በኢትዮጵያና በፈረንሳይ መካከል ያለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መቶ ሃያሰባት ዓመታትን ያስቆጠረ ስለመሆኑ የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ። በነዚህ ሰፊ ጊዜያት ውስጥም የሀገራቱን ብሄራዊ ጥቅሞች ታሳቢ ያደረጉ ዘርፈ ብዙ የትብብር ግንኙነቶች ተፈጥረዋል።
እነዚህ የትብብር ግንኙነቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ከትብብር ግንኙነቶች አድገው ሁሉን አቀፍ ወደሆነ ስትራቴጂክ አጋርነት እየተለወጡ መጥተዋል። ይህም በአዲስ የለውጥ እና የዕድገት ምዕራፍ ውስጥ ላለችው ሀገራችን ትልቅ አቅም እየሆነ ይገኛል።
በተለይም የፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ መልኩ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት፤ ወዳጅነትን እና የጋራ ተጠቃሚነት መሠረት ባደረገ መንገድ ፤ ወደ አዲስ ታሪካዊ ስትራቴጂክ አጋርነት እያሸጋገረ ነው።
ላለፉት አምስት ዓመታት በፈረንሳይ መንግሥት በኩል የኢትዮጵያ ባህር ኃይልን እንደገና ለማደራጀት፤ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ለመጠበቅና ለማደስ ፣ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሙዚየምን ለማደራጀት የተገቡ ቃላትና እና በተግባር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። በሀገራቱ መካከል መተማመንን እና ላቅ ያለ ወዳጅነትንም ፈጥሯል።
መንግሥታቸው የኢትዮጵያውያን የለውጥ ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ፖሊሲዎችን እና የልማት ፕሮጀክቶችን ከመደገፍ ባለፈ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀገራቸው ያላትን ተደማጭነት በመጠቀም ለጀመርነው ሀገራዊ የብልጽግና ጉዞ ተጨማሪ አቅም ሆነዋል።
ከለውጡ ማግሥት እንደ ሀገር የጀመርነውን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በገንዘብ ከመደገፍ ጀምሮ ለስኬታማነቱ ቴክኒካዊ ፍጋፍ በመስጠት ላይ ናቸው። ሀገራችን ከአይ ኤም ኤፍ፣ ከዓለም ባንክ እና ከአውሮፓ ኅብረት የሚያስፈልጋትን የልማት ሀብት በማፈላለግም አጋርነታቸውን በተጨባጭ እያሳዩን ነው።
ሀገራቸው እና ሕዝባቸው ለታሪክ ከሚሰጡት ከፍ ያለ ዋጋ አንጻርም በእድሳት ማጣት ምክንያት አደጋ ውስጥ ገብቶ የነበረውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን የማደስ ሥራ እንዲከናወን በማድረግ ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ያላቸውን ከበሬታ በተግባር አሳይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሰሞኑን ታድሶ ወደ ሥራ የገባውን የታላቁን ቤተመንግሥት የእድሳት ሥራ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ፤ ቅርሶችን ወደ ዘላቂ ሀብትነት መለወጥ የሚችሉበትን ተሞክሮ በተግባር ማየት የቻልንበትን ዕድል ፈጥረው አሳይተውናል።
ከዚህ ተጨባጭ የሀገራቸው ኢንቨስተሮችን ጨምሮ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራትን በማስተባበር በወሳኝ መስኮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ ለመሥራት ቃል ገብተዋል። የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ድጋፍ ለማድረግ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል።
በጦርነት የተጎዱ ሆስፒታሎችን መልሶ መገንባት፤ የሽግግር ፍትህ እና የሕግ የበላይነት ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንደሚሰጡ ተናግረዋል። የባሕር በር መኖር አስፈላጊነት ሆነ ይህንን ማመቻቸት አስፈላጊነት አምነው ሀገራቸው ባላት አቅም ማድረግ የምትችለውን እንደምታደርግ ቃል ገ ብተዋል።
በፕሬዚዳንት ኢማኑኤል በራሳቸው እና በመንግሥታቸው በኩል ፤ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት እያበረከቱ ያለው በመላው ኢትዮጵያውያን እውቅና የተቸረው አዲስ የትብብር ምዕራፍ ጅማሬ ነው። ለዚህ የአውነተኛ ወዳጅነት ተግባርም የበዛ ምስጋና ሊቸረው ይገባል!
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሣሥ 15 ቀን 2017 ዓ.ም