ባለፉት አምስት ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፡- ባለፉት አምስት ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በፖሊሲ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም አመልክቷል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የወጪ ምርቶች ፕሮሞሽን መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ በረከት መሠረት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ባለፉት አምስት ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፤ ገቢው ከዚህ ቀደም በአንድ ዓመት የሚገኝ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ከ178 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት፣ በጥራጥሬና ቅባታማ እህሎች 140 ሺህ ቶን ኤክስፖርት መደረጉን ያመለከቱት አቶ በረከት፤ ላኪዎች ምርቶቻቸውን ለማጓጓዝ የሚያጋጥሟቸውን የፀጥታ ችግሮች ለመፍታት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል ።

ላኪዎች ምርቶቻቸውን ከተመረተበት ቦታ ወደ ወደብ ለማምጣት በሚፈልጉበት ጊዜ ከወረዳ ጀምሮ አስፈላጊው የፀጥታ ድጋፍን እንዲያገኙ በማድረግ ውጤት ማምጣት ተችሏል ያሉት አቶ በረከት፤ ለዚህም ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው የፀጥታ መዋቅር ድረስ በቅንጅት መሠራቱን ጠቁመዋል።

የሀገር ውስጥ ላኪዎች ከውጭ ሀገር ኩባንያዎች ጋር አብረው መሥራት የሚችሉበትን እና የሚያጋጥሟቸውን የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የብቃትና የአፈጻጸም ችግሮች መፍታት የሚያስችላቸውን የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተደርገው ወደ ሥራ መገባቱንም አስታውቀዋል፡፡ ማሻሻያው የኤክስፖርት የሥራ ዘርፍን ሽፋን በማድረግ ከባንክ ብድር በመውሰድ በሥራው ላይ ያልተሠማሩ ከሴክተሩ እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ በረከት ገለጻ፤ ላኪዎች ምርቶቻቸውን ለመሸጥ ያነሱት የነበረው የግብይት አማራጮችን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ በተጨማሪ ሌላ አዋጅ ፀድቆ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡ የግብይት አማራጭ ላኪዎች ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ሳይገደቡ ግብይት እንዲያከናውኑ ማድረግ የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

በሀገር ውስጥ ኤክስፖርት ሥራ ላይ የተሰማሩ ላኪዎች በብዛት ምርቶችን ገዝተው ከመላክ ባለፈ፤ በእርሻው ዘርፍ ለመሠማራት ያላቸው ተነሳሽነት እምብዛም ነው ያሉት ኃላፊው መሬት ወስደው አልምተው መሥራት ለሚፈልጉ ላኪዎች አሁን ላይ ያለውን የኢንቨስትመንት ሪፎርሙ መልካም ዕድል ይዞላቸው እንደመጣ አስታውቀዋል ፤

እነዚህ ባለ ሀብቶች መሬት በቀላሉ እንዲያገኙ ሆነ፤ ወደ ንግድ ሥራ በቀላሉ እንዲገቡ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉ የውጭ ሀገር ባለሀብቶች በፖሊሲ አስቻይ ሁኔታዎችን ለመፍጠር በትኩረት እየተሠራ እንደሆነም አመልክተዋል።

 

ሰሚራ በርሀ እና መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You