አደራ መብላት…

ገመቹ ተስፋዬ፣ ትውልድና እድገቱ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ነው፤ ቤተሰቦቹን ለመደገፍ የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ የተለያዩ ሥራዎችን በመስራት ገንዘብ ለማግኘት ይሞክር ነበር። ነገር ግን በዚያ የሚሰራቸው ሥራዎች በቂ ገቢ ሊያመጡለት አልቻሉም። ገመቹ፣ ከዚህ በፊት አብሮት በመኪና ማጠብ ይሰራ የነበረ ጓደኛው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሥራ ላይ መሆኑን ያውቃል ። በዚያ የተሻለ ሥራ እና ጥሩ ክፍያ ይከፈለኛል የሚል ሀሳብም ስላለው ከብዙ ጊዜ ማመንታት በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥቶ ሥራ ማፈላለጉን ጀመረ ።

አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ከጓደኞቹ ጋር በመኖር የተለያዩ ሥራዎችን ሞክሯል ። የተለያዩ የቀን ሥራዎችን ፣ እቃዎችን ለሰው ማድረስ እና ጓደኞቹ የሚውሉበት ቦታ በመዋል የቀን ገቢ ለማግኘት የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን ይሞክራል ። አሁን የሚሰራበትን የቤተልሄም ሆቴልና አፓርትመንት ሥራ ያገኘው በአጋጣሚ ነበር ። ቂርቆስ ክፍለከተማ ወረዳ 03 ልዩ ስሙ ጨርቆስ ሰፈር አካባቢ እቃ ለማድረስ በሚሄድበት ጊዜ በተቋሙ በር ላይ የተለጠፈውን ማስታወቂያ በመመልከት የተሻለ ሥራ ለማግኘት እድሉን ይሞክራል።

ወደ ሥራው ለመግባትም አፓርትመንቱ ኃላፊዎች ያስቀመጡትን መመዘኛዎች ካሟላ በኋላ ተያዥ የሚለውን የቅርብ ጓደኛውን በማምጣት የሥራ ውሉን በመዋዋል ሥራውን ይጀምራል ።

ገመቹ ወደ አፓርትምንቱ አዲስ ሥራ ከጀመረ በኋላ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በአፓርትምንቱ ጊቢ ውስጥ ነው ። ከጥበቃ ባሻገር በአፓርትመንቱ የማረፊያ ክፍል ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ለቀናት አንዳንዴም ሳምንታት የሚቆዩ በመሆናቸው መልካም የሆነ ተግባቦት አለው ። በሚሰራበት የጥበቃ ሥራ ውስጥ መኪና በማጠብ ፣ በአፓርትመንቱ በእንግድነት ለሚመጡ ሰዎች በመላላክ ተጨማሪ ገቢ ያገኛል ። ቆይታቸውን ጨርሰው የሚሄዱ የአፓርትመንቱ ተጠቃሚዎችም ገመቹ እንደማበረታቻ ጉርሻ (TIP) ሰጥተውት ይሄዳሉ ። ገመቹ በዚህ ሥራ ቦታ ሁለት ዓመት ያክል ጊዜን ቆይቷል ። ይህንን ሥራ ከማግኘቱ በፊት ሌሎች በርካታ ሥራዎችንም ለመስራት እና ሕይወቱን ለመሻሻል ሞክሯል ።

አብረውት የሚኖሩ የገመቹ ጓደኞች በተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው ። ስንታየሁ አብረውት ከሚኖሩ ጓደኞቹ አንዱ ሲሆን የቀን ሥራዎችን በመስራት ተባራሪ እቃዎችን በመሸጥ ኑሯቸውን ይገፋሉ ።

ገመቹ የሚሰራበት ድርጅት ውስጥ በአፓርትመንቱ የተወሰኑ ቀናት የሚቆዩ ተጠቃሚዎች የትራንስፖር አገልግሎት የሚሰጡ ፣ እቃ የሚያመላልሱ ከአንድም ሁለት መኪናዎች በግቢው ውስጥ ይገኛሉ ። ገመቹ የጥበቃ ሥራው እነዚህን የአፓርትመንቱ ንብረቶች መጠበቅን ያጠቃልላል ። የእረፍት ጊዜውን ከእነዚህ ጓደኞቹ ጋር እነሱ የሚሰሯቸውን የተለያዩ ጥቃቅን የድለላ ስራዎችን ከሚሰሩ ጓደኞቹ ጋር ያሳልፋል ። ነገር ግን ገመቹ የሚያሳልፈው የሥራ ጊዜ ቀኑን ሙሉ በአፓርትመንት ውስጥ የሚውል በመሆኑ ከጓደኞቹ ጋር የሚገናኘው ከመሸ በኋላ ወደቤቱ ሲመለስ ነው። ገመቹ ከቀን ፈረቃ ባለፈ ምሽት ላይ አዳሪ የሚሆንባቸው የሥራ ቀናት አሉ። በአፓርትመንቱ ውስጥ በሚያድርበት ጊዜ ጊቢው ውስጥ የሚያድሩ የድርጅቱ መኪኖችን መጠበቅ ይጠበቅበታል ።

ክፉ አመል

አዳሪ በሚሆንበት ጊዜ የተወሰኑ ሰዓታትን ከጓደኞቹ ጋር በአፓርትመንቱ አካባቢ ያሳልፋሉ ። ታዲያ ከጓደኞቹ አንዱ ስንታየሁ አድማሱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በሚሰራበት የታክሲ ተራ አካባቢ ስልክ በመስረቅ በስርቆት ወንጀል ተጠርጥሮ የፍርድ ጊዜ በማረሚያ ቤት ውስጥ ጊዜውን ጨርሶ የወጣ ነው ።

ታዲያ ስንታየሁ ገመቹ የሚውልበት የሥራ ቦታ ትልቅ እና በጣም ጥሩ ነው የሚል አስተያየት ያቀርብለታል። በተደጋጋሚም በአፓርትመንቱ ውስጥ ለመጓጓዣነት የሚያገለግለውን መኪና ላይ አይኑን በመጣሉ ንብረቱን የራሱ ለማድረግ መጓጓቱ ለገመቹም ይህንን ሀሳብ ማጋራቱ አልቀረም። ነገር ግን ገመቹ ይህንን ጉዳት አስቦት የማያውቀው በመሆኑ ለመስማማት ፍቃደኛ አልነበረም ። ነገር ግን በአነስተኛ ደሞዝ ተቀጥሮ ለሚሰራው ገመቹ ጓደኛው የሚሰጠው ምክንያት መኪናው ቢሸጥ ሊያገኝ የሚችለውን ገንዘብ እንዲጓጓ አድርጎታል ።

በእለቱም አዳሪ ተረኛ የነበረው ገመቹ አብሮት የሚኖረው ስንታየሁ ሌላ ጓደኛ የሆነው ደስታ ከአሰላ ከተማ መጥቶ አብሯቸው ይገኛል። ታዲያ ገመቹ የሥራ ቦታ ላይ የሚገኘውን መኪና ስርቆት ሀሳብ በተመለከተ የቀረበውን ሀሳብ ይበልጥ ግልጽ በማድረግ እና ሀሳቡን በመንደፍ ለገመቹ የሰውን ንብረት መውሰድ ቀላል ሆኖ እንዲታየሁ አደረገ። በሀሳቡ በመስማማት የሚመጡበትን ሰዓት ከወሰዱት በኋላ ወዴት እንደሚሄዱ በማስረዳት ገመቹ ወደ ሥራ ቦታው ሰዓቱን ጠብቆ በቦታው ተገኘ ።

ጥፋት በሕብረት

ሔለን ወደ ቤተልሄም አፓርትመንት የሚመጡ ተጠቃሚዎችን ከሚመጡበት ቦታ በመቀበል በዚያ በሚቆዩበት ጊዜ የሚፈልጉትን ነገር በማሟላት ሥራውን በቅርበት የምትቆጣጠር ናት ። በመሆኑም ደንበኞቹ የሚፈልጉትን አገልግሎት ከተሟላ በኋላ የምሽት ጊዜዋን ወደቤቷ በመሄድ ታሳልፋለች ። ገመቹ የአዳሪ ተረኛ በሆነበት በዚህ ቀን በቀጠሯቸው መሰረት ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ የጉዳዩ ጠንሳሽ የሆነው ስንታየሁ እና ጓደኛው ደስታ በመሆን በቦታው ተገኙ ። ይህ ለገመቹ እና ለአባሪዎቹ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖላቸዋል ። ገመቹ የአፓርትመንቱን በር ከከፈተ በኋላ በቅርቡ አብሯቸው መኖር የጀመረው ደስታ ወደመኪናው በመጠጋት እና መኪናው በቀስታ በመንዳት መኪናውን ይዞት ወጣ። በአደራ መልክ የተሰጠውን ኃላፊነት ያልተወጣው ገመቹም በዚህ መኪና ውስጥ በጋራ በመሆን መኪናውን ይዘው ወደ ማምለጥ አመሩ ።

የወንጀሉ ዝርዝር

በ2013 ዓ.ም ነሀሴ ወር ቀን 11 በግምት ከለሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በቂርቆስ ክፍለከተማ ወረዳ 03 ልዩ ቦታው ጨርቆስ ቤተክርስቲያን ተብሎ የሚጠራው አከባቢ ንብረትነቱ የቤተልሄም ሆቴልና አፓርትመንት ውስጥ ተጠርጣሪው ገመቹ ካልተያዙት አባሪዎቻቸው ጋር በመሆን የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 – ኤ79876 ሀይውንዳይ ተሽከርካሪ ከቆመበት ቦታ ተሰርቆ ተወሰደ። የመኪናውን መሰረቅ የተመለከቱት የአፓርትመንቱ ሰራተኞች ወደ ፖሊስ በመቅረብ ቅሬታቸውን አቀረቡ። ፖሊስ የደረሰውን መረጃ በመከተል ምርመራው ማድረግ ጀመረ። ምርመራውን ተጠርጣሪ የሆነው ገመቹ ውሉን በሚፈርምበት ጊዜ ባስቀመጠው አድራሻ መሰረት ፍለጋውን ማድረግ ቀጠለ ። ፖሊስ በዚህ ማጣራት ውስጥ አንደኛ ተጠርጣሪ የሆነውን ገመቹን በዱከም ከተማ በቁጥጥር ስር ካዋለው በኋላ አግኝቶ በማጣራት ከአዲስ አበባ መንገዶች አስተዳደር መኪናው የተመዘገበበትን ባለቤት ትክክለኛ አድራሻ የቤተልሄም ሆቴልና አፓርትመንት ሰራተኛ የሆነችው ሔለን ስም የተመዘገበበ መሆኑን አረጋግጦ ማስረጃ በመያዝ ተጠርጣሪ ያላቸውን በስርቆት የተሳተፉ ግለሰቦች የሚጣቀሙባቸው የባንክ ሒሳብ ሕጉን በተከተለ መሰረት የእግድ ትእዛዝ በማውጣት እና ተጠርጣሪው ያደረጋቸውን የስልክ ልውውጦች ከኢትዮ ቴሌኮም መረጃ በመውሰድ የማጣራት ሥራውን አድርጓል ።

በመኪና ስርቆት የተሳተፉት ተጠርጣሪው ገመቹ እና አባሪዎቹ ስንታየሁ እና ደስታ መኪናው ከሰረቁ በኋላ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር የሚፈጀውን ገንዘብ ባነሰ ገንዘብ በመቶሺዎች በመሸጥ እና ገንዘቡን መከፋፈላቸውን ዐቃቤ ሕግ ተጠርጣሪዎች ከሰጡት ቃል ማረጋገጥ ችሏል ። በቅሬታው መሰረት ፖሊስ ባደረገው ምርመራና ማጣራት አንደኛ ተጠርጣሪ በሰጠው ጥቆማ ተሽከርካሪው ቀን 23 ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ የፊትና የኋላ ሰሌዳው እንዲሁም ሶስተኛ ወገን እንዲሁም ቦሎ ተነስቶ ነገር ግን በመኪናው የሞተር ቁጥር ከአንድ ዓመት በኋላ መኪናው ሊገኝ ችሏል ። ተሽከርካሪው ሲገኝ የፊትና የኋላ ሰሌዳው እንዲሁም ቦሎና ሶስተኛ ወገን ያልተገኘ በመሆኑ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በኤግዚቢትነት ተይዞ እንዲቆይ ተደርጓል ። ፖሊስ ባደረገው ማጣራት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማጠናከር በመኪና ወንጀል ስርቆት ላይ የተሳተፉ አንደኛ ተከሳሽ ገመቹ ተስፋዬ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ደስታ አበራ ጥፋተኛ መሆናቸውን አረጋግጧል ።

የውሳኔ ሒደቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በኤግዚቢትነት የተያዘውን ተሽከርካሪ በስሟ የተመዘገበው ሔለን በድጋሚ እንዲረጋገጥ በማድረግ ንብረቱ እንዲመ ለስላቸው ጥያቄ በማቅረብ ተሽከርካሪውን መልሰው ማግኘት ችለዋል ።

አንደኛ ተከሳሽ ገመቹ ተስፋዬ እና ሁለተኛ ተከሳሽ ደስታ አበራ በተከሰሱበት የመኪና ስርቆት ወንጀል የፌደራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጥር ዘጠኝ ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ክስና ሰማስረጃ ከሕግ ጋር አገናዝቦ አንደኛ ተከሳሽ ገመቹ ተስፋዬን በ10 ዓመት ጽኑ እስራት ፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ደስታን አበራን በሰባት ዓመት ጽኑ እስራት ይቀጡ ሲል ውሳኔውን አስተላልፏል ።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You