ባንኮች አነስተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚታይባቸው አካባቢዎች የገንዘብ ፍሰት ሥርዓትን አስጠብቀው ወደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲሸጋገሩ በማድረግና በአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊና ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት እንዲመዘገብ የሚያደርጉ ወሳኝ አቅሞች ናቸው፡፡
በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የባንኮች ጥንካሬና ድክመት በአንድ ሀገር የወደፊት ዕድገት ላይ ከሚኖራቸው አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ የሚመነጭ ነው፡፡ አጠቃላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚያዊና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እንዲመዘገብ የሚኖራቸውም ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡
ከውጭ የሚገኝ ብድርና ርዳታ መሠረት ያደረገ የሀገር ኢኮኖሚ እንዳይኖር፤ ካለም ቀስ በቀስ ራስን ለመቻል በሚደረግ የመዋቅራዊ የለውጥ ሂደት ፤ ባንኮች የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀምና የብድርና ቁጠባ አገልግሎትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በመስጠት ኢንቨስትመንቱ እንዲጎለብትና የሀገር ውስጥ ልማት እንዲፋጠን የላቀ ሚና ይጫወታሉ፡፡
የታሪክ መዛግብት እንደሚያመለክቱት ፤ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ከተጀመረ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ አለው። የመጀመሪያው ባንክ በ1905 ዓ.ም በዳግማዊ አፄ ምኒልክና በእንግሊዝ ይዞታ ስር በነበረው የግብፅ ብሔራዊ ባንክ መካከል በተደረሰ ስምምነት መሠረት እ.ኤ.አ. የካቲት 16/1906 በአዲስ አበባ ከተማ በንጉሠ ነገሥቱ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል፡፡
አገልግሎቱ በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ በወቅቱ ከፍተኛ የንግድ እቅስቃሴ በነበረባቸው ድሬዳዋ፣ ጎሬና ደሴ ከተሞች ቅርንጫፎችን መክፈት ተችሎ ነበር፡፡ በወቅቱም በተለይ አዲስ አበባ የሚገኘው ዋናው አቢሲኒያ ባንክ የኢትዮጵያን ገንዘቦችና ሣንቲሞች ከማተም ጀምሮ ለመንግሥት ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ተግባራትን ይሰጥ እንደነበር በታሪክ ተመልክቷል፡፡
እ.አ.አ በ1931 ዓ.ም በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሙሉ በሙሉ በእንግሊዞች ቁጥጥር ስር የነበረውን ባንክ ሕጋዊ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያ ባንክ ወደሚል ስያሜ እንዲቀየርና በአዲስ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ ይህም ሀገር በቀል እና ከቅኝ ገዢዎች ነፃ በሆነ ሀገር የተቋቋመ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ባንክ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የባንኩ ዘርፍ በየወቅቱ ያጋጠሙትን መልካም ዕድሎች እና ፈተናዎች ተሻግሮ ዛሬ ላይ ደርሷል። የዛሬ ቁመናውም ቢሆን የዕድሜውን ያህል እንዳልሆነ በዘርፉ የተሠማሩ ምሁራን በስፋት የሚናገሩት የአደባባይ እውነታ ነው።
የሀገራችን ባንኮች በአብዛኛው የሚገኙት በከተሞች አካባቢ ነው። የብድር አገልግሎት የሚሰጡትም ማስያዣ ማቅረብ ለሚችሉ ጥቂት ባለሀብቶች ነበር። እሱም ቢሆን በብዙ ችግሮች የተሳሰረ ስለመሆኑ በብዙ ሲነገር የሚሰማ ነው። ከዚህም ባለፈ የቁጥራቸውን ያህል አቅም የገነቡ አይደሉም።
ለዚህም ሲባል በተለያዩ ወቅቶች አቅማቸውን አቀናጅተው ለተሻለ ተወዳዳሪነት ዝግጁ እንዲሆኑ ምክረ ሃሳብ ሲሰጣቸው ቆይተዋል። አንዳንዶች በአሁኑ ወቅት ይህን ምክረ-ሃሳብ ለመተግበር እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለመሆናቸውም አንዳንድ መረጃዎች ያመላክታሉ።
በመንግሥትም በኩል በየጊዜው ራሳቸውን በተሻለ መልኩ አብቅተው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ሲደረጉ ተሰምቷል። በፖሊሲ ደረጃም ዘርፉ ለውጪ ሀገር ባለሀብቶች ዝግ ሆኖ እንዲቆይም ተደርጓል ።
በዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ውስጥ ባንኮቻችን በቴክኖሎጂ ፣ በአሠራር ሥርዓት እና በሀብት ራሳቸውን የተሻለ ደረጃ ላይ አድርሰው፤ እንደ ሀገር ለተጀመረው የብልጽግና ጉዞ የሚጠበቅባቸውን ማበርከት የሚያስችል ሁለንተናዊ ቁመና መፍጠር አልቻሉም። ዛሬም ቢሆን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያጸና በራስ መተማመን አልገነቡም።
ይህም ሆኖ ግን እንደሀገር የተጀመረው የፋይናንስ ዘርፉን ሊበራላይዝድ የማድረግ የፖሊሲ አቅጣጫን መሠረት በማድረግ ሰሞኑን የውጪ ባለሀብቶች በፋይናንስ ዘርፍ እንዲሠማሩ የሚፈቅደው ረቂቅ ሕግ ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል። ሕጉ የሀገሪቱን የፋይናንስ ኢንዱስትሪ በማነቃቃት ሂደት ትልቅ አቅም እንዳለው በዘርፉ ባለሙያዎች እየተነገረለት ነው።
በተለይም ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ባንኮች ሀገሪቱ ለቀጣይ ልማቷ የምትፈልገውን ሀብት እና ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ ለማምጣት የጎላ ጠቀሜታ አላቸው ፤ በዘርፉ ያላቸውን የካበተ ልምድ ለሀገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት በማጋራት ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳቸው ይታመናል።
ለሥራ ፈጣሪዎችም ሆነ ፣ ለሜጋ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልገውን ሀብት በተሻለ መልኩ በማቅረብ ፤ ለሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ተጨማሪ መነቃቃት የሚፈጥሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ፤ በባንኩ ዘርፍ ተጠቃሚ ያልሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ከዘርፉ የተሻለ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መልካም ዕድል ይዘው እንደሚመጡም ይታመናል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ታኅሣሥ 16 ቀን 2017 ዓ.ም