“ሁሉም ወገን አማራጭ ለማይገኝለትና አትራፊ ለሆነው ሠላም እጁን መዘርጋት አለበት”›› – አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) የቀድሞው የሕወሓት ታጋይና የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር

አዲስ አበባ፡- የቅርቡም ሆነ የሩቁ ታሪክ እንደሚያሳየው ችግሮችን በጦር መሣሪያ ለመፍታት መነሳት ኪሳራ እንጂ ትርፍ ስለሌለው ሁሉም አማራጭ ለማይገኝለት ሠላም እጁን መዘርጋት እንዳለበት የቀድሞ የሕወሓት ታጋይ እና የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የቀድሞ የሕወሓት ታጋይና የህዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ላይ እንደተናገሩት፤ እስከ አሁን ድረስ ብዙ ጠመንጃ ተመዟል፤ ብዙ ጦርነት ተካሂዷል፡፡ ብዙ ሕዝብ አልቋል፤ ብዙ ንብረት ወድሟል፡፡ በልማት ላይ መዋል ይችል የነበረ ብዙ ሀብት ተቃጥሎ በኖ ቀርቷል። ይህ የሚያሳየው ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። በዚህ መነሻነትም ምንም አማራጭ ለማይገኝለትና አትራፊ ለሆነው ሠላም እጁን መዘርጋት አለበት፡፡

ጦርነት መግደል ወይም መሞት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ ኪሳራ ነው፡፡ በጦር መሣሪያ የሚፈታ ችግር ስለሌለ ሠላምን መፈለግ ይሻላል ብለዋል። ይህንን ያሉት ከቅርብ ከራሳቸው ተሞክሮ መሆኑን የተናገሩት አረጋዊ (ዶ/ር) ፤ መሣሪያ ይዞ መዋጋት ያለ እልቂት ያመጣው ምንም ፋይዳ እንደሌለው መላው ኢትዮጵያዊ ማስታወስ እንዳለበት አውስተዋል፡፡

ሌሎች አገሮች ችግር የለባቸውም ማለት አይደለም። እያደጉ ያሉት ችግሮቻቸውን በሠላማዊ መንገድ እየፈቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጦር የመዘዙ ኃይሎች ወደ ሠላማዊ መፍትሔ ፍለጋ ቢገቡ፤ ለራሳቸውም ሆነ እንዋጋለታለን ለሚሉት ወገናቸው በአጠቃላይ ለሀገራቸው ጠቃሚ በመሆኑ ሠላምን መምረጥ ይገባል ብለዋል፡፡

ሠላምን ማስከበር የየትኛውም መንግሥት ግዴታ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ለሕዝቡ ሠላም የማምጣት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ መንግሥት ለሠላም ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ መንግሥት በሰሜን ብዙ ትንኮሳዎች ቢኖሩም ችግሮች በሠላም እንዲፈቱ ከሚገባው በላይ መንቀሳቀሱ ሊያስመሰግነው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ መንግሥት የሠላም እንቅስቃሴው የበለጠ ትርጉም ሊያመጣ በሚችል መልክ አጠንክሮ መቀጠል አለበት። ነገር ግን በአንድ እጅ ማጨብጨብ የማይቻል በመሆኑ፤ መሣሪያ ያነገቱ ወገኖች ለሕዝብ እና ለሀገር ካሉ የሠላም አማራጩን ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

መንግሥት የሠላም ጥሪ ሲያደርግ የታጠቁ ኃይሎች ለመወያየት ፈቃደኛ ሆነው በሠላማዊ መንገድ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባ አመልክተው፤ እነዚህ ወገኖች እውነት ሕዝባዊ አቋም ካላቸው በሠላማዊ መንገድ ቢንቀሳቀሱ ሠላም ፈላጊ በሙሉ ይደግፋቸዋልየሚል እምነት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

መንግሥትም የሠላማዊ መንገድ ላይ አጠንክሮ ቢገፋበትም በአንድ እጅ ስለማይጨበጨብ፤ ሁሉም ቢተባበር ትልቅ ለውጥ ሊመጣ እና መፍትሔ ሊገኝ ይችላል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሁኔታ በውዥንብር መካከል መሆኑን እና ከውዥንብር የሚወጣበት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የፌዴራል መንግሥት በዚህ ላይ መፍትሔ ለማምጣት እየጣረ መሆኑንም አንስተዋል።

መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አካታች የፖለቲካ ድርጅቶች የሚሳተፉበት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲመሠረት ግፊት ማድረግ ይጠበቅበታል ያሉት አረጋዊ (ዶ/ር)፤ ይህ የመደማመጥ ሁኔታ ከተፈጠረ እና አሁን ያለው የለውጥ አዝማሚያ ከተደገፈ በትግራይ ውስጥ ዘላቂ ሠላም ሊሰፍን እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You