– በፓርኮቹ ለ100 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
አዲስ አበባ፡- ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚገኙ 177 ማምረቻ ሼዶች 90 በመቶ ያህሉ በባለሀብቶች የተያዙ መሆናቸውን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታውቀዋል። በፓርኮቹ ለ100 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንም ጠቁሟል፡፡
የኮርፖሬሽኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ በለጠ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው 13 ፓርኮች ውስጥ ከሚገኙ ማምረቻ ሼዶች 90 በመቶ በባለሀብቶች ተይዘዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው በሁሉም ፓርኮች 177 የሚሆኑ የማምረቻ ሼዶች እንዳሉ ገልጸው፤ ከ3ሺህ ሜትር ስኩዌር ጀምሮ እስከ 11ሺ ሜትር ስኬዌር ወይም አንድ ነጥብ አንድ ሄክታር ስፋት ያላቸው ትላልቅ የማምረቻ ሼዶች መኖራቸው አመላክተዋል፡፡
ካሉት ሼዶች 90 በመቶ ያህሉ በባለሀብቶች የተያዙ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ጳውሎስ፤ ወደ ቀሪዎቹ 10 በመቶ ሼዶች ለመግባት የተዋዋሉና በሂደት ላይ ያሉ ባለሀብቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ባለሀብቶች የለማ መሬት በሊዝ ወስደው በራሳቸው ግንባታው የሚሠሩባቸው ሼዶች እንዳሉ ጠቁመው፤ ሼዶች በሙሉ ሥራ ላይ እንዲውሉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታወቀዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ፓርኮች ሥራ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ በፓርኮቹ ለ100 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታወቀዋል፡፡ ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ለ26ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ያስተዳድራል ያሉት አቶ ጳውሎስ፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ ፓርኮቹ ያሉበትን ደረጃ በመገምገም አስራ አንዱን ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን እንዲሸጋገሩ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣናን ጨምሮ 10 ኢንዱስትሪ ፓርኮች አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላታቸው ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የተሸጋገሩ መሆናቸው አስታውቀዋል። ይህም ወደ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
የተቀሩት ሁለቱ ፓርኮች (አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና አዲስ ኢንዱስትሪ ቪሌጅ) አሁን ላይ መሟላት ያለባቸው መሠረተ ልማቶች ያላሟሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ማደግ አለመቻላቸው ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያልተሸጋገሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የማሸጋገር ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት አቶ ጳውሎስ፤ አረርቲ ኢንዱስትሪ ፓርክ ያልተሟሉለትን መሠረተ ልማቶች የማሟላት ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አዲስ ኢንዱስትሪ ቪሌጅ ግን መሐል ከተማ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ለማድረግ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች መኖራቸው አመላክተዋል፡፡
ወደ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ያደጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮችም ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ አዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ባሕርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ኮምቦልቻ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ መቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ ጅማ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ሰመራ ኢንዱስትሪ ፓርክ መሆናቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም
ወርቅነሽ ደምሰው