ ጋር ከፍተኛ ጦርነት የሚያደርግበት ወቅት በመሆኑ ሀገሪቱ ላይ መረጋጋት አይታይም ነበር። የዓለም ቤተሰብ ያረፈው አስመራ ከተማ ፀፀራት አካባቢ (ቃኘው የሚባል ወታደራዊ ካምፕ በሚገኝበት ሥፍራ) ነበር። ይሁን እንጂ በዚያም ከአንድ ዓመት በላይ መቆየት አልቻለችም። ምክንያቱ ደግሞ ጦርነት እየተባበሰ በመምጣቱ ነበር። በተለይ መኖሪያ ቤታቸው የወታደር ካምፕ አካባቢ ስለነበር የከባድ መሳሪያም ሰለባ ሆኖ ነበር።

ከጦርነቱ ባሻገር የዓለም የአስመራ ቆይታ እንደ ቀድሞው የልጅነት ጊዜዋ አልነበረም። አስመራ ወላጆቿ ጋር እንደደረሰች በሰውነቷ (እግሯና የጀርባ አጥንቷ አካባቢ) የተለየ ህመም ታስተናግድ ጀመር። ጎንደር እያለች የሰውነቷ መገጣጠሚያ አካባቢ ህመም ይሰማት የነበረ ቢሆንም እንዳሁኑ የከፋ አልነበረም። ይህ ህመም ተባብሶ በእግሯ መሄድ እንዳትችል አስገደዳት። አጋጣሚው ከጦርነቱ ጋር ተደምሮ የቤተሰቡን የሕይወት አቅጣጫ የቀየረ ፈተናን ፈጠረ።

የሻዕቢያና ወያኔ አማፂያን ከደርግ ጋር የሚያደርጉት ጦርነት መባባሱ ቤተሰቡ ዳግም ከነበረበት ስፍራ እንዲለቅ አስገደደው። አባታቸው እዚያው መቅረት ስለነበረባቸው እናታቸው እሷንና አራት እህት ወንደሞቿን ይዘው በወታደር አውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ መጡ። ዓለም ወደ ትራንስፖርት ቦታ ስትጓዝ በእግሯ እየተራመደች አልነበረም፤ ባጋጠማት የአካል ጉዳት ምክንያት ለመንቀሳቀስ የቤተሰብ ድጋፍ (መታዘል) ያስፈልጋት ነበር። ይህን ጊዜ ነበር የአካል ጉዳት ያስከተለባትን ፈተና ለመጋፈጥ አዲሱን ማንነትና የሕይወት ውጣ ውረድ ለመቀበል የሚያስችል ግዴታ ውስጥ የገባችው።

ፈተናን የመጋፈጥ ፅናት

በአዲስ አበባ ሕይወት ለዓለም አልጋ በአልጋ አልሆነችም። የተረጋጋ መኖሪያ ለማግኘት የአክስትና አጎታቸውን ድጋፍ ቢያገኙም ለመረጋጋት ጊዜ ወስዶባቸዋል። በዚያ ላይ ካልጠበቀችው የአካል ጉዳት ህመም ጋር የተጋፈጠችበት ወቅት መሆኑ የእርሷን ጨምሮ የቤተሰቡን ሕይወት ያከበደ ነበር። ብዙም ሳይቆዩ ካረፉበት ለገሀር አካባቢ በአክስታቸው ድጋፍ አሁንም ድረስ ወደምትኖርበት ሰፈር (ገርጂ ሮባ ዳቦ ቤት አካባቢ) በ50 ብር አንድ ክፍል ቤት ተከራይተው መኖር ጀመሩ። ዓለም በአዲስ ቤት በአዲስ የሕይወት መንገድ የሕይወት ገጿን መፃፍ ጀመረች።

በሀገሪቱ የሥርዓት ለውጥ ብዙም ሳይቆይ ነበር የመጣው። ይህ አጋጣሚ በእናቷ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ይዞ የመጣ ነበር። በዚህ ምክንያት ልጃቸውን ወደ ሕክምና ለመውሰድ እና ለማመላለስ አስቸጋሪ አደረገባቸው። ዓለምም ትምህርቷን አቋርጣ ቤት ውስጥ ለስድስት ዓመታት ተቀመጠች።

‹‹የገጠመኝ ችግር ከትምህርት ቢያስቀረኝም በቤት ውስጥ በብዛት መጻሕፍትን ማንበብ ልምዴ አደረኩ። በተጨማሪ የስዕል ተሰጥኦዬን አዳብር ነበር›› የምትለው የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን ሰዓሊና መምህር ዓለም፤ የምታነባቸውን መጻሕፍት ለማግኘት በአካባቢው የሚገኙ ሰዎች በብድር በእህቶቿና በተለያዩ ሰዎች አማካኝነት ታገኝ ነበር።

በእነዚህ ዓመታት ከቤት መውጣት ስለማትችል በምትፈልግበት ጊዜ ከጎረቤትም ሆነ ዘመድ ጋር የመገናኘት አጋጣሚ አልነበራትም። በጊዜው ሲበዛ ዝምተኛ ከመሆኗ የተነሳ የአዕምሮ ህመም ያጋጥማታል ብለው ቤተሰቦቿ ይሰጉ ነበር። ለማንበብና ለመሳል ምክንያት የሆኗት አባቷ የሥርዓት ለውጡን ተከትሎ ወደ አዲስ አበባ መጥተው በሹፍርና ተቀጥረው እየሠሩ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአንድነት መኖር ጀምረዋል። አጋጣሚው የምታነበው ጋዜጣ ቶሎ ቶሎ እንድታገኝ እድል ፈጠረላት፤ (የችርቻሮ እቃ መጠቅለያ ሆነው የሚመጡ ጋዜጦችን ጭምር) በማንበብ እና የስዕል ሥራዋ ላይ በማተኮር እውቀቷን ታዳብር ነበር።

ጓደኝነት- አዲስ አቅጣጫ

የሰዓሊ ዓለም የወጣትነት የሕይወት አቅጣጫ የቀየረ አንድ ክስተት ተፈጠረ። አሁን በሕይወት የሌለች መነን ልዑልሰገድ የተባለች በገርጂ እምቡጥ ትምህርት ቤት መምህር ጋር ተዋወቀች። መነን የዓለምን ታሪክ ከሰዎች ሰምታ ስለነበር ቤቷ ድረስ በመሄድ ነበር የተዋወቀቻት።

ስለ ትውውቃቸው በማስታወስ ‹‹መልካም ሰዎች የሰዎችን ሕይወት ያቀናሉ›› በማለት በጊዜው መምህር መነንም የሕይወት አቅጣጫዋን የቀየሩ ድጋፎችን ታደርግላት እንደነበር ትናገራለች። መጻሕፍትን በመከራየት፣ ጓደኛዋ በመሆን እና የምትወዳቸውን ምግቦች እየሠራች በማምጣት በቤት ውስጥ መቀመጧ የሚፈጥርባትን የብቸኝነት ስሜት ጫና እንዳይፈጥርባት አገዘቻት። በተለይ ለዓመታት አቋርጣው የነበረው ትምህርት በርቀት እንድትቀጥል ያበረታታቻትና እድሉን ያመቻቸችላት ይህቺ መልካም ሰው ነበረች።

‹‹መነን ለኔ እግሬ ማለት ነበረች›› ትላለች በጊዜው የሕይወት አቅጣጫዋን እንዴት እንደቀየረችው ስትናገር። መጻሕፍት እንዳትቸገር ከማድረግ ባሻገር ፓን አፍሪካን የርቀት ትምህርት ቤት (ኋላ ላይ ኮሌጅ የሆነው) ተመዝግባ ትምህርቷን እንድትማር ያደረገቻት እርሷ እንደነበረች እየመሰከረች። ቀለም ተጠቅማ በሸራ ላይ ስዕል መሳል እንድትጀምር ምክንያት የነበረችውም መነን ነች። በእሷ አማካኝነት የተዋወቀቻቸውን ሌሎች ወዳጆቿ የስዕል ቀለም ያመጡላት ነበር። በዚህ የመደጋገፍና የቀናነት ስሜት የሰዓሊ ዓለምና የመምህር መነን ጓደኝነት ለ17 ዓመታት መዝለቅ ችሏል።

ሰዓሊ ዓለም በጊዜው መልክዓ ምድሮችን የሚያሳይ (Landscape) የአሳሳል ዘይቤ ላይ ታተኩር ነበር። ለተፈጥሮ የቀረበ ነብስ ስላላት ሥራዎቿም ያንኑ የሚያንፀባርቁ ናቸው። በተለያየ የሕይወት ፈተና ውስጥ የሚያልፉ ሴቶችን የሚገልጽና መንፈሳዊነትን የሚያሳዩ የጥበብ ውጤቶችን ትሠራለች። በቀለምና ሸራ ላይ ስዕሎቿን መሥራት መጀመሯ ደግሞ ከበርካታ ሰዎች ጋር እንድትተዋወቅና ተሰጥኦዋን የሚያደንቁ ወዳጆች እንድታፈራ እድል ፈጠረላት።

የመጀመሪያ የሸራ ላይ ሥራዋን ለአንድ ካቶሊክ ካህን በ150 ብር እንደሸጠች የምታስታውሰው ሰዓሊ ዓለም፤ የምትወደውን እየሠራች ኑሮዋን መደጎም እንደምትችል ያረጋገጠችበት አጋጣሚ እንደተፈጠረ ትናገራለች። አንድም ጊዜ ቢሆን የስዕል ሥራዎቿን መሸጥ እችላለሁ የሚል እሳቤ አልነበራትም። የካቶሊክ ካህኑ የገዟት የእየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ስዕል ግን ከሙያም ባሻገር በሰዓሊነት የኑሮ መሠረት መጣል እንደምትችል ተስፋ እንዲሰጣት በር ከፈተላት።

ወደ ሻሸመኔ-ጂጌሳ

ሰዓሊና የሥነ ጥበብ ማዕከል መስራች ዓለም በጓደኛዋ ምክር የጀመረችውን የርቀት ትምህርት እስከ አስረኛ ክፍል ተምራ ወደ አስራ አንደኛ ክፍል የሚያሸጋግራትን የማለፊያ ውጤት አገኘች። ትምህርቱን ለመቀጠል በዝግጅት ላይ እንዳለች ግን አንድ የሕክምና እድል አገኘች። እድሉን የሰጣት በሻሸመኔ ጅጌሳ አካባቢ የሚገኝ በጣሊያኖች የተመሠረተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንና ድርጅት ነበር። ለዓመታት የፈተናት የአካል ጉዳት ህመም ‹‹መፍትሔ ይገኝለታል›› የሚል ተስፋ ስላሳደረባት በጉጉት ምንም ሳታቅማማ ነበር ወደዚያው ያቀናችው።

‹‹በማዕከሉ እየመጡ ሕክምና የሚሰጡ የውጭ ሀገር ሐኪሞች ነበሩ›› የምትለው ሰዓሊና የሥነ ጥበብ ማዕከል መሥራች ዓለም፤ ሕክምናውን ለማግኘት ስትል ለዓመታት መሽጋበት ከነበረው ቤት ለመውጣትና ወደ ሻሸመኔ ለመሄድ እንደቻለች ትናገራለች። በጊዜው አይደለም ከቤት መውጣት ይቅርና የአካል ጉዳተኞች የሚጠቀሙበት ዊልቸር (መጓጓዣ) አልነበራትም፤ ከናካቴውም ዊልቸር ምን እንደሆነ አታውቅም ነበር።

ዓለም ይህ ውሳኔ ወደ ሌላ የሕይወት አቅጣጫ የመራት እንደነበርም ታስታውሳለች።

‹‹ማዕከሉ በር ላይ ስደርስ ለመጀመሪያ ጊዜ ዊልቸር መጣልኝ›› ትላለች ወቅቱን እያስታወሰች። ግቢው ሰፊ ሲሆን የሙያ ማስተማሪያ ማዕከላትን ጨምሮ የአካል ጉዳት ያስተናገዱ ዜጎችን የሚታከሙበት ተቋም ያቀፈ እንደሆነ እየተናገረች። ወደ ግቢው እንደገባች ነበር እስከ ወዲያኛው አመለካከቷን የቀየረ ትዕይንት አጋጠማት። በማዕከሉ በጣም ብዙ አካል ጉዳት ያስተናገዱ ሰዎችን ተመለከተች። እሷ ካጋጠማት እክል በባሰ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ያለ ሰው ርዳታ ምንም ማድረግ የማይችሉ ሰዎችን ተመለከተች።

‹‹በሁኔታው በጣም ነበር የደነገጥኩት፤ በዓለም ላይ እኔ ብቻ የአካል ጉዳተኛ የሆንኩ ይመስለኝ ነበር›› የምትለው ሰዓሊ ዓለም፤ በማዕከሉ ባየችው ነገር በእጅጉ መገረሟን ታነሳለች። እርሷ የተሻለ ሁኔታ ውስጥ እንደሆነችና መሥራት እንደምትችል እንድታምን ምክንያት የሆናትም ይሄው አጋጣሚ ነው። ሕክምናውን (ቴራፒ) በጀመረችበት ወቅት ለዓመታት ከጉዳቱ ጋር የቆየች በመሆኑ ከፍተኛ የሆነውን ህመም ልትቋቋመው አልቻለችም ነበር። በዚህ ምክንያት በማዕከሉ የተሰጣትን እድል ለመተውና ሕክምናውን ለማቋረጥ ተገደደች።

ስዕል ትምህርት ቤት-አሰላ

ሰዓሊ ዓለም በሕክምናው ባትቆይም በሻሸመኔ ጂጌሳ ማዕከል ነበረች። በዚያ በቆየችባቸው ጊዜ ውስጥ በልምድና በተፈጥሮ ያዳበረችውን የስዕል ችሎታዋን ማሳየት ችላ ነበር። በግቢው ለሚገኙ ጣሊያኖች የተለያዩ ስዕሎችን እያዘጋጀች በስጦታ ታበረክትላቸው ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ጂኖ የሚባለው ጣሊያናዊ ይገኝበታል። በወቅቱ በሥራዎቿ በመደነቁና በችሎታዋ በማመኑ ወደ ፕሮፌሽናል ሰዓሊነት እንድትሸጋገር የሚያግዛት ትምህርት ሊያስተምራት ቃል ገባላት።

ጂኖ በቃሉ መሠረት ዓለምን ትምህርት ቤት አስገባት። የስዕል ትምህርት ቤቱ በአሰላ የሚገኝ ነበር። የመግቢያ ፈተናውን በቀላሉ አለፈች። የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤቱ በካቶሊኮች የተከፈተ ሲሆን በአዳሪ ትምህርት ቤት የሚያስተምር ነበር። ዓለም ብቸኛ ሴት ተማሪ የነበረች፤ በዚያ ግቢ ውስጥ ለማደር አትችልም ነበር። በዚህ ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈልገው እንደ ሞግዚት እያስተዳደሯት እንድትማር ሆነ። በጊዜው አንዳንድ ፈተናዎችን ማለፍ የግድ ቢላትም ለሶስት ዓመታት የዘለቀ የስዕል ትምህርቷን በስኬት አጠናቀቀች።

ከአሰላ ሥነ ጥበብ ማዕከሉ እንደወጣች ጣሊያናዊ ጂኖ እራሱ ቀጠራት። የተለያዩ የስዕል ሥራዎችን እንድትሠራለት ከማድረጉም በላይ ሥነ ጥበብ መምህር አደረጋት። ምክንያቱ ደግሞ በሚያስተምራት ወቅት ያወጣውን ወጪ እንደምትመልስ ውለታ ስለነበራቸው ነው። ጂኖ በሻሸመኔ የአርት ማዕከል ከፍቶ ስለነበር ለአራት ዓመታት በዚያ እንድትሠራ የግድ ሆነ።

በማዕከሉ ከምትሠራው የስዕል ሥራ ባሻገር አንደ ኩየራ፣ ጋምቦና ገጠራማ የሻሸመኔ አካባቢዎች በመሄድ ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶችን ታስተምር ነበር። በጊዜው በሻሸመኔ ተከፍቶ በነበረው አርት ማዕከል ውስጥ ከማስተማር ጎን ለጎን ስዕሎችን በትእዛዝ እየሠራች ወደ ጣሊያን ይላክ እንደነበርም ትገልፃለች።

በጊዜው ሙያዋንና የወደፊት ህልሟን ለማሳካት የሚያስችል እውቀትና የሕይወት ልምድ ብታገኝም ፈታኝ ሁኔታዎችን ማለፍ የግድ ይላት ነበር። ለምሳሌ በገጠራማ አካባቢዎች በመሄድ በምታስተምርበት ወቅት የመንገዱንና የትራንስፖርት ውጣ ወረዱ አንዱ ፈተና ነበር።

‹‹ቀኑን ሙሉ ሳስተምር ውዬ ማታ ነበር ወደ ሻሸመኔ የምመለሰው። ይሁን አንጂ ይህ ፈተና ጠንካራ አድርጎ ቀርፆኛል›› የምትለው ሰዓሊ ዓለም በዚያ ውስጥ ከቤተሰብ በብዙ ኪሎ ሜትር እርቆ ሕይወትን መጋፈጥ፣ እራስን የማግኘት ሩጫና የሥራን ጥቅም መረዳት እንድትችል እድሉን እንደሰጣት ትናገራለች።

የጂኖ አባት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በዓለም ሥራ እና ተሰጥኦ በመደነቃቸው ወደ ጣሊያን ስፖንሰር አድርገው ለማስተማር ፍላጎት ነበራቸው። ነገር ግን በልጃቸው አለመስማማት ምክንያት እድሉን ሳታገኝ ቆየች። ነገር ግን እድሉን በማጣቷ ብዙም አልቆጫትም። ምክንያቱ ደግሞ በዓመታት ቆይታዋ የሙያን ጥቅም፣ ኃላፈነትን የመወጣት እና የሰዓሊነት ችሎታን በተግባር መቅሰም በመቻሏ ነው። ስለ ሁኔታው መለስ ብላ ስታስብ ‹‹ይህ ለኔ በቂ ነበር፤ በጣሊያን ሀገር መማር ብችል መልካም የነበረ ቢሆንም የሚያስቆጨኝ ግን አልነበረም›› ትላለች።

ዳግም ወደ አዲስ አበባ

የጣሊያናዊው ጂኖ የሥነ ጥበብ ማዕከል ከአራት ዓመት በላይ አልዘለቀም። ዓለምም በዚያ አልቆየችም። ከፍሎ ያስተማራትን እዳ ከመመለስ ባሻገር ተጨማሪ ሕይወቷን የምታሻሽልበት ጥሪት የሚያስቋጥር አጋጣሚ አላገኘችም። ነገር ግን ከእርሷ የማይለይ እውቀትና የሥራ ሥነ ምግባርን አዳብራ ነበር ወደ ቤተሰቦቿ ከዓመታት በኋላ የተመለሰችው።

‹‹አዕምሮዬም ሰልጥኗል፤ እውቀትም አግኝቻለሁ። የመሥራት ፍላጎቴ ከፍተኛ ነበር›› የምትለው ሰዓሊ ዓለም ከምንጊዜውም በተለየ የሞራል ስንቅን ይዛ እንደተመለሰች ትናገራለች። ይሁን እንጂ በቤተሰቦቿ ቤት መኖርና እንደልቧ በአካባቢው በዊልቸር ለመንቀሳቀስ ይከብዳት እንደነበር ትናገራለች።

ሰዓሊ ዓለም በመንፈሳዊ ሕይወቷ ጠንካራ መሆኗና አዘውትራ ከቤተክርስቲያን አለመጥፋቷ ሕይወቷ የተስተካከለ እንዲሆንና ለሚገጥማት ፈተና ሸብረክ እንዳትል እንደሚረዳት ትገልፃለች። ተስፋ ላለመቁረጧ ምክንያት የሆናት የመንፈሳዊ ሕይወቷ የሰጣትን መረጋጋት በምክንያትነት ታነሳለች።

የግል ሥራን መጀመር

ከቀደመው ጊዜ በተሻለ ከሰዎች ጋር የነበራት ትውውቅና ህብረት ጠንክሯል። ዛሬ ብቻዋን አይደለችም፤ ብዙዎች ሕይወቷ የተቃና እንዲሆን ይሻሉ። በዚህ ምክንያት የኔ የምትላቸው ሰው በምትኖርበት አካባቢ አነስተኛ የግል ሱቅ እንድትከፍት ቤት ኪራዩን በመክፈል አገዟት። እኚህ ሰው አሁን የባህር ዳር አቡን የሆኑት ልሳነ ክርስቶስ ናቸው።

በጊዜው ሁለት በሁለት በሆነችው ሱቅ ውስጥ የስዕልና የጥበብ ሥራዎችን በመሥራት ለሽያጭ ማቅረብ ጀመረች። በምትሠራቸው የስዕል ሥራዎች የሚማረኩና የጥበብ ፍቅር ያላቸው ሰዎችን ትእዛዝ እየተቀበለች ማቅረብ ጀመረች። በዚያ እራሷን ከመደጎም አልፋ የቤት ኪራይ መክፈል ጀመረች። የዓለም ስኬትና ቀጣይ የተሳካ አቅጣጫ በዚህች ሱቅ አንድ ብሎ ጀመረ።

የሥነ ጥበበ ማዕከል

በሱቋ ውስጥ የስዕል ሥራዎችን ስትሰራ በዚያው አካባቢ ያሉ ህፃናትና ታዳጊዎች ይመለከታሉ። በተደጋጋሚም ከእውቀቷ እንድታካፍላቸውና ስዕል እንድታስተምራቸው ይጎተጉቷት ጀመር። በዚያች ጠባብ ክፍል ጥያቄያቸውን እየተቀበለች ማስተማር ቀጠለች። ይህንን የተመለከቱ የአካባቢው ነዋሪዎችም ልጆቻቸውን ከፍለው ለማስተማር ጭምር ጥያቄ ያቀርቡላት ጀመር። ሶሰት ልጆችን በመቀበል የተጀመረችው ትምህርት ቀስ በቀስ እያደገ መጣ። ቀደም ሲል በሻሸመኔ የነበራት የማስተማር ልምድን አገዛት። የማስተማር ሂደቱ እየሰፋ መምጣቱና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ የሥነ ጥበብ ማዕከል በ2004 ዓ.ም በዚያው በገርጂ አካባቢ እንድትከፍት ምክንያት ሆናት።

ዛሬ ‹‹ዓለም የሥነ ጥበብ ማዕከል›› ከተመሠረተ 13 ዓመታትን አስቆጥሯል። በገርጂ አካባቢ ታዋቂና ብዙዎች ልጆቻቸውን የሚያስተምሩበት ተመራጭ ማዕከል ነው። ከተመሠረተ ጀምሮ እስካሁን አራት ሺህ ተማሪዎችን አስመርቋል። ይህ ማዕከል ለልጆች የጥበብ ትምህርት በመስጠትና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታዳጊዎችን በማሰልጠን ቀዳሚው ነው። ልጆቹ ሥራዎቻቸውን ለእይታ የሚያቀርቡበት ኤግዚቢሽንም በየጊዜው ያዘጋጃል።

ሰዓሊና መምህር ዓለም ዛሬ በዚያው በገርጂ አካባቢ መንግሥት ባመቻቸላት ሼድ ውስጥ ታዳጊዎችን ማስተማሯን ቀጥላለች። ዓለም ጋለሪም እንዲሁ ሥራውን ይሠራል። በተጨማሪነት በኪራይ ማዕከሉን በማስፋፋት ሌሎች ጥበባዊ መሰናዶዎችን ታዘጋጃለች። በማዕከሉ ብዙዎች የስዕል ትምህርት ከማግኘታቸውም ባሻገር መጻሕፍትን ያነቡበታል፤ በሳምንት አንድ ጊዜ የሥነ ጥበብ (አውደ ሃሳብ የውይይት መድረክ) ዝግጅቶች ይደረጋሉ። ልትደርስበት የምታስበው ራዕይ ትውልድ የሚያቀና ለብዙዎች መጠንከር ምሳሌ ስለሆነ ዛሬ ላይ ብዙዎች ከጎኗ ቆመዋል።

ሰዓሊ ዓለም የመጣችበትን መንገድ፣ የገጠማትን ፈተናና ውጣ ውረድ በጠንካራ መንፈስ እና አልበገር ባይነት አልፋዋለች። በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙዎች ቀና ትብብርና ድጋፍ አድርገውላታል። እሷ እዚህ ለመደረሷ ምክንያት ሰዎች የራሳቸውን ጡብ እንዳኖሩት ሁሉ እሷም በመሰል ችግር ውስጥ የሚያልፉ ዜጎችን መደገፍ የሁልጊዜ ምኞቷ ነው። ይህ ሀሳቧ ታዲያ ምኞት ብቻ ሆኖ አልቀረም።

በዚህ ምክንያት ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ‹‹አብረን›› የተሰኘ የበጎ አደራጎት ማዕከል አቋቁማለች። ‹‹በየሄድኩበት አካባቢ ችግር ውስጥ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች ያጋጥሙኛል›› የምትለው ሰዓሊ ዓለም፤ በተለይ የሥነ ጥበብ ፍቅር ያላቸውን 40 የሚደርሱ አካል ጉዳተኞች በማሰባሰብ የሕይወት አቅጣጫቸው መስመር እንዲይዝ ድጋፍ እያደረገች መሆኑን ትገልፃለች። በአብረን ውስጥ 10 አባላት ያለው ቡድን ሲኖር የበጎ ምግባሩ በመደገፍ በጋራ ይሠራሉ።

‹‹አብረን ትኩረቱን ጥበብ ላይ አድርጎ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ እየሠራ ነው›› የምትለው ሰዓሊና መምህር ዓለም፤ አካል ጉዳተኞችን በማሰልጠንና የሕይወት ክህሎት በማስታጠቅ እንደሚሠሩ ትናገራለች። ከቀናት በፊትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአለ ፈለገ ሰላም የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ውስጥ 60 ተፅዕኖ መፍጠር የቻሉ ጋዜጠኞች፣ ዶክተሮች፣ ሰዓሊዎች፣ መምህራን፣ የመንግሥት ኃላፊዎች የተሳተፉበት የስዕል አውደ ርዕይ በመክፈት ለበርካታ ቀናት ለእይታ በቅቷል። ‹‹አብረን ለትውልድ›› የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍም ታትሞ በቅርቡ ይመረቃል። መጽሐፉ አካል ጉዳተኛ ሆነው ተፅእኖ መፍጠር የቻሉ ሰዎች ግለ ታሪክን የያዘ ነው። በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተፅዕኗቸው ከፍ ያለ የአካል ጉዳተኞችን እውቅና የሚሰጥ የሽልማት መርሀ ግብርም ከመጽሐፍ ምረቃው ጎን ለጎን ይካሄዳል።

ሰዓሊና መምህር ዓለም ከዚህም ያለፈ ራዕይ አላት። የስዕል ማስተማሪያ፣ ጋለሪ፣ የንባብ ማዕከሉንና የበጎ አድራጎት ሥራውን (አብረን ድርጅትን) በአንድ ሥፍራ ለማዋሀድና አቀናጅታ ግዙፍ የስብዕና ማዕከል የመክፈት እቅድ አላት። መንግሥት የሀሳቧ ተጋሪ በመሆን ተገቢውን ሥፍራ በማመቻቸት እንደሁልጊዜው ትብብር እንዲያደርግላትም ትጠይቃለች።

ሰዓሊና መምህር ዓለም ባለፉት በርካታ ዓመታት ለትውልድ ምሳሌ የሚሆኑ ሥራዎችን ለሀገሯ አበርክታለች። ለውለታዋ ልዩ ልዩ እውቅናዎችንና ሽልማቶችን አግኝታለች። በአውስትራሊያ በተካሄደ ውድድር ላይ ከአፍሪካ አንደኛ በመውጣት በማሸነፍ እውቅናን አግኝታለች። በጀርመን ሀገር በተካሄደ የአፍሪካን ካላንደር ውድድር አሸናፊና ተሸላሚ ነች። የባሕልና ስፖርት ሚኒስቴርን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሀገር ውስጥ ሽልማቶችና እውቅናዎችን ማግኘት ችላለች። በአሜሪካን ኤምባሲ፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ጨምሮ በሌሎች ዝግጅቶች ላይ እየተገኘች የሕይወት ልምዷን በማጣቀስ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ወጣቶች ሥልጠናዎችን ትሰጣለች።

የዓለም መልዕክት

‹‹መንቀሳቀስ የምችለው በዊልቸር ነው›› የምትለው የዛሬው የሕይወት ገፅታ እንግዳችን፤ አካል ጉዳተኝነት የአካል አለመንቀሳቀስ፣ ማየት አለመቻል ሳይሆን የአስተሳሳብ ችግር እንደሆነ ትናገራለች። አካል ጉዳተኛ የምትለው ቅንነት የሌለውን፣ ሀገሩን ማገልገል የማይችለውን፣ እራስ ወዳድ የሆነና ኃላፊነቱን በአግባቡ የማይወጣውን እንደሆነ ትገልፃለች። በየትኛውም መንገድ ላይ በጠበበ አስተሳሰብ የሚኖር ሰው ለእርሷ አካል ጉዳተኛ እንደሆነ ታስባለች።

እርሷ እዚህ ስኬት ላይ የደረሰችው በመልካም ሰዎች እንደሆነ በመግለፅም ‹‹ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሰዎችን ሕይወት ማቅናት የሚችለው በመልካምነትና በቅንነት መሆኑን ተረድቶ በሁሉም መስክ በኃላፊነትና በበጎነት መሥራት ይኖርበታል›› የሚል መልእክት አስተላልፋለች።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You